አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥር ሰላሳ በዚህች ቀን #ቅድስት_ሶፍያ ከሦስት ድናግል ልጆቿ ጋር በሰማእትነት ሞቱ፣የከበሩ #አምስቱ_ደናግል_ሰማዕታት (ጤቅላ፣ ማርያ፣ ማርታ፣ ዓበያ፣ ዓመታ) በሰማዕትነት አረፉ፣ የሮም ንጉስ ልጅ የከበረች #ቅድስት_ኦርኒ በሰማዕትነት አረፈች፣ የመለኮትን ነገር የሚናገር #የቅዱስ_ጎርጎርዮስ መታሰቢያ ነው፣ ተጋዳይ የሆነ መነኰስ የከበረ #ቅዱስ_አክርስጥሮስ አረፈ።
ጥር ሰላሳ በዚች ቀን የከበሩ ድናግል ጲስጢስ አላጲስና አጋጲስ በሰማእትነት ሞቱ የተባረከች አናታቸው ሶፍያም ከአንፆኪያ ከከበረ ወገኖች ውስጥ ናት።
እነዚህንም ሶስት ልጆች በወለደቻቸው ጊዜ በእሊህ ስሞች ጠራቻቸው ትርጓሜያቸውም ሀይማኖት ተስፋ ፍቅር ነው የራሷም ስም ትርጓሜው ጥበብ ማለት ነው።
ጥቂትም በአደጉ ጊዜ ወደ ሮሜ ከተማ ወስዳ በጎ አምልኮን እግዚአብሄርን መፍራትን የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት አስተማራቸው በከሀዲውም የሮሜ ንጉስ በአርያኖስ ዘንድ ወሬያቸው ተሰማ ወደርሱም የያመጡአቸው በማስተማር ትመክራቸውና ታፀናቸው ነበር። እንዲህም ትላቸዋለች ልጆቼ ተጠበቁ የዚህን የኃላፊውን አለም ክብር በማየት ልባችሁ እንዳይደክምና ከዘላለማዊ ክብር እንዳትርቁ ከሙሽራው ከክርስቶስ ጋር ሁናችሁ ወደ ሰማያዊ ሰርግ እንድትገቡ ጠንክሩ።እድሜያቸውም የታላቂቱ አስራ ሁለት የሁለተኛይቱ አስር የሶስተኛይቱ ዘጠኝ ነው።
እናታቸውም ወደ ንጉስ በአቀረበቻቸው ጊዜ ታላቂቱን ጲስጢስን እኔን ስሚ ከቤተ መንግስቴ ታላላቆች ለአንዱ አጋባሻለሁ ብዙ ስጦታም እሰጥሻለሁ ለአጵሎን ስገጂ አላት። እርሷም እርሱንና የረከሁ አማልክቶቹን ሰደበች እርሱም ተቆጥቶ በብረት ዘንጎች እንዲደበድቧት ጡቶቿንም እንዲቆርጡ እሳትንም ከብረት ምጣድ በታች በማንደድ ባሩድ ሙጫ ሰሊጥን በውስጡ አድርገው እጅግ አፍልተው ወደዚያ ይጨምሩዋት ዘንድ አዘዘ።
በጨመሩዋትም ጊዜ እየፀለየች በብረት ምጣዱ ውስጥ ቆመች ከቶ እሳት አልነካትም ።የምጣዱም ግለት ፀጥ ብሎ እንደ ጥዋት ጊዜ ጤዛ ቀዝቃዛ ሆነ ከዚያ ያሉ ሰዎችም አድነቀው እግዚአብሄርን አመሰገኑት ብዙዎችም በክብር ባለቤት እግዚአብሄር ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ራሶቻቸውንም ቆረጡዋቸውና በሰማእትነት ሞቱ።
ከዚህም በኃላ የቅድስት ጲስጢስን ራስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ምስክርነቷንም ፈፅማ የምስክርነት አክሊልን ተቀበለች እናቷም ስጋዋን አንስታ ወሰደች።ዳግመኛም ሁለተኛዋን አላጲስን አቀረቧትና ደበደቧት ፅኑእ ግርፋትንም ገረፏት ከጋለ ብረት ምጣድ ውስጥ ጨመርዋት በዚያንም ጊዜ ቀዝቅዞ እንደጥዋት ጤዛ ሆነ ንጉሱም ከዚያም እንዲአወጧትና ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ ምስክርነቷንም አድርሳ በመንግስተ ሰማያት የህይወት አክሊልን ተቀበለች እናቷም ስጋዋን ወሰደች።
ቅድስት ሶፊያም ከስቃይ የተነሳ እንዳትደነግጥ ስለ ልጅዋ ስለ አጋጲስ ትፈራ ነበር ታፅናናትና እንድትታገስ ታደርጋት ነበር በዚያንም ጊዜ ወስደው ከመንኮራኩር ውስጥ ጨመርዋት እግዚአብሄርም መልአኩን ልኮ ያንን መንኮራኩር ሰበረው እርሷም ፊቷን በመስቀል ምልክት አማትባ ወደሚነደው እሳት ተወርውራ ገባች በዚያንም ጊዜ እሳቱ እንደ ጥዋት ውርጭ የቀዘቀዘ ሆነ ከዚያ ያሉትም ሰዎች ብርሀን የለበሱ ሁለት ሰዎች ከነጫጭ ልብሶች ጋር ሲጋራድዋት አይተው እጅግ አደነቁ ብዙዎችም በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ራሶቻቸውንም ቆርጠዋቸው በሰማእትነት ሞቱ ያቺንም የዘጠኝ አመት ልጅ የከበረች አጋጲስን ራሷን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ።ምክስርነቷንም ፈፀመች ሁሉም የማያልፍ የማይጠፋ ሰማያዊ መንግስትን ወረሱ።
የከበረች ሲፊያም የሶስት ልጆቿን ስጋቸውን ወስዳ ገነዘቻቸው ወደ ከተማውም ውጭ አድርሶ በዚያ ቀበረቻቸው በሶስተኛውም ቀን ወደ መቃብራቸው ሄዳ አለቀሰች ነፍሷንም ይወስድ ዘንድ ወደ እግዚአብሄር ለመነች ልምናዋንም ተቀብሎ ነፍሷን ወሰደ ምእመናን ሰዎችም መጥተው ገንዘው ከልጆቿ ጋር ቀበርዋት።
በከሀዲው ንጉስ ላይ ግን እግዚአብሄር ጭንቅ የሆነ ደዌ ላከ አይኖቹም ፈረጡ አጥንቶቹም እስከሚታዩ ስጋው ሁሉ ተሰነጣጠቀ እጆቹም ተቆራረጡ ከእርሱም ደምና መግል ፈሰሰ ትልም ይወድቅ ነበር ሁለመናውም ተበላሽቶ በክፉ ሞት ሞተ።ስለ እነዚያ ደናግል ጌታ ተበቅሎታልና።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#አምስቱ_ደናግል_ሰማዕታት (ጤቅላ፣ ማርያ፣ ማርታ፣ ዓበያ፣ ዓመታ)
በዚችም እለት የከበረች ጤቀላ ከእርሷ ጋር ከሚኖሩ አራት ደናግል ጋር ፎላ በሚባል ኃጥእ ቄስ እጅ በሰማዕትነት ሞተች።
ይህም ፎላ የሚባል ቄስ በዓመፅ የሰበሰበው ብዙ ገንዘብ እንዳለው በከሀዲ መኮንን ዘንድ ነገር ሰሩበት መኮንኑም ገንዘቡን ሁሉ እንዲወርሱት አዘዘ ፎላም ወደ መኮንኑ ሄዶ ገንዘቡን እንዲመልስለት ማለደው። መኮንኑም ስለ እነዚህ ደናግል ሰምቶ ወደርሱ እንዲአመጡአቸው አዘዘ በመጡም ጊዜ ፎላን መኮንኑ ለፀሀይ ይሰግዱ ዘንድ እሊህን ደናግል ብትሸነግላቸው ገንዘብህን እመልስልሀለሁ አለው።
ፎላም ሊሸነግላቸው ጀመረ ደናግሉም አንተ የሰይጣን ልጅ የክብር ባለቤት ክርስቶስን እንክደው ዘንድ እንዴት ትፈትነናለህ አንተ ቀድሞ መምህራችን የነበርክ ስትሆን ብለው ዘለፉት።
መኮንኑም ቃላቸውን በሰማ ጊዜ በጅራፍ እንዲገርፏቸው አዘዘ እነርሱ ግን መናገራቸውን አልተውም ስቃይንም አልፈሩም። መኮንኑም ፎላን የበከተ ብትበላ ደምንም ብትጠጣ ገንዘብህን እመልስልሀለሁ አለው በሰማም ጊዜ ልቡናውን አፅንቶ ሊገድላቸው ሄደ እንደ አስቆሮቱ ይሁዳ ልቡ በገንዘብ ፍቅር ተነድፎዋልና።
ደናግሉም እንዲህ አሉት ከሀዲ ሆይ የመድኃኒታችንን ክርስቶስን ስጋውንና ደሙን በእጅህ ተቀብለን አልነበረምን ስለ ገንዘብ ፍቅር እኛን የክርስቶስን በጎች ታጠፋ ዘንድ እንዴት መጣህ እንዲህም እያሉ ሰልፍ እንደተማረ አርበኛ ሰው በሰይፍ ራሶቻቸውን ቆረጠ።
መኮንኑም የፎላን ብላሽነትና ድንቁርና አይቶ በሰይፍ ገደለው ነፍሱንም ገንዘቡንም ሀይማኖቱንም አጣ። የደናግሉም ስማቸው ጤቀላ፣ ማርያ፣ ማርታ፣ አመታ፣ ዓበያ ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ቀን ስሙ መርቅያኖስ የሚባል ለጣዖት የሚሰግድ የሮም ንጉስ ልጅ የከበረች ኦርኒ በሰማዕትነት አረፈች።የዚችም ቅድስት እናቷ ክርስቲያናዊት ናት አባቷም እልፍኝ ሰርቶላት በወርቅና በብር ልብሶች ከአጌጡ አስራ ሁለት ደናግል ጋር ወደዚያ አስገባት ከልጁ ጋር ይሰግዱላቸው ዘንድ አስራ ሰባት ጣዖታትን አወጣላቸው በላይዋም በሩን ዘጋ በዚያም ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ኖረች።
በአንዲትም ዕለት ዐይኖቿን ወደ ምስራቅ ቀና በአደረገች ጊዜ ርግብን አየች በአፏም የዘይት ቅጠል ይዛ ነበር ከማዕድዋም ላይ ጥላው ወጣች ዳግመኛም ወደምእራብ ስትመለከት ቁራ መጣ በአፉም ከይሲ ይዞ ነበር ከማዕዷም ላይ ጥሎት ወጣ አደነቀችም።
በዚያንም ጊዜ አባቷ የሰጣት መምህርዋ መጣ ያንንም ራእይ አወራችለት እርሱም ሲተረጉምላት ርግብ የጥበብ ነገር ነው የዘይቱም ቅርንጫፍ በጥምቀት የሚገኝ ክብር ነው ቁራም ንጉስ ነው።ከይሲውም መከራ ነው አንቺም በርቺ ጠንካራ በክርስቶስ ስም መከራ ትቀበይ ዘንድ አለሽና የህይወት አክሊልንም ትቀበያለሽ አላት።
ከዚህም በኃላ በአደገች ጊዜ አባቷና እናቷ ወደርሷ ወጥተው ስለ ጋብቻ ተናገርዋት የከበረች ኦርኒም እስከ ሰባት ቀን ታገሱኝ አለቻቸው ከዚህም በኃላ እርሱ የመረጠውን መንገድ ይመራት ዘንድ ወደ እግዚአብሄር ፀለየች።
የእግዚአብሄርም መልአክ መጥቶ በርቺ ኃይልንም ልበሺ ሀዋርያው ጢሞቴዎስም ወዳንቺ መጥቶ የወንጌልን ትእዛዝ ያሰተምርሻል አላት።ወዲያውኑ ጢሞቴዎስ መጥቶ የቤቷን ግድግዳ ሰንጥቆ ወደርሷ ገባ ሁሉንም አስተማራት ከበታቹም ውኃ ፈለቀ በውኃውም ላይ ፀለየና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃትና ከእርሷ ዘንድ ሄደ።
በዚያንም ጊዜ ቅድስት ኦርኒ ተነስታ የአባቷን ጣዖቶች ሰበረች አባቷና እናቷም በመጡ ጊዜ እንደቀድሞው ስለ ጋብቻ ተናገርዋት እርሱም እኔስ ለሰማያዊ ሙሽራ ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠርቻለሁ በስሙም ተጠምቄአለሁ አለቻቸው።
ንጉስ አባቷም የልጁን ነገር በሰማ ጊዜ ታላቅ ቁጣን ተመላ ከአዳራሽዋም እየጎተተ አወረዳት እናቷም እያለቀሰች በራስዋም ላይ አመድ እየነሰነሰች ትከተላት ነበር በሰንሰለት ታስረው የሚቀለቡ አራት ፈረሶችን አምጥተው ከጅራታቸው ላይ ቅድስት አርኒን በራስዋ ጠጉር አስረው እንዲአስጎትቷት ንጉስ አባቷ አዘዘ። አንዱ ፈረስም ስንሰለቱን በጥሶ ሲያመልጥ የንጉሱን ቀኝ እጅ ቆረጠውና ወዲያውኑ ወድቆ ሞተ የከበረች ኦርኒም ተነስታ ፀሎት አደረገችና ንጉስ አባቷን ከሞት አስነሳችው የተቆረጠ እጁንም እንደቀድሞው መለሰችው ህዝቡም ይህን ድንቅ ስራ አይተው ከንጉስ አባቷ ጋር በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ በእጆቿም ሰላሳ ሽህ ያህል ሰዎች ተጠመቁ።
ንጉስ ዳኬዎስም ሰምቶ ወደዚያች አገር ገባ የከበረች ኦርኒንም ይዞ በራስዋ ጠጉር ይሰቅሏት ዘንድ አዘዘ በጨመሩዋትም ጊዜ ሁሉም በእግዚአብሄር ኃይል ሞቱ ደግሞ በመጋዝ እንዲሰነጥቋት አዘዘ መጋዙም ተሰበረ ንጉሱም ሞተ።
የዳኬዎስም ልጁ ሰምቶ መጣ ያቺንም አገር ከበባት ቅድስት ኦርኒንም ይዞ የተሳሉ መርፌዎችንም በእጆቿና ሸእግሮቿ እንዲሰገስጉ በጀርባዋም ላይ አሻዋ የተመላ ዳውላ አድርገው ከአራት ፈረሶች ላይም አስረው ስጋዋ ተበጠጥሶ እስቲጠፋ ድረስ እንዲአስሮጧቸው አዘዘ በዚህም አልቻሏትም።ያንንም ከሀዲ የእግዚአብሄር መልአክ ኦርኒም ጦር ወግቶ ገደለው የከበረች ኦርኒም ሀይማኖትን እያስተማረች በሽተኞችን እየፈወሰች ሙታንን እያስነሳች ተቀመጠች።
አራተኛ ንጉስም መጣ የቅድስት ኦርኒንም ዜና ሰምቶ ወደርሱ አስቀረባትና ለአማልክት ትሰዋ ዘንድ አስገደዳት እምቢ ባለችውም ጊዜ ከእሳት ውስጥ እንዲጨምሩዋት አዘዘ ከእሳትም ውስጥ በደኃና ወጥታ የረከሱ አማልክቶቹን ዘለፈች ንጉሱም ይህን ድንቅ ስራ አይቶ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ።
አምስተኛው የፋርስ ንጉስ መጣ የከበረች ኦርኒንም ይዞ በእጁ በያዘው ጦር ወጋትና ሞተች ከእግዚአብሄር የታዘዘ መልአክም መጥቶ ከሞት አስነሳት በክብር ባለቤትም በክርስቶስ ስም እያስተማረች ወደ ከተማው ውስጥ ገባች ከጥቂት ቀኖችም በኃላ ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት ተነጥቃ ወጣች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ቀን የመለኮትን ነገር የሚናገር የጎርጎርዮስ መታሰቢያ ነው። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት በሌላም በኩል "ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ" እየተባለም ይጠራል፡፡ ሀገሩ ቂሳርያ ነው፡፡ በመጀመሪያ የሕግ ባለሙያ የነበረ ሲሆን በኋላ ግን የቍስጥንጥንያ ሊቀጳጳስ ሆኖ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በሐዋርያነት አገልግሏል፡፡
በደራሲነቱ ምድራውያን መላእክት ከተሰኙት ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የአምላክን ሰው መሆንና ምሥጢረ ሥላሴን እጅግ አስፍቶና አራቆ ያስተማረ ከመሆኑም በላይ ‹‹ዳግማዊ ዮሐንስ ነባቤ መነኮት›› ተብሎ እስኪጠራ ድረስ በነገረ መለኮት የተራቀቀ ታላቅ ሊቅ መምህር ነው፡፡ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙን የማይጠቅስ መጽሐፍና መምህር የለም፡፡ ሃይማኖተ አበው አጥብቆ የሚጠራው የቤተ ክርስቲያናችን መመኪያ ነው፡፡ የአርመንን ኦርቶዶክስ ያቀና ሲሆን መንበሩን የኖኅ መርከብ ባረፈችበት አራራት ተራራ ላይ ነው የሠራው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚች እለት ተጋዳይ የሆነ መነኰስ የከበረ አክርስጥሮስ አረፈ። ይህም አባት በዮርዳኖስ ገዳም የሚኖር ነበር ከመነኰሳቱም አንዱ እየሰገደ እንዲህ ብሎ ጠየቀው "አባቴ አክርስጥሮስ ሆይ ከኔ ጋር ፍቅርን አደርግ እጠቀምበትም ዘንድ ስራህን ሁሉ ንገረኝ" አለው።
ሽማግሌውም አክርስጥሮስም እንዲህ ብሎ መለሰለት "ልጄ ሆይ ግልማሳ ሆኜ ሳለ በመነኰስኩ ጊዜ በዚያ እፀልይ ዘንድ በለሊት ወደ ቅዱስ ቴዎድሮስ መቅደስ እሄድ ነበር። አስራ ሁሉት ደረጃዎችም አሏት በየአንዳንዱ ደረጃ መቶ መቶ ስግደቶችን እሰግዳለሁ ደውልንም በሚደውሉ ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያን በመግባት ከወንድሞች ጋር የማህበሩን የፀሎት ስርአት እፈስማለሁ እንዲሁም በማድረግ አስር አመት ኖርኩ።"
"ከሌሊቶቹም በአንዲቱ የተለመደ ፀሎቴን ከፈሰምኩ በኃላ ልቡናዬ በተመስጦ ተማረከ ነጫጭ ልብሶችን የለበሱ ሁለት ሰዎች መቅረዚችን ሲያበሩ እኩሌታዎቹ ሲበሩ እኩሌታዎቹም ሲጠፉ አየሁ። "
"እኔም ይህ ስራ ምንድንው አልኳቸው እንዚያም አባቶች ባልንጀራውን የሚወድ መቅረዙ የበራበታል አሉኝ እኔም ደግሜ መቅረዜ የቱ ነው አልኃቸው እነርሱም ሂድ ከወንድሞችህ ጋር ተፈቀር እኛ እናበራልሀለን አሉኝ በነቃሁም ጊዜ ማንንም አላገኘሁም።"
ከዚህም በኃላ አባ አክርስጥሮስ ብቻውን ወደ ደብረ ሲና ሄዶ በዚያ እየተጋደለ ሀምሳ አመት ኖረ ወደርሱም እንዲህ የሚለው ቃል መጣ "ከአባቶችህ ጋር ትኖር ዘንድ ወደ ገዳምህ ተመለስ ከዚህም በኃላ በተመለሰ ጊዜ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment