ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 28 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 28

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ሃያ ስምንት በዚህች ቀን #ቅዱስ_ሰረባሞን በሰማዕትነት ያረፈበት፣ በደብረ ቊናጽል ተጋድሏቸውን የፈጸሙ #አባ_ሊቃኖስ የተሰወሩበት ነው።


ኅዳር ሃያ ስምንት በዚህች ቀን የሀገረ ኒቅዮስ ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ሰረባሞን በሰማዕትነት አረፈ።
ይህም ቅዱስ በኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ለሆነ ለእስጢፋኖስ ከዘመዶቹ ውስጥ ነው። የአባቱም ስም አብርሃም ነው እርሱ የሌዊ ልጅ የዮሴፍ ልጅ ለስምዖን ወንድም ለእስጢፋኖስ እናት ወንድሟ የሆነ ነው። በተወለደም ጊዜ በአባቱ ስም ስምዖን ብለው ጠሩት አባቱም ሲሞት ክርስቲያን ይሆን ዘንድ ወደደ።
ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ወደ ኤጲስቆጶስ አባ ዮሐንስ እንዲሔድ አዘዘው እንዳዘዘውም ሔደ። እርሱም የመድኃኒታችንን የክርስቶስን ሰው የመሆኑን ምሥጢር ገለጠለት ግን ዘመዶቹ የሆኑ አይሁድን ስለፈራ በኢየሩሳሌም አገር የክርስትና ጥምቀትን ሊአጠምቀው አልደፈረም።
ኤጲስቆጶሱም ስለርሱ ምን እንደሚያደርግ ሲያስብ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጣለት ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎናስ እንዲልከው አዘዘችው።
ሰረባሞንም እየተጓዘ ሳለ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ቀደም ብሎ በሰው አምሳል ወደ ቴዎናስ ቀርቦ ስለ ቅዱስ ሰረባሞን አስረዳው ሰረባሞንም በደረሰ ጊዜ የእግዚአብሔርን ሕግ አስተምሮ የከበረች የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው።
ከዚህም በኋላ ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ በሆነች በአባ ሳዊሮስ ገዳም ውስጥ መነኰሰ አባ ቴዎናስም በአረፈ ጊዜ በእርሱ ፈንታ አባ ጴጥሮስ ተሾመ። ያን ጊዜም መልክተኞችን ልኮ ይህን አባ ሰረባሞንን ወደርሱ አስመጥቶ በሊቀ ጵጵስናው ሥራ እንዲራዳው አደረገ።
ከዚህም በኋላ ኒቅዮስ ለሚባል አገር ኤጲስቆጶስነት ሾመው። ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትም በእርሱ ደስ አላቸው እግዚአብሔርም በእጆቹ ድንቆች ተአምራትን አደረገ በአገሩ አቅራቢያ ሰዎች የሚያመልኳቸው የጣዖታት ቤቶች ነበሩ ያጠፋቸውም ዘንድ እግዚአብሔርን ለመነው በዚያንም ጊዜ ምድር አፏን ከፍታ ዋጠቻቸውና በቦታው ላይ ባሕር ሁኖ ሸፈናቸው። እግዚአብሔርም ከሀገረ ስብከቱ ጣዖታትን ደመሰሰ ዳግመኛም አብን ወልድን መንፈስ ቅዱስን አንድ አካል የሚያደርግ የሰባልዮስን ስድብ አስወገደ።
ዲዮቅልጥያኖስም ክዶ ጣዖታትን በአመለከ ጊዜ ቅዱስ ሰረባሞን የአማልክትን አምልኮ እንደሚሽር ነገሩት እርሱም ሰምቶ ተቆጣ ወደረሱም እንዲአመጡት አዘዘ ሲወስዱትም ከንጉሥ መልክተኞች ጋር እስክንድርያ ከተማ ደረሰ ሊቀ ጳጳሳት ጴጥሮስም ወደርሱ መጣ ከእርሱም ጋር ብዙ ካህናት ነበሩ ሰላምታም ሰጡት ፊቱም እንደ እግዚአብሔር መልአክ ፊት ብሩህ ሁኖ አዩት።
ወደ ንጉሡም በደረሰ ጊዜ በተለያዩ በብዙ ዓይነት ሥቃይ አሠቃየው ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ያለ ጥፋት በጤንነት አስነሣው። ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙዎች አመኑ።
ሕዝቡ ሁሉ በእርሱ ምክንያት በጌታችን እንዳያምኑ ንጉሡ ፈርቶ የእንዴናው ገዥ አርያኖስ ወዳለበት ወደ ላይኛው ግብጽ ሰደደው በዚያ እንዲአሠቃየውና ራሱንም በሰይፍ እንዲቆርጥ በዚያንም ወቅት መኰንኑ አርያኖስ የኒቅዮስ ከተማ ወደብ አቅራቢያ በመርከብ ውስጥ ነበር። መርከቢቱም ቆመች ከቦታዋም ሊአንቀሳቅሱዋት አልተቻላቸውም ቅዱስ ሰረባሞንንም አውጥተው ለሀገሩ ደቡብ ወደ ሆነ ቦታ ወስደው በዚያ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት ምእመናንም መጥተው ሥጋውን ወስደው በክብር ገነዙትና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከሥጋውም ድንቆች ተአምራት ሆኑ።

በዚችም ቀን በኢትዮጵያ ምድር በደብረ ቊናጽል ተጋድሏቸውን የፈጸሙ አባ ሊቃኖስ ተሰወሩ።
አቡነ ሊቃኖስ ከዘጠኙ ቅዱሳን ውስጥ አቡነ ሊቃኖስ ለየት የሚሉበት ነገር ቢኖር ዓሥሩም የእጆቻቸውና የእግሮቻቸው ጣቶች እንደፋና ያበሩ ነበር፡፡ ይህንንም ገድለ አቡነ አረጋዊ "ቆመው ጸሎት በሚጸልዩበት ጊዜ ዓሥሩ የእጆቻቸው ጣቶችና ዓሥሩ የእግሮቻቸው ጣቶች እንደፋና የሚያበሩበትና እንደመብረቅ የሚብለጨልጩበት ጊዜ አለ" በማለት ይገልጸዋል፡፡ በሥዕላቸውም ላይ ይህንኑ ለማሳየት አባቶቻችን የራሳቸውን ጥበብ ተጠቅመዋል፡፡
የአቡነ ሊቃኖስ ገዳማቸው በደብረ ቁናጽል አክሱም ከአባ ጰንጠሌዎን ገዳም አቅራቢያ ይገኛል፡፡ ጻድቁ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደረጉ ነበር፡፡ መላእክትም ዘወትር ባለመለየት ይጎበኙዋቸው ነበር፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዘወትር እየተገለጠላቸው ይባርካቸውና ቃልኪዳን ይሰጣቸው ነበር፡፡
በጸሎታቸውም አጋንንትን አውጥተዋል፣ ድውያንን ፈውሰዋል፣ ዕውራንን አብርተዋል፣ ሙታንን አንሥተዋል፡፡ ስለዘጠኙ ቅዱሳን ሐዋርያዊ አገልግሎት ከአቡነ አረጋዊ ገድል ጋር ጥቅምት 14 በስፋት ስለተጻፈ ከዚያ ላይ ይመለከቷል፡፡
ከተስዓቱ ቅዱሳን ውስጥ አራቱ ሞትን ሳያዩ ተሰውረዋል፡፡ አቡነ አረጋዊ ጥቅምት 14 ቀን ተሰወሩ፡፡ አቡ ገሪማ ሰኔ 17 ቀን፣ አቡነ አፍጼ ግንቦት 29 ቀን፣ አቡነ ሊቃኖስ ህዳር 28 ቀን ተሰወሩ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages