ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 2 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 2

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ሁለት በዚህች ዕለት የትጉሃን መላእክት ወገን የሆነ የገዳማውያን ሁሉ አለቃ የከበረ #ታላቁ_ቅዱስ_ጳውሊ አረፈ፣ የደብረ ዝጋግ ገዳም አበ ምኔት የከበረ አባት #ቅዱስ_ለንጊኖስ አረፈ፣ የከበረ #ሐዋርያ_ቅዱስ_ቶማስ ተአምራትን አደረገ፡፡


#ቅዱስ_አባ_ዻውሊ_ገዳማዊ (የበረሃው ኮከብ)
የካቲት ሁለት በዚህች ዕለት የትጉሃን መላእክት ወገን የሆነ የገዳማውያን ሁሉ አለቃ የከበረ ታላቁ ጳውሊ አረፈ።
ይህም ቅዱስ ከእስክንድርያ አገር ጴጥሮስ የሚባል ወንድም አለው አባታቸውም የገንዘቡ ብዛት ሊቈጠር የማይቻል እጅግ ባለጸጋ ነበር በአረፈም ጊዜ የኀዘናቸው ቀን ሲፈጸም ርስቱንና ገንዘቡን ሊካፈሉ ጀመሩ ጴጥሮስም ታላቁን ክፍል ወደራሱ በመውሰድ የሚያንሰውን ለጳውሊ የሚሰጠው ሆነ። ስለዚህም ጳውሊ አዘነና ከአባቴ ርስት በትክክል ለምን አትሰጠኝም አለው እርሱም አንተ ወጣት ስለሆንክ ታባክነዋለህ እስከ ምታድግ እኔ እጠብቅልሃለሁ ብሎ መለሰለት።
ስለዚህም ጳውሊ ተቆጣና እርስ በርሳቸው ተጣሉ ይፈርድላቸውም ዘንድ ወደ ዳኛ ሔዱ እነርሱም ወደ ዳኛ ሲሔዱ ሰዎች ተሸክመውት ወደ ሚቀብሩበት ሲወስዱት ብዙዎችም የተከተሉትን የሞተ ሰውን አገኙ ጳውሊም ከተከተሉት አንዱን ሰው ዛሬ የሞተው ማን ነው ብሎ ጠየቀው። ያም ሰው እንዲህ ብሎ መለሰለት ልጄ ሆይ ዕወቅ አስተውል ይህ የሞተ ሰው በወርቅ በብር እጅግ ባለጸጋ የሆነ ሁል ጊዜ ደስ የሚለው ነበር አሁንም እነሆ ይህን ሁሉ ትቶ ራቁቱን ወደ መቃብር ወደማይመለስበት መንገድ ይሔዳል በኃጢአት ማዕበል ውስጥ እያለ ሙቷልና።
አሁንም ልጄ ሆይ ስለ ነፍሳችን ድኅነት ልንታገል ይገባናል እኛ መቼ እንደምንሞት አናውቅምና ነገር ግን በዚህ ዓለም ውስጥ ገንዘብ ኑሮት ሥልጣንም ኑሮት ሳለ ይህን ሁሉ የተወ የተመሰገነ ነው እርሱ የቅዱሳን ሀገር በሆነች በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ታላቅ ክብርን ይቀበላልና።
የከበረ ጳውሊም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ከልቡ አዘነ እንዲህም አለ የዚህ የኃላፊው ዓለም ገንዘብ ምኔ ነው ምን ይጠቅመኛል ከጥቂት ቀኖች በኋላ ትቼው ራቁቴን የምሔድ አይደለሁምን አለ። ከዚህም በኋላ ወደ ወንድሙ ተመልሶ ወንድሜ ሆይ ወደ ቤታችን እንመለስ ከእንግዲህ ስለ ገንዘብ ምንም ምን ከአንተ ጋር አልነጋገርም አለው።
ከዚህም በኋላ ከወንድሙ ሸሽቶ ከሀገሩ ወጣ ከመቃብር ቤት ውስጥም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት መንገዱን ይመራው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እየጸለየና እየማለደ ኖረ። ወንድሙ ጴጥሮስም በሀገር ውስጥ እየዞረ ሲፈልገው ሰነበተ ግን አላገኘውም ታላቅ ኃዘንንም አዘነ። የተመሰገነ ጳውሊ ግን ሦስት ቀኖች ያህል በዚያች መቃብር ቤት ሲኖር መብልና መጠጥን አላሰበም ፍርሀትና ድንጋፄም አልደረሰበትም አምላካዊ ኃይል ትጠብቀው ነበርና።
በአራተኛዪቱም ዕለት እግዚአብሔር ወደርሱ መልአኩን ላከ ከዚያም ነጥቆ ወሰደው በምሥራቅ በኵል በምትገኝ በረሀ ውስጥ አኖረው በዚያም የውኃ ምንጭ አለ መልአኩም ሰላምታ ሰጥቶት ወደ ሰማይ ዐረገ የከበረ ጳውሊም አራዊት የሚኖሩበትን ጒድጓዶች አግኝቶ ወደ አንዲቱ ፍርኩታ ገባ ልብሱንም ሰኔል ሠርቶ ለበሰ። እንዲህም ብሎ ጸለየ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ርኀራኄ ከሌለው ጠላት እጅ ጠብቀኝ አድነኝም ተጋድሎዬን እስከምፈጽም ተጸናኝ ዘንድ ቸርነትህ ወደእኔ ትምጣ የትውልድ ሁሉ ንጉሥ ሆይ ኃይል ጌትነት ክብር ገንዘብህ ነውና ለዘላለሙ።
በዚያችም ዋሻ ውስጥ ሰማንያ ዓመት ኖረ ከሰውም ከቶ ማንንም አላየም ልብሱም ከሰኔል ቅጠል የተሠራ ነው እግዚአብሔር ወደ ማታ ሁል ጊዜ ወደርሱ ቁራን ይልክለታል ከርሱም ጋራ ግማሽ እንጀራ አለ ያንን ለከበረው ጳውሊ ይሰጠዋል።
የክብር ባለቤት እግዚአብሔርም ቅድስናውንና ጽድቁን ይገልጥ ዘንድ በወደደ ጊዜ መልአኩን ወደ ታለቅ አባት ወደ እንጦንዮስ ላከ ይህም እንጦንዮስ በበረሀ ውስጥ መኖርን የጀመረ እርሱ እንደሆነ በልቡ ያስብ ነበር መልአኩም እንዲህ አለው እንጦንዮስ ሆይ ከአንተ የሁለት ቀን ጎዳና ርቆ በበረሀ ውስጥ ሰው አለ የዓለም ሰዎች ከሚረግጥባቸው የእግሩ ጫማዎች እንደ አንዲቱ ሊሆኑ የማይገባቸው ስለ ርሱም ጸሎት ዓለም ተጠብቆ የሚኖር ምድርም ፍሬዋን የምትሰጥ ጠል በምድር ላይ የሚወርድ በምድር በሚኖሩ ኃጢአተኞች ሁሉ ላይ ፀሐይ የሚወጣ የሰውም ፍጥረት በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ተጠብቆ የሚኖር።
አባ እንጦንዮስም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ተነሥቶ ወደ በረሀው መካከል ተጓዘ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ሁኖ ጎዳናውንም እንደሚጠርግለት አምኖ ሲጓዝ የሰውና የአራዊትን ፍለጋ አገኘ ያንንም ፍለጋ ተከትሎ ከቅዱስ ጳውሊ በዓት ደረሰ በሩንም አንኳኳ የከበረ አባ ጳውሊ ግን ከሰይጣን ሥራ እንደሆነ አስቦ ታላቅ ደንጊያ ወስዶ ከመዝጊያው ጀርባ አኖረ አባ እንጦንዮስም ይሰጠኝ ዘንድ ፈለግሁ አገኝ ዘንድ ለመንኩ ይከፈትልኝም ዘንድ ቡሩን አንኳኳሁ ብሎ አሰምቶ ተናገረ። በዚያንም ጊዜ ከፈተለትና ገባ እርስ በርሳቸውም በመንፈሳዊ ሰላምታ አጅ ተነሣሥተው በአንድነትም ጸልየው ተቀመጡ።
አባ እንጦንዮስም አባቴ ሆይ ስምህ ማነው አለው አባ ጳውሊም አንተ ስሜን ካላወቅህ እስከዚች ቦታ ለምን ተጓዝክ ብሎ መለሰለት በዚያችም ሰዓት እግዚአብሔር የእንጦንዮስን ልቡን ገለጠለትና ገዳማዊ ጳውሎስን አየው ዘንድ ስለተገባኝ እኔ ብፁዕ ነኝ አለ ከዚህም በኋላ እርስ በእርሳቸው የእግዚአብሔርን ልዕልናውን ቸርነቱን ይነጋገሩ ጀመር በመሸም ጊዜ ቍራ መጥቶ አንዲት ሙሉ እንጀራ ጣለለት አባ ጳውሊም አባ እንጦኒን አንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደሆንክ አሁን አወቅሁ እስከ ዛሬ ሰማንያ ዓመት በዚህ በረሀ ስኖር እግዚአብሔር ሁልጊዜ የሚልክልኝ ግማሽ እንጀራ ነበር እነሆ አሁን ምግብህን ላከልህ አለው። ከዚህም በኋላ ተነሥተው የማዕድ ጸሎት ጸለዩ በልተውም እግዚአብሔርን አመሰገኑት መላ ሌሊቱንም ሲጸልዩ አደሩ።
ነግቶ ፀሐይ በወጣ ጊዜም እርስ በርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጡ አባ እንጦኒም አባቴ ሆይ በዚህ ሁሉ ዘመን ሥጋውንና ደሙን ከወዴት ትቀበላለህ አለው የከበረ ጳውሊም እግዚአብሔር መልአኩን ይልክልኛል በቀዳሚት ሰንበትና በእሑድ ሰንበት በየሳምንቱ ከሥጋውና ከደሙ ያቀብለኛል በዘመኑም ሁሉ እንዲህ ያደርግልኛል ብሎ መለሰለት።
ከዚህም በኋላ አባ እንጦኒ አባ ጳውሊን አባቴ ሆይ ይህ አስኬማ በምድር ላይ ይበዛ እንደሆነ ወይም አለመብዛቱን ትነግረኝ ዘንድ እሻለሁ አለው። የከበረ ጳውሊም ወደ ሰማይ ተመለከተና ፈገግ አለ። ከዚህም በኋላ አዘነ ጩኾም አለቀሰ አባ እንጦንዮስም ፈገግ ስትል በአየውህ ጊዜ ደስ አለኝ በአዘንክም ጊዜ አዘንኩ አለው። የከበረ ጳውሊም እንዲህ ብሎ መለሰለት እሊህ ተራሮችና በረሐዎች እግዚአብሔር ከሁሉ አገሮች መርጦ ለሚሰበስባቸው ንጹሐን ርግቦች ማደሪያዎች ይሆናሉ።
ዳግመኛም ይህ ስም ያልፋል ስማቸውም መነኰሳት ይባላሉ እነርሱም ብዙ ዘመናት ደስ ይላቸዋል እግዚአብሔርም ከቁጣው ቀን አስቀድሞ ከዚያ ያፈልሳቸዋል። ከእነርሱም በኋላ ሰምተው ለመምህሮቻቸው የማይታዘዙ ትውልድ ይነሣሉ ስለ ነፍሳቸውም ድኅነት በቀንና በሌሊት የማይተጉና የማይጸልዩ ናቸው።
ያን ጊዜ እግዚአብሔር ተቆጥቶ ይፈርዳል የማያስተውሉ ሕግ የሌላቸው አረማውያንም ተነሥተው ገዳማቱንና አድባራቱን ያጠፋሉ ብዙ ዘመናትም ምድረ በዳ ይሆናሉ የቅዱሳን መታሰቢያቸው አይጠፋም እግዚአብሔርም በሌሎች ሰዎች ልቡና ይቅርታውን ያሳድርባቸዋል እነርሱም ወደ ገዳማቱና ወደ አድባራቱ በመሔድ በውስጣቸው ዳግመኛ ይኖራሉ ሰይጣንም ወደ ገዳማት ሔዶ በመካከላቸው ጸብን ይዘራል እነርሱም የእግዚአብሔርን ፍቅር ገንዘብ በማድረግ ጨክነው አልታገሡባትምና ምንኵስናቸውን አስኬማቸውን ትተው ወደ ዓለም ይወርዳሉ በትዕግሥታችሁ ነፍሳችሁን ገንዘብ ታደርጓታላችሁ የሚለውን ጽሑፍ አላስተዋሉምና።
እንጦንዮስም የከበርክ አባቴ ጳውሊ ሆይ ፊትህን አይ ዘንድ የታደልኩባት ሰዓት የተባረከች ናት አለ። የከበረ አባ ጳውሊም አሁን ወደ ማደሪያህ ሒድ ቈስጠንጢኖስ ለሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስ የሰጠውን ልብስ እርሱም አንተን ያለበሳትን ያቺን ከአንተ ጋር ይዘሃት ና ሥጋዬን በርሷ ትገንዝ ዘንድ ብሎ ተናገረው የተሠወረውን በማወቁ እጅግ አደነቀ የተነበየለትንም ትንቢት ሁሉ አመነ። ዳግመኛም እንዲህ አለው በሰው ሁሉ ላይ እንደተሠራ ከዓለም የምወጣበት ጊዜዬ ቀርቧልና ፈጥነህ ሒድና ተመለስ እርሱም ከአባ ጳውሊ ዘንድ ወጥቶ ወደ በዓቱ እስኪደርስ የሁለት ቀን ጎዳና ተጓዘ ያቺንም ልብስ ይዞ ተመለሰ በመንገድም እየተጓዘ ሳለ በአየር ውስጥ አባ ቡላን የመላእክትንም ማኅበር አየ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ይሉ ነበር።
ሁለተኛም እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጠህ ሰላምታ ፍቅር አንድነት ይገባሃል የእግዚአብሔር ሰው አንተ ጳውሊ የተመሰገንክ ነህ እንግዲህስ በሰማያዊ መንግሥት ከመላእክት ጋር ደስ ይበልህ የጨለማውን ዓለም ትተህ የብርሃን ሀገርን አግኝተሃልና ወደ ዘላለማዊ ተድላ ደስታ ይወስዱሃልና የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆንክ አንተ ገዳማዊ ጳውሎስ በትውልድህ የከበርክና የተመሰገንክ ነህ እንዲህ እያሉ ተሠወሩ።
የከበረ እንጦኒም ይህች ወደ ሰማይ የሚያሳርጓት የአባቴ የጳውሊ ነፍስ ናት አለ ወደ በዓቱም በገባ ጊዜ እንደ ሰገደ ሁኖ እጆቹም በመስቀል ምልክት ተዘርግተው አገኘው አንሥቶም ሸፈነው አባቴ ሆይ በሰማያዊ ማደሪያህ ሁነህ አስበኝ ብሎ በላዩ አለቀሰ።
ከዚህም በኋላ ተነሥቶ በዚያች ልብስ ሥጋውን ገነዘና በላዩ የቤተ ክርስቲያንን የጸሎት ሥርዓት ፈጸመ አደረሰም ከዚህም ቀጥሎ ከእርሱ ጋር የተማከርኩት ነገር የለም ምን ላድርግ ብሎ አሰበ በዚያንም ጊዜ አንበሶች መጡ እጅ ነሡትም ቀድሞ እንደሚያውቁትም ዘንበል ብለው የእግሩን ትቢያ ላሱ መቃብሩን በየት ቦታ እንቆፍርለት እንደሚሉ አመለከቱት እርሱም ምልክታቸውን አውቆ በቁመቱ ልክ ለክቶ ሰጣቸው አንዱ በራስጌ አንዱ በግርጌ ሁነው ቆፈሩ በአደረሱም ጊዜ በቃችሁ ብሎ አመለከታቸው እሊህ አንበሶችም ወጥተው ሰገዱለት። እርሱም ባረካቸውና ወደ ቦታቸው ሔዱ የከበረ እንጦኒ ወደ መቃብር አስገብቶ ዘጋው። ከሰኔል ቅጠልም የተሠራች ዐጽፉን ወሰደ የአባቱን ገንዘብ እንደሚወርስ ልጅ ነውና ወደ እስክንድርያም ሔደ፡፡ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስም ገብቶ ከከበረ አባ ጳውሊ የሆነውን ሁሉ ነገረውና ያቺን ከሰኔል የተሠራች ዐጽፍ ሰጠው።
ሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስም የከበረ ጳውሊን ዜና በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለው ያቺንም ዐጽፍ ተቀብሎ በእርሱ ዘንድ አኖራት በየዓመቱም በከበረ በልደት በዓል በጥምቀትም በዓል በመድኃኒታችን ክርስቶስ ትንሣኤ በዓልም ሦስት ጊዜ ይለብሳት ነበር።
ጌታችንም የቅዱስ ጳውሊን የልብሱን ክብር ሊገልጥ ወደደ በዚያችም ወቅት አንድ ወጣት ልጅ ሞተ አባ አትናቴዎስም ያቺን ልብስ በሞተው ላይ አኖራት ወዲያውኑ ተነሣ ይህንንም ያየ ኤጲስቆጶስ አባ ኤስድሮስ ምስክር ሆነ ይችም ተአምር በአገሮች ሁሉ ተሰማች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን ከእስክንድርያ ውጭ የደብረ ዝጋግ ገዳም አበ ምኔት የከበረ አባት ለንጊኖስ አረፈ።
ይህም ቅዱስ ከኪልቅያ አገር ነው በዚያም መነኰሰ መምህሩም ክርስቶስን የሚወድ ሰው ከሚሰጠውም ክብር የሚሸሽ ነበር። በዚያንም ጊዜ የገዳማቸው አበ ምኔት አረፈ ይህንንም ስሙ ሉክያኖስ የተባለ አረጋዊ መምህሩን አበ ምኔትነት ሊሾሙት መነኰሳቱ ወደዱ እርሱም ደቀ መዝሙሩን ለንጊኖስን ይዞ በጭልታ ከኪልቅያ ወጥቶ ወደ ሶርያ አገር ሔደ በአንዲት ቤተ ክርስቲያንም ግቢ በአንድነት ተቀመጡ በእጆቻቸውም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶችን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ወደደ ከሰዎችም ዘንድ ከንቱ ውዳሴና ክብር ሆነባቸው።
አባ ለንጊኖስም በመምህሩ ምክር ወጥቶ ወደ ግብጽ አገር ሔደ ወደ ደብረ ዝጋግ ገዳምም በገባ ጊዜ በደስታ ተቀበሉትና ከእሳቸው ጋራ ኖረ ከዚህም በኋላ አበ ምኔቱ አረፈ ተጋድሎውን ትሩፋቱንና ደግነቱን ስለ አወቁ በደብረ ዝጋግ ገዳም ላይ አባ ለንጊኖስን አበ ምኔት አድርገው ሾሙት።
ከጥቂትም ወራት በኋላ መምህሩ አባ ሉክያኖስ መጣ የመርከቦችን ጣሪያዎች እየሠሩ በእጆቻቸውም ከሚሠሩት እየተመገቡ በአንድ ልብ በመሆንም በአንድነት ኖሩ እግዚአብሔርም በእጆቻቸው ብዙዎች የሆኑ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ ከዚህም በኋላ አባ ሉክያኖስ አረፈ።
የኬልቄዶንን ጉባኤ በሰበሰበ በከሀዲው መርቅያኖስም ዘመን ወደ ሀገሮችም ሁሉ መልእክተኞችን ላከ ከእርሳቸውም ጋር አንዱን ክርስቶስን ወደ ሁለት ባሕርይ የምትከፍል የረከሰች የሃይማኖቱ ደብዳቤ አለች። ከንጉሥ መልእክተኞች ሦስቱ ወደ ደብረ ዝጋግ በደረሱ ጊዜ ያንን ደብዳቤ ለአባ ለንጊኖስ ሰጡት በዚህ ጽሑፍ እንድታምኑ በውስጡም እንድትፈርሙ ንጉሥ መርቅያኖስ አዝዞአል አሉት።
አባ ለንጊኖስም ከቅዱሳን አባቶቼ ጋር ሳልማከር እኔ ምንም ምን መሥራት አልችልም እንድንማከርም እናንተም ከእኔ ጋር ኑ አላቸውና የቅዱሳን በድኖች ወደ አሉበት ዋሻ ውስጥ አስገባቸውና የከበራችሁ አባቶቼ ሆይ እናንተ ዐርፈን ተኝተናል አትበሉ እነሆ አንዱን ክርስቶስን ሁለት ባሕርይ የሚያደርግ በውስጡ የተጻፈበትን ይህን ደብዳቤ አምጥተዋልና በቃሉ አምን ዘንድ በውስጡም እፈርም ዘንድ ታዙኛላችሁን ወይም አታዙኝም የምሠራውንም ካልነገራችሁኝ ሕያው እግዚአብሔርን ዐፅሞቻችሁን ከዚህ ቦታ አወጣለሁ አላቸው።
ያን ጊዜ ሰዎች ሁሉም እየሰሙ ከአሰከሬናቸው የአባቶቻችንን የሐዋርያትንና የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱን የቀናች ሃይማኖትን አትተው ይህንንም የረከሰ ደብዳቤ አትከተል ከአስከሬናችን ቦታ አርቀው እንጂ የሚል ቃል ወጣ የንጉሥ መልእክተኞችም ይህን ነገር ሰምተው እጅግ አደነቁ በላያቸውም ታላቅ ፍርሀት አደረባቸው ወደ ንጉሥም አልተመለሱም ራሳቸውን ተላጭተው መነኰሱ እንጂ እስከ አረፉም ድረስ ብዙ ዘመን እየተጋደሉ ኖሩ።
የከበረ አባ ለንጊኖስም ያማረ ተጋድሎውን ጨርሶ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ የሕይወት አክሊልንም ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የከበረ ሐዋርያ ቶማስ ተአምራትን አደረገ፡፡ ጌታችን ወደ አዘዘው ሊአስተምር በወጣ ጊዜ ከመንገድ ጥቂት ፈቀቅ አለ ድንገትም የሞተ ጐልማሳ አየ መልኩ እጅግ የሚያምር ነበር ሐዋርያውም አቤቱ ይህን ጥፋት አይ ዘንድ ወደዚህ አመጣህኝን ነገር ግን ፈቃድህ ይሁን አለ።
ከዚህም በኋላ ስለሞተው ሰው ጸለየ ያን ጊዜ ታላቅ ከይሲ ከደንጊያዎች ውስጥ ወጥቶ በጅራቱ ምድሩን እየደበደበ መጣ የክርስቶስ ሐዋርያ ሆይ እኔ ካንተ ጋር ምን አለኝ ሥራዬን ልትዘልፍ መጣህን ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ ሐዋርያውም አዎን ሥራህን ተናገር አለው።
ከሲውም እንዲህ አለ በዚህ ቦታ አንጻር መልከ መልካም ሴት ነበረች እኔ የምወዳት ናት ይህም ጐልማሳ ሲስማት አየሁት በሰንበት ቀንም ከርሷ ጋር አደረ ስለዚህም ነክሼ በመርዝ ገደልኩት ሐዋርያውም መርዝህን ከሱ ትወስድ ዘንድ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዤሃለሁ አለው።
ሔዶም ከዚያ ከሞተው መርዙን መጠጠና ወሰደ ወዲያውኑ ተነፍቶ አበጠ ተሠንጥቆም ሞተ የሞተውም ሰው ድኖ ተነሣ። ስለዚች ምልክትም ብዙዎች በክብር ባለቤት ጌታችን አመኑ እርሱም ሃይማኖትን አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages