ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 5 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 5

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ አምስት በዚህችም ቀን የንጹሕ ድንግል #ቅዱስ_አባት_አባ_ገብረ_ናዝራዊ፣ የኬልቅዩ ልጅ #የታላቁ_ነቢይ_ቅዱስ_ናሆም#የቅድስት_አውጋንያ#የቅዱስ_ፊቅጦር የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው።
ታኅሣሥ አምስት በዚህችም ቀን ለእግዚአብሔር ሕግ የሚቀና ገድለኛ የሆነ ንጹሕ ድንግል ቅዱስ አባት አባ ገብረ ናዝራዊ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ በወገን የከበሩ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው አባቱም የቤተ ክርስቲያንን ሕጓንና ሥርዓቷን የሚጠብቅ ካህን ነው እናቱም ፈጣሪዋን የምትወድ ደግ ሴት ናት።
ይህም ቅዱስ በተወለደ ጊዜ በዕውቀት እግዚአብሔርን በመፍራት በመማር አደገ ከዚህም በኋላ ዲቁናን በተሾመ ጊዜ የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትን የሚያነብ ሆነ። በኦሪትም ውስጥ የሰንበትን ቀን የሻረና ሥራ የሠራባት በሞት ይቀጣ የሚል አገኘ ከወንጌልም ውስጥ እንዲህ የሚል አገኘ ከእነዚህ ትእዛዛት ታንሳለች ብሎ የሚያስተምር አንዲቱን የሻረ ለሰውም እንዲህ ብሎ የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማያት የተለየ ይሆናል የምያደርግ እና የምያስተምር ግን እርሱ በመንግስተ ሰማይ ታላቅ ይሆናል ዳግመኛም መድኃኒታችን አባትና እናቱን ያልተወ ሰውነቱንም ለመከራ አሳልፎ ያልጣላት ሊያገለግለኝ ደቀ መዝሙሬም ሊሆነኝ አይችልም ያለውን አስተዋለ።
ከዚህም በኋላ ወደ አቡነ ጎርጎርዮስ ሔደ እርሱም ጽጋጃ በሚባል ገዳም የአቡነ አኖሬዎስ ገዳም የአቡነ አኖሬዎስ ልጅ ነው ከዚያም መነኵሶ በጾም በጸሎት በስግደት እየተጋ ኖረ። ከዚህም በኋላ ቅስና ተሾመ ከዚያም ወደ ትግራይ አገር ሔዶ ከአባ ያዕቆብ ጋር ተገናኝቶ በቅዱሳት መጻሕፍት ቃሎች ተነጋገሩ።
ከዚህም በኋላ ሀሳቡን ገለጠለት አባ ያዕቆብም እንዴት ይቻላል አለው አባ ገብረ ናዝራዊም እግዚአብሔር ይረዳኛል አለ። ከአባ ያዕቆብም ጎልት ተቀብሎ እርስ በርሳቸው በእግዚአብሔር ፈቃድ ተለያዩ። ከዚህም በኋላ ተስፋፍቶ ገዳምን ሠራ ብዙ ሰዎችም ወደርሱ ተሰብስበው መነኰሳትን ሆኑ ስለሰንበታትና በዓላትም አከባበር እንደሚገባ ሥርዓትን ሠራ። ለመነኰሳትም ከመድኃኒታችን ከልደቱና ከጥምቀቱ በዓል ከሰንበታትና ከበዓለ ሃምሳ በቀር በየሰሞኑ ሁሉ እስከ ማታ ያለማቋረጥ መጾም እንደሚገባቸው ሥርዓትን ሠራ። ዳግመኛም የሌላውን ገንዘብ እንዳይነኩ፣ እንዳይረግሙ፣ በሕያው እግዚአብሔርም ስም እንዳይምሉም ለልጆቹ ይህን ሁሉ ያስተምራቸው ነበር።
ለእርሱ ግን ለሚጸልየው ጸሎት ልክ የለውም ነቢይ ዳዊት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ። ምስጋናውም ዘወትር በአፌ ውስጥ አለ ያለውን አስቦ ዳግመኛም ትእዛዝህን በማሰብ እጫወታለሁ ሕግህን እሻለሁ ትእዛዞችህንም አስተምራለሁ ቃልህንም አልረሳም ያለውን አስቦ።
ዳግመኛም ከሰባውና ደም ካለው ጣዕም ካላቸውም መብሎች ሁሉ ይከለከላል የጌታውን መከራ ለነፍሱ ያሳስባታልና ዕንባው ያለ ማቋረጥ ይፈስ ነበር ያለማቋረጥም ይሰግዳል ያመሰግናልም እንግዳና መጻተኛውን ይቀበላል በጽዮን ዘር በኢየሩሳሌም ቤቶች ያሉት ብፁዕ ነው ያለውን የነቢይ ቃል አስቦ ድኆችንና ችግረኞችን ይጉበኛቸዋል ።
ለዚህም አባት ትሩፋቱ ብዙ ነው ደጋግ ተአምራትንም በማድረግ በሰው ልቡናም ተሠውሮ ያለውን በማወቅ ብዙ የተለያዩ ሀብቶች ተሰጥተውታል ለልጆቹም የቀናች ሃይማኖትን አስተማራቸው በእርሷም እንዲጸኑ አዘዛቸው ከዚህም በኃላ በሸመገለ ጊዜ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ ።

በዚህች ቀን የኬልቅዩ ልጅ ታላቁ ነቢይ ናሆም አረፈ። ከስምዖን ነገድ የሆነ ይህ ጻድቅ ነቢይ ከነቢዩ ሙሴ በትንቢቱ ዐሥራ ሰባተኛ ነው። በካህኑ ዮዳሄ፣ በነገሥታቱ በኢዮአስ፣ በአሜስያስ፣ በልጁ በኢዝያን ዘመን ትንቢት ተናገረ ስለ ክህደታቸውና ጣዖታትን ስለማምለካቸውም የእስራኤልን ልጆች ገሠጻቸው።
እግዚአብሔርም ምንም መሐሪና ይቅር ባይ ምሕረቱም የበዛ ቢሆን ካልተመለሱ ጠላቶቹን ይበቀላቸው ዘንድ እንደአለው ለሚቃወሙትም የፍርድ ቀን እንደሚጠብቃቸው በትንቢቱ ገለጠ። ዳግመኛም ስለ ከበረ የወንጌል ትምህርትና ስለ ሐዋርያት እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ "የምሥራች የሚናገሩ ሰዎች እግራቸው እነሆ በተራራ ላይ ቁሟል ሰላምንም ይናገራሉ።"
ስለ ነነዌም ውኃና እሳት ያጠፉአት ዘንድ እንዳላቸው ትንቢት ተናግሮ እንደቃሉ ሆነ ከዕውነት መንገድ ተመልሰው በበደሉ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር በውስጧ ታላቅ ንውጽውጽታ አድርጎ እሳትም አውርዶ እኩሌታዋን አቃጥሏልና። በንስሐ ጸንተው ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን ግን ከክፉ ነገር ከቶ ምንም ምን አልደረሰባቸውም። የትንቢቱንም ወራት ሲፈጽም እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

በዚህችም ቀን ደግሞ ከሮም አገር ቅድስት አውጋንያ በሰማዕትነት አረፈች። የዚችም ቅድስት የአባቷ ስም ፊልጶስ ነው። እርሱም የእስክንድርያ አገር ገዥ ነበር ጣዖትንም ያመልካል ስሙ መምድያኖስ የሚባል የሮም ንጉሥም ለጣዖት የሚሰግድ ነው። ይቺም ቅድስት አውጋንያ በእስክንድርያ ከተማ ተወለደች። እናቷም ክርስቲያን ስለሆነች በሥውር የክርስቲያን ሃይማኖትን አስተማረቻት።
በአደገችም ጊዜ ታላላቆች መኳንንት አጯት አባቷም ይህን በነገራት ጊዜ "አባቴ ሆይ መጀመሪያ ወደ እስክንድርያ ገዳም እንድገባና እንድጎበኝ ተራሮችን በማየት ዐይኖቼ አይተው ደስ ይለኝ ዘንድ ፍቀድልኝ" አለችው። አባቷም ሰምቶ ሁለት ጃንደረቦችን ጨምሮ የወደደችውን ታደርግ ዘንድ ፈቀደላት።
በወጣችም ጊዜ የመነኰሳቱን ገዳማት ሁሉ ዞረች ስሙ ቴዊድሮስ የሚባል ጻድቅ ደግ ኤጲስ ቆጶስ ወደሚኖርባትም በልቧ ያለውን ሁሉ ነገረችው ከጃንደረቦቿም ጋር ተጠምቃ በዚያ መነኰሰች በወንድ አምሳልም ሁና ስሟን አባ አውጋንዮስ አሰኘች እርሷ ሴት እንደሆነች ማንም አላወቀም።
ወደ አባቷም ባልተመለሰች ጊዜ በቦታው ሁሉ ፈለጋት ሲአጣትም በርሷ አምሳል ጣዖት ሠርቶ ማታና ጧት እየሰገደላት ኖረ። አንድ ዓመትም ከኖረች በኃላ የዚያ ቦታ አበ ምኔት አረፈ መነኰሳቱም መረጧትና አበ ምኔት አድርገው ሾሟት እግዚአብሔርም አጋንንትን ታስወጣ ዘንድ የዕውራንን ዐይኖች ትገልጥ ዘንድ ደዌውን ሁሉ ታድን ዘንድ ሀብተ ፈውስን ሰጣት።
ከዚህም በኋላ ሰይጣን በአንዲት ሴት ልብ ክፉ አሳብ አሳደረባት ከአዳነቻት በኋላ ወንድ መስላታለችና ገዳምህንና ምንኰስናህን ትተህ ለኔ ባል ሁነኝ ብዙ ገንዘብ አለኝና አለቻት። አባ አውጋንዮስ የተባለችው ቅድስቷም እናቴ ሆይ ከእኔ ዘንድ ሂጂ ሰይጣን በከንቱ አድክሞሻል አለቻት። በአሳፈረቻትም ጊዜ ወደ እስክንድርያ ገዥ ሒዳ እንዲህ አለችው እኔ ወደ ዕገሌ ቦታ በሔድኩ ጊዜ ሊደፍረኝ ሽቶ ወጣት መነኰሴ በሌሊት ወደእኔ መጣ ወደ አገልጋዮቼም ስጮህ ከእኔ ዘንድ ወጥቶ ሸሸ።
መኰንኑም በሰማ ጊዜ ይኸውም የቅድስት አውጋንያ አባቷ የሆነ መነኰሳቱን ሁሉ አሥረው ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ በአደረሷቸውም ጊዜ እንዲአሠቃያቸው ለሌላ መኰንን አሳልፎ ሰጣቸው። ከሥቃይም ጽናት የተነሣ ከእርሳቸው የሞቱ አሉ።
የመነኰሳቱንም መጎሳቈል በአየች ጊዜ መኰንን አባቷን እንዲህ አለችው "ጌታዬ ሆይ ምሥጢሬን ዕውነቱን እነግርህ ዘንድ የምፈልገውንም እንዳትከለክለኝ ማልልኝ" አለችው። በማለላትም ጊዜ ወደ ሥውር ቦታ ወስዳ ምሥጢርዋን ሁሉ ገለጠችለትና ልጁ አውጋንያ እርሷ እንደሆነች አስረዳችው። መኰንኑም አይቶ በእውነት አንቺ ልጄ አውጋንያ ነሽ እኔም በአምላክሽ አመንኩ አላት።
በዚያንም ጊዜ መነኰሳቱን ይፈቷቸው ዘንድ በመሠቃየት የሞቱትንም ይቀብሩአቸው ዘንድ አዘዘ። ወዲያውኑ ከቤተሰቦቹ ሁሉ ጋር ተጠምቆ ሁሉም ክርስቲያን ሆኑ።
የእስክንድርያ ሰዎችም የሃይማኖቱን ጽናት በአዩ ጊዜ በወንጌላዊው ማርቆስ ወንበር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት ክብር ይግባውና የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት እያስተማረ ብዙ ዓመታትን ኖረ። ከዚህም በኋላ በእርሱ ላይ ሌላ ከሀዲ መኰንን ተነሥቶ ይህን ሊቀ ጳጳሳት ፊልጶስን በሥውር ይገድሉት ዘንድ ጭፍሮቹን ላከ በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ገደሉት የሰማዕታትንም አክሊል አገኘ ።
የሮሜ ሊቀ ጳጳሳትም የቅድስት አውጋንያን ዜና በሰማ ጊዜ ወደርሱ ወስዶ እርሱ በሠራው ገዳም ላይ እመ ምኔት አድርጎ ሾማት። የመነኰሳይያቱም ብዛት ሦስት ሽህ ሦስት መቶ ነው፤ እነዚያንም ከእርሷ ጋር የኖሩ ሁለት ጃንደረቦች በሁለት አገሮች ላይ ኤጲስ ቆጶስትነት ሾማቸው።
ከዚህም በኋላ ሌላ ከሀዲ መኰንን በተሾመ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሷን ለሞት አሳልፋ እስከ ሰጠች ድረስ ቅድስት አውጋንያን ይዞ በጽኑ ሥቃይ አሠቃያት የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለች።

በዚችም ቀን ደግሞ ከአስዩጥ አውራጃ ሻው ከሚባል ከተማ ቅዱስ ፊቅጦር በሰማዕትነት አረፈ።
የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም መርመር የእናቱ ማርታ ይባላል እነርሱም ያለ ፍርሀት እግዚአብሔርን የሚያመልኩት እውነተኞች ጻድቃን ናቸው ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውምና ክብር ይግባውና ጌታችንን እየለመኑ ኖሩ ለድኆችም ምጽዋትን ይሰጡ ነበር። እግዚአብሔርም ልመናቸውን ተቀበለ ይቺ የተባረከች ማርታም ይህን ሊቅ ፊቅጦርን ፀንሳ ግንቦት ዘጠኝ ቀን ወለደችው እግዚአብሔርን በመፍራትም ሠርተው ቀጥተው አሳደጉት።
ሃያ ዓመትም ሲሆነው አባቱ ወደ ንጉሥ አቀረበውናንጉሡም በአባቱ ፈንታ ምስፍን ሾመው አባቱ በዕድሜውሸምግሎ ነበርና።
ከጥቂት ወራትም በኃላ ጣዖታትን የማያመልኩ ክርስቲያኖችን ሁሉ ይገድል ዘንድ የንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ መልእክት ወደ እንጽና አገር መኰንን ደረሰ ። መኰንኑም ክርስቲያኖችን እየፈለገ ወደ ሻው ከተማ ደረሰ ያን ጊዜ ክብር ይግባውና ክርስቶስን እንደሚአመልከው ክፉዎች ሰዎች ይህን ቅዱስ ፊቅጦርን ወነጀሉት ያን ጊዜም እንዲአመጡት አዘዘና በአመጡት ጊዜ ለጣዖታት እንዲሠዋ አስገደደው እምቢ በአለውም ጊዜ በወህኒ ቤት እንዲአሥሩት አዘዘ።
በዚያም እያለ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደሰማይ አወጣው የወህኒ ቤት ጣባቂዎችም በአጡት ጊዜ ተሸበሩ ከሰባት ቀኖችም በኋላ አግኝተውት ወደ መኰንኑ ወሰዱት መኰንኑ ግን ራራለትና ወደ ንጉሡ ሰደደው ንጉሡም እግዚአብሔርን ከማምለክ ይመልሰው ዘንድ በማባበል ብዙ ሸነገለው። መመለስም በተሳነው ጊዜ አውጣኪያኖስ ወደሚባል መኰንን ሰደደው ። እንዲህም ብሎ አዘዘው እነሆ ፊቅጦርን ወደንተ ልኬዋለሁ ያንተን ምክር ከሰማ ለአማልክት ይሠዋ ካልሰማህ ግን ግደለው እንጂ አትራራለት።
ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ሊወስዱት እጆቹንና እግሮቹን አሠሩ በአፉም የብረት ልጓም አግብተው በመርከብ አሳፈሩት የእግዚአብሔርም መልአክ ወርዶ ከማሠሪያውም ፈትቶ ወደ መኰንኑ አደረሰው ቅዱስ ፊቅጦርም መኰንኑንና ከሀዲውን ንጉሥ ሊረግም ጀመረ መኰንኑም ተቆጣ ጽኑዕ ሥቃይንም አሠቃይቶ በወህኒ ቤት አሠረው። በዚያም ሳለ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን በብርሃን ሠረገላ ላይ ሁኖ ተገለጠለትና ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚያችም ቀን ጀምሮ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙ በሽተኞችን የሚፈውስ ሆነ።
መኰንኑም ይህን ሰምቶ ተቆጣ ወደርሱ አስመጣውና ይመልሰው ዘንድ ደግሞ ሸነገለው ቅዱስ ፊቅጦር ግን የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ በዚያንም ጊዜ በፈረስ ጅራት ላይ አሥረው የአንድ ቀን መንገድ ያህል እንዲጐትቱት ከዚያም ከውሽባ ቤት እሳት ማንደጃ ውስጥ እንዲጨምሩት አዘዘ እንዲህም መልካም ተጋድሎውን ፈጸመ።
ሥጋውን ግን ከዚያ ውሽባ ቤት አላወጡትም በመሰላል ወርደው በአማሩ ልብሶች ገንዘው በሽቱዎች አጣፈጡት እንጂ በላዩም ቤተ ክርስቲያንን ሠሩ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages