ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 7 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 7

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ሰባት በዚች ቀን #በዓለ_ሥሉስ_ቅዱስ ሕንጻ ሰናዖርን ያፈረሱበትና ቅዳሴ ቤታቸው ነው፣ የከበረ አባት የሮሜ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ሶል_ጴጥሮስ አረፈ፡፡


ጥር ሰባት በዚች ቀን በዓለ ሥላሴ የሚከበረው ስለ ሁለት ምክንያቶች ነው:: ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን ሌላው ደግሞ ቅዳሴ ቤታቸው ነው::
ሰናዖር ከሺዎች ዓመታት በፊት በአሁኗ ኢራቅ አካባቢ እንደ ነበረ የሚነገርለት ግዛት ሲሆን ስሙ ለሃገሪቱም: ለንጉሡም በተመሳሳይ ያገለግል ነበር:: ከናምሩድ ክፋት በሁዋላ ሰናዖርና ወገኖቹ ከሰይጣን ተወዳጁ::
ከጥፋት ውሃ (ከኖኅ ዕረፍት) በሁዋላ በሥፍራው በአንድነት ይኖሩ ነበርና እርስ በርሳቸው "ኑ ሳንበተን ስማችን የሚጠራበትን ሕንጻ እንሥራ:: በዚያውም አባቶቻችን በውሃ ያጠፋ እግዚአብሔርን እንውጋው" ተባባሉ::
ቀጥለውም ሰማይ ጠቀስ ፎቅን ገነቡ:: ከሕንጻው መርዘም የተነሳ በጸሐይ አብስለው በልተዋል ይባላል:: ቀጥለውም ጦር እያነሱ ፈጣሪን ሊወጉ ወርውረዋል::
መቼም የእነዚህን ሰዎች ክፋትና ቂልነት ስንሰማ ይገርመን ይሆናል:: ግንኮ ዛሬ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም እየተሠራ ያለው ከዚህ የከፋ ነው:: ቸርነቱ ቢጠብቀን እንጂ እንደ ክፋታችንስ ጠፊ ነበርን::
ርሕሩሐን ሥላሴ ግን የሰናዖር ሰዎች የሠሩትን አይተው ማጥፋት ሲችሉ አላደረጉትም:: የባሪያቸውን የኖኅን ቃል ኪዳን አስበዋልና:: ይልቁኑ "ንዑ ንረድ ወንክአው ነገሮሙ ለከለዳውያን-ቁዋንቁዋቸው እንደባልቀው" አሉ እንጂ::
ከለዳውያን ልሳናቸው ተደበላልቆ 71 ቁዋንቁዎች ተፈጠሩ:: እነርሱም ስምምነት አጥተው ተበተኑ:: ሥላሴም ያን ሕንጻ በነፋስ ትቢያ እንዲሆን በተኑት:: ስለዚህም እስከ ዛሬ ሥፍራው "ባቢሎን (ዝሩት)" ሲባል ይኖራል::
ልክ የዛሬ 324 ዓመት አድያም ሰገድ ኢያሱ በኢትዮዽያ በነገሡ በ10ኛው ዓመት (በ1684 ዓ.ም) በጐንደር ከተማ ንግሥተ አድባራት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተሰርታ ተጠናቃለች::
ጥር 7 ቀንም ሊቁ ክፍለ ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን: ሠራዊት: መሣፍንትና ሊቃውንት ባሉበት ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል:: በዕለቱም ታላቅ ሐሴት ተደርጉዋል:: ኢያሱ አድያም ሰገድ ኃያል: ደግ: ጥበበኛ: አስተዋይ: መናኝ ንጉሥ ነውና::
ቤተ ሥላሴን አስጊጿታልና ከዚህ ቀን ጀምሮ ጥር ሥላሴ በድምቀት የሚከበር ሆኗል:: ነገር ግን በተሠራች በ16 ዓመቷ ደጉ ኢያሱ ከተገደለ በሁዋላ ቤተ ክርስቲያኑ በአደጋ ፈርሷል:: ዛሬ የምናየው በ1708 ዓ.ም በልጁ በአፄ ዳዊት ሣልሳዊ የታነጸውን ነው::
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን የከበረ አባት የሮሜ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት ሶል ጴጥሮስ አረፈ። ይህንንም አባት ስለ ተጋድሎው ገናናነት ስለ አገልግሎቱም ስለ ትሩፋቱ ስለ አዋቂነቱና ስለ ደግነቱ ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ መልጥያኖስ ከአረፈ በኋላ መርጠው ሊቀ ጵጵስና በሮሜ ሀገር ላይ ሾሙት። በሐዋርያት አለቃ በጴጥሮስ ወንበር በተቀመጠ ጊዜ የዕሌኒ ልጅ የሆነ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስን የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው ከከሀድያን ጋር ስለሚያደርገው ጦርነት ምክንያት ገና አልተጠመቀም ነበርና የጣዖታትንም ቤቶች አፍርሶ የእግዚአብሔርን አብያተ ክርስቲያናት ሠራቸው።
የዚህም አባት የሶል ጴጥሮስ ገድሉ እጅግ ብሩህ የሆነ ነው እርሱ ሁል ጊዜ ሕዝቡን ያስተምራቸዋልና ከልቡናቸውም ከሰይጣን የሆነ ጥርጥርንና ክፉ ሐሳብን ያርቃል። ከእነርሳቸው ሥውር የሆነውንም የመጻሕፍት ምሥጢር ተርጕሞ ያስገነዝባቸዋል። አይሁድንና ዮናናውያንን ሁል ጊዜ ይከራከራቸው ነበር ከእርሳቸውም ብዙዎችን መልሶ ወደ ቀናች ሃይማኖት አስገባቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ስሙም በምእመናን ዘንድ ፈጽሞ የሚያስፈራ ሆነ።
እግዚአብሔርን ስለ ማወቅና ስለ ወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን ብዙ ድርሳናትን ደረሰ። በተሾመ በሰባተኛውም ዓመት ስለ አርዮስ በኒቅያ ከተማ ሃይማኖታቸው የቀና የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት የከበሩ አባቶች የአንድነት ስብሰባ ሆነ ይህም አባት ሶል ጴጥሮስ ከእርሳቸው አንዱ ነበር አርዮስንም ከተከታዮቹ ጋር ረገመው አውግዞም ለየው።
በሹመቱም ዐሥራ አንድ ዓመት ኖረ መልካም ተጋድሎውን ፈጽሞ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages