ስንክሳር_ዘወርኀ_ታህሣሥ 7 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታህሣሥ 7

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ሰባት በዚችም ዕለት ከቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወለድ #በከበሩ_ነቢያት አፍ ለመሰበኩ መታሰቢያ ነው፣ በደብረ ሲሐት የሚኖር #አባ_ዳንኤል አረፈ፣ #ቅዱስ_አባት_አባ_ማቴዎስ አረፈ።


ታኅሣሥ ሰባት በዚህችም ዕለት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ እንደሚወለድ በከበሩ ነቢያት አፍ ለመሰበኩ መታሰቢያ ሆነ ።
ይህች ዕለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት "ስብከት" ትባላለች። ስብከት ማለት በቁሙ "የምስራች፣ አዲስ ዜና መንገርን" የሚመለከት ሲሆን ዋናው ምሥጢር ግን ከነገረ ድኅነት (ከመዳን ትምሕርት) ጋር የተገናኘ ነው።
በዚህ ዕለት (ሳምንት) ሁሉም ነቢያት ከነ ትንቢታቸው ይታሰባሉ። ዘመነ ስብከትም ከታሕሳስ 7 እስከ 13 ያለውን ይይዛል። ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ እግዚአብሔር አዳምን በ7 ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ። በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር፣ ርደተ ገሃነም ተፈረደበት። በሁዋላ ግን ንስሃ ስለ ገባ "ከ5 ቀን ተኩል (5,500 ዘመን) በሁዋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው።
ከዚህ በሁዋላ ለ5,500 ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር። ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር፣ ሱባኤ ይቆጠር፣ ምሳሌም ይመሰል ገባ።
ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ። ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሣፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል:: ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት/ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል።
ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም፣ በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል። እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል። መድኅን ክርስቶስም ተወልዶ አድኗቸዋል።
ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር) መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው። ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ።
ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም። በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ። (ሐዋ.11፥27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ።
ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል፣ "እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ። (ቅዳሴ ማርያም)
የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ አንዳንዶቹም በእሳት፣ አንዳንዶቹም በሰይፍ፣ አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል። ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል።
ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል። ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል። (ዮሐ.4፥36)
ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል ሽተዋልም። "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል። (ማቴ. 13፥16፣ 1ዼጥ.1፥10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ።
ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት 15ቱ አበው ነቢያት: 4ቱ ዐበይት ነቢያት: 12ቱ ደቂቀ ነቢያት እና ካልአን ነቢያት ተብለው በ4 ይከፈላሉ::
#15ቱ_አበው_ነቢያት ማለት፦ ቅዱስ አዳም አባታችን፣ ሴት፣ ሔኖስ፣ ቃይናን፣ መላልኤል፣ ያሬድ፣ ኄኖክ፣ ማቱሳላ፣ ላሜሕ፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴ እና ሳሙኤል ናቸው።
#4ቱ_ዐበይት_ነቢያት ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል፣ ቅዱስ ኤርምያስ፣ ቅዱስ ሕዝቅኤልና፣ ቅዱስ ዳንኤል ናቸው።
#12ቱ_ደቂቀ_ነቢያት የሚባሉት ሆሴዕ፣ አሞጽ፣ ሚክያስ፣ ዮናስ፣ ናሆም፣ አብድዩ፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ኢዩኤል፣ ዕንባቆም፣ ዘካርያስ እና ሚልክያስ ናቸው።
#ካልአን_ነቢያት የሚባሉት ደግሞ፦ ኢያሱ፣ ሶምሶን፣ ዮፍታሔ፣ ጌዴዎን፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ ኤልያስ እና ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው::
ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ፦
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም)፣ የሰማርያ (እሥራኤል) እና የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::
በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
* ከአዳም እስከ ዮሴፍ #የዘመነ_አበው_ነቢያት
* ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል #የዘመ_መሳፍንት_ነቢያት
* ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት #የዘመነ_ነገሥት_ነቢያት
* ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ #የዘመነ_ካህናት_ነቢያት ይባላሉ።

በዚህች ቀን በአባ መቃርስ ገዳም በደብረ ሲሐት የሚኖር አባ ዳንኤል አረፈ። ይህም አባ ዳንኤል ስሟን እንጣልዮስ አስኝያ የነበረች ንግሥት በጥሪቃን የገነዛት ነው እርሷም ከሞቷ በኋላ እንጂ ሴት እንደሆነች አልታወቀችም ነበር።
በአንዲት ቀንም ወደ እስክንድርያ አገር ከረድኡ ጋር ሲጓዝ ስሙ ምህርካ የሚባል እብድ አገኘ ብዙ እብዶችም ይከተሉታል ለአገር ሰዎችም በእውነት ያበደ ይመስላቸው ነበር አባ ዳንኤልም እጁን ይዞ ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ ወስዶ ትሩፋቱን ተጋድሎውን ነገረው እንዲነግራቸውም በአማሉት ጊዜ ከዝሙት ጦር በመሸሽ ራሱን እብድ እንዳስመሰለ ነገራቸው ሰምተውም እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
በአንዲትም ዕለት ወደ አንዲት አገር ደረሰ በዚያም አውሎጊስ የሚባል ለድኆች የሚራራ እንግዳም የሚቀበል ደንጊያ በመውቀር የሚኖር ሰው አገኘ እርሱንም ተቀብሎ በደስታ አሳደረው መልካም ሥራውንም በአየ ጊዜ ድኆችን የሚረዳበት ገንዘብን ለአውሎጊስ ይሰጠው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ስለርሱ ለመነ ጌታችንም በሕፃን አምሳል ተገለጠለትና ገንዘብ ባገኘ ጊዜ ጠባዩን እንዳይለውጥ አንተ ትዋሰዋለህን አለው አባ ዳንኤልም አዎን እዋሰዋለሁ አለ።
ከዚህም በኋላ አውሎጊስ በድስት የመላ ወርቅን አግኝቶ ያንን ይዞ ወደ ንጉሥ ሒዶ የጭፍራ አለቃ ሆኖ ተሾመ ጠባዩንም ለወጠ። ጠባዩንም እንደለወጠ አባ ዳንኤል ሰምቶ ሊመክረውና ሊገሥጸው ሔደ የአውሎጊስ ወታደሮችም ለመሞት እስኪደርስ ድረስ ደበደቡት በዚህም እያዘነ ሳለ ያ ሕፃን በሕልም ታየው አባ ዳንኤልንም ለምን በሌላ ሰው ነገር ገባህ ብሎ እንዲሰቅሉት አዘዘ። ከዚህም በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መጥታ ለሕፃኑ ሰገደች እግሮቹንም እየሳመች ስለ አባ ዳንኤል ለምና ከስቅለት አዳነችው።
ከዚህም በኋላ ሌላ ንጉሥ በነገሠ ጊዜ አውሎጊስን ሊገድለው ፈለገው ያን ጊዜ አውሎጊስ ሸሸ ወደ አገሩም ደርሶ ወደ ቀድሞ ሥራው ተመለሰ። በአንዲት ቀንም በሌሊት በበረሀ ውስጥ በጨረቃ ብርሃን ሲጓዝ በተራራ ላይ ተቀምጣ ሴት አገኘ ጠጉሩዋም ሥጋዋን ሁሉ ሸፍኖአል እየተጋደለች ሠላሳ ስምንት ዓመት የኖረች ናት ምሥጢርዋንም ሁሉ ነግራው ከዚህ በኋላ አረፈች።
ከዚህም በኋላ በአንዲት ዕለት የልዮንን ደብዳቤ ሰዎች አምጥተው በሕዝብ ፊት አነበቧት አባ ዳንኤልም ዘሎ የልዮንን ደብዳቤ ነጥቆ ቀደዳትና የኬልቄዶን ሃይማኖት የተገወዘ ነው አለ ወታደሮችም አይተው ደበደቡት ከገዳሙም አሳደዱት።
በአንዲት ዕለትም አባ ዳንኤል ከደናግል ገዳም ደርሶ ደጁን አንኳኳ አባ ዳንኤልም እንደሆነ አውቀው ከፈቱለትና በደስታ ተቀበሉት ከእነርሱም አንዲቷ ራሷን እብድ አስመስላ በደጅ የምትተኛ አለች ስለርሷ እመ ምኔቷን ጠየቃት እርሷም እብድ ናት አለችው። እርሱም መስተጋድልት ቅድስት ሴት እንጂ እብድ እንዳልሆነች ነገራት። እብድ የተባለችውም በሌሊት ተነሥታ የከበራችሁ እኅቶቼ ስለ አሳዘንኳችሁ ይቅር በሉኝ ብላ ጽፋ ያንን ትታ ታጣች ደናግሉም እጅግ አዘኑ ተጸጸቱም።
በውስጡ ብዙ ደናግል የሚኖሩበት ገዳም ነበረ መዝጊያውም የጸና ነው። ገንዘባቸውንም ይበረብሩአቸው ዘንድ ሰይጣን ወንበዴዎችን በላያቸው አስነሣ የወንበዴዎች አለቃም በመራቀቅ በራሱ ላይ ቆብ አድርጎ በአባ ዳንኤል አምሳያ ለብሶ ደጃፋቸውን ሒዶ በማንኳኳት አባ ዳንኤል ነኝ አለ አይተውም ከፈቱለት በደስታም ተቀብለው እግሩን አጠቡትና ስለ በረከት የእግሮቹን እጣቢ በየፊታቸው ረጩት ከውስጣቸው አንዲት ዕውር ነበረች ውኃው ሲነካት ዐያኖቿ በሩላት ደናግሉም አንተ አባ ዳንኤል ንዑድ ክቡር ነህ አሉት የሽፍቶቹም አለቃ አይቶ ደነገጠ ተጸጸተም ከአባ ዳንኤልም ዘንድ መንኲሶ የሚጋደል ሆነ።
ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ነገረው ጥቂት ጊዜም ታመመ ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየና በሰላም አረፈ።

በዚህችም ቀን ለታወቀች እስዋን ለተባለች ገዳም አበ ምኔት የሆነ የሚጋደል ቅዱስ አባት አባ ማቴዎስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ በፈሪሀ እግዚአብሔር ጸንቶ ያደገ ነው ከገዳማትም በአንዱ መንኲሶ በጾም በጸሎት ተወስኖ የሚጋደል ሆነ በገዳሙም ውስጥ ለራሱ መኖሪያ ሠራ ደቀ መዛሙርቱ አባ ሰራብዮንና አባ ኅድራ ሥራውን ተጋድሎውንና ተአምራቱን እንደተናገሩ መረብንም በመሥራት ሽያጩን ለድኆች ይመጸውታል።
እነርሱም እንዲህ ብለው ተናገሩ በአንዲት ዕለት ከማደሪያው በውጭ ተቀምጠን ሳለ በማደሪያው ውስጥ አንዱ ከሌላው ጋር እንደሚነጋገር ሁኖ ቃልን ሰማን በገባንም ጊዜ ከእርሱ በቀር ያገኘነው የለም። አባታችን ሆይ በውጭ ሳለን ከአንተ ጋር ሰው እንደሚነጋገር ድምፅ ሰምተን ነበር በገባን ጊዜ ከአንተ በቀር ያገኘነው የለም አልነው ። በብዙ ትሕትና እንዲህ አለን ልጆቼ ሆይ የምትጠብቀኝን የሞት ፃዕርና ሥቃዮችን ለነፍሴ በማሳሰብ የኃጢአቴን ብዛት አስቤ ከራሴ ጋር ተነጋገርኩ። ለድኃ ማቴዎስ ወዮለት ንጽሕናን ቅድስናን በለበሱ የመላእክት የጻድቃንና የሰማዕታት ጉባኤ አንድነት በአለበት በልዑል እግዚአብሔር መንበር ፊት ራቁቱን ያቆሙታልና እንዲህም አድርጎ የኃጥአንን ሥቃይ የጻድቃንን መልካም ዋጋ ለልጆቹ አስተማራቸው።
ቅዱስ ማቴዎስም በሠራት ገዳም ውስጥ ጸሎትን ተጋድሎን አገልግሎትን በማድረግ ጸንቶ ኖረ ገዳሙንም በአባ ጳኩሚስ ስም አከበረ እርሷም የታወቀች ሰሌን ያለባት ተራራ ናት።
ርኩሳን የሆኑ ረቂቃን ሰይጣናትም በቀንና በሌሊት የሚያስፈራሩት ሆኑ በየዓይነቱ በተለያየ መልክ ፊት ለፊት እያያቸው እነርሱ በፊቱ ይሮጣሉ በኋላውም ይከተሉታል እርሱ ግን አይፈራቸውም እጁንም ዘርግቶ በመስቀል ምልክት ሲአማትብ በዚያን ጊዜ በነፋስ ፊት እንዳለ ጢስ ይበተናሉ።
በአንዲትም ዕለት ጥቂት እንጀራና ውኃ በመንቀል ከገዳም ውስጥ ይዞ በበረሀ ውስጥ ወደአለች ዋሻው እንዲሔድና እርሱ በማግሥቱ እስቲመጣ በዚያ እንዲጠብቀው ረድኡን ሰራብዮንን አዘዘው። ሰራብዮንም ወደ ዋሻው ሲደርስ ሁለት ታላላቅ አራዊት በውስጥ ተኝተው አገኘ ፈርቶ በሩን ዘግቶ ከዐለት ቋጥኝ ላይ ወጣ።
ከዚህም በኋላ አባ ማቴዎስ የዳዊትን መዝሙር እያነበበ መጣ ረድኡንም አይቶ ፈገግ ብሎ ሳቀ ሰራብዮን ሆይ እኔ ወዳንተ እስከምመጣ ወደ ዋሻው ውስጥ ለምን አልገባህም አለው ። እርሱም ረድኡ አባቴ ሆይ ሁለት ታላላቅ አውሬዎች ተኝተው ስለ አገኘሁ እነርሱን ፈርቼ አልገባሁም አለው ።
ንጽሐ ነፍስ ያለው የዋህ የሆነ የተመሰገነ አረጋዊም ልጄ እመነኝ እኔ ከእነርሱ ጋር ስኖር ዐሥራ ሁለት ዓመት ሆነኝ ያሳደግኋቸውም እኔ ነኝ ይህንንም እንጀራና ውኃ እንድታመጣ ያዘዝኩህ ለእነርሱ ነው አለው ።
ከዚህም በኋላ በሩን በከፈተ ጊዜ እነዚያ አውሬዎች ወደርሱ መጥተው ቅዱስ አባ ማቴዎስን እግሮቹን ላሱ ባልንጀሮችም ሁነውት በታላቅ መለማመጥ ተገዙለት ያንንም ውኃ ከገንዳ ላይ አፍስሶላቸው ጠጡ እንጀራውንም በሉ ከዚያም በኋላ ወደ ዱር ሔዱ ።
ይህም አባ ማቴዎስ የዜናው መሰማት በቦታው ሁሉ እስከመላ ድረስ ተአምራትን እያደረገ ኖረ በየዓይነቱ በሆነ ደዌ የተያዙትን ያመጡለታል ። እርሱም በላዩ በአደረች በእግዚአብሔር ኃይል ይፈውሳቸዋል ።
ከተአምራቶቹም አንዱ በአንዲት ቀን ጋኔን ያደረበት ዲዳ ሰውን ወደርሱ አመጡ ቅዱስ ማቴዎስንም በአየው ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ሰውዬውን ከምድር ላይ ጣለው ቅዱሱም በዘይት ላይ ጸለየ በመስቀል ምልክትም አማትቦ ቀባው በዚያንም ጊዜ ድኖ አእምሮው ተመለሰ የሚሰማና የሚናገርም ሆነ ደስ ብሎትም ወደቤቱ ሔደ ።
ጨዋዎችም በመጡ ጊዜ ማዕድ ያቀርብላቸውና በሰላም በፍቅር ያሰናብታቸዋል እነርሱም ለበረከት እያሉ ጥቂት ቁራሽ ወደ ቤታቸው ይወስዳሉ በበሽተኞችም ላይም በአደረጉት ጊዜ ወዲያውኑ ድነው እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል።
ሁለተኛ ተአምር በአንዲትም ዕለት ደም ግባቷ ያማረ ጋኔን ያደረባትን ብላቴና ወደርሱ አመጡ እርሷ ብዙ ጊዜ ልብሷን ትቀዳለች ወደርሷም መቅረብ የሚችል የለም ወላጆቿም በታላቅ ኀዘን ውስጥ ይኖራሉ ቅዱስ አባ ማቴዎስም በላይዋ ጸለየና ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ዘይቱን ቀብቶ አዳናት።
ሦስተኛ ተአምር በአንዲት ዕለት እጅግ በከፋችና ታላቅ በሆነች ኃጢአት ላይ የወደቀች ኃጢአተኛ ሴት ወደርሱ አመጡ እርሷ ፀንሳ የመውለጃዋ ጊዜ የደረሰ ነው በቀንና በሌሊትም በምጥ ሕማም ትሠቃይ ነበረ አባ ማቴዎስም ልጄ ሆይ ኃጢአትሽን እመኚ በእግዚአብሔር ፊት አትዋሺ አላት። እርሷም እንዲህ አለችው እኔ ከሁለት ወንድማማቾች ጋር እነርሱ ሳያውቁ ሳመነዝር ኖርኩ በጸነስኩም ጊዜ ሕፃኑን በመርዝ አውጥቼ ለውሾች ሰጠሁት አባ ማቴዎስም በሰማ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ በዚያንም ጊዜ ለሌሎች መቀጣጫ ትሆን ዘንድ ምድር አፏን ከፍታ ዋጠቻት።
የዚህም አባት ተአምራቶቹ ብዙ ናቸው ተነግሮ አያልቅም በአንዲትም ቀን በበረሀ ውስጥ ሲጓዝ ጅብ ልብሶቹን በጥርሶቻ ይዛ ሳበችውና በሠንጣቃ ገደል ውስጥ የወደቁ ልጆቿን አሳየችው በአወጣላትም ጊዜ ሰገደችለት እግሮቹንም ላሰች።
ከዚህም በኋላ ዕረፍቱ ሲቀርብ በታኅሣሥ ሦስት ቀን ወደ ሠርግ እንደሚጠራው ራእይን አየ ይኸውም የቅዱሳን አባቶች የአባ እንጦንስ፣ የአባ መቃርስ፣ የአባ ጳኪሚስ፣ የአባ ቴዎድሮስ፣ የአባ ሙሴ ጸሊም፣ የአባ ሲኖዳ የአንድነት ተድላ ደስታ ወዳለበት ነው። እነርሱም በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ከእኛ ጋር ትኖር ዘንድ ወደእኛ መምጣትህ መልካም ነው አሉት ብዙ አትክልቶችና ዙፋኖች ወዳሉት ታላቅ አዳራሽም ደጅ አደረሱት ማቴዎስ ይገባ ዘንድ የአዳራሹን ደጆች ክፈቱ የሚልንም ቃል ሰማ ከዚህም በኋላ በዚሁ ወር በሰባት አረፈ ሦስት አክሊላትንም ተቀበለ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን በጻድቅ በነቢያት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages