ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 23 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 23

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ሃያ ሦስት በዚህች ዕለት #ልበ_አምላክ_ቅዱስ_ዳዊት ዐረፈ፣ ቅዱሳን አባቶቻችን #አባ_ሳሙኤል#አባ_ስምዖንና #አባ_ገብርኤል እንዲሁም #አባ_ጢሞቴዎስ_ገዳማዊ ዕረፍታቸው፡፡


ታኅሣሥ ሃያ ሦስት በዚህች ዕለት ልበ አምላክ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት ዐረፈ፡፡ ይህም ንጉሥ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት መልካም ጒዞን የተጓዘ ከእራኤልም ነገሥታት ሁሉ እውነተኛ ፍርድን ያደረገ ነው እርሱም አገሩ ቤተልሔም የሆነች ከይሁዳ ነገድ ነው ሳኦልም የእግዚአብሔር ትእዛዝ በተላለፈ ጊዜ ለእስራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ መረጠው ነቢይ ሳሙኤልንም ቅብዐ መንግሥትን የእሴይን ልጅ ይቀባ ዘንድ ላከው። ሳሙኤልም ታላቁን ኤልያብን ተመለከተ መልኩ ያማረ አካሉም የጸና ነበርና እግዚአብሔር ግን አልመረጠውም። "የኤልያብ ፊቱን አትይ የመልኩንም ማማር አትመልከት እግዚአብሔር ሰው እንደሚያይ የሚያይ አይደለምና" አለው እንጂ "ሰው መልክ ያያል እግዚአብሔር ግን ልብን" ያያል።
ከእሴይ ከሰባቱ ልጆች በኋላ ነቢይ ሳሙኤል ዳዊትን በእስራኤል ልጆች ላይ ይነግሥ ዘንድ ቀባው እግዚአብሔርም በሥራው ሁሉ ከእርሱ ጋር ሆነ። ከልቡናው ንጽሕና ከየዋህነቱም ብዛት የተነሣ ጠላቱን ሳኦልን ብዙ ጊዜ ሲያገኘው በላዩ ምንም ምን ክፉ ነገር አላደረገበትም። በአንዲትም ዕለት ሳኦል ከእስራኤል ሁሉ የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎችን ይዞ ዳዊትን ከሰዎቹ ጋር ይፈልገው ዘንድ ዋሊያዎች ወደሚታደኑበት ሔዶ በጐዳና አጠገብ ያሉ ዘላኖችም ወደሚሠማሩበት ደረሰ በዚያም ዋሻ ነበር ሳኦልም ይናፈስ ዘንድ ወደዚያች ዋሻ ውስጥ ተቀምጠው ነበር። ዳዊትም ተነሥቶ ቀስ ብሎ ከልብሱ ጫፍ ቆረጠ። በሁለተኛም ጊዜ በድንክ አልጋ ላይ ተኝቶ ወዳለበት ከአቢሳ ጋር ገብቶ ከራስጌው ጦሩንና ውኃ ያለበትን ረዋቱን ይዞ ተመልሶ ሔደ ክፉ ነገርንም አላደረገበትም ሰዎቹም ጠላትህ ሳኦልን ግደለው በአሉት ጊዜ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን ልዘረጋ አይገባኝም ብሎ መለሰላቸው።
ስለ ሳኦልም መገደል አንድ ሰው በነገረው ጊዜ ዳዊትም "ያንን ሰው ማን ገደለው" አለው ሰውዬውም "እኔ ገደልሁት" አለው ዳዊትም እጅግ አዘነ ልብሱንም ቀደደ ያንንም ሳኦልን እኔ ገደልሁት ያለውን ሰው ገደለው። እግዚአብሔር በዚህ በጻድቅ ዳዊት ልብ ብዙ ትሩፋትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ቅንነትን፣ ትዕግሥትን ፍቅርን አከማቸ ክብር ያለው ንጉሥ ሲሆን ራሱን ውሻ ትል እንስሳም አድርጎ ይጠራል ስለዚህም ከምድር ነገሥታት ሁሉ ከፍ ከፍ አደረገው እንዲህም ብሎ አመሰገነው "የእሴይን ልጅ ዳዊትን እንደ ልቤ ሆኖ አገኘሁት ፈቃዴን ሁሉ የሚያደርግ ታማኝ ሰው ነው"።
እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች ኢየሩሳሌምንም ስለ ዳዊት ደግነት ብዙ ጊዜ ጠበቃቸው እርሱ ካለፈ በኋላም በነቢያቶቹ አንደበት አከበረው ነገሥታትንም ከእርሱ ዘር አደረገ። እርሱም በሁሉ ዓለም የታወቀ የመዝሙሩን መጽሐፍ ደረሰ ይኸውም በሰይጣናት ላይ ጋሻና ጦር የሆነ መልካም ቃልንም የተመላ በሰማይና በምድርም ያሉ በእርሱ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ነው።
ቅዱስ ዳዊትም ፊቱ እንደ ሮማን ቀይ ነው ቁመቱም መካከለኛ የሆነ አካሉም የጸና ብርቱ ነበር ታናሽ ብላቴናም ሁኖ ሳለ እርሱ የአባቱን በጎች ሲጠብቅ አንበሳ ወይም ተኵላ መጥቶ ከመንጋው ውስጥ በግ ነጥቆ በሚወስድ ጊዜ ተከትሎ ገድሎ ከአፉ ያስጥለው ነበር ሊጣላውም ቢነሣበት ጒረሮውን ይዞ ይሠነጥቅዋል። ከፍልስጥዔማውያንም ጋራ ሰልፍ በሆነ ጊዜ ብርቱ ሰው ስሙ ጎልያድ የሚባል ከጌት ሰዎች የተወለደ ቁመቱ ስድስት ክንድ ከስንዝር የሆነ ከኢሎፍላውያን ሰፈር ወጣ። በራሱ ላይ የነሐስ በርቦርቴ ደፍቷል የነሐስ ጽሩርም ለብሷል በርሱ ላይ ያለ የብረቱና የነሐሱ ሁሉ ሚዛኑ አምስት ሽህ ወቄት ነበር። በእግሮቹ ባቶችም ላይ የነሐስ ሰናፊል ታጥቆ ነበር በጫንቃውም መካከል የነሐስ እባቦች ነበሩ። የጦሩም ዛቢያ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ ሁኖ በላዩ ሽቦ ነበረበት የጦሩም ብረት መጠን ስድስት መቶ ወቄት ነበር ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሔድ ነበር።
ቁሞም ወደ እስራኤል ሰፈር ይጮህ ነበር "ከእኛ ጋር ትዋጉ ለምን ወጣችሁ እኔ የኤሎፍላውያን ወገን ነኝ ከእናንተ የሳኦል ባሮች አይደላችሁምን ከእናንተ አንድ ሰው መርጣችሁ ወእኔ ይውረድ ከእኔ ጋር መዋጋት ችሎ ቢገድለኝ ባሮች እንሆናችኋለን እኔ ከርሱ ጋራ ችዬ ብገድለው እናንተ ባሮች ሁናችሁ ትገዙልናላችሁ" አላቸው። ያም ኢሎፍላዊ ለወገኖቹ "ዛሬ በዚች ቀን አንድ ሰው ስጡኝና ሁለታችን ለብቻችን እንደዋጋ ብሎ የእስራኤልን አርበኞች እነሆ ተገዳደርኳቸው" አላቸው። እስራኤል ሁሉና ሳኦልም ይህን የኢሎፍላዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ ደነገጡ እጅግም ፈሩ የእራኤልንም ወገኖች እንዲህ እየተገዳደራቸውና እየተመካባቸው አርባ ቀኖች ያህል ኖረ ከእስራኤልም ወገን ወደርሱ ይወጣ ዘንድ የደፈረ የለም።
በዚያም ወራት ቅዱስ ዳዊት ወንድሞቹን ሊጐበኝ ወጣ ያንንም የኢሎፍሊ ወገን የሆነ ሰው የእግዚአብሔር ወገኖችን ሲገዳደራቸው በአየው ጊዜ አምላካዊ ቅናትን ቀና ሳኦልንም እንዲህ አለው "እኔ ሔጄ ይህን ያልተገረዘ ቈላፍ ገድዬ ዛሬ ከእስራኤል ሽሙጥን አርቃለሁ። ሕያው የሚሆን የእግዚአብሔርን አርበኞች ይገዳደር ዘንድ ይህ ቈላፍ ቁም ነገር ነው ከድብ አፍና ከአንበሳ አፍ ያዳነኝ እርሱ እግዚአብሔር ከዚህ ካልተገረዘ ኢሎፍላዊ እጅ ያድነኛል"። ሳኦል "ሒድ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን" አለው። ዳዊትም ወንጭፋን በእጁ ያዘ ከወንዝ መካከልም ሦስት ደንጊያዎችን መረጠና ወደዚያ ኢሎፍላዊ ሔደ። ጎልያድም ዳዊትን በአየው ጊዜ ናቀው እንዲህም አለው "ደንጊያና በትር ይዘህ ወደኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ውሻ ነኝን" ዳዊትም "ከውሻ የምትሻል አይደለህም ከውሻ ትብሳለህ እንጂ" ቈላፍ ጎልያድም ዳዊትን በጣዖቶቹ ስም ረገመው።
ያም ኢሎፍላዊ ዳዊትን "ወደ እኔ ና ሥጋህን ለሰማይ ወፎችና ለዱር አራዊት እሰጣሁ" አለው ዳዊትም ያንኑ ኢሎፍላዊ "አንተ ጦር ሰይፍና ጋሻ ይዘህ ወደኔ ትመጣለህ እኔ ግን አሸናፊ በሚሆን በእግዚአብሔር ስም ወዳንተ እመጣለሁ። ዛሬ የእስራኤልን አርበኞች የተገዳደርክ አንተን ዛሬ እግዚአብሔር በእጄ ይጥልሃል እገድልህምአለሁ ራስህንም እቆርጣለሁ የኢሎፍላውያን ሠራዊት ሬሳና ያንተን ሬሳ ዛሬ ለዱር አራዊትና ለሰማይ ወፎች እሰጣለሁ ሰዎችም ሁሉ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር እንዳለ ያውቃሉ ሠራዊትም ሁሉ እግዚአብሔር በጦርና በሰይፍ የሚያድን እንዳይደለ ያውቃሉ ድል የእግዚአብሔር ገንዘብ ነውና"።
ቅዱስ ዳዊትም እጁን ወደ ድጉ ሰዶ አንዲት ደንጊያ አውጥቶ ወነጨፋት ያንንም ኢሎፍላዊ ግንባሩን ገመሰው ያቺም ደንጊያ ከግንባሩ ገብታ ናላውን በጠበጠችው በምድር ላይም በግንባሩ ተደፋ። ዳዊትም ሩጦ የገዛ ሰይፉን አንሥቶ ራሱን ቆረጠው ከእስራኤልም ልጀጆች ስድብን አራቀ። ቅዱስ ዳዊትም መላው ዕድሜው ሰባ ነው መንግሥትን ሳይዝ ሠላሳ ዓመት ኖረ ከያዘ በኋላ አርባ ዓመት ኖረ። የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ከመምጣቱ በፊት በሽህ አንድ መቶ ሃያ ዓመት ውስጥ ትንቢት የተናገረበት ዘመን ነው በሰላምም ዐረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን አባ ሳሙኤል፣ አባ ስምዖንና አባ ገብርኤል ዕረፍታቸው ነው፡፡
አባ ሳሙኤል የተባለው ይኽም ቅዱስ ባሕታዊ ሆኖ ቀርጣሚን በምትባል አገር የሚኖር ነው፡፡ በዚያም አቅራፎስ የሚባል ሰማዕት ዐፅም ስለነበር ከእርሱ በረከትን እየተቀበለ እየተሳለመ ይኖር ነበር፡፡ ሰሊባ የሚባል አንድ መኮንን ነበር፡፡ እርሱም ስምዖን የሚባል ልጅ አለው፡፡ ልጁም ለሞት በሚያበቃ ጽኑ ሕማም ታመመ፡፡ መኮንኑ በልጁ ላይ ይጸልይ ዘንድ ወደ አባ ሳሜኤል ላከ፡፡ ነገር ግን አባ ሳሙኤል ሲደርስ ልጁ ሞቶ አገኘው፡፡ አባ ሳሙኤልም በጸሎቱ ከሞት አስነሣው፡፡ ልጁ ስምዖንም ከሞት ከተነሣ በኋላ የአባ ሳሙኤል ደቀመዝሙሩ ሆነ፡፡ ሁለቱም በጋራ በተጋድሎ አብረው ኖሩ፡፡
ቅዱስ ስምዖን ውኃ ሊቀዳ ሲሄድ ሰይጣን እንስራውን ሰበረበት፡፡ አባቱም ሌላ መቅጃ ቢሰጠው እርሱንም ሰበረበት፡፡ የታዘዘ መልአክ ተገለጠላቸውና ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ አዘዛቸው፡፡ ንጉሥ አንስጣስዮስም ቤተ ክርስቲያኑን ሠራላቸው፡፡ እነርሱም ለመነኮሳትና ለነዳያን መኖሪያ 500 መኖሪያ ቤቶችን ሠሩ፡፡ አባ ሳሙኤልም ባረፈ ጊዜ መነኮሳት ልጆቹን ለአባ ስምዖን አስረክቦ በሰላም ዐረፈ፡፡ መነኮሳቱም 12 ሺህ እስኪሆኑ ድረስ በዙ፡፡ አባ ስምዖንም በሚገባ ይመራቸው ነበር፡፡ በዘመኑም "ትንሣኤ ሙታን የለም" የሚል ሰይጣን በልቡ ያደረ አንድ መናፍቅ ተነሣ፡፡ አባ ስምዖንም ቢመክረውና ቢያስተምረው የማይለስ ሆነ፡፡ አባ ስምዖንም በሞተ ሰው ላይ ጸልዮ ያንን ሙት አስነሥቶ እንዲመሰክርለት ቢያደርገው አላምን አለው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ስምዖን ወደ እግዚአብሔር ቢጸልይ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያንን መናፍቅ አቃጠለውና ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡ አባ ስምዖንም አገልግሎቱን ፈጽሞ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡
ከአባ ስምዖንም በኋላ አባ ገብርኤል ተሹሞ መለኮሳቱን የሚጠብቅ እረኛ ሆነ፡፡ እርሱም ምግባሩ ያማረ ሃይማኖቱ የሰመረ በትሩፋት በተጋደሎ ያጌጠ ነው፡፡ ብዙ አስደናቂ ተአምራትንም የሚያደርግ ሆነ፡፡ ከዕለታም በአንደኛው ቀን መነኮሳቱ ለእንጀራ ማቡኪያ የሚሆን እጅግ ትልቅ የሆነ የድንጋይ ገንዳ ወደ ገዳሙ ሊያስገቡ ቢሉ ከክብደቱ የተነሣ እምቢ አላቸው፡፡ አባ ገብርኤልም በዚህ ጊዜ በገዳሙ ያሉት ሁሉ ወጥተው እንዲራዱ በቃላቸው ባዘዙ ጊዜ 10 ሺህ ሰዎች ከሙታን ተነሡ፡፡ አባ ገብርኤልም ይህን አይቶ "እናንተን ያልኩ አይደለም በሕይወት ያሉትን ነው እንጂ" አሏቸውና ወዲያው ወደ መቃብራቸው ተመለሱ፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አንድ ሰው ብዙ የሆነ ወርቁን ከአንዱ መነኩሴ ዘንድ በአደራ አስቀምጦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፡፡ ሰውየውም በተመለሰ ጊዜ መነኩሴው ለማንም ሳይናገር በሞት ዐርፎ አገኘው፡፡ የመነኩሴውም ረድእ አባቱ ያስቀመጠበትን ቦታ እንዳልነገረው አስረዳ፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ገብርኤል ወደሟቹ መነኩሴ መቃብር ሄዶ መቃብሩን ስለዚያ ወርቅ ጠየቀው፡፡ ሟቹም መነኮሴ ወርቁን ያኖረበትን ቦታ ለአባ ገብርኤል ነገረውና ወስዶ ለባለቤቱ ሰጠው፡፡ ባለወርቁም እጅግ እያደነቀ ወርቁን ተቀብሎ በሰላም ሄደ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ዕለት አባጢሞቴዎስ ገዳማዊ ዐረፈ፡፡ ይኸውም ደጋግ የሆኑ ወላጆቹ የቤተ ክርስቲያንን ትምህት እያስተማሩ አሳደጉት፡፡ በደገም ጊዜ ዓለምን ንቆ መንሶ ገዳም በመግባት በተጋድሎ መኖር ጀመረ፡፡ መጻተኞችንና ጦም አዳሪዎችን ይመግባቸው ዘንድ ከገዳሙ አቅራቢያ መኖሪያን አበጀ፡፡ ነዳያንንም እየመገበ በመንፈሳዊ ተጋድሎው እየጸና 5 ዓመት ያህል ከኖረ በኋላ የበጎ ነገር ጠላት የሆነ ሰይጣን በቅናት ተነሣበትና የእጅ ሥራውን ትገዛ ዘንድ አንዲት ጋለሞታን ወደ እርሱ አመጣበት፡፡
እርሷም ወደ አባ ጢሞቴዎስ ከመመላለሷ የተነሣ የኃጢአት ፍቅር አድሮባቸው በመብል ጊዜ አብረው የሚመገቡ ሆኑ፡፡ ከዚህም በኋላ ከእርሷ ጋር በኃጢአት ወደቀና በኃጢአት ሥራ ውስጥ 7 ወር ያህል ኖረ፡፡ እግዚአብሔር ሁለቱንም አልጣላቸውምና በዕለተ ምፅዓት በፊቱ የሚቆሙ መሆናቸውን አሳሰባቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ጢሞቴዎስ ተነሥቶ ጥቅጥቅ ወዳለ ጫካ ገብቶ በዚያ እየታደለ ብዙ ዘመን ኖረ፡፡ እግዚአብሔርም ጣፋጭ የሆነች የውኃ ምንጭንና ቴምርን አዘጋጀለት፡፡ እርሷን እየተመገበ በተጋድሎ ሲኖር ሰይጣን ዳግመኛ በቅናት ተነሣበትና አስጨናቂ የሆድ ሕማም አመጣበት፡፡ አባ ጢሞቴዎስ ከሕማሙ ጽናት የተነሣ በግንባሩ ምድር ላይ የወደቀ ሆኖ ቀረ፡፡ በዚህም ጊዜ ነፍሱን ‹‹ነፍሴ ሆይ ይህ የሠራሽው የኃጢአትሽ ፍሬ ነውና በዚህ ደዌሽ ታገሺ›› ይላት ነበር፡፡ በዚህም አስጨናቂ ሕማም ውስጥ ሆኖ 4 ዓመት ኖረ፡፡
ከ4 ዓመትም በኋላ መሐሪና ይቅር ባይ የሆነ እግዚአብሔር ለአባ ጢሞቴዎስ መልአኩን ላከለት፡፡ መልአኩም የአባ ጢሞቴዎስን ሆድ በእጁ አሸው፡፡ ጎኑንም በጣቱ ሰነጠቀና ጨንጓራውንና አንጀቱን አፀዳለት፡፡ በኋላም ወደቦታው መልሶ እንደቀድሞው አያይዞ አዳነውና "እነሆ እንግዲህ ጤነኛ ሆንክ፣ ዳግመኛ አትበድል ከዚህ የከፋ እንዳይደርስብህ" አለው፡፡ አባ ጢሞቴዎስም በበረሃ እየተጋደለ 40 ዓመት ኖረ፡፡ ከዚያ በፊት በገዳም 17 ዓመት በዋሻ 10 ዓመት ኖሯል፡፡ በእነዚህም ዘመናቱ ከልብስ ተራቁቶ ኖረ፡፡ የራሱም ፀጉር ከፊትና ከኋላ ሸፍኖት ነበር፡፡ ስለ አገልግሎቱ፣ ስለ ተጋድሎውና ስለ አምልኮቱ የዱር አራዊት እስኪደግዱለትና የእግሩን ትቢያ እስኪልሱለት ድረስ እግዚአብሔር ትልቅ ጸጋን ሰጠው፡፡ አገልግሎቱንም ፈጽሞ ታኅሣሥ 23 በሰላም ዐረፈ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages