ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 14 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, December 9, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 14

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ዐሥራ አራት በዚህች ቀን ቅዱስ_መርትያኖስ_ዘጠራክያ አረፈ፣ የአባ_ዳንኤል_ገዳማዊ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።


ኅዳር ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የሀገረ ጠራክያ ኤጲስቆጶስ ቅዱስ አባት አባ መርትያኖስ አረፈ።
ይህም ቅዱስ ሶርያ ከምትባል አገር ነው ወላጆቹም ክርስቲያን ናቸው እርሱም በገድል የተጠመደ ተጋዳይ ነው አርዮሳውያንንም የሚቃወማቸው ከሀድያን የሚላቸው አውግዞም የሚያሳድዳቸው ሆነ። ስለዚህም በእርሱ ላይ ታላቅ መከራ ደረሰበት። በሚያልፍባትም ጎዳና ጠብቀው ይይዙታል አብዝተውም ገርፈው እግሩን ይዘው በሜዳ ውስጥ ይጎትቱታል እንዲህም ብዙ ጊዜ አደረጉበት። ከዚህም በኋላ ከእርሳቸው ሸሽቶ ወደ ሩቅ አገር ተጉዞ ከኤርትራ ባሕር ዳር ደረሰ ከምድር የሚበቅሉ ቅጠሎችን እየተመገበ በዚያ በዋሻ ውስጥ ብዙ ዓመታትን ኖረ።
ኤጲስቆጶስም ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር መረጠው እነሆ የተጋድሎውና የትሩፋቱ ዜና በተሰማ ጊዜ ከዚያ ወስደው ጠራክያ በሚባል አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት እንደ ሐዋርያት ሥርዓት በሹመቱ በጎ አካሔድን ተጓዘ በዘመኑም በብዙዎች ላይ ሰላም ፍቅር ቸርነት ሆነ።
እግዚአብሔርም በእጆቹ ታላላቅ ተአምራትን አደረገ በጎዳናም አልፎ ሲሔድ የሞተ ሰው አየ ሌላም ዓመፀኛ ልቡ የደነደነ በሐሰት ከእርሱ ላይ አራት መቶ የወርቅ ዲናር አለኝ ያንን ካልሰጡኝ አላስቀብርም ብሎ ዘመዶቹን ሲከለክል ነበር። ይህም ቅዱስ የሞተውን ይቅበሩት ተዋቸው ብሎ ብዙ ለመነው እርሱ ግን አልሰማውም። በዚያንም ጉዜ ይህ ቅዱስ ወደ እግዚአብሔር እየጸለየ ማለደ ያን ጊዜ የሞተው ሰው ተነሥቶ ምንም ምን ዕዳ እንደሌለበት ተናገረ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርትያኖስ ያንን ዓመፀኛ በሰው ፊት እንዲህ አለው ለምን በሐሰት ተናገርክ የተሠወረውን የሚያውቅ እግዚአብሔርን አትፈራውምን በዚያንም ጊዜ ያ ዓመፀኛ ሞተ ከሞት የተነሣው ግን በሰላም ወደ ቤቱ ገባ።
ከዚህም በኋላ ይህ ቅዱስ መርትያኖስ ብዙ ዘመናትን ኖረ መልካም አገልግሎቱንም ፈጽሞ እግዚአብሔርንም ደስ አሰኝቶ በሰላም አረፈ።

በዚህችም ቀን ለፋርስ ንጉሥ ተአምራት ያደረገና ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳመነው የአባ ዳንኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።
የእምነቱም ምክንያት እንዲህ ነው ይህ ንጉሥ ጽኑዕ የሆነ የሆድ በሽታ ታሞ ነበር፤ ባለ መድኃኒቶችም ሊአድኑት አልቻሉም። ንጉሡም ከማዕዱ የሚመግበው አብሮት የሚኖር ሥራየኛ ሰው ነበረው። ንጉሡም እንዲህ አለው "ያንተ ከእኔ ጋር መኖር ጥቅሙ ምንድን? ነው ከዚህ በሽታ ካልፈወስከኝ እገድልሃለሁ።"
ሥራየኛውም ንጉሡን በተንኮል እንዲህ ብሎ ተናገረው "ንጉሥ ሆይ የምነግርህን ካደረግህ ከደዌህ ትድናለህ። አሁንም ለአባትና እናቱ አንድ ብቻ የሆነ ልጅ ይፈልጉልህ እናቱ አሥራ ትያዘው አባቱም ይረደው በእርሱም ደም ትድናለህ።" መሠርዩ ይህን ማለቱ ግን እንዲህ ያለ ሥራ መሥራትን ንጉሥ ይፈራል ወይም ልጁን የሚሰጥ አይገኝም ብሎ አስቦ ነው።
ንጉሥም በሚገዛው አገር ውስጥ ፈልገው በአንድ ሺህ የወርቅ ዲናር ሕፃን ልጅ ይገዙለት ዘንድ አሽከሮቹን አዘዘ። በዚያችም አገር አንድ ልጅ ያላቸው ድኆች የሆኑ ባልና ሚስት ነበሩ እነርሱም ይህን ነገር ሲሰሙ ልጃቸውን ወደ ንጉሥ ወሰዱ ልጁም በማልቀስ እኔ በፈጠረኝ እግዚአብሔር ላይ ተማምኛለሁና እርሱም ያድነኛል ይል ነበረ።
እናቱም አጥብቃ አሠረችው አባቱም ሊያርደው በንጉሡ ፊት ሾተሉን መዘዘ፤ በዚያንም ጊዜ ሕፃኑ አይኖቹን ወደ ሰማይ ቀና አድርጎ ወደ እግዚአብሔር በልቡ ሲጸልይ ከንፈሮቹን አንቀሳቀሰ። እግዚአብሔርም በንጉሡ ልብ ርኅራኄን አሳደረ ፈትታችሁ ልቀቁት ብሎ አዘዘ። ወደርሱም አቅርቦ "ዐይኖችህን ወደ ሰማይ በአቀናህ ጉዜ ምን አልክ?" አለው። "ጌታዬ ሆይ ልጅን የሚገፋው ቢኖር አባትና እናቱ ያድኑታል ከዚያም የጸና ሥራ ቢኖር ንጉሥ ዳኛ ያድነዋል እኔ ግን ከሁላችሁም ርዳታ በአጣሁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ለመንኩ" አለው። ንጉሡም ሰምቶ ራራለት አንድ ሽህ የወርቅ ዲናርንም ሰጠው።
ስለዚህም እግዚአብሔር ይቅር ሊለው ወዶ መነኰስ ዳንኤልን ላከለት። እርሱም ወደ ንጉሡ በደረሰ ጊዜ በፊቱ ተአምራትን አድርጎ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሳመነውደ ከበሽታውም ፈወሰው። ከቤተሰቦቹ ሁሉ ጋርም አጠመቀው። ከዚህም በኋላ ወደ በዓቱ ተመልሶ እየተጋደለ ኖረ። እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶች ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages