አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
#ቅዱስ_ገብርኤል_እመቤታችንን ያበሰረበት መታሰቢያ ነው፣ የመላእክት አለቃ #የቅዱስ_ገብርኤል ዳህና በሚባል አገር ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራችበት ነው፣ #የብርሃን_እናቱ_ድንግል_ወላዲተ_አምላክ ለወዳጇ #ለቅዱስ_ደቅስዮስ ሰማያዊ ወንበርና ልብስ የሰጠችበት እና የዕረፍቱ ዕለት ነው፡፡
ታኅሣሥ ሃያ ሁለት በዚህች ዕለት ብርሃናዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን አምላክን እንደምትወልድ ያበሰረበት መታሰቢያ ነው፡፡ ይኸውም ‹‹ልዑል እግዚአብሔር ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልን ‹ሂድና ለጽዮን ልጅ ለድንግል የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ወደአንቺ መጥቶ ኃይለ ልዑል ወልድ ሥጋሽን ለብሶ ሰው ይሆናል፤ ይኸውም ካንቺ የሚወለደው ጽኑዕ ነው ብለህ ንገራት› አለው፡፡ ‹ደንቆሮዎች የሚሰሙበት፣ ድዳዎቸ የሚናገሩበት፣ ዕውራንም የሚያዩበት፣ ሙታን የሚነሡበት፣ ለምጻሞች የሚነጹበት፣ ሐንካሳዎች የሚሄዱበት፣ በጨለማ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ብርሃን የሚያዩበት ጊዜ እነሆ ደረሰ ብለህ ንገራት› አለው፡፡
ቅዱስ ገብርኤልም ይህን ሰምቶ በግንባሩ ተደፍቶ ልዑል እግዚአብሔርን ‹ጌታ ሆይ! የምትነግረኝ ይደረግ ዘንድ እንደምን ይሆናል?› አለው፡፡ ጌታም ‹የጀመርኩትን ቸርነት ፈጸምኩ፣ የወይን ግንድ ይቆረጣል (ወልደ እግዚአብሔር ይሞታል)፣ ወይራም ከበለስ ጋር ይተከላል (መስቀል ይተከላል)፣ ቅጽሮችም ይቀጸራሉ (ምግባር ከሃይማኖት ጋር ይሠራል)፣ የኤልፍና የሌሚ ወገን ይነሣል፡፡ ገብርኤል ሆይ! ሄደህ ለዳዊት ልጅ ‹እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ› ብለህ አብሥራት› አለው፡፡ ‹ለዘለዓለም ነግሦ የሚኖረውን እነሆ ትፀንሳለሽ በላት› አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ይህን ሰምቶ ሰገደ፡፡ ልብሱንም በላዩ ይዞ በመስቀል ቀኝ ይወርድ ዘንድ ወደደ፡፡ ጌታም ‹መግባትህና መውጣትህ በፍቅር አንድነት ይሁን› አለው፡፡ ‹ዘካርያስን ረግመህ አንደበቱን እንዳሰርህ እርሷን እንዳታሳዝናት ይልቁንም አብዝተህ ደስ አሰኛት አንጂ› አለው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ይህን ሰምቶ ፈጽሞ ደስ እያለው ሊባኖስ ከሚባል ተራራ እስኪሰማ ድረስ ክንፉን እያማታ ወረደ፡፡ በዚህም ጊዜ በዙሪያው ያሉ ሁሉ ‹ይህ የምንሰማው ምንድነው?› ይሉ ነበር፡፡ የተደረገበትንም ቦታ አላወቁትም ነበር፡፡››
እመቤታችንን በ3 ዓመቷ እናትና አባቷ ብፅዓት አድርገው ለእግዚአብሔር ሰጥተዋታልና ካህናትም በቤተ መቅደስ ከመካነ ደናግል አስገብተዋት በመልአኩ በቅዱስ ፋኑኤል አማካኝነት ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመጣላት ያንን እየተመገበች ቅዱሳን መላእክት እየጎበኟት 12 ዓመት ኖራለች፡፡ በ15 ዓመቷ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ጌታችንን እንደምትወልድ በዚህች ዕለት አብሥሯታል፡፡ በመጀመሪያ እመቤታችን ውኃ ቀድታ ስትመለስ የጠተማ ውሻ እያለከለከ ሲመጣ ብታየው ለፍጥረት ሁሉ የምትራራ ናትና በወርቅ ጫማዋ ለዛ ለተጠማው ውሻ ውኃ ስታጠጣ አብሯት የነበሩ ሴቶች ‹‹ማድጋሽን አጎደልሺው፣ ቀድቼ እሞለዋለሁ እንዳትይ ጉድጓዱ ጥልቅ ነው መቅጃም የለሽም›› አሏት፡፡ ክብርት እመቤታችንም ‹‹ውሃ የሚገኘው ከወደላይ ነው እንጂ ከወደታች ነውን? ፍጥረቱን ያጠጣ ጌታ ይሞላልኛል›› አለቻቸው፡፡ ማድጋዋም በተአምራት ሞልቶ ተገኘ፡፡ ሴቶቹም ዳግመኛ ‹‹በዚህ ዘመን አምላክ ከድንግል ይወለዳል ይላሉ ካንቺ ይሆን?›› እያሉ ሲዘብቱባት ወዲያው ከወደኋላዋ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ‹‹እነሆ ትጸንሻለሽ›› አላት፡፡ እመቤታችንም ዞር ብትል የተናገራትን አጣችው፡፡ በዚህም ጊዜ ‹‹አባቴን አዳምን እናቴን ሔዋንን ያሳተ ጠላት ይሆናል›› ብላ ሄደች፡፡
ዳግመኛም እመቤታችን ከቤት ደርሳ ማድጋዋን ስታስቀምጥ መልአኩ አሁንም በድምፅ ‹‹እነሆ ትጸንሻለሽ›› አላት፡፡ እመቤታችንም ይህን ጊዜ ‹‹ምነው ይህስ ነገር ደጋገመኝ እንዲህ ያለውን ነገር ቤተ መቅደስ ሄደው ሊረዱት ይገባል›› ብላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዳ ወርቅና ሐር እያስማማች ስትፈት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እሁድ ቀን በ3 ሰዓት በገሃድ ተገለጸላትና እጅ እየነሳ እየሰገደ አበሠራት፡፡ ‹‹የዕውነተኛ ንጉሥ እናቱ እመቤታችን ላንቺ ፍቅር አንድነት ይባል›› አላት፡፡ ዳግመኛም ‹‹አንቺ ከሴቶች ይልቅ ተለይተሸ ንዕድ ክብርት ነሽ›› አላት፡፡ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናቸ ክብርት እመቤታችንም የብርሃናዊውን መአልክ የቅዱስ ገብርኤልን ቃል በሰማች ጊዜ ‹‹እንዲህ ያለውን ሰላምታ እንደምን ይቀበሏል! እንዴትስ መቀበል ይቻላል? እንጃ›› አለችው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ‹‹ማርያም ሆይ! መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፣ ኃይለ ልዑል ወልድም ሥጋሽን ይለብሳልና አይዞሽ አትፍሪ›› አላት፡፡ ዳግመኛም ‹‹ይህ ካንቺ የሚወለደው ጽኑ ከሃሊ ነው፡፡ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ፣ እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፣ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም›› አላት፡፡ እመቤታችንም መልአኩን ‹‹ምድር ያለ ዘር ፍሬን አትሰጥምና እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?›› አለችው፡፡ መልአኩም መልሶ ‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ እርሷ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፡፡ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፣ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና›› አላት፡፡ ክብርት እመቤታችንም ይህን ጊዜ ‹‹እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ›› አለችው፡፡ መልአኩም ከእርሷ ዘንድ ሄዶ ተሠወረ፡፡ አካላዊ ቃልም በማኅፀኗ አደረ፡፡ በዚያችም ቅጽበት የእመቤታችን የፊቷ መልክ ተለወጠ፣ እንደፀሐይም አሸበረቀ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚች ቀን የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤል የበዓሉ መታሰቢያ ዳህና በሚባል አገርም ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራችበት ተአምራትም ያሳየበትና በዚች ቀን ቤተ ክርስቲያኒቱ የከበረችበት ነው የዚያች አገር ኤጲስቆጶስ አርኬላዎስ ምስክር የሆነበት ነው።
ይህም መልአክ ስለ ወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን ምሥጢር የታመነ ሆኖ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተላከ "የደስታ መገኛ ደስ ይበልሽ ጸጋን የተመላሽ ሆይ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው አንቺም ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ" አላት።
ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መወለድም ካህኑን ዘካርያስን ያበሠረው እርሱ ነው ይህ መልአክ እጅግ የከበረ የተመረጠ ገናና የሆነ ነውና ስለ እኛ ወደ እግዚአብሔር ይማልድ ዘንድ ልባችንን አንጽተን ወደዚህ የከበረ መልአክ እየለመንን መታሰቢያውን ልናደርግ ይገባል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ዳግመኛ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናቸ ክብርት እመቤታችንን የከበረ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ባበሠራት መሠረት ቅዱስ ደቅስዮስ በዓልን ያደረገበት እና ቅዱስ ደቅስዮስ ያረፈበት ዕለት ነው፡፡ በዓልን የማክበሩ ምክንያትም እንዲህ ሆነ፡- መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ያበሠራትና የጌታችንም ፅንሰት የተከናወነው በመጋቢት ወር በ29ኛው ቀን በዕለተ እሁድ በ3 ሰዓት ነው፡፡ ታዲያ ምነው በታኅሣሥ 22 ብሥራቱና ፅንሰቱ ተከበረ? ቢሉ መጋቢት 29 ቀን ሰሙነ ሕማማት ላይ ይውላልና በዚህ ወቅት ደግሞ ፍጹም ሐዘን ልቅሶ ጾም ጸሎት ይያዛል እንጂ ደስታ ፌሽታ እልልታ ጭብጨባ የለም፡፡ ዓቢይ ጾም ፍጹም የሐዘን ወራት ነው፡፡ ታቦት አውጥቶ በዓል ማክበር ስህተት ነው፤ የአባቶችንም ሥርዓት ማፍረስ ነው፡፡ ምስጋና ይድርሳቸውና ቅዱሳን አባቶቻችን ሁሉንም ነገር በሥርዓት በሥርዓቱ አድርገው ሰፍረው ቆጥረው አስቀምጠውልናል፡፡ ከዓቢይ ጾም በኋላ ያሉትን 50 ቀናት ረቡዕና ዓርብንም ጭምር ሥጋ እንኳን እንድንበላ ነው ሥርዓት የሠሩልን፡፡ አባቶቻችን የሠሯት ሕግ ፍጽምት ናት፡፡ በዚህም መሠረት አባቶቻችን ሥርዓትን ሠሩልንና የመጋቢት 27 የጌታችንን የስቅለቱን በዓል ወደ ጥቅምት 27 ቀን አምጥተው እንዲሁም የመጋቢት 5 የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስን የዕረፍት በዓል ወደ ጥቅምት 5 ቀን አዙረው እንዲከበር አድርገዋል፡፡ የመጋቢት 29 የብሥራቱን በዓል ደግሞ ወደ ታኅሣሥ 22 ቀን አዙረውት በዚህ ዕለት እንዲከበር አድርገውታል፡፡ አንድም ነገረ ልደቱን ከማክበር አስቀድሞ ነገረ ፅንሰቱን ማዘከር ማክበር ተገቢና መሆንም ያለበት ነውና ነው፡፡ ይህንንም ያደረገው ታላቁ አባት ቅዱስ ደቅስዮስ ነው፡፡ በእመቤታችን ፍቅር ልቡ የነደደው ይህ ታላቅ አባት የእመቤታችንን ተአምራቶቿን የጻፈላትም እርሱ ነው፡፡ እርሱም ከፍቅሩ ጽናት የተነሣ የእመቤታችንን የተአምራቷን መጽሐፍ ሰብስቦ አዘጋጀ፡፡
አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናቸ ክብርት እመቤታችንም ተገለጸችለትና መጽሐፉን በእጇ አንሥታ ይዛ ‹‹ወዳጄ ደውስዮስ ሆይ! ይህን መጽሐፍ ስለጻፍክልኝ ባንተ ደስ አለኝ፣ አመሰገንኩህ፣ እንዳከበርከኝ እኔም አከብርሃለው›› አለችው፡፡ ከዚህም በኋላ ከእርሱ ተሠወረች፡፡ ደቅስዮስም እመቤታችንን ከመውዱ የተነሣ ፈጽሞ ደስ አለው፡፡ ፍቅሯም እንደ እሳት አቃጠለው፡፡ የእርሷን ክብር አብዝቶ ይጨምር ዘንድ ምን እንደሚያደርግ የሚሠራውን ያስብ ጀመር፡፡
ከዚህም በኋላ በዚያን ጊዜ ጾም ስለነበር ሰዎች አስቀድመው ሊያከብሩት ያልተቻላቸውን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ባበሠራት ቀን በዓሏን አከበረ፡፡ እርሱም የከበረ የሚሆን የልደትን በዓል ከማክበር አስቀድሞ በ8 ቀን አደረገ፡፡ ይኸውም ታኅሣሥ በባተ በ22ኛው ቀን ነው፡፡ ይኽችውም ሥርዓቱ እስካሁን ጸንታ ኖራለች፡፡ ሰዎቹም በዓሉን ባከበሩ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናቸ ክብርት እመቤታችን በእጇ የከበረ ልብስ ይዛ ዳግመኛ ለቅዱስ ደቅሲዮስ ተገለጸቸለትና ‹‹አገልጋዬ የሆንክ ወዳጄ ደቅስዮስ ሆይ! በዕውነት አመሰገንኩህ፣ በአንተ ደስ አለኝ፣ ሥራህንም ወደድኩ፡፡ በእኔም ደስ እንዳለህና የከበረ መልአክ ገብርኤል እኔን በአበሠረበት ቀን በዓሌን ስላከበርክ ሰውንም ሁሉ ስለእኔ ደስ ስላሰኘህ እኔም ዋጋህን ልሰጥህ መጥቻለሁ፤ አንተ በዚህ ዓለም እንዳከበርከኝ እኔም በሰው ሁሉ ፊት አከብርህ ዘንድ እወዳለሁ›› አለችው፡፡ ይህንንም ካለችው በኋላ ‹‹እርሷን ትለብስ ዘንድ ይህችን ልብስ እነሆ አመጣሁልህ፤ በላዩም ትቀመጥ ዘንድ ይህን ወንበር አመጣሁልህ ፡፡ ከሰው ወገን አንድ ስንኳ ይህችን ልብስ ሊለብሳት በዚህችም ወንበር ላይ ሊቀመጥ የሚቻለው የለም፡፡ ይህንን ነገሬን የሚተላለፍ ቢኖር እኔ እበቀለዋለሁ›› አለችውና ሰማያዊ ልብስና ሰማያዊ ወንበር ሰጠችው፡፡ እመቤታችንም ይህንን ተናግራ ከባረከችው በኋላ ከእርሱ ተሠወረች፡፡
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ደቅስዮስ በዚሁ በዓለ ብሥራትን ባከበረበት ዕለት ታኅሣሥ 22 ቀን ካረፈ በኋላ አንድ ሌላ ኤጲስቆጶስ በተሾመ ጊዜ እመቤታችን ለቅዱስ ደቅስዮስ የሰጠችውን ልብስ ለበሰ፣ በወንበሩም ላይ ተቀመጠ፡፡ ሰዎችም ይህን አይተው ‹‹እባክህ ይቅርብህ እመቤታችን እንዲህ ብላ ተናግራለችና›› ቢሉት በመታጀር ‹‹እርሱም (ደቅስዮስም) ሰው እኔም ሰው፣ እርሱም ኤጲስቆጶስ እኔም ኤጲስቆጶስ›› ብሎ በትዕቢት ተናገረ፡፡ በወንበሩም ላይ እንደተቀመጠ ወድቆ ሞተ፡፡ ይህንንም ያዩ ሁሉ ከእመቤታችን ተአምር የተነሣ አደነቁ፡፡ እጅግም ፈርተው እመቤታችንን አከበሯት፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ ለቅዱስ ደቅስዮስ የተለመነች ክብርን የተመላች ድንግል ወላዲተ አምላክ ለእኛም ትለመነን! አምላካችን ልጇ በምልጃዋ ይማረን!
No comments:
Post a Comment