ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 6 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 6

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ስድስት በዚህች ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ #በዓለ_ግዝረቱ ነው፣የአባታችን #የጻድቁ_ኖኅ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ #ነቢዩ_ኤልያስ በሕይወት ሳለ በሥጋ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ ያረገበት፣ #ታላቁ_ቅዱስ_ባስልዮስ_ዘቂሣርያ አረፈ፣ የታላቋ ሰማዕት #ቅድስት_አርሴማ ልደቷ ነው፡፡




ጥር ስድስት በህዚች ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ ግዝረት በመግባት የኦሪትን ሕግ ፈጸመ ልሳነ ዕፍረት ሐዋርያው ጳውሎስ ጌታ ክርስቶስ በሥጋው ግዝረትን ተቀበለ ለአባቶች የተሰጠውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ ብሎ እንደተናገረ።
ለብዙዎችም ጌታችን ወደ ቤተ ግዝረት እንዳልገባና እንዳልተገረዘ ይመስላቸው ነበር እነርሱ እንዳሰቡት ሁኖ ቢሆን ኑሮ አይሁድ ታላቅ ምክንያትን የሚያገኙ በሆኑ ነበር ጌታችን ግን የግዝረትን ሕግ ፈጸመ ለእኛ በግዝረት ፈንታ የክርስትና ጥምቀትን ሰጠን የፋሲካውንም ቂጣ በላ በእርሱም ፈንታ ሥጋውንና ደሙን ሰጠን።
የከበረ ወንጌል ስምንተኛው ቀን በተፈጸመ ጊዜም ሕፃኑን ሊገዝሩት ወሰዱት ሳትፀንሰው መልአኩ እንዳወጣለት ስሙን ኢየሱስ አሉት እንዳለ ንጽሕት ድንግል እመቤታችን ማርያም ጻድቅ አረጋዊ ዮሴፍን እንደ ሕጉ ልጄን እንዲገርዘውና ስሙንም እንድንሰይመው ብልህ የሆነ ገራዥ ሰው አምጣልኝ አለችው። ዮሴፍም ሔዶ የሚገርዝ ባለሙያ አመጣ ያ ባለሙያም ሕፃኑን ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በእናቱ በንጽሕት ድንግል ማርያም ክንድ ላይ አየው እንድገርዘው ሕፃኑን በጥንቃቄ ያዙት አላቸው።
ሕፃን ጌታ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው ባለሙያ ገራዥ ሆይ ደሜ ሳይፈስ ትገርዘኝ ዘንድ ትችላለህን በዚያች ዕለት ካልሆነ በቀር ደሜ አይፈስምና ጐኔን በጦር ሲወጉኝ ያን ጊዜ ውኃና ደም ይፈሳል ለአዳምና ለሚያምኑ ልጆቹ መድኃኒት ይሆናል።
የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ያ ባለሙያ በሰማ ጊዜ አደነቀ ዕቃውንም ሰብስቦ ተነሥቶ ከሕፃኑ ጌታ እግር በታች ሰገደ ያንጊዜም ምላጮቹ በእጆቹ ላይ ቀልጠው እንደ ውኃ ሆኑ የከበረች ድንግል እመቤታችንን ማርያምን ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው ይህ ልጅሽ ስለርሱ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት የሕያው አምላክ ልጅ ነው አላት።
ሕፃኑም ለዚያ ባለሙያ ዳግመኛ መልሶ እንዲህ አለው እኔ ነኝ ትገዝረኛለህን ወይስ ተውክ ወይም ያባቶቼ አባቶች እንዳደረጉ እኔ ላድርግ ያም ባለሙያ የአባቶችህ አባቶች እነማን ናቸው አለው ሕፃን ጌታችንም አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ የሕዝቡ ሁሉ አባቶች የሆኑ ናቸው ለእነርሱም ይህ ግዝረት አስቀድሞ ከአባቴ ዘንድ ተሰጣቸው ባለሙያውም እኔ ከአንተ ጋር እናገር ዘንድ አልችልም በአንተ ህልውና መንፈስ ቅዱስ አለና አለው።
በዚያንም ጊዜ ሕፃኑ ጌታችን ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ አባት ሆይ ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብ አስቀድሞ ግዝረትን የሰጠሃቸው ያቺን ግዝረት ዛሬ ለእኔ ስጠኝ አለ። ያን ጊዜ ያለ ሰው እጅ በሕፃኑ ሥጋ ላይ ግዝረት ተገለጠች። ድንግልናዋ ሳይለወጥ ከድንግል ማሕፀን እንደ መውጣቱ የጌታችን ግዝረቱ የማይመረመር ሆነ እንዲሁ ወደ ሐዋርያት በተዘጋ አዳራሽ መግባቱና መውጣቱ እንደማይመረመር እንዲሁ እንደ ፈቀደ ከረቀቀ ጥበቡ ችሎታውን በመገረዝ ከሥጋው ምንም ምን ሳይቆረጥ ገለጠ።
አዳምንና ልጆቹን ያድናቸው ዘንድ በፈቃዱ ከጐኑ በመስቀል ላይ የሚፈሰው ደምና ውኃ ካልሆነ በቀር ብዙም ሆነ ጥቂት ሊሆን አይችልም እርሱ በፈቃዱ ሕጉ እንዲፈጸም አስቀድሞ አዘዘ እንጂ።
ያም ባለሙያው ገራዥ ይህን ተአምር ባየ ጊዜ የሕፃኑንም ነገር በሰማ ጊዜ እጅግ አደነቀ የክብር ባለቤት ከሆነ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር በታች ሦስት ጊዜ ሰገደና በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ የእስራኤልም ንጉሥ ነህ አለው። ከዚህም በኋላ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተአምራቱ ያየውንና የሰማውን እየተናገረ ወደ ቦታው ሔደ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ዳግመኛ የአባታችን የኖኅ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው እርሱም ከአባታችን አዳም ዐሥረኛ ትውልድ ነው። እርሱም ከታናሽነቱ ጀምሮ ኃጢአት እንደሚበዛ ክፋትም እንደሚመላ ደጋጎች እንደሚያንሱ ሥጋ የለበሰ ሁሉ በጥፋት ውኃ እንደሚደመሰስ አምላካዊ ምሥጢርን የሚያይ ሆነ ስለዚህም ፊቱ የተቋጠረ ሁኖ ፈጽሞ ያለቅስ ነበር።
አምስት መቶ ዓመትም ድንግልናውን ጠብቆ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ለአባታችን አዳም ሥጋ ሲያገለግል ኖረ ከዚህም በኋላ ሚስት እንዲያገባ ጌታ አዘዘው ሥጋ የለበሰ ሁሉ እንደሚደመሰስ ከርሱ ዘር በቀር የሚተርፍ እንደሌለ ነገረው። የአቡዚር ልጅ የሆነች ሐይከል የምትባል ሴት አገባ ወደርሷም ሦስት ጊዜ ገባ ሴምን ካምን ያፌትን ወለዳቸው።
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው ከዚህ ከደብር ቅዱስ ዕንጨቶችን ቊረጥ አራት ማእዘን አድርገህ ላንተ መርከብን ሥራ ውጭዋንና ውስጧንም የደሮ ማርና ሙጫ ለቅልቃት አለው። አቈልቋይዋን ሦስት መቶ ወርዷን ኃምሳ ቊመቷን ሠላሳ ክንድ አድርገህ ሥራት አለው።
ለዚያችም መርከብ መስኮት አውጣላት አንዲት ክንድ ስትቀር ለመጨረስም በደረሰች ጊዜ በዚያ የጐን ደጃፍ አውጣላት የአደራሽነትዋ እርከንን ሥራላት ሦስት ክፍል አድርገህ ሥራት። የመጀመሪያው ክፍል ለአራዊትና ለእንስሳ ይሁን ሁለተኛው ክፍል ለአዕዋፍና ለተንቀሳቃሽ ሁሉ ይሁን ሦስተኛውም ክፍል ለአንተና ለልጆችህ ከሚስቶቻቸው ጋር ይሁን።
ሁለተኛም እንዲህ አለው ከሚመገቧቸው መብሎች ሁሉ አስገባ ባንተ ዘንድ አኑር ላንተ ለአውሬዎችም ለእንስሶችም ሁሉ ምግብ ይሆንልሃል። ከዚህም በኋላ ኖኅ ርዝመቱ ሦስት ክንድ ጒኑ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የዕንጨት ደወል ሦስት ጊዜ የሚደውልበትን ሠራ በመጀመሪያ ለሥራ እንዲሰበሰቡ ሁለተኛው ለመብል ሲሆን ሦስተኛው ለዕረፍት ነው።
ከጥፋት ውኃ ስለመዳን መርከብን ሲሠራ የቃየል ልጆች ኖኅን አይተው ዘበቱበት እንዲህም አሉ ይህ ሽማግሌ አብዷል ውኃዎች ወደ ተራራዎች ራስ ይወጣሉ እንዴት ይለናል። ከዚህም በኋላ ኖኅ የአባታችን አዳምን ሥጋ ወሰደ ሤም ወርቁን ካም ከርቤውን ያፌት ዕጣኑን ወስደው ወደ መርከብ አስገቡ።
ኖኅም ወደ መርከብ ገባ ሚስቱ ልጆቹና የልጆቹ ሚስቶች ከጥፋት ውኃ ለመዳን ከርሱ ጋር ገቡ። ከንጹሐን እንስሳትና አዕዋፍ ተባዕትና እንስት ሰባት ሰባት ንጹሐን ካልሆኑ እንስሳትም ሁለት ሁለት ሴትና ወንድ አስገባ።
ከዚህም በዚያች ቀን ምንጮች ሁሉ ተነደሉ የሰማይም መስኮት ተከፈተ። በምድር ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ዝናም ሆነ ውኃውም ሞልቶ መርከቢቱን አንሳፈፋት ምድርንም ለቀቀች።
ውኃውም በምድር ላይ እጅግ በዛ ከሰማይ በታች ያሉትን ረጃጅም ተራራዎችን ሸፈነ። ውኃውም በላያቸው ዐሥራ አምስት ክንድ ያህል ከፍ ከፍ አለ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ከአዕዋፍ ከእንስሳ ከምድር አራዊት ሁሉ በምድር የሚኖርና ሰውም ሁሉ ሞተ።
ውኃውም በምድር ላይ መቶ ሃምሳ ቀን አየለ እግዚአብሔርም ኖኅን አሰበው ከእርሱ ጋር በመርከብ ውስጥ ያሉትን እንስሶች ሁሉ ነፋስንም በምድር ላይ አመጣ ውኃውም ጐደለ። የቀላይ ምንጮች ተደፈኑ የሰማይም መስኮት ተዘጋ ከሰማይ የሚወርደውም ዝናም ቆመ ውኃውም እያለቀ ከምድር ይሸሽ ጀመር ከመቶ ኃምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጎደለ።
መርከቢቱም በሰባተኛው ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን በዐሥራ ሰባተኛውም ሠርቀ ሌሊት በአራራት ተራራ ላይ አረፈች። ውኃው እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ እየጎደለ ይሔድ ነበር ዐሥራ አንድ ወርም በሆነ ጊዜ ከወሩ በመጀመሪያው ቀን የተራራዎች ራሶቻቸው ታዩ።
ከአርባ ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቧን መስኮት ከፍቶ ውኃው ከምድር ላይ ጎድሎ እንደሆነ ያይ ዘንድ ቁራን ላከው ሔደ ግን ውኃው ከምድር እስከ አለቀ ድረስ አልተመለሰም።
ከእርሱ ቀጥሎ ውኃው ከምድር ላይ ጐድሎ እንደሆነ ታይ ዘንድ ርግብን ላካት። እግርዋንም የምታሳርፈበት ቦታ አላገኘችም ወደርሱ ወደ መርከብም ተመለሰች ውኃው በምድር ሁሉ ላይ ነበርና እጁን ዘርግቶ ወደርሱ ወደመርከብ አስገባት።
ሰባት ቀንም ቆይቶ ዳግመኛ ምድርን ታይ ዘንድ ርግብን ላካት ርግብም በማታ ጊዜ ወደርሱ ተመለሰች በአፉዋም የዘይት ቅጠል ይዛ ነበር ኖኅም ውኃው ከምድር ላይ እንደ ጐደለ ዐወቀ። ሰባት ቀንም ቆይቶ ዳግመኛ ርግብን ላካት ደግማ ወደርሱ አልተመለሰችም።
የኖኅም ዕድሜ ስድስት መቶ አንድ ዓመት በሆነ ጊዜ በመጀመሪያው የወሩ መባቻ ውኃው ከምድር ላይ ተቋረጠ ኖኅም የሠራውን የመርከብ ድፍነት ገለጠ። ጨረቃ ሠርቅ ባደረገችበት በዐሥራ ሁለተኛው ቀን በሁለተኛው ወር ምድር ደረቀች።
እግዚአብሔርም ኖኅን አንተ ሚስትህም ልጆችህም የልጆችህ ሚስቶችም ካንተ ጋር ያለም ሁሉ ከመርከብ ውጡ አለው። ኖኅም ወጣ ሚስቱ ልጆቹም የልጆቹም ሚስቶችም ከርሱ ጋር እንስሳቱም ሁሉ ወጡ።
ኖኅም ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ ከእንስሳት ከአዕዋፍ ንጹሕ ከሆነው ሁሉ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕትን አቀረበ። እግዚአብሔርም መልካም መዓዛን አሸተተ እግዚአብሔርም እንዲህ አለ ስለ ሰው ክፋት ምድርን ሁለተኛ እንዳላጠፋ ተናገርኩ በሰዎች ልቡና ክፋት ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ሁልጊዜ ጸንቶ ኑሮዋልና ከዚህ በፊት እንዳደረግሁት ሥጋ የለበሰውን በሕይወት ያለውን ሁሉ ዳግመኛ አላጠፋም።
ምድር ፀንታ በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ዘር መከር ቅዝቃዜና ሙቀት በጋና ክረምት መዓልትና ሌሊት አይቋረጥም። እግዚአብሔር ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው እንዲህም አላቸው ብዙ ተባዙ ምድርን ምሉዋት ግዟት ከእናንተ ጋር ኪዳኔን አጸናለሁ እንግዲህ ወዲህ ሥጋ የለበሰ ሁሉ በጥፋት ውኃ አይሞትም ።
በናንተና በኔ መካከል በምድርም መካከል ለመሐላዬ ምልክት አድርጌ ቀስቴን በደመና ውስጥ አኖራለሁ። ከጥፋትም በኋላ ኖኅ ምድርን ይቆፍራት ያርሳትም ጀመር የወይን ተክልን ተከለ ወይን ጠጥቶም ሰክሮ በድንኳኑ ውስጥ ተራቈተ የከነአን አባት ካም የአባታቸውን ዕርቃን አይቶ ሳቀ ወደ ውጭ ወጥቶም ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው።
ያፌትና ሴም ልብስ ወስደው ሁለቱም በትከሻቸው ላይ አደረጉ የኋሊት ሒደው የአባታቸውን ዕርቃን ሸፈኑ ፊታቸውን ወደኋላ አዞሩ የአባታቸውንም ዕርቃን አላዩም። ኖኅም ከወይኑ ስካር በነቃ ጊዜ ታናሹ ልጁ ያደረገበትን ሁሉ ዐወቀ ኖኅም እንዲህ አለ ከነአን የተረገመ ይሁን ለወንድሞቹም ተገዥ አገልጋይ ይሁን። የሴም ፈጣሪ እግዚአብሔርም ይመስገን እግዚአብሔርም የያፌትን አገር ያስፋ። በሴም ቤትም ይደር ከነአንም አገልጋይ ይሁን።
ኖኅም ከጥፋት ውኃ በኋላ ሦስት መቶ ኃምሳ ዓመት ኖረ የኖኅም መላ ዕድሜው ዘጠኝ መቶ ኃምሳ ሆነ በሰላምም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ነቢዩ ኤልያስ በሕይወት ሳለ በሥጋ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ ያረገበት የመታሰቢያው ቀን ሆነ።
ለፈጣሪው ቀናተኛ የሆነ የዚህም ነቢይ በንጉሡ በአክአብና አስጸያፊ በሆነች በሚስቱ በኤልዛቤል ስለ ክፉ ሥራቸው ሰውነቱ በየዕለቱ ትደክም ነበር ከዚህም በኋላ መንፈሱ ተበሳጨች አክአብንም በእነዚህ ዓመታት ከአፌ ቃል በቀር ዝናብና ጠል እንዳይወርድ በፊቱ የቆምኩ የእስራኤልና የመላእክት ፈጣሪ እግዚአብሔር ሕያው ነው አለው።
የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ መጥቶ ከዚህ ቦታ ወደ ምሥራቅ ሒድ በዮርዳኖስ አውራጃ ባለች በኮራት ከዚያ ወንዝ ተሠወር ከዚያም ወንዝ ውኃን ጠጣ በዚያም ይመግቡህ ዘንድ ቁራዎችን አዛቸዋለሁ አለው።
ኤልያስም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ ሒዶም በዮርዳኖስ አንጻር ባለ በኮራት ወንዝ ተቀመጠ። ቁራዎችም ጧት ዳቦን ማታ ሥጋን ያመጡለት ነበር ከዚያም ወንዝ ውኃን ይጠጣል። ከብዙ ወራትም በኋላ ያ ወንዝ ደረቀ ዝናብም በምድር ላይ አልዘነበም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ ተነሥተህ የሲዶና ክፍል ወደምትሆን ወደ ስራጵታ ሒደህ በዚያ ተቀመጥ ድኃ ሴት በዚያ ትመግብህ ዘንድ እነሆ አዝዣለሁ አለው።
ተነሥቶ ወደ ስራጵታ ሒዶ ወደ አገር አደባባይ መግቢያ ሲደርስ በዚያ ዕንጨት ስትለቅም አንዲት ድኃ ሴትን አገኘ ኤልያስ በኋላዋ ቁሞ ጠርቶ ጥቂት ውኃ በማሰሮ አምጭልኝ ልጠጣ አላት። እሷም ልታመጣ ሔደች ዳግመኛ ከኋላዋ ጠርቶ እግረ መንገድሽን በእጅሽ ቁራሽ እንጀራን አምጭልኝ አላት።
ያችም ሴት በማድጋ ካለ እፍኝ ሙሉ ዱቄት በማሰሮም ካለ ከጥቂት ዘይት በቀር እህል እንደሌለኝ ፈጣሪህ እግዚአብሔር ሕያው ነው። እነሆም ጥቂት እንጨትን እለቅማለሁ ሔጄም ለልጄና ላንተ አዘጋጃለሁ በልተነውም እንሞታለን አለችው።
ኤልያስም በእግዚአብሔር እመኚ ሒደሽ እንዳልሽ አድርጊ ነገር ግን ለእኔ አስቀድመሽ ትንሽ አምባሻ ጋግረሽ አምጭልኝ ለልጅሽና ላንቺ ግን ኋላ ታደርጊያለሽ አላት። እግዚአብሔር እንዲህ ብሏልና በምድር ላይ ዝናብን እስቲአዘንብ ድረስ በማድጋሽ ያለ ዱቄትሽ በማሰሮሽም ያለች ዘይትሽ አታልቅም አላት። ያቺም ሴት ሒዳ አዘጋጀች እሷና እሱ ልጅዋም በሉ።
ከዚህም በኋላ የባለቤቷ የዚያች ሴት ልጅ ታመመ ነፍሱ ከሥጋው እስከምትለይ በሽታው ጸናበት። ያቺም ሴት ኤልያስን ኃጢአቴን አዘክረህ ልጄ ይሞት ዘንድ ወደ እኔ የመጣህ ነቢየ እግዚአብሔር እኔ ካንተ ምን አለኝ አንተስ ከእኔ ምን አለህ አለችው።
ኤልያስም ያንን ልጅሽን ስጪኝ ብሎ ከእቅፏ ላይ አንሥቶ እሱ ወደሚያድርበት ሰገነት አውጥቶ በአልጋው ላይ አስተኛው። ኤልያስም ወዮልኝ አቤቱ እኔ በዚች ድኃ ሴት ዘንድ አድሬአለሁና አንተ ግን ተቈጥተህ ልጅዋን ገደልክባት አቤቱ የዚችን ሴት ጩኸቷን ስማት አለ።
በዚያም ልጅ ላይ ሦስት ጊዜ እፍ አለበት እግዚአብሔርንም አቤቱ ፈጣሪዬ የዚህ ልጅ ነፍሱ ከሥጋው ጋር ትዋሐድ ብሎ ለመነው እግዚአብሔርም የኤልያስን ልመናውን ሰማው የዚያም ልጅ ነፍሱ ከሥጋው ጋር ተዋሕዳ ዳነ። ይህም ሕፃን ነቢይ ዮናስ እንደሆነ ይነገራል።
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ኤልያስን በምድር ላይ ዝናምን አዝንማለሁና ሒደህ ለአክአብ ተገለጥለት ብሎ አዘዘው ኤልያስም ወደ አክአብ ሔደ። አክአብም ኤልያስን በአየው ጊዜ እስራኤልን የምትገለባብጣቸው አንተ ነህን አለው። ኤልያስም ፈጣሪያችሁ እግዚአብሔርን የተዋችሁት ሒዳችሁ ጣዖታትን ያመለካችሁ አንተና የአባትህ ወገኖች ናችሁ እንጂ እኔስ እስራኤልን አልገለባብጣቸውም አለው።
አሁንም ወደ እስራኤል ልከህ ከእኔ ዘንድ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰብስባቸው አራት መቶ ኃምሳ የሚሆኑ ነቢያተ ሐሰትን ከኤልዛቤል ማዕድ የሚመገቡ አራት መቶ የሚሆኑ በዛፉ መስገጃ የተሾሙ ነቢያተ ሐሰትንም ሰብስባቸው አለው።
አክአብም ወደ እስራኤል ሁሉ ልኮ ሁሉንም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰባቸው። ኤልያስም ወደ እስራኤል ሁሉ ቀርቦ እግዚአብሔር ፈጣሪ ከሆነ አርሱን አምልኩ ቤል አምላክ ከሆነ እርሱን ተከተሉ እስከ መቼ ድረስ በሁለቱ ስሕተቶቻችሁ ትጠራጠራላችሁ አላቸው።
ኤልያስም ሕዝቡን የእግዚአብሔር ነቢይ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ የጣዖቱ ነቢያት አራት መቶ ሃምሣ በዛፉም መስገጃ የተሾሙት እነሆ አራት መቶ ናቸው። ሁለት ወይፈኖችንም ይስጡን እነርሳቸውም አንዱን መርጠው አርደው በየብልቱ አወራርደው በዕንጨቶቹ ላይ ይከምሩት እሳትን ግን አያንድዱ። እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አርዳለሁ እሳትንም አላነድም እነርሱም የጣዖቶቻቸውን ስም ይጥሩ እኔም የፈጣሪዬን የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ ከእርሱም እሳትን ከሰማይ ያወረደ ፈጣሪ ነው አላቸው ሕዝቡም መልካም ቃል ተናገርክ ብለው መለሱለት።
እነርሱም የመረጡትን በሬ ለአማልክቶቻቸው አስቀድመው መሥዋትነትን አቀረቡ ግን የተቀበላቸው የለም ኤልያስም መሥዋዕቱን በአቀረበ ጊዜ ከእግዚአብሔር ታዝዛ እሳት ከሰማይ ወርዳ መሥዋዕቱን ዕንጨቱን በጒድጓድ ያለ ውኃውንም አቃጠላቸው መሬቱንም ላሰችው።
ኤልያስም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው ጣዖቱን የሚያገለግሉ ነቢያተ ሐሰትን ያዝዋቸው ከእነርሱም የሚያመልጣችሁ አይኑር አላቸው ሕዝቡም ነቢያተ ሐሰትን ያዙ ኤልያስም ቂሶን ወደ ሚባል ወንዝ አውርዶ እየወጋ ጣላቸው። ከዚህም በኋላ ዝናብ ዘነበላቸው ደስ ብሏቸውም ምስጉን እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
አክአብም ለሚስቱ ኤልዛቤል ኤልያስ ያደረገውን ሁሉ አሳፋሪዎች ነቢያቶችንም በጦር ወግቶ እንደ ገደላቸው ነገራት ባልኖርባት አንተ ኤልያስ ኑረህባት አንተ ባትኖርባት እኔ ኤልዛቤል ኑሬባት ነገ ይህን ጊዜ ሰውነትህን ከነሳቸው እንዳዱ ሰውነት ባላደርጋት የያዘችውን ጥላ አማልክቶቼ እንዲህ ይጣሉኝ እንዲህም ይግደሉኝ ብላ ወደ ኤልያስ ላከች።
ስለዚህም ኤልያስ እጅግ አዝኖ እንዲህ አለ አቤቱ ነቢያቶችህን ገደሉ መሠዊያዎችህንም አፈረሱ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ ነፍሴንም ሊገድሏት ይሿታል። እግዚአብሔርም ለጣዖት ያልሰገዱ ለኔ ሰባት ሽህ ሰዎችን አስቀርቻለሁና አትፍራ ያንተንም ነፍስ ማንም ሊወስዳት የሚችል የለም። ነገር ግን በሥጋህ ሕያው እንደሆንክ ወደ ሰማይ አወጣሃለሁ አለው።
አክአብም ከሞተ በኋላ የሞአብ ሰዎች አመፁ አካዝያስም ታሞ በሰማርያ ባለ እልፍኝ ተኛ ከዚች በሽታዬ እድን እሞትም እንደሆነ ወደ አቃሮን ጣዖት ወደ ዝንቡ ካህን ሔዳችሁ ጠይቁልኝ ብሎ መልክተኞችን ላከ እነርሱም ሊጠይቁለት ሔዱ።
ነቢዩ ኤልያስም መልክተኞቹን በዚህ ደዌ እንደምትሞት ዕወቅ ብላችሁ ለንጉሣችሁ ንገሩት አላቸው። ንጉሡም ኤልያስ እንደሆነ ዐውቆ ይጠሩት ዘንድ ከኃምሳ ወታደሮች ጋር የኃምሣ አለቃውን ላከ ሔደውም በተራራው ራስ ተቀምጦ አገኙት አለቃውም ነቢየ እግዚአብሔር ሆይ ንጉሥ ይጠራሃል ፈጥነህ ውረድ ና አለው ኤልያስም የእግዚአብሔር ነቢይ ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዳ አንተንና ወገኖችህን ታቃጥላችሁ አለው እሳትም ወርዳ እርሱንና ኃምሳውን ወታደሮች አቃጠለቻቸው።
ንጉሡም ዳግመኛ ከአለቃቸው ጋራ ኃምሳ ሰዎችን ወደርሱ ላከ አለቃቸውም የእግዚአብሔር ነቢይ ንጉሥ ይጠራሃልና ፈጥነህ ውረድ አለው ኤልያስም እኔ የእግዚአብሔር ነቢይ ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዳ ታቃጥልህ ከአንተ ጋር ያሉትን ኃምሳውንም አለው እሳትም ከሰማይ ወርዳ አቃጠለቻቸው።
ከዚህም በኋላ ንጉሡ ሦስተኛ የኃምሣ አለቃ ላከ እርሱ ግን ወደ ነቢዩ ኤልያስ በትሕትና መጥቶ ሰገደለት የእግዚአብሔር ነቢይ ሆይ ተገዛሁልህ ሰውነቴ በፊትህ ትክበር የእነዚህም የባሮችህ ሰውነት ትክበር አለው። ኤልያስም ተነሥቶ ወረደ ከእሳቸውም ጋር ወደ ንጉሡ ሔደ ንገሡንም እንዲህ ብሎ ተናገረው እግዚአብሔር እንዲህ አለ ቃልን ከጣዖት ትጠይቅ ዘንድ የእስራኤል ፈጣሪ የለምን ወደ አቃሮን ጣዖት ወደ ዝንቡ ካህን እንዴት ላክህ ነገሩ እንዲህ አይደለም በዚያ ሞትን ትሞታለህ እንጂ ከተኛህበት መኝታህ አትነሣም አለው ወዲያውኑ ሞተ።
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ኤልያስን ወደ ሰማይ በሚያወጣበት ጊዜ ኤልሳዕና ኤልያስ ከገልገላ ተነሥተው ሔደው ወደ ዮርዳኖስ ደረሱ ኤልያስም መጠምጠሚያውን አውርዶ ጠቅሎ የዮርዳኖስን ውኃ መታበት ውኃውም ተከፍሎ ወዲያና ወዲህ ቆመ ሁለቱም ሁሉ በደረቅ ተሻገሩ ወጥተውም በምድር በዳ ቆሙ።
ኤልያስ ኤልሳዕን ካንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ሳልወጣ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምነኝ አለው ኤልሳዕም ኤልያስን በአንተ ያደረ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ዕጥፍ ሁኖ የደርብኝ አለው።
ኤልያስም ኤልሳዕን ድንቅ ነገርን ለመንከኝ ነገር ግን ካንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ሳርግ ብታየኝ ይሁንልሀ ባታየኝ ግን አይሆንልህም አለው። በዚያንም ጊዜ የእሳት ሠረገላና የእሳት ፈረስ መጣ ወደ መካከላቸውም ገብቶ አራራቃቸው ኤልያስም እንደዚህ በንውጽውጽታና በጥቅል ነፋስ ወደ ሰማይ ዐረገ። ኤልሳዕም አይቶ የእስራኤል ኃይላቸውና ጽናታቸው አባ አባ ብሎ ጮኸ ከዚህ በኋላ ዳግመኛ አላየውም ልብሶቹንም ለሁለት አድርጎ ከፈላቸው ኤልያስም ለኤልሳዕ መጠምጠሚያውን ጣለለት በኤልሳዕም ራስ ላይ ወረደ የኤልያስም ሀብተ መንፈስ ቅዱስ በኤልሳዕ ላይ ዕጥፍ ሁኖ አደረ ኤልያስም የሠራውን ተአምራት ኤልሳዕ ዕጥፍ አድርጎ ሠራ።
ይህም ኤልያስ በኋላ ዘመን ከኄኖክ ጋር ይመጣ ዘንድ አለው ሐሳዊ መሢሕንም ይቃወሙታል እርሱም ይገድላቸዋል በድናቸውም በአደባባይ ተጥሎ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ይቆያል ከዚህም በኋላ ይነሣሉ የሙታን ትንሣኤም ይሆናል ይህም ኤልያስ ዕውነተኛ ነቢይ አስቀድሞ የነበረ በኋላም የሚገለጽ ነው በብሉይ ዘመንም ኑሮው በበረሀ ውስጥ ነበር።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የከበረና ታላቅ የሆነ አባት የቂሣርያ ኤጲስቆጶስ ባስልዮስ አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ኤስድሮስ ይባላል እርሱም ከአንጾኪያ አገር ሰዎች ንጹሕና ቅዱስ የሆነ ቄስ ነው አምስት ልጆችንም ወልዶአል እነርሱም ባስልዮስ፣ ጎርጎርዮስ፣ ጴጥሮስ፣ ኬርዮን፣ መክርዮን ናቸው ሁሉም ከፍጹማንነት የደረሱ ቅዱሳን ናቸው።
በዚህ በከበረ ባስልዮስ ላይ መንፈስ ቅዱስ መልቶበት በሁሉ ዘንድ የታወቀች ቅዳሴውን ደረሰ እግዚአብሔርም በእጆቹ ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ በገድሉ መጽሐፍ እንደተጻፈ። ከእርሳቸውም ሰባቱ እሊህ ናቸው አንደኛው የስብስጥያ ኤጲስቆጶስ የወንድሙ የጴጥሮስ ዜና ነው እርሱ አንዲት ሚስት እንደነበረችው ሕዝቡም ስለዚህ ነገር እንዳሙት ወሬውም ወደ ቅዱስ ባስልዮስ በደረሰ ጊዜ ከሚስቱ ጋር ያለውን ምሥጢሩንና ገድሉን እነርሱ ንጹሐን ደናግል እንደሆኑ ለሕዝቡ ገለጠላቸው። የእግዚአብሔር መልአክም በክንፎቹ ሲጋርዳቸው እንዳየ አስረዳቸው በዚያንም ጊዜ በቅዱስ ጴጥሮስ ላይና በከበረች ሚስቱ ላይ የእግዚአብሔር መልአክ ክንፎቹን ሲጋርድ ሕዝቡ አዩ እጅግም አደነቁ የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንም አመሰገኑት በደላቸውንም ይቅር ይላቸው ዘንድ ከእግሩ በታች ወድቀው ቅዱስ ጴጥሮስን ለመኑት።
ሁለተኛው ተአምር ሃይማኖት ለዋጮች መናፍቃን በግፍ ስለወሰዱዋት ቤተ ክርስቲያን በርዋን መክፈት እንዳልተቻላቸው ቅዱስ ባስልዮስ በጸሎቱ ዘግቷታልና ከዚህም በኋላ ሃይማኖታቸው ለቀና ምእመናን ተከፍታላቸው ገቡ።
ሦስተኛ የቅዱስ ኤፍሬም ዜና ነው ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ በአየ ጊዜ ይህ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ባስልዮስ ነው የሚል ቃልን ሰማ። ቅዱስ ኤፍሬምም ወደ ቂሣርያ በደረሰ ጊዜ የቅዱስ ባስልዮስን ደግነቱንና ትሩፋቱን አየ ከእርሱም ዲቁና ደግሞ ቅስና ተሾመ በቅዱስ ኤፍሬም ላይም ቅዱስ ባስልዮስ ጸልዮ በዮናኒ ቋንቋ እንዲናገር አደረገው።
አራተኛ ተአምር ስለ ሥራው ሁሉ የሚቈጥር ጠንቋይ ከቶ በአቈጣጠሩ የማይሳሳት ቅዱስ ባስልዮስም በታመመ ጊዜ የሚሞትበትን ጊዜ ዐውቆ ይህን ጠንቋይ ጠርቶ መቼ እሞታለሁ አለው ጠንቋዩም ማታ ነፍስህ ከሥጋህ ትለያለች አለው። የከበረ ባስልዮስም እስከ ጥዋት ካልሞትኩ ክርስቲያን ትሆናለህን አለው ጠንቋዩም አዎን አለ። የከበረ ባስልዮስም የክብር ባለቤት ጌታቻንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነውና በዕድሜው ላይ ሦስት ቀኖችን ጨመረለት ያም ጠንቋይ አመነ ከቤተሰቦቹ ሁሉ ጋር ተጠምቆ ክርስቲያን ሆነ።
አምስተኛ ተአምር ክርስትናውን ክዶ ክህደቱንም ጽፎ ለሰይጣን ስለ ሰጠ ባርያ ዜና ነው ቅዱስ ባስልዮስም በዋሻ ውስጥ ይህን ባርያ ዘጋበት የክህደቱንም ደብዳቤ ሰይጣን እስከ መለሰለት ድረስ ስለርሱ ወደ እግዚአብሔር ለመነ ያንንም ባርያ አዳነው።
ስድስተኛ ተአምር ድንግል ስለሆነ ቄስ ዜና እርሱም ሚስቱም ከእነርሳቸውም በቊስል ደዌ የታመመ አለ የከበረ ባስልዮስም እንደ አወቀባቸው በዚያችም ሌሊት ከታመመው ዘንድ እንደ ተኛ ስለርሱም እግዚአብሔርን እንደለመነውና ከደዌው እንዳዳነው።
ሰባተኛ ተአምር ስለ አንዲት የከበረች ሴት ዜና እርሷም ኋጢአቷን ሁሉ ጽፋ በክርታስ አሽጋ ኃጢአቷ ሁሉ እስከሚደመሰስ እንዲጸልይላት ቅዱስ ባስልዮስን ለመነችው ከአንዲት በደል በቀር ኃጢአቶቿ ሁሉ እስከተደመሰሱ ድረስ ጸለየላት። ወደ ቅዱስ ኤፍሬምም እንድትሔድ አዘዛት ቅዱስ ኤፍሬምም ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ሳይሞት ፈጥነሽ ተመለሽ የካህናት ሁሉ አለቃ ስለሆነ የሚደመስስልሽ እርሱ ነውና ብሎ ነገራት በተመለሰችም ጊዜ ሙቶ በዐልጋ ተሸክመው ወደሚቀብሩበት ሲወስዱት አገኘችው መሪር ልቅሶም አልቅሳ ያንን ክርታስ ከአስክሬኑ ላይ ጣለችው በደሏም ተደመሰሰላት ሕዝቡም ሁሉ ይህን ድንቅ ሥራ አይተው እጅግ አደነቁ ለሚፈሩት ይህን ታላቅ ጸጋ የሚሰጥ እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
ይህ የከበረ ባስልዮስ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከጻፍነው ሌላ ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶችን አድርጓል ብዙዎችንም ተግሣጾችንና ድርሳናትን ለመነኰሳትም ትምህርቶችን ደርሷል። ከብሉይና ከሐዲስም አምላካውያን የሆኑ ብዙ መጻሕፍቶችን ተርጒሟል ሥርዓቶችንም ሠራ እነርሱም በሁሉ ቦታ ይገኛሉ ከዚህም በኋላ በሰላም አርፎ በክብር በብዙ ምስጋና ቀበሩት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የታላቋ ሰማዕት የቅድስት አርሴማ ልደቷ ነው፡፡ የቅዱስት አርሴማ አባቷ ቴዎድሮስ ከሌዋውያንና ከኃያላን ነገሥታት ወገን ሲሆን እናቷ አትኖስያ ደግሞ ከጳጳሳት አለቆች ወገን ናት፡፡ ወላጆቿ በሃይማኖት በምግባር ያጌጡ በበጎ ትሩፋት የተመሰገኑ ደጋግ ቅዱሳን ናቸው፡፡ በጾም፣ በጾሎት፣ በምጽዋትና ዓሥራት በኩራትን በማውጣት በመንፈሳዊ ሥራ ሁሉ እየተጉ ቢኖሩም ነገር ግን እስክ እርጅናቸው ዘመን ድረስ ልጅ ስላልነበራቸው ያዝኑ ነበር፡፡ እናቷ ቅድስት አትኖስያ እንደ ነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና ጠዋት ማታ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በእግዚአብሔር ፊት ታለቅስ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የልቧን ፈቃድ ይፈጽምላት ዘንድ ወደደና የቂሣርያውን ሊቀ ጳጳሳት ልድዮስን ስለ እርሷ ይጸልይላት ዘንድ አዘዘው፡፡
ሊቀ ጳጳሳቱም ስለ ቅድስት አትኖስያ ጸለየላት፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የሊቀ ጳጳሳቱንና የቅድስት አትኖስያን ጸሎት ሰምቶ መልኳ እጅግ ያማረችን ሴት ልጅ ቅድስት አርሴማን ሰጣት፡፡ እናቷም እየተንከባከበች አሳድጋት ዕድሜዋ ከፍ ሲል አምላክን በወለደች በእመቤታችን ስም ወደተሠራች ቤተ ክርስቲያን ታገለግል ዘንድ ሰጠቻት፡፡ ቅድስት አርሴማ ወጣት በሆነች ጊዜ ወላጆቿ ባል ያጋቧት ዘንድ ወደዱ ነገር እርሷ ይህንን ፈጽሞ አልወደደችምና ወላጆቿን "እኔ የሰማያዊው የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ እንጂ ምድራዊ ሙሽራ አይደለሁም" አለቻቸው፡፡
ቅድስት አርሴማ ከእርሷ በፊትም ሆነ ከእርሷ በኋላ በመልክና በውበት የሚመስላት የለም፡፡ ይህን ዓለም እንደትቢያ በመቁጠርና ፍጹም በመናቅ ጌታችንን ከተከተሉት ቅዱሳት ደናግል አንስት ውስጥ በመልክና በውበት ቅድስት አርሴማን የሚመስል የለም፡፡ አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን በቀር የሚበልጣት ማንም የለም፡፡ እርሷም በምግባር በሃይማኖት ያጌጠች በመንፈሳዊ ተጋድሎ የበረታች በትሩፋት የበለጸገች ናት፡፡ ብሉይን ከሐዲስ አጠናቃ ተማረች፡፡ የአገሮችንም (የሮምያን፣ የጽርዕን፣ የሶርያን፣ የኪልቅያን) ቋንቋዎች ታውቅ ስለነበር ቅዱሳት መጻሕፍትንም ወደ ተለያዩ አገራት ቋንቋዎች ትተረጉማለች፡፡
ቅድስት አርሴማ 15 ዓመት በሆናት ጊዜ ከሃዲውን ዲዮቅልጥያኖስን ሰይጣን አስነሥቶት ነገሠ፡፡ ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን እርሱ መልኳ ውብ የሆነ ብላቴና ድንግል ሊአገባ ሽቶ በየሀገሩ ሁሉ ሒደው መርጠው ያመጡለት ዘንድ አሽከሮቹን አዘዘ። ይችንም የሚመስላት የሌለ ቅድስት አርሴማን በሮሜ አገር በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ አገኙዋት። ሥዕሏንም ሥለው ለንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ላኩለት ንጉሡም ሥዕሏን በአየ ጊዜ እጅግ ደስ አለውና ለሠርግ እንዲመጡ ወደ መኳንንቱ ላከ።
እሊያ ደናግልም ይህን ነገር በአወቁ ጊዜ ይረዳቸው ዘንድ ድንግልናቸውንም ይጠብቅ ዘንድ አልቅሰው ወደ እግዚአብሔር ለመኑ። ከዚህም በኋላ ተነሥተው በሥውር ሸሹ የንጉሥ ድርጣድስ ግዛት ወደ ሆነ ወደ አርማንያ ሀገርም ደርሰው በአንድ ቦታ ተቀመጡ ከእርሳቸውም ጋር የተሰደዱ ቁጥራቸው ሰባ አምስት የሆነ ወንዶች፣ ሴቶችም ሠላሳ ዘጠኝ የሆኑ ከእርሳቸው ጋራ አሉ። ምግባቸውን አያገኙም ነበርና በታላቅ ችግር ውስጥ ኖሩ ከእነርሱም መብራት የምትሠራ አንዲት ሴት ነበረች ከእርሷም የእጅ ሥራ ከሚገኘው በየጥቂቱ ይመገባሉ።
ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም የከበረች አርሴማን በፈለጋት ጊዜ አላገኛትም ግን በአርማንያ አገር እንዳለች ስለርሷ ሰማ። ደግሞ ለአርማንያ ንጉሥ ለድርጣድስ ስለርሷ ከዲዮቅልጥያኖስ ሸሽታ እንደ መጣች የአርሴማን ሥራ ነገሩት እርሱም አንዱን የአርማንያ መኰንን ለእኔ ጠብቃት ወደ እኔም ላካት ብሎ አዘዘው።
ደናግሉም ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ ሌላ ቦታ ተሠወሩ ወደ ንጉሥም ወነጀሉአቸው ንጉሡም ቅዱስት አርሴማን በክብር አድርገው ያመጧት ዘንድ አዘዘ እርሷም ወደ እርሱ መምጣትን እምቢ በአለች ጊዜ እየጎተቱ ወስደው ወደርሱ አደረሷት።
የቅድስት አርሴማንም ላህይና ደም ግባቷን በአየ ጊዜ ድንግልናዋን ሊያረክስ ሽቶ እናቷ አጋታን አባብላ እሺ ታሰኝለት ዘንድ አዘዛት አጋታም ወደርሷ ሒዳ ልቧን አስጨከነች እንዲህም አለቻት። ዕወቂ ይህ ርኲስ አረሚ እንዳያረክስሽና ሰማያዊ ሙሽራሽን እንዳትተዪ እርሱም ክብር ይግባውና የእግዚአብሔር ልጅ ሕያው ክርስቶስ ነው።
ንጉሡም ይዞ ወደ እልፍኙ ሊአስገባት ከአደባባይ መካከል ተነሥቶ ድንግል አርሴማን ያዛት። በዚያንም ጊዜ በቅድስት አርሴማ ላይ የእግዚአብሔር ኃይል አደረባትና በምድር ላይ ጣለችው እርሱ ግን በጦርነት እጅግ የጸና አርበኛ ስለ ነበር በታናሽ ሴት ብላቴና ስለተሸነፈ ያን ጊዜ አፈረ። ራሷንም በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጧት ከዚህም በኋላ ደናግሉን ሁሉ ከእናታቸው አጋታ ጋር ይገድሏቸው ዘንድ አዘዘ።
አንዲት የታመመች ድንግል ነበረች በዐልጋዋ ላይም እንደተኛች ወደ ወታደሮች ጮኸች መጥተውም እንደ እኅቶቿ ራሷን ቆረጡ ሁሉም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ እነዚያንም ከሮሜ አገር አብረው የመጡ ወንዶችን ገደሏቸው ቁጥራቸውም ሰባ አምስት ናቸው ሥጋቸውም በተራራ ላይ የተጣለ ሁኖ ቀረ።
ሰማዕታትም ከተገደሉ በኋላ በንጉሡ ላይ ጋኔን ተጫነበት መልኩም ተለውጦ እንደ እርያ ሆነ። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ወደርሱ መጥቶ በላዩ ጸልዮ እስከ አዳነው ድረስ ስለዚህም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ። የቅዱሳን ሰማዕታትንም ሥጋቸውን ከተጣለበት ሰብስበው በአማረ ቦታ አኖሩአቸው ያማረች ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንም ተሠራችላቸው። ከእነርሱም ታላላቅ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ። በዚህችም ቀን ልደቷ ተከብሮ ይዉላል፡፡
ለእርሱም ለጌታችን ከቸር አባቱ ጋራ ማሕየዊ ከሆነ መንፈስ ቅዱስም ጋራ ክብር ምስጋና ስግደትም ይሁን፤ እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages