አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የካቲት ዐሥራ ሦስት በዚች ቀን የከበረ #ቅዱስ_ሰርግዮስ በሰማዕትነት ሞተ፣ የእስክንድርያ አገር #ሊቀ_ጳጳሳት_ጢሞቴዎስ አረፈ፣ ለሶርያ መስፍን ልጁ የሆነ ለተመሰገነ ለሁለተኛው #ቅዱስ_አውሳብዮስ የምስክርነቱና የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ ታላቁ ሰማዕት #ቅዱስ_ፊቅጦር የተወለደበት ነው፡፡
የካቲት ዐሥራ ሦስት በዚች ቀን የከበረ ሰርግዮስ በሰማዕትነት ሞተ አባትና እናቱ ወንድሞቹም ከእርሱ ጋር ሌሎችም ብዙ ሰዎች ሞቱ። የዚህም ቅዱስ ሰርግዮስ አባትና እናቱ ደጎች ናቸው ።
የአባቱ ስም ቴዎድሮስ የእናቱ ስም ማርያም ነው ዕድሜውም ሃያ ዓመት ሲሆነው በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ይሞት ዘንድ በልቡ አሰበ ወደ መኰንኑ ቆጵርያኖስም ቀርቦ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመነ፣
መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን ያሠቃዩት ዘንድ ያሥሩትም ዘንድ አዘዘ ጌታችንም ነፍሱን ወደ ሰማይ አምጥቀው የቅዱሳን ሰማዕታትን መኖሪያ ያሳዩዋት ዘንድ አዘዘ አይታም ተጽናናች ከሥቃይ ከሕማሙም ፈወሰው።
ቀሲስ አባ መጹንና ሁለት ዲያቆናትም ተጋድሎውን ሰሙ ያን ጊዜም ተነሥተው ወደ አትሪብ አገር ገዥ ቀርበው በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ታመኑ የጸና ግርፋትንም ይገርፋአቸው ዘንድ አዘዘ እንዲሁም አደረጉባቸው። ሕዝቡም ሁሉ በዙሪቸው ሆነው ይመለከቷቸው ነበር ስለ ቄሱና ከእርሱ ጋር ስላሉትም አዘኑ ቄሱ ግን ፊቱን ወደርሳቸው መልሶ ገሠጻቸው አስተማራቸውም በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በቀናች ሃይማኖት እንዲህ ጽኑ አላቸው።
ከዚህም በኋላ በውኃ ላይ ጸለዮ በላያቸው ረጨ በዚያንም ጊዜ በላያቸው ወርዶአልና የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብለው በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ራሶቻቸውንም በሰይፍ ቆረጧቸው የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥት ሰማያት ተቀበሉ።
ከዚህም በኋላ ቄሱን ከውሽባ ቤት ማንደጃ ውስጥ ይጨምሩት ዘንድ መኰንኑ አዘዘ እግዚአብሔርም ከእሳት አዳነው። ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ተገለጠለትና እርሱ ስለ ክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ሦስት ጊዜ ምስክር እንደሚሆን አስረዳው ከእሳት ማንደጃው ውስጥም አወጣው። መኰንኑም ወደ እስክንድርያ ሀገር ላከው ተጋድሎውንና ምስክርነቱን በዚያ ፈጸመ የምስክርነቱን አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ከዚህ በኋላ መኰንኑ ቆጵርያኖስ የከበረ ስርግዮስን ያቀርቡት ዘንድ አዘዘ ታላቅ ሥቃይንም አሠቃየው የነሐስ መንኰራኩሮችንም አምጥተው ከውስጣቸው አሰገብተው አበራዩት ሕዋሳቱም አራት ክፍል ሁኖ ሥጋው ሁሉ ተቆራረጠ ጌታችንም አድኖ ያለ ጉዳት በጤና አስነሣው።
ዳግመኛም እንዲሰግድለት ጣዖትን አመጡ ቅዱሱ ግን ሲረግጠው ወድቆ ተቀጥቅጦ ደቀቀ መኰንን ቆጵርያኖስም አይቶ በክብር ባለቤት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አመነ አምላክ ቢሆን ራሱን ማዳን በቻለ ነበር አለ።
ከዚህም በኋላ የጭፍራ አለቃ ስሙ አውህዮስ የሚባል የከበረ ሰርግዮስን ፈልጎ ያዘው ቆዳውንም ገፈው በተቀላቀለ ኮምጣጤና ጨው ቁስሉን ያሹት ዘንድ አዘዘ ጌታችን ግን በሥቃዮች ላይ ያጸናውና ያበረታው ነበር።
እናቱና እኅቱም ሰምተው ወደርሱ መጡ በአዩትም ጊዜ በላዩ አለቀሱ ከኀዘንም ብዛት እኅቱ ነፍሷን አሳለፈች የከበረ ሰርግዮስም ስለ እኅቱ ወደ ጌታችን ጸለየ ከሞትም ድና በሕይወት ተነሣች።
ያን ጊዜ የሰማዕታትን ገድል የሚጽፍ የአቅፋሐስ ሀገር ሰው የከበረ ዮልዮስ መጣ ገድሉንም ሁሉ ከእርሱ ተረዳ ለሥጋውም እንደሚአስብ ቃል ገባለት ።
ከዚህም በኋላ ደግሞ የከበረ ሰርግዮስን በመንኰራኩር ውስጥ ያሠቃዩት ዘንድ በጆሮዎቹ የእሳት መብራቶችን እንዲጨምሩ የእጆቹንና የእግሮቹን ጥፍሮች እንዲነቅሉ በአንገቱም ከባድ ደንጊያ አንጠልጥለው ከብረት ዐልጋ ላይ አስተኝተው ከበታቹ እሳትን እንዲያነዱ አውህዮስ አዘዘ እንዳዘዘውም አደረጉበት ጌታችን ኢየሱስም ያጸናውና ያለ ጥፋት በጤና ያስነሣው ነበር።
የሠራዊት አለቃ አውህዮስም ማሠቃየቱን በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ የከበረ ሰርግዮስም ሰምቶ እጅግ ደስ አለው ወደ አባቱና ወደ እናቱ ወደ ወንድሞቹም ላከ ዘመዶቹ ሁሉም የእርሱ የሆኑ ሰዎችም መጡ በአፉም ልጓም ለጉመው ቸብቸቦውን ወደሚቆርጡበት ሲስቡት አገኙትና መኰንኑን የረከሱ ጣዖታቱንም ረገሙ መኰንኑም ከከበረ ሰርግዮስ ጋር ሁሉንም ቸብቸቧቸውን እንዲቆርጡ አዘዘ በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።
እንዲህም ሆነ ከሕዝቡ ውስጥ አንድ ታናሽ ሕፃን እግዚአብሔር ዐይኖቹን ገልጦለት የቅዱሳን ሰማዕታትን ነፍሶቻቸውን መላእክት ወደ ሰማያት ሲያወጧቸው አይቶ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ይቅር በለኝ እያለ በከፍተኛ ቃል ጮኸ ። እናትና አባቱም መኰንኑ ሰምቶ ስለርሱ እንዳያጠፋቸው አፉን የሚዘጉ ሆኑ እርሱ ግን እንዲህ እያለ መጮኹን አልተወም በላዩ እስከ ተኙበትና ነፍሱን እስከ አሳለፈ ድረስ ከሰማዕታትም ጋር የምስክርነት አክሊልን ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት የከበረ አባት የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ጢሞቴዎስ አረፈ። እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ ሁለተኛ ነው። ይህንንም አባት ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ መከራና ችግር ደርሶበታል ። እንዲህም ሆነ በዚያ ወራት የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስ ወደ ግብጽ አገር መጣ እርሱም ከዚህ አባት ጢሞቴዎስ ጋር ምእመናንን እያ
ጽናና ከሀገር ወደ ሀገር ከገዳም ወደ ገዳም ከቦታ ወደ ቦታ የሚዘዋወር ሆነ።
በዚህም አባት ጢሞቴዎስ ዘመን ከቊስጥንጥንያ የመጡ ክፉዎች ሰዎች በግብጽ አገር ተገለጡ እነርሱም የክርስቶስን ተዋሕዶ ምትሐት በሚያደርግ መከራውንና ትንሣኤውንም በሚክድ በረከሰ በአውጣኪ ትምህርት የሚያምኑ ናቸው ይህም አባት አውግዞ ከግብጽ አገር አሳደዳቸው።
ዳግመኛም በዘመኑ ምእመን ንጉሥ አንስጣስዮስ አረፈና በርሱ ፈንታ ኬልቄዶናዊ መናፍቅ ዮስጣትያኖስ ነገሠ እርሱም በአባ ጢሞቴዎስ ፈንታ ሊናርዮስን ሊቀ ጵጵስና ሾመው ሃይማኖታቸው የቀና ምእመናንን ሁሉ በኬልቄዶን ግባኤ ወደተወሰነ ሃይማኖት ሊመልሳቸው ወዶ በቅስጥንጥኒያ ጉባኤ ሰብስቦ የአንጾኪያውን ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስን ከኤጲስቆጶሳቶቹ ጋር አስመጣው።
በኬልቄዶን ጉባኤ በተወሰነች በተበላሸች ሃይማኖቱ ያምኑ ዘንድ አስገደዳቸው እነርሱ ግን አልተቀበሉትም ትእዛዙንም አልሰሙም ስለዚህም ሃይማኖታቸው በቀና ምእመናን ሁሉ ታላቅ መከራ አደረሰባቸው።
ይህም አባት ጢሞቴዎስ በመንበረ ሢመቱ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኑሮ በሰላም አረፈ ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት መልካም ስም አጠራርና ጣፋጭ ዜና ያለው ለሶርያ መስፍን ልጁ የሆነ ለተመሰገነ ለሁለተኛው አውሳብዮስ የምስክርነቱና የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። ለርሱም መንፈስ ቅዱስን የተመላች ስሟ አውሎፊያ የሚባል እኅት አለችው ይህንንም ቅዱስ በተግሣጽና ጥበብን በማስተማር አሳደጉት በአደገም ጊዜ እጅግ ደም ግባት ያላትን የሮሜውን ንጉሥ ልጅ በብዙ ክብር አጋበት።
በዚያችም ዕለት ወደ እኅቱ ገብቶ እስቲ ምከሪኝ ልቤ ይህን ጋብቻ አይሻውም ዓለምን ንቆ መተውን እንጂ አላት እኅቱም የዚህ የኃላፊው ዓለም ጣዕም ምን ይጠቅምሃል እንደ ሊቀ ጳጳሳት ድሜጥሮስ በድንግልና መኖር ይሻልሃል አለችው ።
ምሽትም በሆነ ጊዜ ሙሽሪት ወዳለችበት ገብቶ አንገቷን ያዝ አድርጎ ሳማት እኅቴ መልካም ነገርን እነግርሽ ዘንድ እሺ በይኝ አላት በል ተናገር አለችው እርሱም ዕወቂ ይህ ዓለም ፍላጎቱም ሁሉ ኃላፊ እንደሆነ ያንቺም ደም ግባትሽና ላሕይሽ እንደሚጠፋ ከጽድቅ ሥራ ብቻ በቀር የሚጠቅመን የለም አሁንም ሥጋችንን ከምናሳድፍ ድንግልናችንን ጠብቀን መኖር ይሻለናል አላት።
እርሷም ወንድሜ ሆይ እኔም ጋብቻን አልሻም እንዳልክ ይሁን አለችው። በዚህም ምክር ተስማምተው ሁለቱም በአንድነት የጽድቅን ሥራ በመጀመር እየጸለዩ እየጾሙ በየሌሊቱ ከባሕር ውስጥ ቁመው ያድራሉ አትራ ወደምትባልም ቤተ ክርስቲያን እየሔዱ አራት ሺህ ጊዜ ይሰግዳሉ የዳዊትን መዝሙርና የዮሐንስን ወንጌል ያነባሉ ሥጋውንና ደሙን ሳይቀበሉ ሁል ጊዜ እህልን አይቀምሱም።
በአንዲትም ዕለት የሶርያ ንጉሥ ሚስት አውሳብዮስን አይታው እጅግ ወደደችው ከባሮቿም ሁለቱን ልካ ወደርሷ አስወጣችው በዐልጋዋም ላይ ምንጣፎችን አንጥፋ ብጫ ሐር ልብስ አለበሰች በአንገቷም የወርቅ ማርዳ በማድረግ አጌጠች አውሳብዮስንም በልቤ ያለውን እነግርህ ዘንድ ና ከዚህ ተቀመጥ አለችው።
እርሱም ከንጉሥ ሚስት ጋር አልቀመጥም እንደቆምኩ ንገሪኝ አላት እርሷም አንተን ከመውደዴ ብዛት የተነሣ ሰውነቴ ይናወጣል ሁለመናዬም ይቀልጣልና ና ከእኔ ጋር ተኛ አለችው እርሱም አንተን ከመውደዴ ብዛት የተነሳ ሰውነቴ ይናወጣል ሁለመናዬም ይቀልጣልና ና ከእኔ ጋር ተኛ አለችው እርሱም ከንጉሥ ሚስት ጋር መተኛት የሚገባኝ ሳይሆን የእግዚአብሔርም ትእዛዝ እንዲህ አልሆነምና ለአንቺ ጋር አልተኛም አላት ።
ልትይዘውም በወደደች ጊዜ አመለጣትና ሩጦ ሒዶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ እርሷም በታላቅ ድምፅ ጮኸች ባሮቿም ደረሰው እመቤታችን ሆይ ምን ሆንሽ አሏት። እርሷም ይህ ሥራየኛ አውሳብዮስ ወደኔ ገብቶ የማይገባ ነገርን ተናገረኝ አይሆንም ባልሁትም ጊዜ ሥራይን ስላደረገብኝ መንቀጥቀጥና ጻዕር ያዘኝ አለቻቸው።
ከዚህም በኋላ ከቤተ ክርስቲያን አውጥተው ያመጡት ዘንድ ዐሥራ አራት መምህራንን አዘዘች ወደርሷም ባደረሱት ጊዜ በብረት ዘንጎች ይደበድቡት ዘንድ እጆቹንና እግሮቹንም አሥረው ከከተማ ውጭ በአራት ዕንጨቶች ላይ ይሰቅሉት ዘንድ አዘዘች ከባሮቿም አንዲቷን ልካ እርሷም ከተሰቀልክበት እንድታወርድህ ለእመቤቴ ያለችህን እሺ በላት አለችው እርሱም የአመንዝራን ቃል አልሰማም አላት።
በዚያንም ጊዜ መጸለይ ጀመረና እንዲህ አለ አቤቱ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ ፈጣሪ እግዚአብሔር ሆይ አባቶቻችንን ከመከራቸው ሁሉ ያዳንካቸው አንተ ነህና እኔን ባርያህን አውሳብዮስን አድነኝ ዳንኤልንም ከአንበሶች አፍ ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነህ አንተ ነህና ያላንተ ረዳት የለኝምና ከዐመፀኛዪቱና ከግፈኛዪቱ ሴት እጅ አድነኝ።
ከዚህም በኋላ ዳግመኛ አንገቱን በገመድ አንቀው በመቶ ስሳ ፍላፃዎች ይነድፉት ዘንድ አዘዘች ይህንንም በአደረጉበት ጊዜ የመላእክት አለቆች ሚካኤልንና ገብርኤልን ጌታችን አዘዛቸው እነርሱም ከሰውነቱ ውስጥ ፍላፃዎችን አወጡ ያለ ጉዳትም ጤነኛ ሆነ።
ንጉሥም ከሔደበት በገባ ጊዜ ለስቅላትና ለሞት አሳልፈሽ የሰጠሽው የአውስብዮስ በደሉ ምንድን ነው ብሎ ጠየቃት የንጉሡም ሚስት ላንተ መናገርን አፍራለሁ አንተንም እፈራለሁ አለችው አትፍሪኝ በዪ ንገሪኝ አላት እርሷም ብቻዬን ተቀምጬ ሳለሁ ይህ ሥራየኛ ሰው ወደ እኔ ገብቶ ሊናገሩት የማይገባ ሥራ ለመነኝ በከለከልኩትም ጊዜ በሥራዩ አሳመመኝ አለችው።
ንጉሡም አውሳብዮስን ከተሰቀለበት አውርደው ወደርሱ ያቀርቡት ዘንድ አዘዘ ሲቀርብም ንጉሡ አውሳብዮስን በሚስቴ ላይ ክፉ መሥራትን ለምን አሰብክ አለው አውሳብዮስም ይህ ነገር እውነት ይመስልሃልን ብሎ መለሰለት ንጉሥም ይህ የምሰማው ነገር እውነት ነውን በማለት ባሮቹን መረመራቸው ።
እነርሱም ጌታችን ንጉሥ ሆይ እኛ ግን ጩኸት ሰምተን ወደ አደራሹ በደረስን ጊዜ ንግሥት እመቤታችንን እየጮኸች አገኘናት ምን ሆንሽ በአልናትም ጊዜ ይህንኑ ነገረችን አሉት።
ይህንንም በሰማ ጊዜ እንደ አንበሳ ጮኸ ቸብቸቦውንም በሰይፍ እንዲቁርጡ ሥጋውንም እንደ ላም ሥጋ ቁራርጠው ከአደሮ ማር ጋር ከምንቸት ውስጥ ጨምረው አፉን ዘግተው በእሳት ያበስሉት ዘንድ አዘዘ በዚያንም ጊዜ የመላእክት አለቆች ሚካኤልና ገብርኤል መጡ ከምንቸትም ውስጥ አውጥተው ከሞት አድነው አስነሡት።
ከተነሣም በኋላ በሀገር ውስጥ ሲጓዝ ሰዎች አገኙት ሕያው እንደሆነም ለንጉሥ ነገሩት ንጉሥም እንዲአመጡትና አራት ዛንጅሮችን በአካላቶቹ ውስጥ እንዲአስገቡ አንዱን በአንገቱ ውስጥ አንዱን በወገብ አንዱን በጐኑ አንዱን በጉልበቱ ውስጥ አስገብተው እጅና እግሩንም አሥረው ከእሳት ውስጥ ይጨምሩት ዘንድ አዘዘ የከበሩ ሚካኤልና ገብርኤል መጥተው እሳቱን አቀዘቀዙ የመላእክት አለቃ ዑራኤልም ነጥቆ ወደ ሰማይ አሳረገውና በዚያ ዐሥራ አራት ዓመት ኖረ።
ከዚያም በኋላ ወደ ምድር ተመልሶ ወርዶ የወንጌልን ሃይማኖት እያስተማረ አርባ ዓመት ኖረ በእርሱ ትምህርትም ሰማንያ አምስት ሺህ አረማውያን አመኑ ጌታችን ኢየሱስም ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውንም ለሚያደርግ እስከ ሰባት ትውልድ ሊምርለት ቃል ኪዳን ሰጠው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦር የተወለደበት ነው፡፡ የዚህ ቅዱስ እናቱ ማርታ አባቱ ደግሞ ኅርማኖስ ይባሉ ነበር፡፡ አባቱ የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ ባለሟል በነበረ ሲሆን ቅዱስ ፊቅጦርም በገዛ አባቱ እጅግ ተሠቃይቶ ምስክርነቱን የፈጸመው ታላቁ ሰማዕት ነው፡፡
ኅርማኖስ የተባለው ወላጅ አባቱ የክርስቲያኖችን ደም እንደ ውኃ ያፈስ የነበረው የዲዮቅልጥያኖስ ልዩ አማካሪና የሠራዊቱ አለቃ ነበር፡፡ እናቱ ሣራ ግን በክርስቶስ አምና የተጠመቀች ክርስቲያን ነበረች፡፡
እንዲያውም ልጇን ቅዱስ ፊቅጦርን ከመውለዷ በፊት የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ወዳለበት ሄዳ "እመቤቴ ማርያም ለኢየሱስ ክርስቶስ ደስ የሚያሰኘውን ልጅ ስጪኝ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ደስ የማያሰኝ ልጅ ከሆነ ግን ማኅፀኔን ዝጊልኝ" ብላ በጸለየችው ጸሎት ነው ቅዱስ ፊቅጦርን ያገኘችው፡፡
ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር በዓለም ላይ ያሉ በክርስቶስ ያመኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ በግፍ ያስገድል በነበረበት ወቅት የተገኘ ታላቅ ሰማዕት ነው፡፡ ፊቅጦርን ገና 15 ዓመት እንደሆነው ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ "ከፍ ባለ ስልጣን አስቀምጥሃለሁ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና ንብረትም እሰጥሃለሁ፣ በእስክንድርያም ላይ ገዥ አድርጌ እሾምሃለሁ ክርስቶስን ማመንህን ተውና ወደ ቤተ መንግሥቴ ግባ" ቢለውም ቅዱስ ፊቅጦር ግን ብዙ መከራንና ሥቃይን ተቀብሎ ሰማዕት መሆንን መረጠ፡፡ ቅዱስ ፊቅጦርም ዲዮቅልጥያኖስን "ክርስቶስን በምታፈቅረው ጊዜ አፈቀርኩህ ወደ አንተም መጣሁ፤ ክርስቶስን በጠላኸው ጊዜ ግን እኔም ጠላሁህ፣ ቤትህንም ጠላሁ" ብሎታል፡፡
ከብዙ ጊዜም በኋላ ዲዮቅልጥያኖስ ቅዱስ ፊቅጦርን በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛ ማዕረግ አድርጎ ሾመው፡፡ እርሱ ግን ይጾማል ይጸልያል እንጂ በንጉሡ ቤት አይበላ አይጠጣም ነበር፡፡ ዕድሜውም 27 ነበር፡፡ አባቱንም ከጣዖት አምላኪነቱ እንዲመለስ ቢመክረው ሄዶ ለንጉሡ ከሰሰው፡፡ ፊቅጦርም "ለአንተ ለጣዖት አምላኩ አገልጋይ አልሆንም" በማለት በንጉሡ ፊት ትጥቁን ፈቶ ጣለ፡፡ የቅዱስ ፊቅጦር ወላጅ አባቱ ኅርማኖስ የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ የቅርብ እንደራሴና መስፍን ስለነበር ልጁ ፊቅጦርን የንጉሡን ሹመትና ልመና እንዲቀበል ብዙ ሲያግባባው ነበር፤ አባቱም ልጁ በሀሳቡ እንዳልተስማማለት ሲያውቅ ከዲዮቅልጥያኖስ ጋር ተማክሮ ልጁን ቅዱስ ፊቅጦርን ወደ እስክንድርያና ወደ ተለያዩ ሀገሮች በግዞት ተልኮ በዚያም ተሠቃይቶ እንዲሞት ፈደበት፡፡
ወደ ግብፅም ልከው በዚያ እጅግ አሠቃዩት፡፡ መልአክም ነጥቆ ወስዶ በሰማያት የሰማዕታትን ክብር አሳይቶት ወደ ምድር መለሰው፡፡ ክፉዎቹም በብረት አልጋ አስተኝተው ከሥሩ እሳት አነደደዱበት፡፡ በሌላም ልዩ ልዩ በሆኑ ማሠቃያዎች እጅግ አሠቃዩት፡፡ መልአክም ተገልጦ ፈወሰው፡፡ ወደ እንዴናም አጋዙትና በዚያም ብዙ አሠቃዩት፡፡ ምላሱን ቆረጡት፤ በችንካርም ጎኖቹን በሱት፤ ቁልቁል ሰቅለውም ቸነከሩት፤ በእሳትም ውስጥም ጨመሩት፤ ዐይኖቹን አወጡት፤ እሬትና መራራ ሐሞትንም አጠጡት፡፡ ደግመውም ዘቅዝቀው ሰቀሉት፡፡ ጌታችንም ተገልጦ ካጽናናው በኋላ ፈወሰውና ፍጹም ጤነኛ አደረገው፡፡ ፊቅጦር፣ ፋሲለደስ፣ ቴዎድሮስ በናድልዮስ፣ አውሳብዮስና መቃርዮስ እነዚህ ሰማዕታት በአንድነት በአንድ ዘመን አብረው ኖረው ተሰውተው ሰማዕት የሆኑ የሥጋም ዝምድና ያላቸው የነገሥታት ልጆች ናቸው።
ዲዮቅልጥያኖስም የቅዱስ ፊቅጦርን ዐይኑን አስወለቀው፣ ነገር ግን የታዘዘ መልአክ መጥቶ የዓይኑን ብርሃን መልሶለታል፡፡ ሰማዕቱ በመዝለል ባሕር የሚሻገር እንደ አሞራ የሚመስል ፈረስ ነበረው፡፡ ከዚህም በኋላ ማሠቃየቱ ቢሰለቻቸው ሚያዝያ 27 ቀን አንገቱን ሰይፈው በሰማዕትነት እንዲያርፍ አድርገውታል፡፡
ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር አንድ የሚነገር ትልቅ ታሪክ አለው፡፡ እርሱም በሰማዕትነት ካረፈ ከብዙ ዘመን በኋላ በራእይ ተገልጦ በ8ኛው ሺህ ዘመን በሀገራችን በኢትዮጵያና በግብፅ እንዲሁም በቁስጥንጥንያና በሮም ወደፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ በግልጽ የተናገረ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ስለ ሃይማኖት ቅዱስ ፊቅጦር ያየው ራእይ›› የሚል መጠሪያ ያለው ይህ ራእይ በሀገራችን ጎጃም ደብረ ጽሞና ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment