ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲተት 22 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲተት 22

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ሃያ ሁለት በዚች ቀን የኤጲስቆጶስ #ቅዱስ_አባ_ማሩና የዕረፍቱ መታሰቢያና #የፋርስ_ሰማዕታት ሥጋቸው የፈለሰበት ነው፣ ታላቅና ክቡር የሆነ መስተጋድል #ቅዱስ_አባ_ቡላ መታሰቢያው ነው።


የካቲት ሃያ ሁለት በዚች ቀን የኤጲስቆጶስ አባ ማሩና የዕረፍቱ መታሰቢያና በከሀዲ በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በፋርስ አገር ለተገደሉ ሰማዕታት ሥጋቸው የፈለሰበት ነው።
ኤጲስቆጶስ ማሩናንም ስለ ድንቆች ተአምራቶቹ ስለ ትሩፋቱና ስለ ጽድቁ የአኖሬዎስና የአርቃዴዎስ አባት ታላቁ ቴዎዶስዮስ ንጉሥ ወደ ፋርስ ንጉሥ ላከው ከእርሱም ጋር እጅ መንሻ በመካከላቸው ስለ አለው ፍቅር ተላከ። ወደ ሳቦር ወደ ፋርስ ንጉሥም በደረሰ ጊዜ ታላቅ ክብርንም አከበረው በቤተ መንግሥቱም እልፍኝ ውስጥ አኖረው። ይህ ቅዱስም የንጉሡ ልጅ ጋኔን አድሮባት እንደታመመች በሰማ ጊዜ የከበረ አባ ማሩና ብላቴናዪቱን ጠርቶ በፊቱ አቁሞ በላይዋ ጸለየ ጋኔኑም ከእርሷ ወጥቶ ዳነች ንጉሡም ልጁ እንደዳነች አይቶ እጅግ ደስ አለው የአባማሩናንም ፍቅርና አክብሮት ጨመረ።
ከዚህም በኋላ አባ ማሩና በፋርስ ሀገር በሰማዕትነት ስለሞቱ የከበሩ ሰማዕታት ሥጋቸውን ስለ መሰብሰብ ከንጉሥ ዘንድ ፈለገ ንጉሡም የሰማዕታትን ሥጋቸውን ይሰበስቡ ዘንድ ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው በውስጧ ሥጋቸውን ያኖሩ ዘንድ አዘዘ ያች ቤተ ክርስቲያንም በዚች ዕለት ከበረች።
ዳግመኛም በታላቋ ከተማ ውስጥ በከበረ አባ ማሩና ስም ያማረች ቤተ ክርስቲያንን ሠሩ እርሷም ማረፊያ የተባለች ናት። ከዚህም በኋላ ይህ አባት ወደ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ተመልሶ በሮሜ አገር ሁለት ዓመት ተቀመጠ የእነዚያ ሰማዕታት ቤተ ክርስቲያን በከበረችበት በዚች ዕለት አረፈ ከቤተ ክርስቲያኒቱም ክብር ጋር በዓሉንና መታሰቢያውን የሚያከብሩለት ሆኑ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን ታላቅና ክብር የሆነ አቢብ የተባለ መስተጋድል አባ ቡላ መታሰቢያው ነው። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አብርሃም የእናቱም ስም ሐሪክ ነው እነርሱም ከሮሜ አገር ሉፊ ከሚባል አውራጃ ናቸው በዘመናቸውም ከሀዲው ንጉሥ መክስምያኖስ በክርስቲያን ወገኖች ላይ መከራ ስለ አመጣ ስደት ሁኖ ነበርና እነርሱም በስደት ብዙ ዘመን ኖሩ።
ልጅንም በአጡ ጊዜ የተባረከ ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ በጾም በጸሎት ተወስነው ወደ እግዚአብሔር ለመኑ የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም ተገለጠላቸውና ፍሬ የመላበትን ዘለላ ሰጣቸው።
ይህም ቅዱስ በተፀነሰ ጊዜ በቤታቸው አጠገብ ታላቅ ዛፍ በቀለ በቅጠሉም ላይ በሮማይስጥ ቋንቋ ቡላ የእግዚአብሔር አገልጋይ በጽዮንም አድሮ የሚኖር የያዕቆብ ፈጣሪ ያከበረው የሚል ጽሑፍ ነበረበት።
በተወለደም ጊዜ ክርስትና ሳያስነሡ ዓመት ሙሉ አኖሩት እመቤታችን ማርያምም ለሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ለሰለባስትርዮስ ተገልጣ ወደ አብርሃም ቤት ሒዶ ሕፃኑን እንዲአጠምቀው አዘዘችው እርሱም ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው ስሙንም ቡላ ብሎ ሰየመው እናትና አባቱም ሳይነግሩት ቡላ ስለ ሰየመው አደነቁ ዕፁብ ዕፁብ አሉ።
ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱ በጸለየ ጊዜ የቊርባን ኅብስትና ወይን የተመላ ጽዋ ከሰማይ ወረደ እርሱም ቀድሶ ሥጋውንና ደሙን ከሕፃኑ ጋር አቀበላቸው በዚያንም ጊዜ ሕፃኑ የአንድ ዓመት ልጅ ሲሆን በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ አብ በግብር በአካል በሰም ልዩ ነው በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ ወልድ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው በባሕርይ በህልውና በመለኮት በአብ ከወልድ ጋር አንድ የሆነ መንፈስ ቅዱስ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው ብሎ ተናገረ።
ከጥቂት ዘመንም በኋላ አባትና እናቱ ኅዳር ሰባት ቀን ሙተው ሕፃኑ ብቻውን ቀረ። ሕፃኑም ዐሥር ዓመት በሆነው ጊዜ ለጣዖት መስገድን የሚያዝ ከሀዲ መኰንን መጣ ቅዱስ ቡላም በሰማ ጊዜ ወደ መኰንኑ ሒዶ የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ መኰንኑም በአካል ታናሽነቱን አይቶ እጅግ አደነቀ በዚያንም ጊዜ በችንካር እንዲቸነክሩት ሥጋውንም እንዲሠነጣጥቁት ቆዳውንም ከዐጥንቱ እንዲገፉ እጆቹንና እግሮቹንም በመጋዝ እንዲቆርጡ ጀርባውንም እንዲገርፉ በሾተሎችና በጦሮች መካከል አድርገው ከመንኰርኵር ውስጥ እንዲጨምሩት ዳግመኛም በመንገድ ላይ እንዲጐትቱት አዘዘ የመላእክት አለቃ ሚካኤልም መጥቶ አዳነው ያለ ጉዳትም ጤነኛ አደረገው።
ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ መኰንን ሒዶ እርሱንና የረከሱ ጣዖቶቹን ረገመ መኰንኑም ተቆጥቶ በሚያዝያ ወር ዐሥራ ስምንት ቀን ራሱን በሰይፍ ቆረጠው ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወርዶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው ወደ አንድ ገዳምም ወስዶ የምንኲስና ልብስንና አስኬማን በመስቀልም ምልክት አለበሰው። እንዲህም አለው ከቅዱሳን ጻድቃን አንድነት ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር አዝዞሃል።
ያን ጊዜም ቅዱስ አባ ቡላ ከደረቅ ተራራ ላይ ወጣ ያለ ማቋረጥም በውስጧ እየተጋደለ ኖረ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራውንና ስቅለቱን በአሰበ ጊዜ ከረጅም ዕንጨት ላይ በመውጣት ራሱን ወደታች ሁል ጊዜ ይወረውር ነበር።
በአንዲትም ቀን ከዛፍ ላይ በተወረወረ ጊዜ ሰይጣን ሊገድለው ስለ በረታበት ሞተ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና መድኃኑታችን ከሞት አነሣውና እንዲህ አለው ከእንግዲህ ስምህ ቡላ አይሁን አቢብ ይባል እንጂ የብዙዎች አባት ትሆናለህና።
እርሱም የክርስቶስን ፍቅር እጅግ ጨመረ ፊቱንም እየጸፋ ሥጋውን በየጥቂቱ እየቆረጠ ጀርባውንም ሰባት መቶ ጊዜ እየገረፈ ኖረ ጌታችንም ይፈውሰው ነበር በየእሑድም ቀን ከቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም እንደተወለደ በሌሎች ቀኖችም እንደተያዘና ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበለ ሁኖ ይገለጽለት ነበር።
ስለዚህም ሳይበላ ሳይጠጣ አርባ ሁለት ዓመት ኖረ ዳግመኛም ናላው ፈስሶ እስቲአልቅ ዐሥራ ሁለት ወር በራሱ ተተክሎ ኖረ። በአንዲትም ቀን የጌታችንን መከራ በአሰበ ጊዜ ሰይፉን በአንጻሩ ተከለ ከዕንጨት ላይም ወጥቶ በላዩ ወድቆ ሞተ ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምም ከአእላፍ መላእክት ጋር መጥታ የእኔና የልጄ ወዳጅ ሰላምታ ይድረስህ አለችው። ከበድኑም ቃል ወጥቶ የሰማይና የምድር ንግሥት እመቤቴ ሰላምታ ይገባሻል አላት እርሷም በከበሩ እጆቿ ዳሥሣ ከሞት አስነሣቸው።
ዕድሜውንም ፈጽሞ ከዚህ ዓለም የሚወጣበት ጊዜ ሲደርስ ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ በእጁ ልዩ የሆኑ አክሊሎችን የሚያበሩ ልብሶችንም ይዞ ተገለጠለት። ወዳጄ አቢብ ሆይ በማያልቅ ተድላ ደስታ ደስ አሰኝህ ዘንድ ወደ እኔ ና ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ እኔ ኃጢአቱን አስተሠርይለት ዘንደ በራሴ ማልኩልህ። ወይም ለተራቆተ የሚያለብሰውን ለተራበም የሚያጠግበውን ለተጠማ የሚያጠጣውን የገድልህን መጽሐፍም የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውንና የሚሰማውን በጸሎትህም የሚታመኑትን ሁሉ እስከ ዐሥር ትውልድ እምራቸዋለሁ። ይህንም ብሎ አፉን ሳመው በደረቱም ላይ አድርጎ ወደአየር አወጣው የመላእክትንም ምስጋና በሰማች ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ገባች። የእረፍቱ ቀንም ጥቅምት ሃያ አምስት ይከበራል፡፡ (የጥቅምት 25 ስንክሳር)
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ለዘለዓለሙ ከእኛ ጋር ትሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages