አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ሃያ ሰባት በዚህች ቀን አባታችን አቡነ_ተክለ_ሐዋርያት ዕረፍታቸው ነው፣ ሕዋሳቱ የተቆራረጠ ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘግሙድ በሰማዕትነት አረፈ፣ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ቅዱስ_ፊልሞና_ሐዋርያ ዕረፍቱ ነው፣ በንሑር ከሚባል አገር ቅዱስ_ጢሞቴዎስ በሰማዕትነት አረፈ።
ኅዳር ሃያ ሰባት በዚህች ቀን አባታችን አቡነ ተክለ ሐዋርያት በክብር አርፈዋል።
አባታቸው የእናርዕት አገረ ገዥ የነበሩት እንድርያስ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ እሌኒ ይባላሉ፡፡ የትውልድ ሀገራቸው ሸዋ ሲሆን በዚሁ የምትገኘውን ታላቋን የደብረ ጽሙናን ገዳም የመሠረቱ ሲሆን በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን የነበሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ገና በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ አጋንንትን እያቃጠሉ ያጠፏቸው ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ተምረው ከጨረሱ በኋላ ገና በድቁና እያገለገሉ ሳለ 40 ቀን በማክፈል ይጾሙና ይጸልዩ ነበር፡፡
አባታችን የመነኮሱትና ብዙ ተጋድሎአቸን ፈጽመው ወደ ሰማይ ተነጥቀው ሥላሴን እስከማየት የደረሱት በደብረ ሊባኖስ ነው፡፡ ያመነኮሷቸውም ሁሉን በስውር ያለውን የሚውቁት አቡነ ዮሐንስ ከማ ናቸው፡፡ አባታችን ማታ ማታ ከባሕር ውስጥ ገብተው ሲጸልዩ እያደሩ በቀን 30 ፍሬ አተር ብቻ እየተመገቡ ይጾሙ ነበር፡፡ ስውራን የሆኑ ቅዱሳን አባታችም እየተገለጡላቸው ምሥጢራትን ይነግሯቸዋል፡፡ ከስግደታቸውም ብዛት የተነሣ የአባታችን ሁለት የእጆቻቸው አጥንቶች ተሰበሩ፡፡ ከቁመታቸውም ብዛት የተነሣ እግሮቻቸው አበጡ፡፡ ስምንት ስለታም ጦሮችን ያሉበትን የብረት ሰንሰለት በወገባቸው ታጥቀው ሁለት ሁለቱን በፊት በኋላ በቀኝ በግራ አድርገው ታጠቁ፡፡ እነዚህም ጦሮች ከልደት፣ ከጥምቀትና ከትነሣኤ በዓል በቀር ከወገባቸው ላይ አያወጧቸውም ነበር፡፡
በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሲቀመጡ፣ ሲነሡና ሲሰግዱ ጦሮቹ ሰውነታቸውን ሲወጓቸው በዚያን ጊዜ የጌታችንን በጦር መወጋቱንና መከራውን ያስባሉ፡፡ በታመሙም ጊዜ "ኃጢአተኛ ሰውነቴ ሆይ ስለአንቺ የተቀበለውን የክርስቶስን መከራ አስቢ" እያሉ ሰውነታቸውን ይጎስማሉ፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነጥቆ ወስዶ ከገነት ዕፅ አምጥቶ አባታችንን ካሸታቸው በኋላ ግን ርሃብና ጥም የሚባል ነገር ጠፍቶላቸዋልና ምድራዊውን ነገር ለመቅመስ የሚጸየፉ ሆኑ፡፡ ጻድቁ ቅስና እንዲሾሙ የገዳሙ አበምኔት ግድ ቢሏቸውም አባታችን ግን እምቢ ስላሉ "ለጳጳሱ መልእክት አድርስልኝ" ብለው በዘዴ ልከዋቸው ጳጳሱም በመንፈስ ተረድተው ቅስና ሾመዋቸዋል፡፡
ጻድቁ በአቡነ አትናቴዎስ መቃብር ላይ ሄደው አጥብቀው ይጸልዩ በነበረበት ወቅት ብርሃን ይወርድላቸው እንደነበር እግዚእ ክብራ የተባለች አንዲት ትልቅ ጻድቅ እናት ትመለከት ነበር፡፡ አባታችን ሁልጊዜ "ሦስት ነገሮችን እፈልጋለሁ እነርሱም ከሐሜት ስለመራቅ፣ ክፉ ነገርን ከማየት ስለመራቅና ከንቱ ነገርን ከመስማት ስለመራቅ ናቸው" እያሉ ይናገሩ ነበር፡፡ አቡነ ተክለ ሐዋርያት የታላቁን አባት የአቡነ አትናቴዎስን መቃብር ለማየት በሄዱ ጊዜ ቆመው ሲጸልዩ ከእግራቸው በታች ጸበል ፈልቆ በጽዋ ውኃ ሲፈስ አገኙት፡፡ ውኃውንም ወስደው ቦታውን ላሳየቻቸው ለእግዚእ ክብራ ሰጧት፡፡ እርሷም መካን ለነበረችው ገረዷ ሰጠቻትና ገረዷም በጻድቁ ጸሎት የፈለቀውን ውኃ ጠጥታ ልጅ ወለደች፡፡ ይህ አባታችን ያፈለቁት ጸበል ዛሬም ድረስ ሲፈስና ሕሙማንን ሲፈውስ ይገኛል፡፡
ጸድቁን የታዘዘ መልአክ መጥቶ ወደ በረሃ እንዲገቡ ስለነገራቸው ወደ ምድረ ሐጋይ ሄደው በዚያ ታላቅ በረሃ ውስጥ ለ41 ዓመታት ጽኑ ተጋድሎን ተጋድለዋል፡፡ ባሕር ውስጥ በሚገኝ ዋሻ ውስጥም ገብተው ብዙ ዘመን በጸሎት ኖረዋል፡፡ ሰዎች የአባታችንን የእግራቸውን እጣቢ ሕመምተኞች ላይ በረጩት ጊዜ በላያቸው ላይ ያደረባቸው ርኩስ መንፈስ እየጮኸ ይወጣል፡፡ ቅዱሳን መላእክት ዘወትር እየመጡ አባታችንን ይጎበነኟቸዋል፡፡ እመቤታችን ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስከትላ እየመጣች ትጎበኛቸዋለች፡፡ ብዙ ተጋድሎ ባደረጉበት ዋሻ ውስጥም ሳሉ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ተገልጦላቸው በቦታው ላይ ታላቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ መላእክትም ወደ ሰማይ አሳርገዋቸው በሥሉስ ቅዱስ መንበር ፊት አቁመዋቸው ታላቅ ምሥጢርን አይተዋል፡፡
አቡነ ተክለ ሐዋርያት ለመድኃኔዓለም ሥጋና ደም ትልቅ ክብር ያላቸው አባት ናቸው፡፡ አንድ በከባድ በሽታ ይሠቃይ የነበረ ሰው "ነፍሴ ከሥጋዬ ሳትለይ ፈጥናችሁ ወደ ቤተ ክርስቲያን ውሰዱኝና የጌታችንን ሥጋና ደም ልቀበል" ብሎ ቤተሰቦቹን ለመነ፡፡ ቤተሰቦቹም ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደውት ሥጋ ወደሙን ከተቀበለ በኋላ ከሆዱ ውስጥ ዥንጉርጉር ደምና ሐሞት ከመግል ጋር ወጣ፡፡ በዚህም ጊዜ ካህናቱ ስለ ሥጋ ወደሙ ክብር ብለው በዕቃ ተቀበሉት፡፡ ሽታው ግን ቤተ ክርስቲያኑን አናወጸው፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችን ተክለ ሐዋርያት መድኃኔዓለም ክርስቶስ ስለእኛ ብሎ በዕለተ ዐርብ መራራ ሐሞትና ከርቤ መጠጣቱን አስበው ከሰውየው ሆድ ውስጥ የወጣውን ደም የተቀላቀለበትን መግልና ሐሞት ስለ ሥጋ ወደሙ ክብር ብለው በቤተ ክርስቲያኑ በተሰበሰቡት ሰዎች ፊት አንሥተው ጠጡት፡፡ ይህም የሆነበት ዕለት እሁድ ነበርና አባታችን እዚያው ቤተ ክርስቲያኑ ዋሉ፡፡ መድኃኔዓለም ክርስቶስም አባታችን ወዳሉበት መጥቶ "ወዳጄ ተክለ ሐዋርያት ሆይ ሰላምታ ይገባሃል፡፡ በሰው ሁሉ ፊት እንዳከበርከኝ እኔም በምድራውያንና በሰማያውያን መላእክት ሁሉ ፊት አከብርሃለሁ" ካላቸው በኋላ ሌላም ብዙ ቃልኪዳን ገባላቸው፡፡ ሰባት አክሊላትንም ካቀዳጃቸው በኋላ ዕጣ ክፍላቸው ከመጥምቁ ዮሐንስና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር መሆኑን ነግሯቸዋል፡፡
ከዚህም በኋላ አባታችን ወደተለያዩ የሀገራችን ገዳማት በመሄድ ከቅዱሳን በረከትን ከተቀበሉ በኋላ በየሄዱባቸው ገዳማት 40 ቀንና 40 ሌሊት ይጾማሉ፡፡ ከሰንበት በቀርም ምንም ምንመ አይቀምሱም፡፡ ሰንበትም በሆነ ጊዜ የዕንጨቶችን ፍሬ ብቻ ይመገባሉ፡፡ አባታችን ከዋልድባ ገዳም ወጥተው ወደ ደባብ ገዳም በመሄድ በዚያ አርባዋን ቀን ከጾሙ በኋላ ጌታችን ተገለጠላቸውና "ተነሥተህ ወደ አልተጠመቁ አሕዛብ አገር ሂድ በዚያ በአንተ እጅ የሚጠመቁና የሚድኑ ብዙ አሕዛብ አሉና በስሜ አስተምር" አላቸው፡፡ አባታችንም ተነሥተው "ሀገረ ጽልመት" ወደሚባል ወዳልተጠመቁ አሕዛብ አገር ሄደው የአገሪቱን ንጉሥና ሕዝቡንም በጠቅላላ አስተምረው በተአምራቶቻቸው አሳምነው አጥምቀዋቸዋል፡፡ በዚያም ሀገር ለአሕዛብ እየጠነቆለ የሚኖር አንድ መሠርይ ነበርና አባታችንን አግኝተውት አስተምረው በላዩ ያለበትን ርኩስ መንፈስ አውጥተውለት አጥምቀውታል፡፡
አባታችን የእግዚአብሔርን ወዳጅ የሊቀ ነቢያትን መቃብር ያሳቸው ዘንድ ጌታችንን በለመኑት ጊዜ ጌታችን በሌሊት ተገልጦላቸው ወስዶ የሙሴን መቃብር አሳይቷቸዋል፡፡ የአባታችን በትራቸው እንደሙሴ በትር ተአምር ትሠራ ነበር፡፡ ሕመምተኞች በትሯን አጥበው የእጣቢውን ውኃ ሲጠጡት ፈጥነው ከሕመማቸው ይፈወሱ ነበር፡፡ በጌታችን የጥምቀት በዓል ቀን አባታችን ተክለ ሐዋርያት ጸሎት በማድረግ ሰዎችን ሲያጠምቁ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሳቸው ላይ ይታይ ነበር፡፡ በቆሙበትም ቦታ የብርሃን ምሰሶም እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶ ተተክሎ ታይቷል፡፡ አባታችን ቅዱሳት ገዳማትን ለመሳለም ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ የሚዘዋወሩት በብርሃን ሰረገላ ነበር፡፡ በደመናም ተጭነው ሲሄዱ ያዩአቸው ቅዱሳን አሉ፡፡ የመኮትን ቃል ወንጌልን ሲጸልዩ ቅዱሳን መላእክት መጥተው በክንፋቸው ይጋርዷቸው ነበር፡፡ የአቡቀለምሲስን ራእይ በጸለዩ ጊዜ ራሱ ዮሐንስ ወንጌላዊው መጥቶ በአጠገባቸው ይቆም ነበር፡፡
አባታችን የዕረፍታቸው ጊዜ በደረሰ ሰዓት የብርሃን እናቱ እመቤታችን ሚካኤልንና ገብርኤልን ሰማዕቱን ቅዱስ ጊዮርጊስን አስከትላ መጥታ "የጳውሎስ አበባ የጴጥሮስ ፍሬ የልጄ ተክል ወዳጄ ተክለ ሐዋርያት ሆይ ሰላምታ ይገባሃል" አለቻቸው፡፡ ዳግመኛም "እነሆ የተመኘኸውን ታገኘዋለህና፣ ጊዜው ቀርቧልና ጽና በርታ እኔንና ልጄን የለመንከንን ነገር አስብ" ብላቸው ተሰወረች፡፡ አባታችን በተደጋጋሚ እመቤታችንንና ጌታችንን ስለ ስሙ ብለው ሰማዕት ይሆኑ ዘንድ ይለምኑ ስለነበረ ነው እመቤታችን ይህንን የነገረቻው፡፡
ከዚህም በኋላ የንጉሡ የዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ባለቤት አባታችንን "ስለ ክርስቶስ ብለሁ መጥተው አስትምሩን ምከሩን" ብላ ለመነቻቸውና አባታችን ሄደው መከሯት፡፡ ልጃቸውን ገላውዴዎስን አስተምረው ባረኩት፡፡ ለንጉሡ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብም ብዙ ምሥጢርን ነገሩት፡፡ ንጉሡም በአቅራቢያው የእመቤታችን ታቦት ካለችበት ቦታ ሦስት ወር ከእርሱ እንዲቀመጡ ለመናቸው፡፡ እሳቸውም በዚያ ሲቆዩ የንጉሡ ወታደሮች በፈረስ ግልቢያና በድብደባ እየተገዳደሉ አይተው አዘኑ፡፡ "ይህ የአረመኔዎች ሥራ ነው" ብለው ሕግንና ሥርዓትን ሊያስተማሯቸው አስበው ወደ ንጉሡ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ እንዲያናግራቸው መልእክተኛ ላኩበት፡፡ ንጉሡም "ዛሬ አይመቸኝም" አላቸው፡፡ አባታችንም መልአክተኛውን ስለ ሰዎቹ በከንቱ መሞትና ሌላንም መልእክቶችን ላኩለት፡፡ መልእክተኛውም የመዘምራን አለቃ ደብተራ ስለነበር አባታችንን "እኔ እያለሁ ለአንተ ነቢይነትን ማን ሰጠህ?" ብሎ በክፉ ቃል ተናገራቸውና ሄዶ ከንጉሡ ጋር በክፉ ወሬ አጣላቸው፡፡ ወደ ንጉሡ ገብቶ "ንጉሥ ሆይ ይህ መነኩሴ ጻድቅ ነኝ ይላል፣ አንተን ግን ይሰድብሃል ባንተ ላይም ብዙ ዘለፋ ይናገራል…" አለው፡፡ ንጉሡም በጣም ተቆጥቶ አባተችን አስመጥቶ "ለምን ይዘልፉኛል?" አላቸው፡፡ አባታችንም ዘለፋ ሳይሆን ሊሆን የማይገባውን ነገር ሁሉ ነገሩት፡፡ ይልቁንም ስለሴቶቸና ስለፍርድና መሥራት ስለማይገባው ነገር ሁሉ ሲናገሩት ንጉሡም ደፍረው ስለተናገሩት በኃይል ይደበድቧቸው ዘንድ አዘዘ፡፡ ከአፍና አፍንጫቸውም ደም እንደውኃ እስኪርድ ድረስ ደበደቧቸውና አሠሯቸው፡፡
ዳግመኛም ንጉሡ ቢያስመጣቸው ደግመው ስለጥፋቱ ገሠጹት፡፡ አሁንም ጽኑ ድብደባን አደረሱባቸውና አሠሯቸው፡፡ በዚያም ብዙ አሠቃዩአቸው፡፡ በዚህም ጊዜ እመቤታችን ለአባታችን ለተልጣላቸው "እነሆ የልጄን ትእዛዝ ፈጸምህ የተመኘኸውን አገኘህ፣ ነገር ግን ሁለት የትዕግስት በር ይቀርሃል እርሱን ከፈጸምክ ልጄ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ያሳርፍሃል" አለቻቸው፡፡ አባታችንም እመቤታችንን "ሰማዕትነት ስጪኝ ያልኩሽ በክርስቲያናዊ እጅ ነውን? ነገር ግን አማላጅነትሽ ሰማዕትነትን ለመፈጸም ያጽናኝ" አሏት፡፡
ከዚህም በኋላ የንጉሡ ጭፍሮች አባታችንን በጠጠር ጎዳና ላይ እየጎተቷቸው ብዙ አሠቃዩአቸው፡፡ የንጉሡ ስምንት ጭፍሮች በመቀጣጠብ "ንጉሡ መቼ እሞታለሁ" ብሎሃል እያሉ በመሾፍ አባታችንን ወደ ዱር ወስደው በአቅማቸውን ያህል በኃይል ደበደቧቸው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ባያጸናቸው ኖሮ በአንደኛው ሰው ዱላ ብቻ ነፍሳቸው በወጣች ነበር፡፡ በእሥርም 8 ወር ከተቀመጡ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት የሚያርፉበት ጊዜ ስለደረሰ ቅዱሳን መላእክት ከእሥር ቤት ነጥቀው ወስደው ወደ ሰማይ አሰረጓቸውና በሥሉስ ቅዱስ ፊት አቆሟቸው፡፡ በዚያም ለሦስት ሳምንት ቆዩ፡፡ ጌታችንም ለአባታችን ብዙ የሕይወትን ምሥጢር ነገራቸው፡፡ እንደጸሐይ የምታበራዋን የምድርን ማዕዘነ ዓለም የምታክል ሰማያዊት ሀገር ርስት አድርጎ ሰጣቸው፡፡ "ስምህን ከሚጠሩ ልጆችህ፣ የገድልህን መጽሐፍ ከጻፉ ካጻፉ ከሰሙ፣ ዝክርን ካዘከሩ በጸሎትህ ከተማኑ ልጆችህ ጋር የምትኖርባት ዕድል ፈንታህ ናት" አላቸው፡፡
አባታችንም ጌታችንን "አቤቱ ፈጣሪዬ ሆይ ይህን ቃልኪዳን የሰጠኸኝ አንተን የሚያስደስት ምን ነገር አደረኩልህ በቸርነትህ ነው እንጂ" አሉት፡፡ ጌታችንም "ዕድል ፈንታህ ጽዋ ተርታህ እውነተኛ የእኔ ምስክር ከሚሆን ጊዮርጊስና ወዳጄ ከሚሆን ከዮሐንስ ጋራ ይሁን" አላቸው፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ሰባት አክሊትን አቀዳጃቸውና "አንዱ ስለ ድንግልናህ ነው፣ አንዱ ሃይማኖትህን ለማስተማር ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ አገር ስለሄድክ ነው፣ አንዱ ቅዱሳንን ለመጎብኘት እየተዘዋወርክ ከቅዱሳን ጋራ ስለተነጋገርክበት ነው፣ አንዱ ስለየዋህነትህ ኃላፊ ዓለምን ስለመናቅህ ነው፣ አንዱ ስለተወደደ ክህነትህ ነው፣ አንዱ ታግሰህ ስለመጋደልህ ነው፣ አንዱም ደምህን ስለማፍሰስህ ነው" አላቸው፡፡ ጌታችን ይህን ቃልኪዳንና ክብር ከሰጣቸው በኋለ "ከዚህ ከሚጠፋው ዓለም አሳርፍሃለሁ" አላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ከተነጠቁበት ከሦስት ሳምንት በኋላ ተመልሰው ከእሥር ቤቱ ሆነው ያዩትን ሁሉ ለአንድ ወዳጃቸው ለሆነ ቄስ ተክለ ኢየሱስ ነገሩት፡፡
ዳግመኛም አባታችን በእሥር ቤት ሳሉ በመላአክት እጅ ተነጥቀው ወደ ሰማይ ከተወሰዱና ከጌታችን ቃልኪዳን ከተቀበሉ በኋላ የብርሃን እናቱ ክብርት እመቤታችን እንዳነጋገረቻቸው ተናገሩ፡፡ "እመቤታችን ማርያም 'ዘርዐ ያዕቆብን ይቅር በልልኝ፣ ኃጢአቱንም ተውለት፣ በልጄ ፊት ቀርበህ 'ግፌን ተመልከትልኝ' አትበል እርሱ ዘወትር ስሜን ይጠራልና፣ ስለ ድንግልናዬም የሚያስተምር ነውና' አለኝ፡፡ እኔም የእመ ብርሃንን ርኅራኄ አደነቅሁና 'እመቤቴ ሆይ! አንቺ እያዘዝሽኝ ወድጄ ነውን የምመረው! እኔ ኃጢአተኛ ለምን ይቅር አልልም ይቅር እላለሁ እንጂ ነገር ግን የአንቺ ጸሎት ሁላችንንም ይማረን' አልኋት፡፡"
አቡነ ተክለ ሐዋርያት በመጨረሻ ዘመናቸው በንጉሡ አደባባይ ኅዳር 27 ቀን ሲያርፉ ቅዱሳን መላእክት መጥተው ገንዘው ቀብረዋቸዋል፡፡ በመካነ መቃብራቸውም ላይ ብርሃን ተተክሎ ታይቷል፡፡ ንጉሡ ዘርዐ ያዕቆብም በመካነ መቃብራቸው ላይ ብርሃን መውረዱንና ብዙ ተአምራት ማድረጉን በሰማ ጊዜ እጅግ አደነቀ፡፡ ብዙ ምልክትም አገኘ፡፡ አባታችን ሰማዕትነትን ይቀበሉ ዘንድ ተመኝተው ራሳቸው ለምነዋልና መደብደብ መሠቃየታቸው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ንጉሡም መነኮሳት ልጆቻቸውንም ጠርቶ የአባታችንን ሥጋ በክብር እንዲያፈልሱ ነገራቸው፡፡ ርስት ጉልት የሚሆን መሬት ሰጣቸው፡፡ ነገር ግን ዐፅማቸው ከመፍለሱ በፊት ንጉሡ በሞት ስላረፈ ልጁ በእደ ማርያም በአባቱ ትእዛዝ መሠረት የአባታችንን ዐፅም ከ13 ዓመት በኋላ ወደ ደብረ ጽሞና በክብር አፍልሶታል፡፡ ታቦታቸው ደብረ ሊባኖስ አውራጃ አጋት መድኃኔዓለም ይገኛል፡፡
ዳግመኛም በዚህች ቀን ለፋርስ ንጉሥ ለሳፎር ልጅ ለንጉሥ ሰክራድ ከጭፍሮቹ ውስጥ የሆነ ሕዋሳቱን የተቆራረጠ ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት አረፈ።
ይህም ንጉሥ ሰክራድ እጅግ ይወደው ነበር ስለ መንግሥቱ ሥራ ሁሉ ከእርሱ ጋር ይማከር ነበርና ስለዚህም የቅዱስ ያዕቆብን ልቡና አዘንብሎ ፀሐይንና እሳትን እንዲአመልክ አደረገው ።
በሃይማኖቱም ከንጉሡ ጋር እንደተስማማ የተቀደሱ እናቱ ሚስቱና እኅቱ በሰሙ ጊዜ እንዲህ ብለው ጽፈው ወደርሱ ላኩ የቀናች የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት ትተህ የፍጡራንን ጠባይ ለምን ተከተልክ እሊህም ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት እሳት ናቸው ዕወቅ ከዛሬ ጀምሮ በንጉሥ ሃይማኖት ከኖርክ እኛ ከአንተ የተለየን ነን።
የመልእክታቸውንም ጽሑፍ በአነበበ ጊዜ መሪር ልቅሶን አለቀሰ በዚህም የጥፋት ምክር ጸንቼ ብኖር ከቤተ ሰቦቼና ከወገኖቼ የተለየሁ መሆኔ ነው ። ደግሞስ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እንዴት እቆማለሁ አለ ከዚህም በኋላ የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍቶች ማንበብ ጀመረ የንጉሡን አገልግሎትም ተወ ለንጉሡም ወዳጅህ ያዕቆብ እነሆ አገልግሎትህን አማልክቶችህንም ማምለክ ተወ ብለው ነገሩት።
ንጉሡም ልኮ ወደርሱ አስቀርቦ አገልግሎትህን ለምን ተውክ አለው ቅዱስ ያዕቆብም እንዲህ አለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ ወንጌል በሰው ፊት ያመነብኝን ሁሉ እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ በሰው ፊት የካደኝንም በአባቴ ፊትና በመላእክት ፊት እክደዋለሁ ብሏልና ስለዚህ አገልግሎትህን ፍቅርህን አማልክቶችህንም ማምለክ ትቼ ሰማይና ምድርን ፀሐይን ጨረቃን ከዋክብትን የሚታየውንና የማይታየውን ለፈጠረ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የምሰግድ ሆንኩ።
ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ ደሙ እንደ ውኃ በዝቶ እስቲፈስ ታላቅ ግርፋትን እንዲገርፉት አዘዘ እርሱ ግን ከበጎ ምክሩ አልተመለሰም ዳግመኛም ሕዋሳቱን በየዕለቱ እንዲቆርጡ አዘዘ የእጆቹንና የእግሮቹን ጣቶች ሃያውን ቆረጡ ክንዶቹንና እግሮቹን እስከ ጭኖቹ ድረስ ወደ አርባ ሁለት ቁራጭ በየጥቂቱ ቆረጡት ። በሚቆርጡትም ጊዜ ሁሉ ጌታዬና ንጉሤ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ዕንጨት ቅርንጫፍ ሰውነቴን በይቅርታህ ገናናነት ተቀበል የወይን አታክልት ያለው በየሦስት ዓጽቅ ሲቆርጡለት ዓጽቆቹ በዝተው ይበቅላሉ ይሰፋሉ በሚያዝያ ወር አብቦ ያፈራልና እያለ የሚዘምርና የሚያመሰግን ሆነ ።
ደረቱና አካሉ እንደ ግንድ ድብልብል ሆኖ በቀረ ጊዜ ነፍሱን ለመስጠት እንደ ደረሰ አውቆ በዚያን ጊዜ በዓለም ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሁሉንም ይምራቸው ዘንድ እግዚአብሔርን ለመነው እንዲህም አለ ለእኔ ግን ወደ አንተ የማነሣው አካል አልቀረልኝም ሕዋሳቶቼ ተቆርጠው በፊቴ የወደቁ ስለሆነ አሁንም ነፍሴን ተቀበላት አለ ።
በዚያንም ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ አረጋጋው አጸናውም ያን ጊዜ ነፍሱ ደስ አላት ነፍሱንም ከመስጠቱ በፊት ወታደሩ በፍጥነት መጥቶ የከበረች ራሱን በሰይፍ ቆረጠ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ ሥጋውንም ምእመናን ሰዎች ወስደው በመልካም አገናነዝ ገነዙትና በንጹሕ ቦታ አኖሩት ። እናቱ ሚስቱና እኅቱ በሰማዕትነት እንደሞተ በሰሙ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው ወደ ቅዱስ ያዕቆብም ሥጋ መጥተው ተሳለሙት አለቀሱለትም የከበሩ ልብሶችንም በላዩ አኖሩ ጣፋጮች የሆኑ ሽቱዎችንም ረጩበት ።
በደጋጎች ነገሥታት በአኖሬዎስና በአርቃዴዎስ በሌሎችም ዘመን አብያተ ክርስቲያን ታነፁ ገዳማትና አድባራትም ተሠሩ የሰማዕታትንም ሥጋ በውስጣቸው አኖሩ ታላላቆች ድንቆች ተአምራትም ከእሳቸው የሚታዩ ሆኑ ። የፋርስ ንጉሥም ሰምቶ በቦታው ሁሉ የሰማዕታትን ሥጋ ያቃጥሉ ዘንድ አዘዘ በሚገዛውም አገር ውስጥ ምንም ምን እንዳይተው አማንያን ሰዎችም መጥተው የቅዱስ ያዕቆብን ሥጋ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት ከዚያም ወደ ሀገረ ሮሀ ከሀገረ ሮሀም የከበረ ኤጲስቆጶስ ጴጥሮስ ወደ ግብጽ አገር ወደ ብሕንሳ ከተማ ወሰደው ። በዚያም ጥቂት ጊዜ ኖረ ከርሱ ጋርም መነኰሳት ነበሩ ከቀኑ እኩሌታም ሲጸልዩ የቅዱስ ያዕቆብ ሥጋ ከብዙ የፋርስ ሰማዕታት ሥጋ ጋር በአለበት ሰማዕታት አብረዋቸው ዘመሩ ባረኳቸውም ቅዱስ ያዕቆብም እግዚአብሔር እንዳዘዘ ሥጋዬ በዚህ ይኑር አለ ከዚህም በኋላ ተሠወሩ ።
ከዚህም በኋላ የከበረ ኤጲስቆጶስ ጴጥሮስ ወደ አገሩ ሊመለስ በወደደ ጊዜ ሥጋዬ በዚህ ቦታ ይኑር ያለውን የቅዱስ ያዕቆብን ቃል ተላልፎ የቅዱስ ያዕቆብን ሥጋ ወሰደ በዚያንም ጊዜ አስቀድሞ ወደ አመለከተው ቦታ ከእጆቻቸው መካከል ተመለሰ ከሥጋውም ታላላቅ የሆኑ ተአምራት ተገለጡ ።
በዚህችም ዕለት ከሰባ ሁለቱ አርድእት የአንዱ የፊልሞና የዕረፍቱ መታሰቢያው ነው።
ቅዱስ ፊልሞና ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሲሆን ብዙ ጊዜ "ጥዑመ - ቃል (አንደበቱ የሚጣፍጥ)" ተብሎ ይጠራል። በዘመነ ሐዋርያት በጣም ልጅ በመሆኑ እየተሯሯጠ ለአበው ይታዘዝ ነበር።
ጌታን አምኖ ተከትሎ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ተምሮ፣ ከቅዱስ መንፈሱ ነስቶ፣ ከቅዱስ እንድርያስ ጋር ለስብከት ወጥቷል። ሃገረ ስብከቱም ልዳ ነበረች። እርሱ ሲያነብ (ሲያስተምር) ሰው ሁሉ በተመስጦ ይሰማው ነበር። ሊገድሉት የመጡ ወታደሮች እንኳ በተደሞ መግደላቸውን ይረሱት ነበር።
አንዳንድ ቀን ደግሞ ወፎችና ርግቦች ያደምጡት፣ ያወሩትም ነበር። ይህቺ ቀን ለቅዱስ ፊልሞና ዕለተ ዕረፍቱ ናት።
በዚህችም ቀን በንሑር ከሚባል አገር ቅዱስ ጢሞቴዎስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሁልጊዜ በጾም በጸሎት ተጠምዶ የሚኖር ነው ስሟ ሞራ የሚባል ሚስት አለችው እርሷም የአጎቱ ልጅ ናት በሥራዋ ሁሉ ደስ የምታሰኘው መልካም ሴት ናት።
እንደዚህም በፍቅርና በስምምነት ሲኖር ከከሀዲ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ዘንድ የጣዖታት ቤቶች ይከፈቱ ዘንድ አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ ትእዛዝ ወጣ። ቅዱስ ጢሞቴዎስም ይህን ሰምቶ እጅግ ደስ አለው። እርሱ ስለ ክርስቶስ ፍቅር ደሙን ያፈስ ዘንድ ይህን ዘመን ይጠብቀው ነበርና ለሚስቱም ሊሠራው ያሰበውን ነገራት እርሷም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን አለች።
ከዚህም በኋላ መንገዱን ያቀናለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ጌታችንም በዚያች ሌሊት በሕልሙ ተገልጾለት ወዳጄ ጢሞቴዎስ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን እነሆ ከጻድቃኖቼ ቁጥር ውስጥ ቆጥሬሃለሁ አሁንም ተነሣ ሚስትህንም ይዘህ ወደ ብህንሳ ከተማ ሒዳችሁ ጣዖታትን በሚያመልኩ ሁሉ ሕዝብ ፊት በስሜ ታመኑ አለው። በነቃ ጊዜም ለሚስቱ ነገራት እርሷም ይህንኑ የሚመስል ሕልሟን ነገረችው።
ከዚህም በኋላ ተነሥተው በአንድነት ሔዱ ወደ መኰንኑ ወደ ቊልቊልያኖስም ደረሱ መሰንቆና እንዚራ እያስመታ ለጣዖታቱ በዓልን ሲያከብር አገኙት ያንጊዜ ወታደሮቹ ይዘው በመኰንኑ ፊት አቆሙት ሚስቱም ተከተለችው መኰንኑም ለጣዖት መስገድን እያግባባ በርኅራኄ ቃል ተናገረው ቅዱሱ ግን እርሱንና የረከሰች ሃይማኖቱን ሰደበ ስለዚህም መኰንኑ ተቆጥቶ ከሚስቱ ጋር ወደ ወህኒ ቤት እንዲአስገቡት አዘዘ።
ከጥቂት ቀኖች በኋላም ከሚስቱ ጋር አውጥተው ደማቸው እንደ ውኃ እስቲፈስ በአለንጋዎች እንዲገረፉአቸው አዘዘ ያለ ርኅራኄም ገረፏቸው ሚስቱም በዚህ ሥቃይ ምስክርነቷን ፈጸመች።
ዳግመኛም ለጣዖታት መስገድን እሺ ይለው ዘንድ ቅዱስ ጢሞቴዎስን ማባበል ጀመረ እምቢ ባለውም ጊዜ የነዳጅ ድፍድፍ ሥጋውን ቀብተው ከእሳት ማንደጃ ውስጥ እንዲጨምሩት አዘዘ በጨመሩትም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ከዚህ ቃጠሎ አዳነው ።
ከዚህም በኋላ ሁለተኛ ወደ ወህኒ ቤት መለሱት ተአምራትንም የሚያደርግ ሆነ በአንዲት ዕለትም በዚያ ሲጸልይ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ መጥቶ ቃል ኪዳንን ገባለት ሰላምታንም ሰጠው።
በማግሥቱም ከእሥር ቤት አውጥተው ወደ በንሑር ከተማ ወስደው ቅድስት ራሱን ቆረጡ ያን ጊዜ ንውጽውጽታ ሆነ አየርም መላእክትን ተመላች አማንያን ሰዎችም መጥተው ሥጋውን ወስደው በመልካም አገናነዝ ገንዘው ቀበሩት። የመከራውም ዘመን በአለፈ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ሠሩለት ሰኔ ሃያ ሰባት ቀንም አከበርዋት ሥጋውንም በውስጥዋ አኖሩ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment