ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 16 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, December 9, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 16

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን የቅዱስ_አቡናፍር ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው፣ የእስክንድርያ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_ዮሐንስ ያረፈበት ነው፣ ቅዱስ_ኪስጦስ በሰማዕትነት ያረፈበት ነው፣ ቅድስት_ጣጡስ በሰማዕትነት ያረፈችበት ነው፣ የመነኰስ አባ_ዳንኤልና_የንጉሥ_አኖሬዎስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው።


ይኸውም ቅዱስ አቡናፍር ጥቂት የሰሌን ፍሬዎችን ብቻ እየተመገበ በበረሃ ውስጥ 60 ዓመት የኖረ ታላቅ ጻድቅ ነው፡፡ በእነዚህ ድፍን 60 ዓመታት ውስጥ ከቶ የሰውን ፊት አላየም፡፡ ዛሬ ከምስር ከተማ ውጪ የተሠራች ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ዕለት ነው፡፡
አቡነ አቡናፍር መልካም ሽምግልና ያለው ስም አጠራሩ የከበረ በገዳም የሚኖርና በገድል የተጠመደ አባት ነው፡፡ ከላይኛው ግብፅ የተገኘ ሲሆን ታሪኩን የተናገረለት ጻዲቁ አባ በፍኑትዮስ ነው፡፡ ይኸውም አባ በፍኑትዮስ ወደ በረሃ ውስጥ በገባ ጊዜ አንዲት የውኃ ምንጭና አንዲት የሰሌን ምንጣፍ አግኝቶ በዚያ እየተጋደለ ብዙ ዘመን የኖረ ነው፡፡
በአንዲት ዕለት አባ በፍኑትዮስ ወደ እርሱ ሲመጣ አባ አቡናፍር አየው፡፡ አባ በፍኑትዮስም የሰይጣንን ምትሐት የሚያይ መስሎት ደነገጠ፡፡ አባ አቡናፍር ፀጉሩና ጽሕሙ ሰውነቱን ሁሉ ሸፍኖታል እንጂ በላዩ ላይ ልብስ አልነበረውም፡፡ አባ በፍኑትዮስንም በመስቀል ምልክት ባርኮ አጽናናው፡፡ አቡነ ዘበሰማያትንም ከጸለየ በኋላ ‹‹አባ በፍኑትዮስ ሆይ ወደዚህ መምጣትህ መልካም ነው›› ብሎ በስሙ ከጠራው በኋላ ፍርሃቱን አራቀለት፡፡
ከዚህም በኋላ ሁለቱም በጋራ ጸልየው የእግዚአብሔርን ገናናነት እየተነጋገሩ ተቀመጡ፡፡ አባ በፍኑትዮስም አኗኗሩንና እንዴት ወደዚህ በረሃ እንደመጣ ታሪኩን ይነግረው ዘንድ አባ አቡናፍርን ለመነው፡፡ አባ አቡናፍርም ታሪኩን እንዲህ ብሎ ነገረው፡- "እኔ ደጋጎች እውነተኞች መነኮሳት በሚኖሩበት ገዳም ውስጥ እኖር ነበር፡፡ የገዳማውያንን ልዕልናቸውን ሲናገሩ ሲያመሰግኗቸውም ሰማሁ፡፡ እኔም ‹ከእናንተ የሚሻሉ አሉን?› ብዬ ጠየኳቸው፡፡ እነርሱም ‹አዎን እነርሱ በበረሃ የሚኖሩ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበሩ ናቸው፤ እኛ ለዓለም የቀረብን ስለሆንን ብንተክዝና ብናዝን የሚያረጋጋን እናገኛለን ብንታመም የሚጠይቀንና የፈለግነውን ሁሉ እናገኛለን፣ በበረሃ የሚኖሩ ግን ከዚህ ሁሉ የራቁ ናቸው› አሉኝ፡፡ ይህንንም ስሰማ ልቤ እንደ እሳት ነደደና ወደ ፈቀደው መንገድ ይመራኝ ዘንድ በእኩለ ሌሊት ተነሥቼ ጸለይኩ፡፡ ከዚህም በኋላ ተነሥቼ ወጥቼ ስጓዝ አንድ አባት አገኘሁና የገዳማውያንን ገድላቸውን እያስተማረኝ ከእርሱ
ጋር ተቀመጥኩኝ፡፡ ከዚያም ወደዚህ ቦታ ደረስኩ፡፡ እግዚአብሔር ያዘጋጀልኝን ይህችን ሰሌን አገኘኋት፡፡ በየዓመቱ 12 ዘለላ ታፈራለች፤ ለየወሩም የምመገበው አንዱ ዘለላ ይበቃኛል ውኃም ከዚህች ምንጭ እጠጣለሁ፡፡ በዚህችም በረሃ እስከዛሬ 60 ዓመት ኖርኩ፡፡ ከአንተም በቀር የሰው ፊት ከቶ አይቼ አላውቅም" ብሎ አቡነ አቡናፍር ጣፋጭ ታሪኩን በዝርዝር ነገረው፡፡ ይህንንም ሲነጋገሩ የታዘዘ መልአክ መጥቶ የጌታችንን ሥጋና ደም አምጥቶ አቆረባቸው፡፡ ቀጥለውም ጥቂት የሰሌን ፍሬ ተመገቡ፡፡ ወዲያውም የአቡነ አቡናፍር መልኩ ተለወጠ፤ እንደ እሳትም ሆነ፡፡ ወደ እግዚአብሔርም በተመስጦ እየጸለየ ሳለ ቅድስት ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፡፡
አቡነ በፍኑትዮስም በፀጉር ልብሱ በክብር ገንዞ ቀበረው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ በፍኑትዮስ በዚያች ቦታ ይኖር ዘንድ ወደደ ነገር ግን ያቺ የሰሌን ዛፍ ወደቀች፤ የውኃዋም ምንጭ ደረቀች፡፡ አባ በፍኑትዮስም ወደ ዓለም ተመልሶ የገዳማውያንን ዜና ይልቁንም የአባ አቡናፍርን ዜና ይሰብክ ዘንድ የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆነ፡፡
የአቡነ አቡናፍር ዕረፍታቸው ሰኔ 16 ቀን ነው፡፡ ኅዳር 16 ደግሞ ከምስር ከተማ ውጪ የተሠራች ቤተ ክርስቲያናቸው የከበረችበት ዕለት ነው፡፡

በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ስምንተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት አባ ዮሐንስ አረፈ። ይህም ቅዱስ አባት የቆጵሮስ ሀገር ሰው ነው እጅግም ባለጸጋ ነው በእስክንድርያ አገርም የሚኖር ሆነ አባቱ አገረ ገዥ ነበርና ሚስትም አግብቶ ልጆችን ወለደ ከዚህም በኋላ ሚስቱም ልጆቹም ሞቱ።
በዚያንም ጊዜ ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጠ መጸወተ እርሱም መንኵሶ በታላቅ ገድል የተጠመደ ሁኖ በጎ ሥራዎችን ትሩፋትን ጨምሮ በመሥራት እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው።
ከበጎ ሥራዎቹና ከትሩፋቱም ከቀናች ሃይማኖቱ ከአገልግሎቱና ከደግነቱ ከጽድቁ ማማር የተነሣ በግብጽ አገር የሚኖሩ ኤጲስቆጶሳት ሁሉም ተሰማምተው ይዘው ወሰዱት ያለ ፈቃዱም በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙትና በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ላይ አስቀመጡት ። ያን ጊዜ የከበረ ወንጌልን አነበበ በሹመቱና በክህነቱም ብርሃን ተገለጸ ብዙዎች ድንቆች የሆኑ ተአምራትንም አደረገ።
ለድኆችና ለችግረኞች ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የሚሹትን የሚሰጣቸው ሆነ ስለዚህም የሚራራ ዮሐንስ ተብሎ ተጠራ ። በአይሁድና በአረማውያን ዘንድ የሚአስፈራ ሆነ በመጸሐፈ ገድሉ እንደተጻፈ እጅግ ይፈሩትና ያከብሩት ነበርና መንጋዎቹንም በበጎ አጠባበቅ ጠበቃቸው እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

በዚችም ቀን ቅዱስ ኪስጦስ በመኰንኑ በመክሲሞስ እጅ በሰማዕትነት አረፈ ። ይህንንም ቅዱስ ኪስጦስን መኰንኑ በያዘው ጊዜ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጠ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

በዚችም ዕለት በሮሜ አገር በከሀዲ መኰንን በእስክንድሮስ እጅ ቅድስት ጣጡስ በሰማዕትነት አረፈች። ወደርሱም በአቀረቧት ጊዜ እስክንድሮስ ለአማልክት ሠዊ አላት እርሷም ከፈጠረኝ ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር አልሠዋም ብላ መለሰች።
መኰንኑም የፊቷን መሸፈኛ እንዲገልጡ አዘዘ ውበቷንም አይቶ አደነቀ ዐይኖቿ እንደ አጥቢያ ኮከብ ናቸውና ቁመቷም እንደ ዘንባባ ደም ግባቷም እንደ ጽጌረዳ ነው በዚያንም ወራት የሚመሳሰላት የለም ነበር።
ንጉሡም በአያት ጊዜ እርሷን በመውደዱ ልቡ ተነጠቀ እንዲህም አላት እሺ በይኝና ለታላቅ አምላክ ለአጵሎን ሠዊ እኔም ለቤተ መንግሥቴ እመቤት አደርግሻለሁ አላት። ቅድስት ጣጡስም እኔ ክብር ይግባውና ከክርስቶስ ከመንጋዎቹ ውስጥ ነኝ ከእርሱ በቀር ለሌላ አልሠዋም ነገር ግን ወደ አማልክቶችህ መሠዊያ ቤት ገብቼ ኃይላቸውን እንዳይ ፍቀድልኝ አለችው።
በዚያንም ጊዜ ወሰዷት በገባችም ጊዜ ጣዖታቱ ይጠፉ ዘንድ ክብር ይግባውና የኃይል ባለቤት ወደ ሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየች ወዲያውኑ ንውጽውጽታ ሁኖ ጣዖታቱ ከመቀመጫቸው ወድቀው ተሰባበሩ ታላቁ አምላካቸው አጵሎንም ቊልቊል ወድቆ ተቀጠቀጠ ከጣዖቱ አገልጋዮችም ብዙዎች ሞቱ በአጵሎን ላይ አድሮ የሚኖር ርኩስ መንፈስ እንዲህ ብሎ ጮኸ።
ጣጡስ ሆይ እኔ ካንቺ ምን አለኝ አንቺስ ከእኔ ምን አለሽ እነሆ ማደሪያዬን ቀጥቅጠሽ ከእርሱ አውጥተሽኛልና ንጉሡም ይህን አይቶ ተቆጣ በግምባርዋ ደፍተው በበትሮች እንዲደበድቧት በአለንጋዎችም እንዲገርፏት አዘዘ። ከሥጋዋም በወተት አምሳል ነጭ ደም ፈሰሰ ወደ እግዚአብሔርም በለመነች ጊዜ የሚደበድቧትን የእግዚአብሔር መላእክት የሚያሠቃዩአቸው ሆኑ ቅድስት ጣጡስን ግን ሥቃያቸው የማይነካት ሆነ።
ሁለተኛዋም ለተራበ አንበሳ እንዲሰጧት ንጉሡ አዘዘ። አንበሳውም በደረሰ ጊዜ በፊቷ ሰገደ የእግሮቿንም ትቢያ ላሰ ከሰማይም እኔ ካንቺ ጋር ነኝና ንጽሕት ጣጡስ ሆይ ደስ ይበልሽ የሚል ቃል መጣ። ንጉሡም ከክፉ ነገር የደረሰባት እንደሌለ አይቶ ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ ተጋድሎዋንም ፈጸመች።
በሌሊትም የሮሜ ጳጳስ መጥቶ በከበሩ ልብሶች ገነዛት በወርቅና በብር ከተለበጠ የእብነ በረድ ሣጥን ውስጥ ጨመራትና በአማረ ቦታ አኖራት ከሥጋዋም ብዙዎች ተአምራቶች ተገለጡ።

በዚህችም ዕለት የመነኰስ አባ ዳንኤልና የንጉሥ አኖሬዎስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው። ይህ አባ ዳንኤል ታላቅ ገድለኛ ነው እንጀራን ዓሣንም ቢሆን ማርንም ዘይትንም ቢሆን ከብቻው ቅጠል በቀር ሳይቀምስ አርባ ዓመት ተኩል በአስቄጥስ ገዳም ኖረ።
ከብዙ ዘመንም በኋላ የመመካት ኀሳብ መጣበት በልቡም እንደእኔ ትርሕምትን መቆምን የታገሠ በገዳም በውኑ አለን አለ ። ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ብርሃናዊ መልአኩን ላከለት መልአኩም ዳንኤል ሆይ በጎ ያልሆነ እንዲህ ያለ ትምክህትን ለምን ትመካለህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትሕትና በቀር ትምክህትን አይሻምና አለው።
አባ ዳንኤልም መልአኩን ጌታዬ ከኔ የሚሻል ካለ ንገረኝ ወደርሱ ሒጄ አየው ዘንድ በመመካቴም ወደ ፈጣሪዬ እለማመጥ ዘንድ አለው መልአኩም ንጹህ ቅዱስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የሮሜና የቁስጥንጥንያ ንጉሥ አኖሬዎስ በመንግሥተ ሰማያት ባልንጀራህ ነው አለው።
አባ ዳንኤልም በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ተደፋ በራሱም ላይ አመድ ነስንሶ ክብር ይግባውና በአምላካዊ ጥበብ ወደ ሮሜ አገር አድርሶ እርሱን አኖሬዎስን ያሳየው ዘንድ ጌታችንን ለመነው።
እንዲህ ሲጸልይም ደመና መጣች ተሸከመችውና ከሮሜ ንጉሥ ከአኖረዎስ ቤተ መንግሥት ደጅ አደረሰችው የንጉሥ አኖሬዎስንም ረዳት አገኘው ረድኡም እጅ ነስቶ ከእርሱ ቡራኬ ተቀበለና አባቴ ሆይ ወደዚህ የመጣህበት ጉዳይህ ምንድን ነው አለው ።
አባ ዳንኤልም ልጄ ሆይ የሚቻልህ ከሆነ ከሀገር መኳንንት ወዳንዱ አድርሰኝና ወደ ንጉሡ እንዲአስገባኝ አለው ። ረዳቱም እኔ ባስገባህ መግባትን አትሻምን አለው ልጄ ሆይ እሻለሁ አስገባኝ እግዚአብሔር ይባርክህ አለው ። ዳግመኛም ረድኡ አባቴ ሆይ ሟች የሆነ ንጉሥን በማየት ምን ታገኛለህ አለው አባ ዳንኤልም ፈጣሪዬ ባያዘኝ ወደዚህ ባልመጣሁ ነበር አለው ረዳቱም ለጌታዬ የሚያሻውን እስከምገዛ ጥቂት ታገሠኝ አለው ።
በዚያንም ጊዜ አምባሻ ጨውና መጻጻ የጎመን ቅጠልም ገዝቶ ወደ ጌታው ወደ ንጉሡና ወደ መምህሩ አውሎጊስ ወሰደ አባ ዳንኤልንም በውጭ ተወው ። ንጉሡም ረዳቱን አንተ አላዋቂ ነህን አባ ዳንኤልን በውጭ የምታስቆመው አለው ይህንንም ብሎ ንጉሡ ከመምህሩ ከአውሎጊስ ጋር ወጣ ለአባ ዳንኤልም ሰገዱለት ሰላምታም ተሰጣጥተው ወደ ቤተ መንግሥት አስገቡትና በአንድነት ተቀመጡ ።
ዘጠኝ ሰዓትም በሆነ ጊዜ ረዳቱ የሚበሉትን አቀረበላቸው በአንድነትም ተነሥተው ጸለዩ አባ ዳንኤልም እንዳይታመም እንጀራ መብላትን ፈርቶ ጌቶቼ እንጀራ ባለመብላቴ በእኔ ላይ አታጒረምርሙ እንዳልታመም ፈርቼ ነው እንጂ በትዕቢት አይደለም አላቸው ። ቅጠልንም ሰጡት ማዕዳቸውንም ፈጽመው ጸሎትን ጸለዩ ከዚህም በኋላ ንጉሥ አኖሬዎስ አባ ዳንኤልን ስለ አመጣጡ መረመረው አባ ዳንኤልም ወንድሜ ሆይ የሚቻልህስ ከሆነ ወደ ንጉሡ አሰገባኝ በጌታ ክርስቶስ ትእዛዝ መጥቻለሁንና አለው ንጉሡም ነገ አስገባሃለሁ አለው ።
በማግሥቱም አኖሬዎስ ዐይን የሚበዘብዝ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ አባ ዳንኤልንም አስገቡት በአየውም ጊዜ ፈርቶ ተንቀጠቀጠ ረዳቱም መፍራቱን አይቶ ወደ ማደሪያው መለሰው ንጉሡም ችሎቱን ሲጨርስ ልብሰ መንግሥቱን ጥሎ የምንኲስናውን ልብስ ለብሶ አባ ዳንኤል ወዳለበት ገባ አባ ዳንኤልም በአየው ጊዜ ወንድሜ ሆይ በልቤ ያለውን ነግሬው ወደ ቦታዬ እመለስ ዘንድ ወደ ንጉሥ ለምን አላስገባኝም አለው አኖሬዎስም አባቴ ሆይ አልገባህምን ለዚች ምድር ንጉሥ ብለው የሰየሙኝ በኃላፊ ዙፍንም ላይ ተቀምጨ ያየኸኝ እኔ አኖሬዎስ ነኝ አለው።
አባ ዳንኤልም በሰማ ጊዜ ከእግሩ በታች ሰገደለት አኗኗሩን ሁሉ ይነግረው ዘንድ ክብር ይግባውና በጌታችን ስም አማፀነው ንጉሥ አኖሬዎስም በእጅ ሥራው ደክሞ ከሚያገኘው በቀር ይህም ሰሌን መታታት ነው ሳይበላ ሳይለብስ አርባ ዓመት እንደሆነው የሚተርፈውንም ለድኆች እንደሚሰጥ ምግቡም እንጀራና ጨው ቅጠል መጻጻ እንደሆነ የማንንም ገንዘብ ለመቀማት እዳልደፈረ ድንግልናውንም እንደጠበቀ ነገረው።
አባ ዳንኤልም ከእግሩ በታች ወድቆ በአንተ ላይ ስለተመካሁ ይቅር በለኝ አለው ከዚህም በኋላ አባ ዳንኤል ፈጽሞ እያዘነ ወደ ቦታው ተመለሰ።
ከሁለት ወሮችም በኋላ መምህሩ አውሎጊስን ተሰናብቶ አኖሬዎስ ከቤተ መንግሥቱ ውስጥ ወጣ እግዚአብሔርም መልአኩን ላከለትና ተሸክሞ ወደ አባ ዳንኤል አደረሰው። በተጋድሎም በመጠመድ ኑረው ገድላቸውንም ፈጸመው በአንዲት ዕለት አረፉ። እንዲሁም አውሎጊስና ረዳቱ በዚያች ዕለት በአንድነት አረፉ።
ለእግዚአብሔርም ምሰጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages