ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት 5 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, March 14, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት 5
 አቡነ_ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ

መጋቢት አምስት በዚችም ቀን ተአምራቱና ትሩፋቱ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነ ቅዱስ አባት ተጋዳይ አባ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የእረፍቱ ቀን መታሰቢያ ሆነ፡፡ ይህም ቅዱስ አባት በተወለደባት ቀን ድንቅ የሆነ ስራን ሰራ ተነስቶ ከእናቱ እቅፍ ወርዶ ከጨለማ ወደ ብርሀን ላወጣኸኝ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን እያለ ለስላሴ ሰግዷልና ምስጋናም አቅርቧልና።
ህፃኑም ሶስት አመት በሆነው ጊዜ የእግዚአብሔር መልክተኛ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ህፃኑን ከእናቱ እቅፍ አንስቶ ብዙ ባህታውያን ወዳሉበት ገዳም ወስዶ በደጅ አኖረው ወደ አበምኔቱ ወደ አባ ዘመደ ብርሀንም ገብቶ ስለ ህፃኑ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ነገረው።
በዚያን ጊዜም ነገሩ እውነት እንደሆነ ይረዳ ዘንድ አባ ዘመደ ብርሀን ተነስቶ ወደ ደጅ ወጣ። መልአኩም እንደ ነገረው ህፃኑ ከበር ተቀምጦ ፈገግታን ተሞልቶ አገኘው። እጅግም ደስ ብሎት ለእግዚአብሄር ሰገደ ህፃኑንም አንስቶ ሳመው ታቅፎም ወደ በአቱ አስገባው።
በፍቅር በስነስርአት አሳደገው። የዳዊትን መዝሙርና ቤተ ክርስቲያን የምትቀበላቸውን መፃህፍት ሁሉ ብሉይንና ሀዲስን አስተማረው። ከዚያም በኃላም ክህነት ይሰጠው ዘንድ ስሙ አብርሀም ወደሚባል ጳጳስ ወሰደው ጳጳሱም በአየው ጊዜ ደስ አለው። የዲቁና ማእረግንም ሾመው እንደ ቀዳሜ ሰማእት እስጢፋኖስም ፀጋንና ሞገስን የተመላ ሆነ።
ከጥቂት ቀኖች በኃላም በጌታችን ትእዛዝ ቅስና ተቀበለ። በፆም በፀሎት በስግደት በብዙ ትጋትም እየተጋደለ በበረሀ ውስጥ ብቻውን ኖረ። በበረሀም ብዙ ዘመናትን ሲኖር ነፍሱን "ነፍሴ ሆይ እወቂ በእግዚአብሔር ፊት ራቁትሽን ትቆሚ ዘንድ እንዳለሽ እንግዲህስ ፅኚ በርቺ ታገሺ!" ይለት ነበር። ቆዳው ከዐጥንቱ እስቲጣበቅ ያለ መብልና ያለ መጠጥ በእንዲህ ያለ ግብር በገድል ተጠምዶ ኖረ።ከእፅዋት ፍሬዎች ወይም ከእንጨት ስሮች አልተመገበምና ለስጋውም የሚጠቅም ምንም ምን ምክንያት አልፈለገም።
ለገብረ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንዲህ አለው ከእንግዲህ በአለም ካሉ ሰዎች ከካህናት ከመነኮሳት ወይም ከምእመናን ህዝባውያን እንዳያውቁህ አደርግልሀለሁ። እንዳንተ ካሉ በቀር አንተ ራስህ ብትፈቅድ እንጂ መላእክትም ይጎበኙሀል። የብርሀን ሰረገላም ይሁንልህ መድረስ ወደምትሻበት ሁሉ ብረር እኔንም ማየትና በፈለግህ ጊዜ ከአባቴና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በሶስትነቴ ታየኛለህ። አሁንም ወደ ኢትዮጵያ ምድር ሂድ በዚያም ከደይን የምታወጥቸው ነፍሳት አሉህ አለው።
ከዚህም በኃላ ስልሳ አንበሶች ስልሳ ነብሮች በፊት በኃላ አጅበውት ወደ ኢትዮጵያ ምድር ተጓዙ። የእግዚአብሔር መልእክተኛ ቅዱስ ገብርኤልም ከአንበሶችና ከነብሮች ጋር በነፋስ ሰረገላ አሳፍሮ ይመራው ነበር። ወደ ምደረ ከብድም አደረሰው ከዚያም ወደ ልዩ ተራራ ወደ ደብረ ዝቋላ ወሰደው።
አባታችንም በባህሩ ቁሞ ምስራቁን ምዕራቡን ሰሜኑን ደቡቡን አራቱን ማእዘን ተመለከተ።የኢትዮጵያ ሰዎች የሚሰሩትን ኃጢአታቸውን በአይኖቹ ፊት የተገለጠ ሆኖ አየ። በራሱም ተዘቅዝቆ ተወርውሮ ወደ ባህሩ ውስጥ ገባ እሊህን የእጅህ ፍጥረቶች የሆኑትን ካልማርካቸው ከእዚህ ባህር እንዳልወጣ በእግሮቼም እንዳልቆም በህያው ስምህ እምላለሁ እያለ ማለ እንዲሁም ሆኖ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ኖረ።
ስምህን የጠራውን መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሀለሁ የሚል ቃል በመልአክ አማካይነት ወደ አባታችን መጣ። አባታችንም መልአኩን መላውን የኢትዮጵያን ሰው ካልማረልኝ ከዚህ ባህር አልወጣም አለው መልአኩም ከአጠገቡ ሄደ።
አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስም በዚያ ባህር ውስጥ መቶ ዓመት ኖረ ስጋው ሁሉ አለቀ ደሙም በባህሩ ውስጥ ፈሰሰ አጥንቶቹም እንደበረዶ ነጭ ሆነው ታዩ። አጋንንትም ከአራቱ ማእዘን በየቀኑ ሰባት መቶ ሽህ ሶስት መቶ ሽህ እየሆኑ በመምጣት በቀስታቸው ይነድፉታል እስከ መቶ አመትም አጥንቶቹን በሻፎ ድንጋይ ይፍቁታል ይህን ሁሉ መከራ በትእግስት ሲቀበል ኖረ።
ከዚህም በኃላ ጌታችን ወደርሱ መጥቶ ከባህሩ ዳር ቆመ። አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስንም መላውን የኢትዮጵያ ሰው ምሬልሀለሁና ተነስተህ ውጣ አለው ያንጊዜም ወጣ አጥንቶቹም እንደ ወንፊት ቀዳደሰ የተበሳሱ ሆነው ተገኙ ጌታም ዳሰሰውና ጤነኛ አደረገው ወደ ምድር ከብድም ሰደደው።
ከዚያም ወደ ላይ ወጥቶ ከፀሀ ከሰማይ በታች እስከ ሰባት አመት ኖረ። ዳግመኛም ወደ ምድረ ከብድ ተልኮ እንደ አምድም የተተከለ ሆኖ ሰባተረ አመት ቆሞ ኖረ። ወደ ሰማይም ሲመለከት ቅንድቦቹን አልከደነም ራሱንም ወደ መሬት ዝቅ አላደረገም ነበር እጆቹም ወደ ሰማይ ተዘርግተዋል። እነሆ ሰይጣንም በቁራ ተመስሎ መጣ አይኖቹንም ወደ ሰማይ ያንጋጠጡ ሁለቱን አይኖቹን አንቁሮ አሳወረው። እርሱ ግን ምንም ሳያጓድል እስከ ሁለት ሳምንት ድረስ እንደ ቀድሞው በመትጋት ሲፀልይ ኖረ።
ከዚህም በኃላ ሚካኤልና ገብርኤል መጥተው በፊቱ ቆሙ በሁለቱ አይኖቹ ላይም እፍ አሉበት ብርሀንም ተሰጥቷቸው እንደ ቀድሞው አዩ። ከሰማይ ታላቅ ኃይል ተሰጥቶሀልና ጠላቶችህን ትበቀላቸው ዘንድ ወደ ዝቋላ ሂድ አሉት ከዚያም መላእክት ከአጠገቡ ሄዱ። እርሱም ተነስቶ ወደ ዝቋላ ተጓዘ በጎዳናም ሲጓዝ ሶስት ሽማግሌዎች ከእንጨት ጥላ በታች ተቀምጠው አየ አባታችንም በአያቸው ጊዜ ልሰውራቸው ብሎ በልቡ አሰበ። እንርሱም ፈጥነው በእግዚአብሔር ዙፋን ተማጥነናልና ሶስታችንንም በጀርባህ እያዘልክ አንዳንድ ምእራፍ ሸኘን እንጂ አትተውን ብለው ተጣሩ። በመጣም ጊዜ ሁለመናቸውን ሽበት የከበባቸው የደከሙ ሽማግሎች ሁነው አገኛቸው አንደኛውንም አንስቶ በጀርባው አዘለው ወደ አንድ ምእራፍም አደረሰው ሽማግሌውም ከዚህ አሳርፈኝ አንተ ደክመሀል የማትበላ የማትጠጣ ስለሆንክ አለው አባታችንም ሽማግሌ ሆይ በምን አወቅከኝ አለ።
ሽማግሌውም ሂደህ ባልንጀሮቼን አምጣልኝ አለው ተመልሶ ሁለቱ ወደአሉበትም ደርሶ ሁለተኛውን ሽማግሌ በጀርባው አዝሎ ወደ ቀደመው ሽማግሌ አድርሶ አብሮ አስቀመጠው ሶስተኛም ተመልሶ ሶስተኛውን ሽማግሌ አዝሎ ሁለቱ ወዳሉበት አድርሶ በአንድነት አኖረው፡፡ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስም እነዚያን አረጋውያን እናነተ ከወዴትናችሁ መአዛችሁ ልብ ይመስጣል እጅግም ደስ ያሰኛል አላቸው።እነርሱ ግን ተነስተው ቆሙ አንድ ሲሆኑ ሶስት ሶስት ሲሆኑ አንድ መሆናቸውን ገለጡለት የአባቶች አለቃ አብርሀም እንደ አየ።
ያንጊዜም የእግዚአብሔርን የጌትነቱን ክብር አየ የእሊያ አረጋውያንም ፊታቸው ተንቦገቦገ ከፀሀይና ከመብረቅ ብልጭታም ሰባት እጅ በራ አባታችንም በምስጢራት ጎርፍ የተዋጠ ሆኖ ፈራ ተንቀጠቀጠ በምድር ላይም ወደቀ። ህልምን የሚአልምም መሰለው ከዚያም ጌታችን አባታችንን አነቃውና መቶ አመት ያህል ስጋህን ሲነዱፉህ አጥንቶችህን ሲፍቁህ የኖሩ አጋንንትን ታጠፋቸው ዘንድ ወደ ዝቋላ ተራራ ውጣ አለው።
እኔ እንደ ወሰድኩህ ባለማወቃቸው በባህር ውስጥ አለ በማለት በትእቢት ላይ ናቸው ሰባቱ ሊቃነ መላእክትም ይረዱሀል መባርቅትም በፊት በኃላ ሆነው ይከተሉሀል አለው።
ያን ጊዜ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ በመብረቅ ላይ ተጭኖ በረረ እነዚያ አጋንንት ወደአሉበትም ወረደ። ደመናትም ከበቡአቸው መላእክትም በእሳት ሰይፍ መተሩአቸው በመብረቅም አጨዱ አቸው አመድም ሆነው በነፋስ በተኑአቸው። የእነዚያም አጋንንት ቁጥራቸው ሰባት መቶ ሺህ እልፍ ከአንዱ ሺህ ነበር። ከዚህም በኃላ ጌታ ክርስቶስን የካዱ ወዳሉበት ወደ ምእራብ ሀገር ወሰደው። ነገስታቱና መሳፍንቱ መኳንንቱም በሚወጡበትና በሚገቡበት ጉዳና ላይ አቆመው ጌታችንም በዚች ጉዳና ብዙ መከራ ያገኝሀል ግን በርታ ታገስ ብሎት በዚያ ተወው። በዚያን ጊዜም የአርብ ንጉስ ጣዖታቱን አስይዞ መኳንንቱን ሰራዊቱን አስከትሎ በዚያች ጎዳና መጣ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስን በጎዳና ውስጥ በተገናኙት ጊዜ ጣኦታቱ ወድቀው ተሰባበሩ።
ንጉሱም አባታችንን በአየው ጊዜ አንተ ጠጉር ለባሽ ምንድነህ ሰው ነህን አለው።አባታችንም አዎን ክብር ያለው የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያው የሆንኩ ሰው ነኝ ብሎ ለከሀዲው ንጉስ መለሰለት። ንጉሱም ዳግመኛ አባታችንን በዚያ አይሁድ በሰቀሉት ታምናለህን አለው አባታችንም በሰው ፊት አምንበታለሁ።ስለ እኔ በተሰቀለው አላፍርበትም ስለ እኔ ብቻ የተሰቀለ አይደለም ስለ አንተና ከአንተ ጋራ ስለ አሉትም ነው እንጂ ንጉስ ሆይ የዘላለም ህይወትን ታገኛላችሁ እመኑበት አለው።
ንጉሱም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ተቆጣ ሰራዊቱንም ጠርቶ በፍጥረት እሳትን አንድዱ ለተሰቀለው ለናዝሬቱ ሰው ባሪያው ነኝ የሚለውን ጠጉር ለባሽ ወስዳችሁ ጨምሩት አላቸው። የእሳቱም ነበልባል በረጅም ዛፍ መጠን ከፍ ከፍ እስከሚል አነደዱ። አባታችን ግን ንጉሱና ሰራዊቱ ሁሉ እያዩት አልፎ በፈቃዱ ወደ እሳቱ ገባ። እሳቱም እንደወንዝ ውኃ ሆነ ሰረዊቱም እጅግ አደነቁ እኩሌቶቹም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። ንጉሱም ሲያደንቁ በአየ ጊዜ ፈፅሞ ተቆጣ ከሰባ ሰባት አርበኞቹ ጋራ በቁጣ ተነስቶ ያደነቁትንና ያመኑትን አንገታቸውን ቆረጠ ።
በዚያችም ቀን የተቆረጡ አርባ መቶ ሺህ ሆነው ተቆጠሩ።ንጉሱም የአባታችንን አንገት ሊቆርጥ ሰይፉን መዞ ተወርውሮ ሄደ። ያን ጊዜም ከመብረቅና ከነጎድጓድ ጋራ ታላቅ ንውፅውፅታ ሆነ ንጉሱንም ከሰራዊቱ ጋራ አጠፋው ከከሀዲው ንጉስ ጋራ የሞቱት ቁጥራቸው አራት ሺህ እልፍ ሆነ።
ጌታችንም አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስን ጠላቶችህንና የኔንም ጠላቶች አጠፋሁልህ አለው።አባተችን ግን በመብረቅ የሞቱትን ሬሳቸውን ነፍሳቸውንም መላእክተ ፅልመት ወደ ስቃይ ሲወስዱአቸው በአየ ጊዜ መድኃኒታችንን እሊህን ስሁታን ማርልኝ ሰው ስሁትና ከዳተኛ ነውና አቤቱ አንተ ግን መሀሪ ይቅር ባይ ታጋሽም ነህ አለው።አባታችንም ይህን ሲናገር ጌታችን ተሰወረ።
አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስም ከዚያ ሄደ ታላቅ ገደልም አገኘ እግሮቹንም በገመድ አስሮ በገደሉ ውስጥ ተዘቅዝቆ ተሰቀለ።ሰይጣንም መጥቶ ያቺን ገመድ ቆረጣት ወደ ታችም ተወርውሮ ወረደ።ቅዱስ ሚካኤልም ቀድሞ አባታችንን ያዘው በእግርህ ላቁምህ ወይም በራስህ አለው በራሴ እቆም ዘንድ ተወኝ አለው ትቶት ሄደ።
በዚያም በራሱ ቁሞ በጥርሶቹም ደንጊያ ነክሶ እስከ ሰላሳ አመት ኖረ አንጀቱና ናላው ሁሉ እየፈሰሰ አልቆ መላ አካሉ እንደእንጨት ቅርፊት ሆነ። ከሰላሳ አመትም በኃላ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባታችንን ገብረ መንፈስ ቅዱስ እያለ ሶስት ጊዜ ጠራው። እርሱም እነሆኝ ጌታዬ አለ ጌታችንም እነዚያን ከሀዱዎች ምሬልሀለሁ ከዚህ ተነሳ አለው።ያን ጊዜ የነከሰውን ደንጊያ ትቶ ተነሳ።ጥርሱም ተነቅሎ በድንጊያ ተተክሎ ቀረ። ክንፎችም ተሰጥተውት እየበረረ ከእግዚአብሔር ፊት ደረሰ ጌታውንም ከማርክልኝ ከስጋቸው ጋራ ተነስተው በመጠመቅ ክርስቲያኖች ይሁኑ ብሎ ለመነው። መድኃኒታችንም በሽተኞችን ልትፈውስ ሙታንን ልታስነሳ ስልጣን ሰጥቼሀለሁ አሁንም ወደተገደሉት ሄደህ በመስቀል ምልክት በላያቸው አማትብ ህይወት መድኃኒት በሆነ ስሜም አስነሳቸው አለው።ያን ጊዜም በድኖቻቸው ወዳሉበት ሂዶ አስነሳቸው አጥምቆም ክርስቲያኖች አደረጋቸው ከእርሳቸውም ሄደ።
ከዚህ ዓለም የሚለይበት በቀረበ ጊዜ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነሆ ተገለጠለት። ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ እስከ አስራ አምስት ትውልድ የምህረት ቃል ኪዳን ሰጠው።የእድሜውም ዘመናት አምስት መቶ ስልሳ ሁለት ሲሆን በሰላም በፍቅር አረፈ። ጌታችንም ነፍሱን ተቀበለ አቅፎም ሳማት በመላእክትና በቅዱሳን ሁሉ ምስጋና አሳረጋት።
ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት፦
1.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ (አባ ገብረ ሕይወት)
2.ቅዱስ አባ ሰረባሞን (በምድረ ግብፅ ምንኩስናን ካስፋፉ ታላላቅ ቅዱሳን አንዱ)
3.አባ ግርማኖስ ጻድቅ (ሶርያዊ)
4.ቅድስት አውዶክስያ ሰማዕት (ከከፋ የኃጢአት ሕይወት ተመልሳ ለቅድስና የበቃች እናት)
5.ቅዱሳን ስምዖንና ሚስቱ አቅሌስያ (የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ወላጆች)
ወርሐዊ በዓላት፦
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
4.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
የአባታችን ጸሎትና ምልጃ በያለንበት ይጠብቀን አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages