ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 15 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, December 9, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 15

  አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ዐሥራ አምስት በዚህች ቀን ቅዱስ_ሚናስ በሰማዕትነት አረፈ፣ የሕፃኑ ሰማዕት ቅዱስ_ቂርቆስ ልደቱ ነው፣ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_ሚናስ_ሁለተኛው ያረፈበትን ነው።
ኅዳር ዐሥራ አምስት በዚህች ቀን የስሙ ትርጓሜ ቡሩክና የታመነ የሆነ ቅዱስ ሚናስ በሰማዕትነት አረፈ። የዚህም ቅዱስ አባቱ አናቅዮስ ከሚባል አገር ነው ስሙም አውዶክስዮስ ነው እርሱም አገረ ገዥነት ተሹሞ ሳለ ወንድሙ ቀንቶበት በንጉሥ ዘንድ ነገር ሠራበት ንጉሡም ወደ አፍራቅያ አገር ሰደደውና በዚያም አገረ ገዢ አድርጎ ሾመው የአገር ሰዎችም ሁሉ ደስ አላቸው እርሱ ለሰው የሚራራ እግዚአብሔርንም የሚፈራ ደግ ሰው ነውና ።
እናቱም ልጅ አልነበራትም በአንዲት ዕለት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በበዓልዋ ቀን ገብታ የክርስቲያንን ወገኖች ያማሩ ልብሶችን ለብሰው ከልጆቻቸው ጋር ደስ እያላቸው ሲገቡ አየቻቸው። በእመቤታችንም በቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ፊት አለቀሰች ልጅን ይሰጣት ዘንድ ወደ ልጅዋ ወደ እግዚአብሔር እንድትለምንላትም ለመነቻት በዚያንም ጊዜ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል አሜን የሚል ቃል ወጣ።
ከዚህም በኋላ ወደ ቤቷ ገብታ ይህን ቃል ለባሏ ነገረችው እርሱም የእግዚአብሔር ፈቃዱ ይሁን አለ። ከጥቂት ቀኖችም በኋላ እግዚአብሔር ይህን የተባረከና የከበረ ልጅን ሰጣት የእመቤታችንም ሥዕል ሚናስ ብላ እንደሰየመችው ስሙን ሚናስ ብለው ሰየሙት። ጥቂት በአደገ ጊዜም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማሩት። ዐሥራ ሁለት ዓመትም ሲሆነው በመልካም ሽምግልና አባቱ አረፈ ከእርሱም በኋላ በሦስተኛ ዓመት እናቱ አረፈች ቅዱስ ሚናስም ብቻውን ቀረ።
መኳንንቱም አባቱን አብዝተው ከመውደዳቸው የተነሣ ሚናስን በአባቱ ፈንታ ምስፍናን ሾሙት እርሱም የክርስቶስን አምልኮት አልተወም።
ዲዮቅልጥያኖስም በካደ ጊዜ ሁሉንም ሰዎች ጣዖታትን እንዲአመልኩ አዘዛቸው ብዙዎችም ክብር ይግባውና በክርስቶስ ስም በሰማዕትነት ሞቱ ። በዚያንም ጊዜ ሚናስ ሹመቱን ትቶ ወደ ገዳም ገባ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ ብዙ ዘመናት ኖረ ። በአንዲትም ዕለት ሰማይ ተከፍቶ ሰማዕታትን የብርሃን አክሊሎችን ሲያቀዳጇቸው አየ። ስለ ክርስቶስ ስም በመከራ የደከመ ይህን አክሊል ይቀበላል የሚል ቃልን ሰማ። በዚያንም ጊዜ ወደ ከተማ ተመለሰና ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመነ ሰዎችም አብዝተው አባበሉት በወገን የከበረ እንደሆነ እነርሱ ያውቁ ነበርና።
መኰንኑም ብዙ ቃል ኪዳን ገባለት ባልሰማውም ጊዜ ጽኑዕ በሆነ ሥቃይ እንዲአሠቃዩት አዘዘ። ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ ። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ ብዙዎችም በእርሱ ምክንያት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በሰማዕትነት ሞቱ።
የቅዱስ ሚናስንም ሥጋ ወደ እሳት እንዲጥሉት መኰንኑ አዘዘ እሳትም አልነካውም ምእመናን ሰዎችም የቅዱስ ሚናስን ሥጋ ወስደው በአማሩ ልብሶች ገነዙት የስደቱ ወራትም እስከሚፈፀም በአማረ ቦታ ውስጥ አኖሩት።
በዚያንም ወራት የመርዩጥ አገር ሰዎች ከአምስቱ አገሮች ሠራዊትን ሊአከማቹ ወደዱ የቅዱስ ሚናስንም ሥጋ ረዳት ይሆናቸው ዘንድ በመንገድም እንዲጠብቃቸው ከእርሳቸው ጋር ወሰዱት።
እነርሱም በባሕር ላይ በመርከብ ውስጥ ሳሉ ፊታቸው እንደ ከይሲ አንገታቸው እንደ ግመል አንገት ያለ አውሬዎች ከባሕር ወጡ ይልሱትም ዘንድ ወደ ቅዱስ ሚናስ ሥጋ አንገታቸውን ዘረጉ ከቅዱስ ሚናስም ሥጋ እሳት ወጥታ እነዚያን አራዊት አቃጠለቻቸው ሰዎችም አይተው አደነቁ ደስታም አደረጉ ፈርተው ነበርና።
ወደ እስክንድርያ አገርም ደርሰው ሥራቸውን ፈጽመው ወደ ሀገራቸው በሚመለሱ ጊዜ የቅዱስ ሚናስን ሥጋ ከእሳቸው ጋር ሊወስዱ ወደው በገመል ላይ በጫኑት ጊዜ ገመሉ ከቦታው የማይነሣ ሆነ። ሁለተኛም በሌላ ገመል ጫኑት እርሱም መነሣትን እምቢ አለ። አብዝተውም ደበደቡት ገመሉም ከቶ አልተንቀሳቀሰም እነርሱም ያ ቦታ እግዚአብሔር የፈቀደለት መሆኑን አወቁ ቦታውንም አዘጋጅተው በዚያ ቀበሩት።
ጌታችንም በበግ እስከገለጠው ድረስ ብዙ ዘመናትን በዚያ ቦታ ኖረ ይህም ቤተ ክርስቲያኑ በከበረችበት በሰኔ ዐሥራ አምስት ቀን ተጽፎአል።

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሕፃኑ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ልደቱ ነው። ቅዱስ ቂርቆስን አባቱ ቆዝሞስ እናቱ ኢየሉጣ ይባላሉ፡፡ በዚህች ቀን የተወለደ ሲሆን ሀገሩ በታችኛው እስያ ልዩ ስሙ ሀንጌቤን ይባላል፡፡ ሦስት ዓመት እንኳን ሳይሞላው በሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወሩ ታላቅ ሰማዕትነትን ተቀብሏል።
ዘመኑ ዘመነ ሰማዕታት ኘበርና በዚያንም ወራት የክብር ባለቤት የሆነ ክርስቶስን በሚያምኑ የክርስቲያን ወገኖች ላይ ታላቅ መከራና ስደት ሆነ። ቅድስት ኢየሉጣም ከታናሽነቷ ጀምራ ደግ ናት። ስደትም እንደሆነ በሰማች ጊዜ መኰንኑን ከመፍራት የተነሣ ቅዱስ ቂርቆስን ይዛ ከሮም ከተማ ተሰዳ የኪልቅያ አውራጃ ከሆነ ከጠርሴስ ደርሳ ከዚያም በሀገሮች ውስጥ እየተዘዋወረች ተቀመጠች ።
ወደዚያች አገርም ያ ከእርሱ የሸሸችው መኰንን እለእስክንድሮስ መጣ ጭፍሮቹም ክርስቲያኖችን ፈለጓቸው። ይቺንም ቅድስት ኢየሉጣን አግኝተው ያዝዋትና ወደ መኰንኑ አደረሷት የክርስቲያን ወገንም እንደሆነች ነገሩት።
መኰንኑም "ሴትዮ ተናገሪ ከወዴት ሕዝብ ወገን ነሽ? ነገድሽ ምንድን ነው? ሀገርሽስ ወዴት ነው?" አላት ። የከበረች ኢየሉጣም እንዲህ ብላ መለሰችለት "የአንጌቤን ሰው ለሆንኩ ለእኔ ወገኖቼ ለኢቆንዮን አገር አለቆች የሆኑ ኤሳውሮሳውያን ናቸው። እኔም በአንተ ምክንያት ሸሽቼ ነበር እነሆ ዛሬ ግን በእጅህ ውስጥ ነኝ" አለችው።
መኰንኑም "በእጄ ውስጥ እንደተገኘሽ ታውቂያለሽን" አላት። "አሁንም የሚሻልሽን ምረጪ ስምሽንም ተናገሪ እኔንም እሺ በይኝና ለአማልክት ሠዊ" የከበረች ኢየሉጣም "ለረከሱ አማልክት እኔ አልሰዋም" አለችው። መኰንኑም "ስምሽን ስጪ ተናገሪ" አላት። እርሷም "የኔ ስም ክርስቲያን መባል ነው" አለችው። መኰንኑም "ይህስ ስንፍና ነው የሚጠቅምሽ አይደለም እንዳትሞቺ ስምሽን ስጪ ተናገሪ" አላት። የከበረች ኢየሉጣም "የኔ ስም ክርስቲያን መባል እንደሆነ ነገርኩህ ሞት የሚሽረው በሰዎች ዘንድ የምጠራበትን ከፈለግህ ስሜ ኢየሉጣ ነው" ብላ መለሰችለት።
መኰንኑም "ጽኑ የሆኑ ሥቃዮችን በላይሽ ሳይመጣ ተነሥተሽ መሥዋዕትን ለአማልክት አቅርቢ" አላት። የከበረች ኢየሉጣም "ዕውነት ነገርን ለመሥራት የምትሻ ከሆነ ዕድሜው ሦስት ዓመት የሆነ ሕፃን ልጅ ይፈልጉ ዘንድ ወደ ሀገሩ መንደር ላክ ወዳንተም ያምጡትና የምንገዛለትንና የምናመልከውን እርሱ ይንገረን" አለችው።
ያን ጊዜም የሦስት ዓመት ልጅ ይፈልጉ ዘንድ መኰንኑ ወታደሮችን ላከ የሀገር ሰዎችም ልጆቻቸውን ሠውረዋልና አላገኙም ከዚያም ከከተማው ቅጽር ውጭ በፀሐይ መውጫ ወዳለው በረሀ በኩል ወጡ የቅድስት ኢየሉጣንም ልጅ አገኙት ይህ ሕፃን የስንት ዓመት ልጅ ነው ብለው ስለርሱ ጠየቁ ሰዎችም ይህ ሕፃን የሦስት ዓመት ሲሆን የክርስቲያናዊት መበለት ልጅ ነው አሏቸው።
ያንንም ሕፃን ይዘው ወደ መኰንኑ ወሰዱት መኰንኑም መልኩ የሚያምርና ደም ግባት ያለው እንደሆነ በአየው ጊዜ "ደስ የምትል ደስተኛ ሕፃን ሰላምታ ይገባሃል" አለው። ሕፃኑም "እኔን ደስተኛ ማለትህ መልካም ተናገርክ፤ ላንተ ግን ደስታ የለህም እግዚአብሔር ለዝንጉዎች ደስታ የላቸውም ብሏልና።" ብሎ መለሰለት መኰንኑም ሕፃኑን "ሳልጠይቅህ ይህን ያህል ትመልስልኛለህን?" አለው። ሕፃኑም "ገና ከዚህ የሚበዛ ነገርን እመልስልሃለሁ" አለው።
መኰንኑም ሕፃኑን "ስምህ ማን ነው?" አለው። "ከንጹሕ ዐዘቅትና ከማይለወጥ ከማይጠፋ ውኃ የተገኘ ሕፃን ስሜ ክርስቲያን መባል ነው" ብሎ መለሰለት። መኰንኑም "ዳግመኛ እንዳትሞት ስምህን ንገረኝ" አለው። የከበረ ሕፃንም "ስሜ ክርስቲያን መባል እንደሆነ ነገርኩህ ሞክሼ ስም የምትሻ ከሆነ እናቴ የሰየመችኝ ቂርቆስ ነው።"
መኰንኑም ሕፃን ቂርቆስን "እሺ በለኝና ለአማልክት ሠዋ በሥጋህም ስታድግ እሾምሃለሁ በብዙ ወርቅና ብርም አከብርሃለሁ" አለው። ሕፃኑም "የሰይጣን መልእክተኛ ለዕውነትም ጠላቷ የሆንክ ከእኔ ራቅ" አለው።
መኰንኑም ሰምቶ ተቆጣ ደሙ እንደ ውኃ እስከሚፈስ ቆዳውን እንዲጨምቁትና እንዲገፉት አዘዘ። የከበረች ኢየሉጣም የልጅዋን ትዕግሥት ባየች ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነችው።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ ጨውና ሰናፍጭ አምጡ አለ የሁለቱንም አፍንጮቻቸውን ከፍተው ያንን ጨውና ሰናፍጭ እንዲጨምሩባቸው አዘዘ ያን ጊዜ ሕፃኑ ትእዛዝህ ለጕረሮዬ ጣፋጭ ሆነ ከማርና ከስኳርም ለአፌ ጣመኝ ብሎ ጮኸ።
ሁለተኛም መኰንኑ እንዲህ ብሎ አዘዘ የረዘሙና የተሳሉ በእሳትም እንደ ፍም የጋሉ ዐሥራ አራት የብረት ችንካሮች አምጡ ሰባቱን በእናቱ አካላት ውስጥ ጨምሩ በሕፃኑም ሁለት በጆሮዎቹ ሁለት በዐይኖቹ ሁለት በአፉና በአፍንጫው አንድ በልቡ ጨምሩ እንዲህ ሲጨመርበት ጆሮዎቹ እንዲያኖሩ ዐይኖቹም ይጠፉ ዘንድ አንደበቱም ይቃጠል ዘንድ ወደ ልቡም ጽኑ ሕማም ገብቶ እርሱ ከዚህ ዓለም በሞት እንዲለይ ለእናቱም እንዲሁ አድርጉ። ችንካሮችም በቅዱሳኑ በሥጋቸው ሁሉ ተጨመሩ።
የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ትእዛዝ የብረቶቹ ግለት ጠፍቶ እንደ በረዶ ቀዘቀዘ ጤነኞችም ሆኑ መኰንኑም ወደ ወህኒ ወስዳችሁ በዚያ አሥራችሁ ዝጉባቸው አለ።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ የሥቃይ መሣሪያ ይሠራ ዘንድ አንዳዝዘው ብረትን የሚያቀልጥ ሰው አምጡልኝ አለ። በአመጡለትም ጊዜ ሰይጣኑ ወደ መኰንኑ ልብ ገብቶ አንደበቱን ዘጋውና መናገር ተሳነው ሕፃኑ ፈጥኖ አክሊልን ለመቀበል እንደሚተጋ ሰይጣን ስለ አወቀ ስለዚህ ዘጋው።
ከዚህም በኋላ ሕፃኑ ሠራተኛውን ጠርቶ እኔንና እናቴን የሚያሠቃዩበትን የሥቃይ መሣሪያ መሥራት ትችላለህን ይህ መኰንን ግን ምንም የሚያውቀው ነገር የለም አለው ሠራተኛውም እንደምትሻው በል ንገረኝ እንደምታዝዘኝ እኔ መሥራት እችላለሁ አለው።
ሕፃን ቂርቆስም ሊአዝዝ ጀመረ እንዲህም አለ ሁለት መላጫዎች ስፋታቸው አራት ክንድ የሆነ ለእኔና ለእናቴ ሥራ። ዳግመኛም የሚያስጨንቅ ራስን የሚመታና የሚሰብር አንገትንም የሚያሥር የሚዝቅም ሹካ ዐይንንም የሚያወልቅ አካልንም የሚበሳሳ አፍንጫንም የሚያጣምምና የሚሰብር ጆሮንም የሚልጥ ሕዋሳትን የሚፈታና የሚለያይ እንደ ልጓም ሁኖ ምላስን የሚቆርጥ በሰውነትም ውስጥ ገብቶ የሚንቀሳቀስ ቆላፋ ጉጠትን ጐኖችንም የሚፍቅና የሚቆለምም አስጨናቂ የሆነ ጉልበቶችንና ጭኖችን የሚሰብር ጅማቶችንም የሚቆራርጥ ሥሮችንም የሚመዝ በዚችም አስጨናቂ መሣሪያ ጅማቶችን የሚታታ አድርግ።
ዳግመኛም በላም አምሳል ሰፊ መቀመጫ ከናስ ሥራ ሦስት ቀዳዳዎችንም በዚያ መቀመጫ ውስጥ ቅደድ። በቁመቴም ልክ ሦስት ችንካሮችን ሥራ የችንካሮቹንም ራስ ከናስ አድርገህ በውስጡ ከሚጠሩት ዘንድ ፈጽሞ የማይለይ ልዩ ሦስት ብለህ ጻፍ።
ዳግመኛም ጠምዝዞ ወደ ላይ የሚያወጣ ሁለት መሣሪያ ሁለት መጋዞችን ሁለት የብረት ምጣዶችን ሥራ አሁንም አንድ ታላቅ ጋን ሠርተህ በውስጡ አንገትን የሚጠመዝዝና የሚሠነጥቅ ተሽከርካሪ መሣሪያ አድርግ።
በውስጥ የተሸሸገ የሆድ ዕቃን የሚመረምር እጅን ከብረት ሥራ እኔ የጻዕር ስቃይን የምሠቃይበት ይህ ነው አለ። ብረት ሠሪውም ሰምቶ እጅግ አደነቀ የሚረዱትንም ከሀገር ውስጥ መቶ ሠራተኞችን ሰብስቦ መሥራት ጀመረ በአርባ ቀንም ጨረሰ።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ እለእስክንድሮስ ቂርቆስንና እናቱን ወደ አደባባይ ያመጡአቸው ዘንድ አዘዘ ያን ጊዜ አንደበቱ ተፈትቶ ነበርና እንዲህም አለ ሕፃኑንና እናቱን ከቆዳቸው ጋር ራሳቸውን ላጩአቸውና በላያቸው የእሳት ፍሞችን ጨምሩ እርር ብለው እንዲቃጠሉ ዳግመኛም አራት ችንካሮችን ከትከሻዎቹ እስከ ተረከዙ ድረስ እንዲተክሉበት አዘዘ የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ ሥቃዮችን ከርሱ አራቀ።
ዳግመኛም ከጥዋት እስከ ማታ ከሥቃይ መሣሪያዎች ውስጥ ጨምረው አዋሏቸው ግን ማሠቃየት ተሳናቸው። ከዚህም በኋላ ከማምጠቂያው ውስጥ ጨምረው መገዙአቸውና አመድ እስከሆኑ ከቅባትና ከጨው ጋር በብረት ምጣድ ውስጥ ቆሉአቸው ጌታችንም ከሞት አስነሥቶ አዳናቸው።
ወደ መኰንኑም በገቡ ጊዜ እንዲህ አላቸው በእውነት ከሙታን ተለይታችሁ የተነሣችሁ ከሆነ ይህ ጫማዬ ከእግሬ ወጥቶ እንደ ቀድሞው ሕያው እንዲሆን አድርጉ ሕፃን ቂርቆስም በጸለየ ጊዜ ያ ጫማ ታለቅ በሬ ሆነ ከአንገቱም ፍየል ወጣ።
በዚያንም ሰዓት ለዐሣራ አንድ ሽህ አራት ሰዎች በሬውንና ፍየሉን አርደው ምሳ እንዲአደርጉላቸው መኰንኑ አዘዘ እንዲህም አለ ይህ በቅቷቸው ከጠገቡ ከዚህም ሌላ ምግብ ካልፈለጉ የተሠራው ሁሉ ዕውነተኛ ነዋሪ ነው። ከዚህም በኋላ አርደው ምሳ አደረጉላቸውና ከፍየሉ ሥጋ ስድስት እንቅብ ከበሬው ሥጋ አራት እንቅብ አተረፉ መኰንኑም የተረፈውን ሥጋ አይቶ ወደ ባሕር እንዲጥሉት አዘዘ።
መኰንኑም ቢያፍር የሕፃኑን ምላስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ጌታችንም ምላሱን መለሰለት። ዳግመኛም በታላቅ ጋን ውኃ እፍልተው ሕፃን ቂርቆስንና እናቱን ኢየሉጣን ይጨምሩአቸው ዘንድ አዘዘ። እናቱም አይታ ፈራች። ልጅዋም ወደ እግዚአብሔር በጸለየላት ጊዜ አምላካዊ ኃይልን አሳደረባትና ከልጅዋ ጋር ወደ ጋኑ ገባች። እንደ ውርጭም ቀዝቀዛ ሆነ ደግሞም በውስጡ መንኰራኲር ወዳለበት የብረት ምጣድ እንዲጨምሯቸውና ሥጋቸው እሰከሚቦጫጨቅ እንዲስቡአቸው አዘዘ የእግዚአብሔርም መልአክ በሕይወት አወጣቸው።
መኰንኑም እነርሱን ማሸነፍ በተሳነው ጌዜ ቸብቸቧቸውን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። በዚያን ጊዜ ለስም አጠራሩ ስግደት የሚገባው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወረደ ሕፃን ቂርቆስንም የምትሻውን ለምነኝ አለው።
ሕፃኑም ሥጋዬ በምድር አይቀበር ስሜን ለሚጠራ መታሰቢያዬን ለሚያደርግ ቤተ ክርስቲያኔን ለሚሠራ የተጋድሎዬን መጽሐፍ ለሚጽፍና ለሚያጽፍ ወይም ለሚያነበው ለቤተ ክርስቲያኔ መባ ለሚያገባ በውስጧም ለሚጸልይ ለሁሉም ፍላጎታቸውን ስጣቸው። ኃጢአታቸውንም ይቅር በል ስሜም በሚጠራበት በዚያች ቦታ የከብት ዕልቂት አይምጣ፤ በሰውም ላይ እባር ቸነፈር በእህልም ላይ ድርቅ የውኃም ማነስ አይሁን።
መድኃኒታችንም የለመንከኝን ሁሉ እሰጥሃለሁ አንተም በቀኜ ትኖራለህ ሥጋህንም ኤልያስ በዐረገበት ሠረገላ ውስጥ አኖራለሁ አለው። ሕፃን ቂርቆስም በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት ጌታችንን አመሰገነው። ከዚህም በኋላ በሌሊቱ እኩሌታም ከእናቱ ጋር አንገቱን ተቆረጠ መድኃኒታችንም በማይጠፋ አክሊል ጋረደው ነፍሶቻቸውንም በታላቅ ክብር ከእርሱ ጋር አሳደገ።

በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስልሳ አንደኛ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ሁለተኛው ሚናስ አረፈ።
ይህን ቅዱስ ሚናስንም በታናሽነቱ ያለ ፍላጎቱ ወላጆቹ ሚስት አጋቡት ትእዛዛቸውን መተላለፍ ስለአልፈለገ የጋብቻውን ሥርዓት ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ፈጸመ። ለርሱ ይህ ሁሉ ሕልም ይመስለው ነበር ወደ ሙሽሪትም ወደ አዳራሽ በአስገቡት ጊዜ ተቀምጦ እንዲህ ብሎ ተናገራት እኅቴ ሆይ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ካጠፋ ምን ይጠቅመዋል እንደ ተጻፈ ሁሉ ያልፋልና ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ለዘላለሙ ይኖራል አሁንም ድንግልናችንን እንድንጠብቅ ነይ ቃል ኪዳን እናድርግ እርሷም ቃሉን ተቀብላ ከእርሱ ጋር ተስማማች።
ከዚህም በኋላ ትቷት ወደ አስቄጥስ ገዳም ሒዶ በአባ መቃርስ ገዳም ውስጥ መነኰሰ ብዙ ዘመናትም በገድል ተጠምዶ ኖረ። ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳትም በአረፈ ጊዜ ይህን ቅዱስ አባት ሚናስን ያለውዴታው ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በወንጌላዊ ማርቆስም ወንበር ላይ መንጋዎቹን በቅን ፍርድ እየጠበቃቸው እያስተማራቸውም ዐሥራ ስምንት ዓመት ኑሮ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages