ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 8 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 8

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ስምንት በዚህች ዕለት #የአቡነ_እስትንፋሰ_ክርስቶስ ተወለዱ፣ በዚህች ቀን የድባው #አቡነ_ሙሴ ልደታቸው ነው፣ #ብፅዕት_እንባመሪና ተወለደች፣ ታላቅ አባት #የአባ_ኪሮስ አረፈ፣ የከበሩ ሴቶች #ቅድስት_በርባራና_ቅድስ_ዮልያና በሰማዕትነት አረፉ፣ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ #አባ_ያሮክላ አረፈ፣ #አባ_ሳሙኤል_ዘደብረ_ቀልሞን አረፈ፣ #ቅዱሳን_አባ_ኤሲና_እኅቱ_ቴክላ በሰማዕትነት አረፉ፣ #አባ_ዮሐንስ_ዘደማስቆ አረፈ፣ የደብረ ድማሕ #ቅዱስ_ተክለ_አልፋ አረፈ።


ታኅሣሥ ስምንት በዚህች ዕለት የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ የልደታቸው መታሰቢያ በዓል ነው፡፡ ታሪካቸውን ከዛሬው ከወርሃዊ በዓላቸው ጋር እናየዋለን፡- አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ አባታቸው መልአከ ምክሩ እናቱ ወለተ ማርያም ይባላሉ፡፡ የተወለዱበት ልዩ ቦታው ወሎ ክፍለ ሀገር ዳውንት ነው፡፡ በተወለዱ ዕለት ተነሥተው በእግራቸው ቆመው ሦስት ጊዜ ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ብለው ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል፡፡ የስማቸው ትርጓሜ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ አንድም የክርስቶስ እስትንፋስ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቃቸውና በመንገዳቸው ሁሉ እየመራቸው ነው ያደጉት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ልቡናቸውን ብሩህ አድርጎላቸው በ5 ዓመታቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃላትን፣ ብሉያትንና ሐዲሳትን፣ ድርሳናትንም ጠንቅቀው ዐውቀዋል፡፡
በተወለዱ በ14 ዓመታቸው ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ደብረ ሐይቅ ገዳም ሄደው ከባሕር ዳር ቆመው የሙሴን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ባሕሩን አሻግሯቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተዋል፡፡ ለ3 ዓመታት ያህል በኃይቅ ገዳም ለመነኮሳት እንጨት በመልቀምና ውሃን በመቅዳት ለአባቶች መነኮሳት ምግብ የሚሆናቸው ዓሣ ከባህር ውስጥ በማውጣት አገልግለዋል፡፡ አባታችን እስትንፋሰ ክርስቶስ 40 መዓልትና 40 ሌሊት ከጾሙ በኋላ ምንም እህል ሳይቀምሱ ጌታችን
ክርስቶስ አስቀድሞ ለሙሴ በደብረ ሲና እንደሰጠው ለአባታችንም ወደ እርሳቸው መጥቶ ዓሥሩን ቃላተ ኦሪትና ስድስቱን ቃላተ ወንጌል በውስጣቸው የተጻፈባቸው ሁለት ጽላቶችን ሰጥቷቸዋል፡፡ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ከሠሩ በኋላ ዕለቱን ስንዴ ዘርተው፣ ወይን ተክለው፣ ጽድን ወይራንና ግራርን ተክለው በአንዲት ቀን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ዕለቱን አድርሰዋል፡፡ ስንዴውን ለመሥዋዕት ወይኑን ለቍርባን በተአምራት አድርሰዋል፡፡
አባታችን በጸሎት ላይ እንዳሉ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተልኮ መጥቶ አባታችንን በደመና ጭኖ ወስዶ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ፊት አቆማቸው፡፡ ጌታንም በቅዱሳኑ ሁሉ እንዲባረኩ ካደረጋቸው በኋላ መልአኩን ‹‹ወደ ተወለድኩባትና ወደ ኖርኩባት ቦታ ወደ ኢየሩሳሌም አድርሰው›› ብሎት ኢየሩሳሌምን አሳልሞ ሀገራችን መልሶ አምጥቷቸዋል፡፡ አባታችን ሁሉንም የኢትዮጵያን ቅዱሳት ገዳማትን ተዘዋውሮ ሲጎበኙ በሕይወተ ሥጋ የሌሉት የየገዳማቱ ቅዱሳን ሁሉ በአካል ይገለጡላቸው ነበር፡፡ ጎጃም ውስጥ እያስተማሩ፣ እያጠመቁ፣ የታመሙትን እየፈወሱ፣ የዕውራንን ዐይን እያበሩና ሙታንን እያሥነሱ ብዙ ካገለገሉ በኋላ ለዘጠኝ ዓመታት በባሕር ውስጥ ገብተው ቁልቁል ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያ ጸልየው የምሕረት ቃልኪዳን ተቀብለዋል፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ጌታችን መጥቶ ‹‹ከመነኮሳት ሁሉ ብልጫ ያለህ ወዳጄ ሆይ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ምሬልሃለሁ ከዚህች ባሕር ውጣ›› በማለት በሞት የሚያርፉበትን ቦታ ነግሯቸዋል፡፡
ጻድቁ ወደ ደብረ አሰጋጅ በሚሄዱበት ጊዜ ጸሐይ ልትገባ ስትል ‹‹በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አውግዤሻለሁ ለመስፍን ኢያሱ በገባኦን እንደቆምሽ አሁንም ቀጥ ብለሽ ቁሚ›› ብለው ገዝተው ፀሐይን አቁመዋል፡፡ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስም ደብረ አሰጋጅ ሲደርሱ ፀሐይ አፍ አውጥታ ‹‹አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ እገባ ዘንድ ፍታኝ›› ስትላቸው ‹‹እግዚአብሔር ይፍታሽ›› ባሏት ጊዜ ጠልቃለች፡፡ ጻድቁ ሌላው በእጅጉ የሚታወቁበት አንድ ትልቅ ቃል ኪዳን አላቸው፡፡ በአምላክ ልቡና የሚገኝ፣ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ልቡና የሚገኝ፣ በቅዱስ ሚካኤልና በቅዱስ ገብርኤል ልቡና የሚገኝ እንደ መልክአ መድኃኔዓለም ያለች እጅግ አስገራሚ ጸሎት አለቻቸው፤ እርሷን ጸሎት በጸለዩ ጊዜ እልፍ ነፍሳትን ከሲኦል ያወጣሉ፡፡ ጸሎቷም የመድኃኔዓለምን የሰውነት ክፍሎች በሙሉ እየጠቀሰች እያንዳንዱ የሰውነት ክፍሎቹ የተቀበሉትን ጸዋትዎ መከራዎች ሁሉ ታዘክራለች፡፡ በእያንዳንዱ ክፍልም የጸሎት ማሳረጊያ አቡነ ዘበሰማያት ይደግማሉ፡፡ ንስሓ የገባ ኃጢአተኛ ሰው እንኳን ቢሆን ይህችን የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስን ጸሎት በጸለየ ጊዜ ሺህ ነፍሳትን ከሲኦል እንደሚያወጣ ጌታችን በማይታበል ቃሉ ለአባታችን ነግሯቸዋል፡፡ እያንዳንዱን የመድኃኔዓለምን የሰውነት ክፍሎች በሙሉ እየጠቀሰች መከራዎቹን የምታዘክረውን ይህቺን በአምላክ ልቡና ያለች ግሩም የሆነች ጸሎት ነፍሳትን ከሲኦል አታወጣም ብሎ የሚጠራጠር ቢኖር መንግስተ ሰማያትን አያያትም፡፡ ጻድቁ ታኅሣሥ 8 ቀን ተወልው ሚያዝያ 9 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡

በዚህች ቀን የድባው አቡነ መሴ ልደታቸው ነው። የትውልድ አገራቸው እስራኤል ልዩ ቦታው ቃና ዘገሊላ ነው። ጽንሰታቸውን ቅዱስ ሩፋኤል መጋቢት 8 ቀን ሲያበስር ልደታቸውን ደግሞ ቅዱስ ገብርኤል ታኅሣሥ 8 ቀን የመወለዳቸውን ብሥራት ተናግሯል፡፡ ሲወለዱ ሚካኤል ወገብርኤል በሰው አምሳል ተገልጠው "የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ" ብለው ስም አወጡላቸው፡፡
በተወለዱም በ40ኛ ቀናቸው ከተጠመቁ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል አቅፎ ይዟቸው ጌታችን በቅዱሳን እጆቹ አቁርቧቸዋል፡፡ በእሳቸውም ምክንያት በዚያች ዕለት በቤተ ክርስቲያን የነበሩት ሰዎች ሁሉ ክቡራን በሆኑ በጌታችን እጆች ቆርበዋል፡፡ የአቡነ ሙሴ አባታቸው ዮስጦስ ለሐዋርያው ናትናኤል አጎቱ ነው፡፡ እናታቸው ጵርስቅላ ጌታችን በሠርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን የለወጠለት የዶኪማስ ልጅ ናት፡፡
ጌታችን ወደ ዶኪማስ ቤት ሠርግ ተጠርቶ የሄደው ዶኪማስ ናትናኤልን ‹‹ሠርጌን እንዲባርክልኝ ጌታ ኢየሱስን ከእናቱ ጋር ጥራልኝ›› ብሎት ነው፡፡ ጌታችን በስብከቱ ‹‹ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልሏቸው›› ብሎ ብሎ ካቀፋቸውና
ካስተማረባቸው ሕፃናት አንዱ ይኽ አቡነ ሙሴ ናቸው፡፡ ጻድቁ ዋሻዎችን እየፈለፈሉ የቅዱሳን ሐዋርያትን ዐፅም በክብር ያስቀምጡ ነበር፡፡ የተሠወሩ አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ ወንጌልን በማስተማር ብዙ መከራ የተቀበሉ አባት ናቸው፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ በግብፅ "ንጉሥ አንስጣስዮስ" ተብለው 40 ዓመት በንግሥና እና በድንግልና ኖረዋል፡፡
ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ በመልአክም ምክር ዮናኒ የተባለውን ሌላ ሰው አንግሠው ወደ አስቄጥስ ገዳም ገብተው መነኮሱ፡፡ በገዳሙም በታላቅ ተጋድሎ ከኖሩ በኋላ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የእኛ ጳጳስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ሲያርፉ በቅዱስ አትናቴዎስ ተሹመው 2ኛው የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆነው ‹‹አቡነ ሰላማ ካልዕ›› ተብለው ተሾመው ወደ አገራችን መጡ፡፡ ከመሾማቸው በፊት አባቶቻችን አቡነ አትናቴዎስን ‹‹ጳጳስ ይላኩልን›› ብለው መልእክት ሲልኩባቸው አቡነ አትናቴዎስም ወደ አስቄጥስ ገዳም በመሄድ እግዚአብሔርን በጸሎት ቢጠይቁት የታዘዘ መልአክ መጥቶ ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሙሴን ላክላቸው›› አላቸው፡፡ መነኮሳቱም ሁሉ እንዲሁ አሉ፡፡ ከዚህም በኋላ ሲሾሙ ሚካኤልና ገብርኤል በወርቅ ወንበር ላይ አስቀምጠዋቸው ‹‹ይገባዋል ይገባዋል›› ብለው ቅብአ ክህነት ቀብተዋቸዋል (ጵጵስና ሾመዋቸዋል፡፡) አቡነ ሙሴም ከተሾሙ በኋላ 14000 መነኮሳትን አስከትለው ወደ ቅድስት አገራችን መጡ፡፡ አቡነ ሙሴ ንግሥናቸውን ትተው ወደ ኢትዮጵያ መተው 16 ፍልፍል ቤተመቅደሶችን የሠሩ ሲሆን 8ቱ የተሰወሩ ናቸው፡፡
በገዳማቸው በቅድስቱ ውስጥ ጥልቀቱ የማይታወቅ እጅግ ጥልቅ የሆነ ጉድጓድ አለ፡፡ በውስጡም ስውራኑ አብያተ ክርስቲያናት ይገኙበታል፡፡ ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተቀረጸውና ፍልፍል የሆነው የገዳማቸው የቤተልሔሙ ስፋት ሜትር ከሃያ ሲሆን ጣራው እንደ አቡነ አሮን ክፍት ሆኖ ሳለ ዝናብ ግን አይገባበትም፡፡ ዝናብ የማያስገባው የቀዳዳው ስፋት አንድ ሜትር በአንድ ሜትር ነው፡፡ ጻድቁ በሀገራችንም ዕፁብ ድንቅ የሆኑ ብዙ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽና ወንጌልን በማስተማር ብዙ ደክመዋል፡፡ በተለይም በዋናነት የሚታወቁት በሰሜን ወሎ አውራጃ ወልድያ ወረዳ መቄት ልዩ ቦታው ገረገራ የሚገኘው ‹‹አዲስ አንባ ዋሻ መድኃኔዓለም›› እና መጀመሪያ እንደመጡ ያረፉባት ‹‹ድባ ማርያም›› ይጠቀሳሉ፡፡
ይህችውም ድባ ማርያም ገዳም ታላቁ አባት እስትንፋሰ ክርስቶስ የመነኮሱባት ናት፡፡ ጻድቁ አቡነ ሙሴ መስከረም 4 ቀን ጌታችን ቃልኪዳን ሲገባላቸው እነዚህን ሁለት ገዳማቸውን ‹‹እንደ አስቄጥስ ገዳም እንደ አቡነ እንጦንስ ማኅበር ይሁኑልህ›› ብሏቸዋል፡፡ በገዳማቸው ከሚኖሩት ቅዱሳን ውስጥ 400 ወንዶች መነኮሳትና 200 ሴቶች መነኮሳያት እንደተሰወሩ መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡
ጻድቁ ሌላው ለየት የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ገና በእናቷ ማኅፀን ሳትፀነስ የቅድስት አርሴማን ጽላት ያሠሩላት መሆናቸው ነው፡፡ ቁመቱ 2 ሜትር ከ70 የሆነ ግሩም ቤተ መቅደስም ፈልፍለው አንጸውላታል፡፡ ጌታችንም የሰማዕቷን ጽናትና ረድኤት ከቦታው እንደማይለይባቸው ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ በቃል ኪዳናቸው የታመኑትን ልጆቻቸውን መተትና መርዝ አይጎዳቸውም፡፡ ይህም ጌታችን የሰጣቸው ልዩ ቃልኪዳናቸው ነው፡፡ ጻድቁ እንደ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ 12 ክንፍ የተሰጣቸው ታላቅ የምሕረት አባት ናቸው፡፡

በዚችም ዕለት የብፅዕት እንባመሪና የተወለደችበት ነው። ቅድስት መሪና ገና ልጅ ሳለች እናቷ ማርያም ሞተችባት:: ደግ አባት አንድ ልጁን በሥጋዊም: በመንፈሳዊም ሳያጐድልባት አሳደጋት:: ዕድሜዋ አሥራ አምስት ዓመት በሆነ ጊዜ ወደ ፊቱ አቅርቦ "ልጄ! እኔ ወደ ገዳም ስለምሔድ አንቺን መልካም ባል ላጋባሽ::" አላት::
ቅድስት መሪናም "ነፍሰ ዚአከ ታድኅን: ነፍሰ ዚአየኑ ታጠፍእ - የአንተን ነፍስ አድነህ እንዴት የእኔን ትተዋታለህ? እኔም እመንናለሁ::" አለችው:: አባቷ የተናገረችው ከልቧ እንደሆነ ሲያውቅ "ልጄ! ገዳም ሁሉ በአካባቢው የወንድ ብቻ ነውና ስሚኝ::" አላት::
እርሷ ግን "አባቴ! ግዴለህም: ስሜን እንደ ወንድ ቀይረህ: አለባበሴንም ለውጥ::" አለችው:: (እንደ ወንድ ለበሰች ማለት ግን እንደ ዘመኑ ዓይነት እንዳይመስላችሁ አደራ!)
ከዚያ አባትና ልጅ ሃብት ንብረታቸውን ሸጠው ለነዳያን አካፈሉ:: በፍጹም ልባቸውም መነኑ:: በደረሱበት ገዳም ቅድስት መሪና በወንድ ስም "እንባ መሪና" በሚል ገባች:: ቀጣዩ ሥራዋ እንደ ወንዶች እኩል መስገድ: መጾምና መጸለይ ነበር::
ይህችን ቅድስት ልናደንቃት ግድ ይለናል:: ማንም በእርሷ አይፈተንም:: አያውቋትምና:: እርሷ ግን ወጣት ሆና: አንድም ሴት በሌለበት ገዳም ጸንቶ መቆየት በራሱ ልዩ ነው:: መልአካዊ ኃይልንም ይጠይቃል::
ተጋድሎዋ በጣም ስለ በዛ ወንድሞች መነኮሳት ይደነቁባት ነበር:: ጺም ስለሌላትና ድምጿ ቀጭን ስለሆነ አልተጠራጠሩም:: ምክንያቱም ጃንደረባ ናት ብለው አስበዋልና:: ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን አባቷ ታሞ ከማረፉ በፊት አበ ምኔቱን ጠርቶ "ወደ ከተማ ልጄን እንዳትልክብኝ: አደራ!" ብሎት ነበር::
ያም ሆኖ አንዳንድ መነኮሳት ቅሬታ በማንሳታቸው ወደ ከተማ ተላከች:: ችግሩ ለተልእኮ ባደሩበት ቤት አንድ ጐረምሳ ገብቶ የአሳዳሪውን ልጅ ከክብር አሳንሷት ሔደ:: ሲወጣም "ድንግልናሽን ያጠፋ ማን ነው? ካሉሽ ያ ወጣት መነኩሴ አባ እንባ መሪና ነው በይ::" አላት::
ከሦስት ወራት በኋላ የዚያች ዘማ ሴት ጽንስ በታወቀ ጊዜ ለአባቷ "አባ እንባ መሪና እንዲህ አደረገኝ::" አለችው::
አባት መጥቶ እየጮኸ መነኮሳትን ተሳደበ:: አበ ምኔቱ ግራ ተጋብቶ ቢጠይቀው "የአንተ ደቀ መዝሙር እንባ መሪና ልጄን ከክብር አሳነሳት::" አለው:: አበ ምኔቱ እውነት መስሎታልና ቅድስቲቱን ጠርቶ ቁጣና እርግማንን አወረደባት:: በዚያች ሰዓት ተንበርክካ አንድ ነገር ወሰነች::
"ሴት ነኝ" ብሎ መናገሩስ ቀላል ነው:: ግን ደግ ናትና የእነዛን አመጸኛ ሰዎች ኃጢአት ልትሸከም ወሰነች:: ቀና ብላ "ማሩኝ ወጣትነት ቢያስተኝ ነው?" አለቻቸው:: ተቆጥተው ዕለቱን እየገፉ ከገዳም አስወጧት:: ከባድ ቀኖናም ጫኑባት:: ከስድስት ወራት በኋላም የእርሷ ልጅ ነው የተባለ ሕፃን አምጥተው ሰጧት::
ይህኛው ግን ከባድ ፈተና ሆነባት። እንዳታጠባው አካሏ በገድል ደርቁአል:: በዚያ ላይ ድንግል የሆነች ሴት ወተት የላትም:: ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት: የበጋውን ሐሩር: የክረምቱን ቁር ራሷ ታግሣ ለሕፃኑ ከእረኞች ወተት እየለመነች: እየመገበች ሦስት ዓመታት አለፉ::
በዚህ ጊዜ ወደ ገዳሙ ከከባድ ቀኖና ጋር ተመለሰች:: ሕፃኑን ስታሳድግ: ለገዳሙ ስትላላክ: ምግብ ስታዘጋጅ: ውኃ ስትቀዳ: የእያንዳንዱን ቤት ስታጸዳ ሰላሳ ሰባት ዓመታት አለፉ:: ሕፃኑም አድጐ ደግ መናኝ ወጣው:: (የቅድስቷ እጆች ያሳደጉት የታደለ ነው::)
በመጨረሻ ቅድስት መሪና (እንባ መሪና) ታማ ዐረፈች:: እንገንዛለን ብለው ቢቀርቡ ሴት ናት:: እጅግ ደንግጠው አበ ምኔቱን ጠሩት:: በዙሪያዋ ከበው እንባቸውን አፈሰሱ:: ጸጸት እንደ እሳት በላቻቸው:: ሥጋዋን በክብር ገንዘው: በአጐበር ጋርደው: በራሳቸው ተሸክመው ምሕላ ገቡ::
ሙሉውን ቀን "ስለ ቅድስት መሪና ብለህ ክርስቶስ ሆይ ማረን?" ሲሉ ዋሉ:: ድንገት ግን ከተባረከ ሥጋዋ "ይቅር ይበለን::" የሚል ድምጽን ሰምተው ደስ ብሏቸው ቀበሯት:: እነዚያ ዝሙተኞችም ከእርሷ ይቅርታን እስካገኙበት ቀን አብደው ኑረዋል::

በዚችም ዕለት በምዕራባዊ በረሀ የሚኖር ታላቅና ክቡር አባት የሆነው የአባ ኪሮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ።
ይህም ቅዱስ የታላቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ወንድሙ ነበር በከተማ ውስጥ የሚሠራውን ዐመፅ በአየ ጊዜ ገንዘቡን ሁሉ ትቶ ከሀገሩ ወጣ። ጌታቸንም መርቶ ወደዚች ምዕራባዊት በረሀ አደረሰው በውስጧም ብዙ ዘመናት ብቻውን ኖረ ከሰው ማንም አላየውም በዚህ ሁሉ ዘመን የዱር አራዊትም ቢሆኑ ።
በአስቄጥስም ገዳም ስሙ አባ ባውማ የሚባል አንድ ቄስ ነበረ እርሱም የንጉሥ ዘይኑን ልጅ ቅድስት ኢላርያን ሥጋዋን የገነዘ ነው ። እርሱም እንዲህ አለ በቤተ ክርስቲያን ወስጥ እያለሁ አባ ባውማ ሆይ ተነሥ ወደ በረሀው ውስጥ ገብተህ ወደ ፀሐይ መግቢያ ሒድ ከቅዱሳን ሁሉ አብዝቶ ፈቃዴን የፈጸመውን የአንድ ገዳማዊ ሥጋ ትገንዝ ዘንድ የሚለኝን ቃል ከሰማይ ሰማሁ።
ያን ጊዜም ደስ ብሎኝ ተነሣሁ በበረሀውም ውስጥ ሦስት ቀን ተጉዤ ከአንድ ገዳማዊ በዓት ደርሼ ደጁን አንኳኳሁ አንድ ሽማግሌ ገዳማዊም ከፈተልኝና እርስ በርሳችን ሰላምታ ተለዋወጥን በዚች በረሀ ሌላ ገዳማዊ አለን ብዬ ጠየቅሁት አዎን አለኝ ። ሁለተኛም ስምህ ማነው አባቴ ሆይ በዚችስ በረሀ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ኖርክ አልሁት ስሜ ስምዖን ነው በዚች በረሀ የኖርኩትም ሰባ ዓመታት ነው አለኝ።
ከእርሱ ዘንድም ወጥቼ ሦስት ቀን ተጓዝኩ ሁለተኛም ስሙ ባሞን የሚባል ገዳማዊ አገኘሁ ሰላምታም ሰጠሁትና በዚች በረሀ ሌላ ገዳማዊ አለን አልሁት አዎን አለ አለኝ ። አራት ቀንም ተጓዝኩ ወደ አባ ኪሮስ በዓት ደረስኩ ቅዱስ አባት ሆይ ባርከኝ እያልኩ ደጁን አንኳኳሁ አባ ባውማ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው ብሎ ከውስጥ ተናገረኝ ። እግዚአብሔር ያከበረህ ሰው በሰላም በፍቅር ወደእኔ ግባ አለኝ ያን ጊዜ ገብቼ ከእርሱ ተባረክሁ በፊቱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ክብር አየሁ የራሱ ጠጉርና ጽሕሙ እንደ በረድ የነጣ ነበር ።
ከዚህም በኋላ ተቀመጥሁ በብብቻውም አቀፈኝ እንዲህም አለኝ እነሆ ይችን ሰዓት እየጠበቅኋት በዚች በዓት ሃምሳ ሰባት ዓመት ኖርኩ ይህንንም ሲል ጥቂት ታመመና ተኛ እየደነገጠ ያቺን ሌሊት አደረ ሲነጋም በበዓቱ ውስጥ ታላቅ ብርሃን በራ ብርሃናዊ ሰውም ገባ በእጁም የብርሃን መስቀል አለ በአባ ኪሮስ አጠገብም ተቀምጦ ሳመዉ ባረከውም አጽናናው ሰላምን ፍቅርን አንድነትን አደረገለት ከእርሱም ተሠወረ እኔም ፈራሁ እንዲህ የሚበራ ይህን ክብር የተጐናጸፈ ይህ ማነው አልሁት ።
እርሱም ልጄ ሆይ ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ልማዱ ስለ ሆነ ሁልጊዜ ይመጣል ያጽናናኛልም አለኝ ። በቀዳሚት ሰንበት ዕለትም ዘጠኝ ሰዓት በሆነ ጊዜ እስከ ሰማይ የሚደርስ ታላቅ ጩኸትን ሰማሁ ከጩኸታቸውም ኃይል የተነሣ ምድር ተናወጸች። እኔም ይህ የምሰማው ጩኸት ምንድነው ብዬ ጠየቅሁት እርሱም ልጄ ሆይ ይህ በሲኦል የሚኖሩ የኃጥአን ጩኸት ነው ስለ ቅድስት ትንሣኤው የእሑድ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ እግዚአብሔር ያሳርፋቸዋልና ስለዚህም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል አለኝ ።
ሐምሌ ሰባት ቀን ቅዱስ አባ ኪሮስ ጩኾ አለቀሰ ዛሬ በግብጽ አገር ታላቅ ምሰሶ ወደቀ ይኸውም የገዳማውያን አለቃ ቅዱስ አባ ሲኖዳ ነው አለ ።
ከዚህም በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ እሑድ ሌሊት እጅግ ደነገጠ በበዓቱም ውስጥ እነሆ ታላቅ ብርሃን በራ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ገብቶ በአባ ኪሮስ ራስ አጠገብ ተቀመጠ ። አባ ኪሮስም መድኃኒታችንን ጌታዬ ሆይ ይህን ሰው ባርከው አለው መድኃኒታችንም የመረጥሁህ አባ ባውማ ሆይ ጽና አትፍራም ሰላሜ በረከቴም ከአንተ ጋራ ይኑር ። አሁንም ታማኝ አገልጋዬ የሆነ የዚህን የቅዱስ ኪሮስን ያየኸውንና የሰማኸውን ወደፊትም ዳግመኛ የምታየውንና የምትሰማውን ገድሉን ጻፍ አለኝ ።
ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን አባ ኪሮስን እንዲህ አለው እነሆ አንተ ትሞታለህና አትዘን ሞትህ ሞት አይደለም የዘላለም ሕይወት ነው እንጂ ። የገድልህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውን የሚሰማውንም ሁሉ በምድርም መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሽህ ዓመት በዓል ምሳ ከእኔ ጋር ይቀመጥ ዘንድ አደርገዋለሁ ከቅዱሳኖቼም ጋራ እቆጥረዋለሁ ። የኃጢአቱንም መጽሐፍ ቀድጄ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ ። ለመሥዋዕት የሚገባውንም ዕጣኑንና ወይኑን መብራቱንም መባ አድርጎ ለሚሰጥም በስምህም ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋትን ለሚያደርግ ዓይን ያላየውን ጆሮም ያልሰማውን በሰው ልቡናም ያልታሰበውን በጎ ዋጋ እኔ እጥፍ ድርብ አድርጌ እሰጠዋለሁ ። በበኵር ቤተ ክርስቲያንም ሥጋዬንና ደሜን አቀብላቸዋለሁ በዚህም ዓለም ቤታቸውን እባርካለሁ ። ልጆቻቸውን አሳድጋለሁ ከበጎ ነገር ሁሉ ምንም ምን አያጡም ።
አሁንም ከዚህ ዓለም ድካም ወደ ዕረፍት የዘላለም ተድላ ደስታ ወዳለበት ወደ ብርሃን ቦታ እወስድህ ዘንድ ጊዜው ደረሰ መድኃኒታችንም ይህን ሲናገር እነሆ ነቢዩና ዘማሪው ዳዊት መጣ መሰንቆውም ከእርሱ ጋራ ነበረች። ይቺ ዕለት በእርሷ ፈጽሞ ሐሤት እናደርግ ዘንድ እግዚአብሔር የሠራት ናት እያለ አመሰገነባት።
መድኃኒታችንም አባ ኪሮስን እነሆ ዘማሪው ዳዊት መጥቷልና ይዘምርልህ ዘንድ የምትሻውን ንገር አለው። ዳዊትም ቅዱስ አባ ኪሮስን በየትኛው አውታር እንድዘምርልህ ትሻለህ ደግሞስ በየትኛው ዜማ በየትኛው ስልት በመጀመሪያው ነውን ወይስ በሁለተኛው ወይስ በሦስተኛው አለው። ቅዱስ አባ ኪሮስም በዐሥሩም አውታር በየስልታቸውና በየዜማቸው ልሰማ እሻለሁ አለ። ያን ጊዜ ዳዊት መሰንቆውን አዘጋጅቶ የጻድቅ ሞቱ በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው አለ ዳግመኛም ጐለመስሁ አረጀሁም የሚወድቅ ጻድቅን አላየሁም አለ ። ዳዊትም ድምፁን አሣምሮ ዘመረ መሰንቆውንም በስልት መታት ። ያን ጊዜም የቅዱስ አባ ኪሮስ ነፍሱ ወጣች መድኃኒታችንም ተቀብሎ ሳማት ለመላእክት አለቃ ለሚካኤልም ሰጣት ።
እኔ አባ ባውማም የቅዱስ አባ ኪሮስን ሥጋውን ቀበርኩ ከበዓቱም በወጣሁ ጊዜ በረሀው በሰማይ ሠራዊት ተመልቶ አየሁ መድኃኒታችንም የቅዱስ አባ ኪሮስ ሥጋው ባለበት በዓት ላይ መስቀሉን አኑሮ ዘጋት ። ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን ለኔ ሰላምታ ሰጥቶኝ መላእክትና የመላእክት አለቆች በፊቱ እያመሰገኑና እየዘመሩ በታላቅ ክብር ዐረገ ። የቅዱስ አባ ኪሮስን ነፍስ ከመድኃኒታችን ጋራ እንደዚህ አሳረጓት ። እርሷም በተሰጣት ክብር ደስ እያላት ዐረገች ።
እኔም አባ ባውማ በዚያ ቦታ ብቻዬን ቀረሁ ተመልሼም ወደ አባ አሞን በዓት ደረስሁ ። ከዚያም የሦስት ቀን መንገድ ተጉዤ ወደ አባ ስምዖን በዓት ደረስሁ ። ከዚያም ሦስት ቀን ተጉዤ ወደ ቦታዬ ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረስ። ለመነኰሳቱም ሁሉ ያየሁትንና የሰማሁትን ሁሉ የቅዱስ አባ ኪሮስን ገድሉን ስለ አባ ሲኖዳም ዕረፍት ትንቢት እንደ ተናገረ ነገርኋቸው።
መነኰሳቱም ሰምተው እጅግ አደነቁ የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ። እኔ አባ ባውማም የቅዱስ አባ ኪሮስን ገድሉን ጽፌ ለሚያነበውና ለሚሰማው ሁሉ መጽናኛ ይሆን ዘንድ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉና ወደ ገዳማትም ላክሁ።

በዚችም ቀን የከበሩ ሴቶች በርባራና ዮልያና በሰማዕትነት አረፉ ። ይችም ቅድስት በርባራ በከሀዲው መክስምያኖስ ዘመነ መንግሥት በቤተ መንግሥት ውስጥ ታላቅ መስፍን ለሆነ ሰው ልጁ ናት ስሙም ዲዮስቆሮስ ነው እርሱም ለልጁ ለበርባራ ማንም እንዳያያት ታላቅ ጽኑ የሆነ ሕንፃ አሠራ ከዚህም ዳግመኛ መታጠቢያ የውሽባ ቤት በግንብ ሠራ የሚከፈቱ ሁለት መስኮቶችንም በውስጡ እንዲሠሩ አዘዘ ። ቅድስት በርባራም ሁለቱን መስኮቶች በአየች ጊዜ ሦስተኛ መስኮትን እንዲሠሩ ሐናፂዎችን አዘዘቻቸው ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝ የሆነ የመስቀሉን ምልክት በውኃ መታጠቢያው ላይ አሠራች ።
አባቷም ወደዚህ ሕንፃ በገባ ጊዜ ይህን ልጁ ያሠራችውን አይቶ አናፂዎችን ጠየቀ እነርሱም ይህን እንድንሠራ ልጅህ አዘዘችን አሉት እርሷንም ጠርቶ ለምን እንዲህ አደረግሽ አላት። እርሷም አባቴ ሆይ አስተውል ልዩ ሦስት በሆነ በሥላሴ ስም ሥራ ሁሉ ይፈጸማልና ስለዚህ ሦስተኛ መስኮት አሠራሁ ይህም መስቀል ዓለሙ ሁሉ በእርሱ በዳነበት በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል አምሳል ነው አንተም አባቴ ሆይ ከስሕተትህ ተመልሰህ የፈጠረህን አምላክ አምልከው አለችው ።
አባቷም ከእርሷ ይህን በሰማ ጊዜ ሰይፉን መዝዞ በኋላዋ ሮጠ እርሷም ሸሸች በፊቷም የነበረች ዐለት ተሠንጥቃ በውስጧ ገብታ ሠወረቻት ። ከዚህም በኋላ ወደ አባቷ ተመለሰች እርሱም እንዲአሠቃያት ለሌላ መኰንን አሳልፎ ሰጣት እርሱም ታላቅ ሥቃይን አሠቃያት በዚያም ዮልያና የምትባል ሴት ነበረች ቅድስት በርባራንም አየቻትና የምታጽናናትና የምታረጋጋት ሆነች ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለቅድስት በርባራ ተገለጸላትና አረጋጋት።
ከዚህም በኋላ አባቷ በሰይፍ ራሷን እንዲቆርጡ የባልንጀራዋ የዮልያናንም ራስ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጧቸው የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ ። በዚያንም ጊዜ ከሰማይ እሳት ወርዶ አባቷንና ጓደኛው የሆነ መኰንን መርትያኖስን አቃጠላቸው ያም በውሽባ ቤት ውስጥ በመስቀል ምልክት ያሠራቸው መታጠቢያ ለታመመ ሁሉ ከእርሱ በታጠበ ጊዜ የሚያድን በውስጡ ታላቅ ፈውስ ያለበት ሆነ ።
ከዚህም በኋላ የቅዱሳት ሰማዕታትን ሥጋቸውን ወስደው ከከተማ ውጭ ባለች ቤተ ክርስቲያን ስሟ ገላልያ በሚባል ቦታ አኖሩአቸው ይህ ሥጋቸውም በቅዱሳን ሰማዕታት በአቡቂርና በዮሐንስ በምስር አገር በአለ ቤተ ክርስቲያናቸው እስከ ዛሬ አለ ።

በዚህች ቀን የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት አባ ያሮክላ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ዐሥራ ሦስተኛ ቊጥር ነው ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ አስቀድሞ አረማውያን ነበሩ በወለዱትም ጊዜ የአረማውያንን ትምህርት መጻሕፍቶቻቸውንም ሁሉ አስተማሩት ።
ከዚህም በኋላ አምነው ተጠመቁ ይህን ልጃቸውንም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማሩት የሐዋርያትንም መጻሕፍት አጠና ሊቀ ጳጳሳት ድሜጥሮስም ዲቁና ሾመው ከዚህም በኋላ በእስክንድርያ አገር ቤተ ክርስቲያን ቅስና ሾመው መንጋውንም በመልካም አጠባበቅ ጠበቀ ።
ሥራውንም ፈጸመ የቤተ ክርስቲያንንም ሕግ ጠንቅቆ አወቀ። አባት ድሜጥሮስም በአረፈ ጊዜ ይህን አባት መርጠው በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት እርሱም ክብር ይግባውና የክርስቶስን መንጋዎች በቀናች ሃይማኖት አጽንቶ ጠበቀ ከአረማውያንም ብዙዎችን ክብር ይግባውና ክርስቶስን ወደ ማመን መልሶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ።
ለቅዱስ ዲዮናስዮስም ለምእመናን እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጠው እርሱ ግን ዓላው ያንን ወደ ቀናች ሃይማኖት እስከሚመልሳቸው ድረስ ያስተምራቸውና ይገሥጻቸው ነበር ። በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበርም ዐሥራ ሦስት ዓመት ኑሮ በሰላም አረፈ ።

በዚችም ቀን ቅዱስ አባት የደብረ ቀልሞን አባ ሳሙኤል አረፈ ይህም ቅዱስ ለግብጽ ደቡብ ከሆነ መጺል ከሚባል አገር ደክሉባ ከሚባል መንደር ነው ። ወላጆቹም ቅዱሳንና ንጹሐን ናቸው ያለ እርሱም ልጅ አልነበራቸውም አባቱም ቄስ ነበር ። በሌሊት በራእይ ፊቱ ብሩህ የሆነ ሰው አየ ። ይህ ልጅህ ለብዙ ሰዎች የታመነ ቸር መምህር ይሆን ዘንድ አለው በዘመኑም ሁሉ ለእግዚአብሔር የተመረጠ ይሆናል አለው ።
አባ ሳሙኤልም ከታናሽነቱ ጀምሮ እንደ ነቢዩ ሳሙኤል ንጹሕ ነው ሁልጊዜም የምንኲስና ልብስን ይለብስ ዘንድ ያስብ ነበር ። በአንዲትም ቀን ወደ አስቄጥስ ገዳም ይሔድ ዘንድ ምክንያት አግኝቶ ከአባቱ ዘንድ ወጣ ግን መንገዱን አያውቅም ነበር ። የእግዚአብሔርም መልአክ በመነኵሴ አምሳል ሁኖ እየመራው አብሮት ተጓዘ በአደረሰውም ጊዜ በበዓት ውስጥ ለሚኖር ለአንድ ስሙ አባ አጋቶን ለሚባል ሽማግሌ መነኰስ ሰጠው እርሱ እጅግ ጻድቅ ሰው ነውና ። ይህም መልአክ ስለ አባ ሳሙኤል ለአባ አጋቶን እንዲህ ብሎ ነገረው ሳሙኤልን ደስ ብሎህ ተቀበለው የምንኲስናንም ልብስ አልብሰው እርሱ የሽምግልናህን ድካም የሚያጽናና ዕውነተኛ ልጅን ይሆንሃልና አንተም የምንኲስናን ሕግ ሁሉ አስተምረው ይህንንም ከተናገረው በኋላ መልአኩ ከእርሱ ተሠወረ ።
ሳሙኤልም በደረሰ ጊዜ አባ አጋቶን በደስታ ተቀበለው እንዲህም አለው የእግዚአብሔር አገልጋይ ሳሙኤል ሆይ መምጣትህ መልካም ነው በሽምግልናዬ ጊዜ ጌታ ወደእኔ ልኮሃልና አለው ወዲያውኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገባውና ከፀጉር በተሠራው ቀሚስና በቆቡ ላይ በቅናትና በአስኬማ ላይ ጸለየና ባረከው የአባቶቼ የአባ እንጦንዮስና የአባ መቃርዮስ ፈጣሪ ከአንተ ጋር ይኑር ልጄ ሳሙኤል ሆይ በችግርህ ሁሉ ረዳት ይሁንህ ብሎ እኒያን የምንኲስና ልብሶችን አለበሰው ።
ቅዱስ አጋቶንም ለአባ ሳሙኤል ትሕትናን አርምሞን አስተማረው አባ ሳሙኤልም ቅዱስና ቡሩክ የሆንክ አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ ከእኔ ጋርም ፍቅርን አድርግ አስተምረኝም እግዚአብሔርም የሚወደውን የምሠራ ያደርገኝ ዘንድ በከበረች ጸሎትህ አስበኝ ይለው ነበር ሁልጊዜ መንፈሳዊ የሆነ የምንኲስናን ሥርዓትም ሁሉ ተማረ ። ቅዱስ አባ ሳሙኤልም በሥራው ሁሉ ይራዳው ነበረ የሚያዝዘውንም ሁሉ እየሠራ ከአባ አጋቶን ጋር ሦስት ዓመት ኖረ ከዚህም በኋላ አባ አጋቶን አረፈ ።
አባ ሳሙኤልም ሰባት ሰባት ቀን እየጾመና ታላቅ ተጋድሎን እየታገለ ኖረ ከዚህም በኋላ በአስቄጠስ በአለች በከበረች በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ቅስና ተሾመ ።
ከጥቂት ቀኖች በኋላም የልዮንን ደብዳቤ ወደ አስቄጥስ ገዳም አምጥተው አነበቧት አረጋውያን መነኰሳትም በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ አባ ሳሙኤል መንፈሳዊ ቅናትን ቀና ከሰዎችም መካከል ተነሥቶ ያቺን ደብዳቤ ነጥቆ ቀደዳት እንዲህም አለ የቀናች የአባቶቻችንን ሃይማኖት የሚለውጥ ሁሉ የተወገዘ ነው ።
የንጉሥ መልክተኛም በአየ ጊዜ ቁጣን ተመላ አባ ሳሙኤልንም በብረት ዘንጎች እንዲደበዱቡት በክንዱም ሰቅለው ፊቱን እንዲጸፉት አዘዘ በጸፉትም ጊዜ አንዲት ዐይኑ ወለቀች ከዚህም በኋላ ከአስቄጥስ ገዳም እንዲአሳድዱት ሁለተኛ አዘዘ ።
ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ለአባ ሳሙኤል ተገለጸለትና ወደ ቀልሞን ተራራ ሒዶ በዚያ ይኖር ዘንድ አዘዘው ወዲያውኑ ሒዶ በዚያ ኖረ የቀናች ሃይማኖትንም ለሰዎች ሁሉ እያስተማረ ተቀመጠ ። ሊቀ ጳጳሳት የሆነው መለካዊ የእስክንድርያ መኰንን ምቆዝዝም ዜናውን ሰምቶ ወደ ቅዱስ አባ ሳሙኤል መጥቶ ታላቅ ግርፋትንም ገርፎ ከገዳሙ አሳደደው ።
ወደ ቀልሞን ገዳም ቤተክርስቲያንም ሒዶ በዚያ ተቀመጠ በዚያም ወራት የበርበር አረማውያን ወደዚያ መጡ ወደ አገራቸውም ሊወስዱት አባ ሳሙኤልን ያዙት ከእርሳቸውም እጅ ያድነው ዘንድ ክብር ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው በአንድ ግመል ላይም በጫኑት ጊዜ ያ ግመል መንቀሳቀስ አልቻለም ታላቅ ድብደባም ደበደቡት በተሳናቸውም ጊዜ ትተውት ሔዱ እርሱም ወደ ቀልሞን ገዳሙ ተመልሶ በምንኲስና ሥርዓት በመጠመድ በሁሉ ተጋድሎ እየተጋደለ ኖረ ።
ከዚህም በኋላ የበርበር አረማውያን ዳግመኛ መጡ ከእርሳቸውም የተነሣ ፈራ ሳሙኤል ሆይ አትፍራ ግን ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተህ ዝም በል ከእርሳቸው ጋር አትናገር እኔም አንዳያዩህ አደርጋቸዋለሁ የሚልን ቃል ሰማ በዚያንም ጊዜ የተመዘዙ ሰይፎቻቸውን ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገቡ እነርሱም እጅግ በሚያስፈራ ድምፃቸው ይጮኹ ነበር ቅዱስ ሳሚኤልም በቤተ መቅደስ ውስጥ ኃጢአትን ሲሠሩ ተመለከተ ስለ ድፍረታቸውም ዝም ማለት አልተቻለውም ተናገራቸው እንጂ እግዚአብሔርን መፍራት የሌላችሁ እናንተ ከሀድያን እግዚአብሔር እንደ ክፉ ሥራችሁ ይክፈላችሁ አላቸው ።
እነዚያ አረማውያንም አንተ ከዚህ ነበርክን እኛ ግን አላየንህም አሉት ከዚህም በኋላ ይዘው ከቤተ ክርስቲያኑ ምሰሶ ጋር አሠሩት ለመሞት እስቲቀርብም ገረፉት ከማሠሪያውም ሲፈቱት በግምባሩ ተደፋ ግመሎች እስካሉበትም ቦታ ጉተቱት ራሱንም በጫማ መቱት ከድብደባ ብዛት የተነሣ መንቀሳቀስ አልተቻለውም በግመልም ጫኑት ከሕመሙም ጽናት የተነሣ መሪር ልቅሶን የሚያለቅስ ሆነ ያም ግመል ወደርሱ ተመልሶ በሰው ቋንቋ እንዲህ ብሎ ተናገረው መደብደብህን መልካም አደረጉ ዝም በል አትናገር ያለህን የፈጣሪህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ተላለፍክ ሞት ይገባሃልና አለው አባ ሳሙኤልም ሲሰማ በእውነት በድያለሁ ነገር ግን እግዚአብሔር ቻይ ነውና መተላለፌን ይቅር ይበለኝ አለ ።
ከዚህም በኋላ ወደ አገራቸው ወሰዱት በዚያም የአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት የሆነውን ከእርሱ አስቀድሞ የማረኩትን አባ ዮሐንስን አገኘውና እርስበርሳቸው ተጽናኑ ። የአባ ሳሙኤልም ጌታው ፀሐይን እንዲአመልክ ያስገድደው ነበር እርሱ ግን ከቶ አልሰማውም ከዚህም በኋላ ከአንዲት ብላቴና ጋር በሰይጣን ምክር እግሩን አቆራኝቶ ግመሎችን እንዲጠብቁ ወደጫካ ሰደዳቸው ቅዱስ ሳሙኤል ከእርሷ ጋር በኃጢአት እንደ ሚወድቅና ዲያብሎስ በአስተማረውና በመከረው ሁሉ እንደሚታዘዝለት አስቧልና ።
በዚህም ሁሉ ቅዱስ ሳሙኤል ኃይልና ብርታት የሚጨመርለት ሁኖ ጌታው ታሞ ለሞት እስከ ቀረበ ድረስ በዚያ ኖረ ። አባ ሳሙኤልም በላዩ ጸለየና ከደዌው ፈወሰው ዜናውም በሀገሩ ሁሉ ተሰምቶ ደዌ ያለባቸው ሁሉ ወደርሱ የሚመጡ ሆኑ እርሱም በዘይቱ ላይ ጸልዮ ሲቀባቸው ወዲያውኑ ይድናሉ ጌታውም ይህን አይቶ እጅግ አደነቀ በአንተ ላይ ያደረግሁትን በደሌን ሁሉ ይቅር በለኝ ብሎ ሰገደለት እጅግም ወደደው አከበረውም የምትሻውንም ጠይቀኝ አደርግልሃለሁ አለው ። አባ ሳሙኤልም ወደ ሀገሬ እመለስ ዘንድ እሻለሁ አለው ጌታውም እጅ መንሻ ብዙ ገንዘብንና ግመሎችን አዘጋጅቶ በፍቅር በሰላም ሸኘው ።
ልጆቹ መነኰሳትም ወደርሱ ተሰበሰቡ አእላፋትም እስከሆኑ ድረስ እጅግ በዙ ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምም ተገልጻለት ይህ ቦታ ለዘላለም ማደሪያዬ ይሆናል አለችው ። ከዚያቺም ዕለት ወዲህ ወደዚህ ገዳም አረማውያን ተመልሰው አልመጡም ። ይህ አባት ሳሙኤልም ብዙ ድርሳናትን ደረሰ ስለ እስላሞችም መምጣት መንግሥትንም ስለመያዛቸው የክርስቲያን ወገኖችንም በቦታው ሁሉ እንደሚአሠቃዩአቸው ትንቢት ተናገረ እነርሱም የአጋር ልጆች ናቸው ።
ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ መነኰሳት ልጆቹን ሰበሰባቸውና በእግዚአብሔር ሕግ ጸንተው እንዲኖሩ እስከ መጨረሻዪቱም ሕቅታ ድረስ ስለ ቀናች ሃይማኖት እንዲጋደሉ አዘዛቸው ። ከዚህም በኋላ ጥቂት ታሞ በሰላም አረፈ ።
ስለርሱም እንዲህ ተባለ አንድ ቀን ከልጆቹ ውስጥ አንዱ አረፈ አባ ሳሙኤልም ወደርሱ በመጣ ጊዜ ነፍሱ ተመልሳለት በመነኰሳቱ ፊት ተነሣ የኃጥአንን ሥቃይ የጻድቃንንም ተድላ ደስታቸውን እንዳየ ተናግሮ ተመልሶ አረፈ ።

በዚችም ቀን ለእስሙናይን በስተምዕራብ ካለ አውራጃ ብጺር ከሚባል መንደር ቅዱሳን አባ ኤሲና እኅቱ ቴክላ በሰማዕትነት አረፉ ። ይህም አባ ኤሲ እጅግ ብዙ ገንዘብ ቦታዎችና በጎችም አሉት የበጎቹንም ጠጉር ሽያጭ ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋት አድርጎ ይሰጥ ነበር እርሱ እግዚአብሔርን እጅግ ይፈራ ነበርና እህቱ ቴክላም እንደርሱ እግዚአብሔርን የምትፈራ ናት።
የአባታቸውም ስም ኤልያስ የእናታቸውም ማርያም ይባላል እነርሱም ልጃቸውን ኤሲን የተወደድክ ልጃችን ሆይ በሕይወታችን ሳለን ልናጋባህና በአንተ ደስ እንዲለን እንወዳለን ብለው ለመኑት እርሱ ግን ይህን አልወደደም እንዲህም አላችው የተባረካችሁ አባቴና እናቴ ሆይ ጸልዩልኝ የምታዝዙኝም ሁሉ በደስታ እቀበላለሁ ስለጋብቻ ግን አትናገሩኝ አላደርገውምና ከዚያንም ጊዜ ወዲህ ስለ ጋብቻ ከቶ አልተናገሩትም እጅግ ይወዱት ነበርና ።
ከዚህም በኋላ ዕድሜው ሃያ ዓመት ሲሆነው አባቱ ሞተ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ እናቱ ሞተች ከሀዲ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም በዚያ ወራት ሰው ሁሉ ጣዖት እንዲሰግድ አዘዘ ቅዱስ ኤሲም የንግድ ዕቃውን ይሸጥ ዘንድ ወደ እስክንድርያ ሔደ ።
ለአባ ኤሲም በእስክንድርያ አገር ጳውሎስ የሚባል ወዳጅ አለው እርሱም ጽኑ በሆነ ደዌ ታሞ ነበር ከደዌውም እስከሚድን አባ ኤሲ በርሱ ዘንድ ተቀመጠ በዚያም ወራት በክርስቲያን ወገኖች ላይ ታላቅ መከራ ሁኖ ነበር ። እኒህ የከበሩ ኤሲና ወዳጁ ጳውሎስ ጣፋጭና መልካም የሆነውን መብል በገንዘባቸው እየገዙ በእስክንድርያ አገር ለሚኖሩ ቅዱሳን ይወስዳሉ እንዲሁም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የታሠሩትን ይጎበኙዋቸዋል ያረጋጓቸዋልም እንደ ባሮችም ያገለግሏቸው ነበር እኒህ ቅዱሳንም የሰማዕትነት አክሊልን እናንተ ትቀበሉ ዘንድ አላችሁ ብለው በእነርሱ ላይ ትንቢት ተናገሩ ።
በዚህም ወራት የህርማኖስ ልጅ ቅዱስ ፊቅጦርን ወደ እስክንድርያ አገር አመጡት አባ ኤሲና ወዳጁ ጳውሎስም በአዩት ጊዜ አደነቁ መንፈሳዊ ቅንአትንም ቀኑበት እርሱ የዚህን የኃላፊውን ዓለም መንግሥት ንቋልና ። ከዚህም በኋላ አባ ኤሲ ወደ መኰንኑ ቀርቦ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ በአለንጋዎችም ብዙ ግርፋትን ገረፉት ሕዋሳቱንም በሾተሎች ሠንጣጠቁ በሥጋውም የችቦ መብራቶችን አደረጉ በሰንሰለትም አሠሩት ሁለተኛም ነበልባሉ እጅግ ከፍ ከፍ እስከሚል በማንደጃ ውስጥ እሳትን አነደዱ ። አባ ኤሲንም ከውስጡ ጣሉት እርሱም እንዲህ ብሎ ጸለየ ጌትነት ገንዘብህ የሆነ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሠለስቱ ደቂቅን ከነደደ እሳት ዳንኤልን ከአንበሶች አፍ ምስክርህ ፊቅጦርንም ከውሽባ ቤት እሳት ያዳንካቸው አንተ ነህና እንደ እነርሱ አድነኝ የሚረዳኝንም ቸር መልአክ ላክልኝ ለአንተም ምስጋና ይሁን አሜን ።
ይህንንም ጸሎት በጸለየ ጊዜ እነሆ ሱርያል መልአክ ከሰማይ ወርዶ በአባ ኤሲ ቀኝ ቆመና ጻድቅ ሰው ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ከመከራህም ሁሉ እርሱ ያድንሃልና አትፍራ አለው ።
በዚያንም ጊዜ የእሳቱ ማንደጃ እንደ ቀዝቃዛ ጠል ሆነ መልአኩም የእቶኑን ግድግዳ ሠንጥቆ የከበረ አባ ኤሲን እጁን ይዞ ያለ ጥፋት በጤና አወጣው በዚያንም ጊዜ አባ ኤሲ ወደ መኰንኑ ሒዶ እንዲህ ብሎ ጮኸ አንተ ከከሀዲ ንጉሥህና ከረከሱ ጣዖቶችህ ጋር እፈር ።
ሕዝቡም ሕያው ሁኖ ያለ ጉዳት አባ ኤሲን በአዩት ጊዜ እጅግ አደነቁ በአንድ ቃልም እኛ በግልጥ ክርስቲያን ነን በቅዱስ አባ ኤሲ አምላክ እናምናለን ብለው ጮኹ መኰንኑም ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክልሊን ተቀበሉ ።
ከዚህም በኋላ አባ ኤሲን ወደ እሥር ቤት እንዲወስዱት መኰንኑ አዘዘ እንዳዘዛቸውም አደረጉ ። ለእህቱም ለቴክላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾላት ወንድሟን አባ ኤሲን ትጎበኘው ዘንድ ወደ እስክንድርያ አገር እንድትሔድ አዘዛት ያን ጊዜ ከእንዴናው ከተማ ተነሥታ ከባሕር ዳርቻ ደረሰች መንፈሳዊት መርከብም ተገለጸችላት ።
እመቤታችን ቅድስት ደንግል ማርያምም ከመጥምቁ ዮሐንስ እናት ከኤልሳቤጥ ጋር በውስጧ አለች አዝነውም ተመለከተቻቸውና እመቤቶቼ ሆይ የደረሰባችሁ ምንድን ነው አዝናችሁ አያለሁና አለቻቸው ቅድስት ኤልሳቤጥም በእርጅናዬ ወራት የወለድኩት አንድ ልጅ ነበረኝ ወስደው አረዱብኝ አለቻት እመቤታችንም ቅድስት ድንግል ማርያምም ለእኔም አንድ ልጅ ነበረኝ እርሱንም ወስደው ሰቅለው ገደሉብኝ አለቻት ። ቴክላም እመቤቶቼ ሆይ በእውነት ጽኑዕ ኀዘን አግኝቷችኋል አለቻቸው ይህንንም እየተነጋገሩ ወንድሟ አባ ኤሲ ወዳለበት አደረሷት የተገለጹላት እነማን እንደሆኑ አላወቀችም ነበር ።
አባ ኤሲም እኅቱ ቴክላን በአያት ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለው እርሷም ከእርሱ ጋር በሰማዕትነት ትሞት ዘንድ ተስማማች ።
ከዚህም በኋላ የሌሊቱ እኩሌታ በሆነ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ሱርያል ለአባ ኤሲ ተገለጸለት በብርሃናውያን ክንፎቹም ተሸክሞ ወደ ሰማይ አወጣው ኢየሩሳሌም ሰማያዊትንም አሳየው ። ቅዱሳንም ሁሉ ወጥተው ሰላምታ ሰጡት የሰው አንደበት ስለርሷ ሊናገር የማይቻለው ልዕልናዋንና ክብርዋን አሳየው በወርቅ በዕንቁ ያጌጡ አደባባዮቿንም ከፀሐይ ብርሃን ሰባት እጅ የሚበልጥ በውስጧ ያለውንም ብርሃን አሳየው ስለ ክብር ባለቤት ጌታችን ክርስቶስ ስም መከራ የተቀበሉ የጻድቃንንና የሰማዕታትን መኖሪያንም ዳግመኛ አሳየው ።
ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ሌላ ቦታ ወስደውና ታላቅ አዳራሽንም አሳየው በውስጡም በወርቅ በዕንቁ የተሸለሙ ሦስት መቶ ምሰሶዎች አሉ ዙፋኖችም በዕንቁ የተሸለሙ አሉ በዚያም አዳራሽ ውስጥ ሁለት መቶ ጭፍሮች ቁመው ነበር ። እነርሱም በወርቅ ዝናር የታጠቁና ያጌጡ ናቸው ከእርሳቸውም እያንዳንዱ ርዝመቱ ዐሥራ አምስት ዐሥራ አምስት ክንድ ይሆናል እኔም ኤሲ ያንን መልአክ ከዓለም ሰዎች ውስጥ በዚህ አዳራሽ አምሳል ማንም ሊሠራ የማይቻለው ይህ አዳራሽ ለማን ነው አልሁት።
መልአኩም እንዲህ አለኝ ወንድሜ አባ ኤሲ ሆይ የምድር ነገሥታት ሁሉም ከዓለሙ ሁሉ ጋር ቢሰበሰቡ ይህን አዳራሽ ከተሸከሙት ከእሊህ ከሦስት መቶ ምሰሶዎች የአንዱን ምሰሶ ሽያጭ ዋጋ አይችሉም አለኝ እኔም አይቼ አደነቅሁ እግዚአብሔርንም አመሰገንሁት ።
ሁለተኛም ይህ የከበረና ያማረ ታላቅ አዳራሽ ለማን ይሆናል አልሁት ያ መልአክም የሠራዊት አለቃ ለነበረ ለህርማኖስ ልጅ ለሰማዕቱ ፊቅጦር ይህ ሁሉ ተሰጠ ። እርሱ ምድራዊ መንግሥትን ሽልማቱንና ጌጡን ክብሩን ሁሉ ንቆ ትቶ መከራ መስቀሉን ተሸክሞ የክብር ባለቤት የሆነ ጌታውን ክርስቶስን ተከትሎታልና ስለዚህ ስለ ኃላፊው ምድራዊ መንግሥት ፈንታ የማይጠፋ መንግሥትን እግዚአብሔር ሰጠው አለኝ ።
ዳግመኛም እንዲህ ብዬ ጠየቅሁት እነዚህ ዙፋኖች እነዚህም ፍሬያቸው ያማረ ዕንጨቶች እሊህም የሚያበሩ አክሊሎች ምንድን ናቸው አልሁት ። እርሱም እንዲህ አለኝ አባ ኤሲ ሆይ እሊህ የዕረፍትና የተድላ ቦታዎች የቅዱሳን ሰማዕታትን መታሰቢያቸውን በምድር ላይ ለሚያደርጉት ሰዎች እግዚአብሔር ያዘጋጀላቸው ነው አባ ኤሲ ሆይ ስማ እኔ ላስረዳህ በሰማዕታት በስማቸው ቤተ ክርስቲያንን የሚሠራ ሰው ሁሉ ወይም ሥጋቸውን የገነዘ ወይም መሥዋዕትን የሰጠ መብራትንም ወይም የተራበ ያበላ የተራቆተም ያለበሰ ወይም ለቤተ ክርስቲያናቸው መጻሕፍትን ገዝቶ የሰጠ ወይም ገድላቸውንና ምስክርነታቸውን የጻፈ በችሎታው መጠን በመታሰቢያቸው ቀን በጎ ሥራ የሠራ ቀዝቃዛ የጽዋ ውኃ የሰጠ ዋጋውን አያጣም ብሎ ክብር ይግባውና ጌታችን በከበረ ወንጌል እንደ ተናገረ ።
ከሰማዕታት ላንዱ ወይም ከጻድቃን መታሰቢያቸውን ሲያደርግ የነበረ ሰው በሞተ ጊዜ ያ ሰማዕት ወይም ጻድቁ መጥቶ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ይሰግዳል ጌታዬና ፈጣሪዬ ሆይ በምድር መታሰቢያየን ስታደርግ ኑራለችና ይቺን ነፍስ ስጠኝ ይላል እርሷንም ይሰጠዋል እርሱም ተቀብሎ ወደዚህ ተድላ ደስታ ወደ አለበት ቦታ ያስገባታል ።
ያቺ ነፍስ እጅግ ኃጢአተኛ ከሆነች ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ቃል ይወጣል በመላእክት አለቃ በሚካኤልም አፍ እንዲህ ተብሎ ይነገራል ሁሉን የያዘ እግዚአብሔር ይቺን ነፍስ ለአንዲት ቅጽበት አንድ ጊዜ እንዲወረውሩዋት አዘዘ ። ከዚያም በኋላ ስለርሷ ለማለደ ለዚያ ሰማዕት ወይም ለጻድቁ ይስጡት ይላል እንደዚህም ለዚያ ሰማዕት ወይም ለጻድቁ ትሰጠዋለች እርሱም ተቀብሎ ይወስዳታል በመጠመቂያም ውስጥ ያጠምቋታል ያማሩ ልብሶችንም አልብሰው ከእነዚህ ከምታያቸው ዙፋኖች በአንዱ ዙፋን ላይ ያስቀምጧታል በማይጠፋ አክሊልም ይጋርዷታል ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ደስ እያላት ለዘላለሙ ትኖራለች ።
ከዚህም በኋላ ያ መልአክ ተሸክሞ ወደ እሥር ቤት መለሰኝ ሰላምታም ሰጥቶኝ ወደ ሰማይ ዐረገ እኔም ስለ ከበረ ስሙ ለሚጋደሉ ስለሚሰጥ ታላቅ ሀብት እጅግ አደነቅሁ ።
በነጋም ጊዜ ቅዱስ አባ ኤሲን ከእኅቱ ቴክላ ጋር ያመጡት ዘንድ መኰንኑ አዘዘ አምጥተውም በጽኑ ሥቃይ በተሽከርካሪዎች መሣሪያ በእሳት ቃጠሎ በብረት ችንካሮች የራሳቸውንም ቆዳ በመግፈፍ አሠቃዩአቸው ። እግዚአብሔርም ያለ ጉዳት በጤና አስነሣቸው ከሥቃያቻውም የተነሣ በሰለቸ ጊዜ ወደ ላይኛው ግብጽ ይወስዳቸው ዘንድ ለእንዴናው አገር መኰንን አሳልፎ ሰጣቸው ስምንት ቀንም ያህል እንደ ተጓዙ መርከቢቱ ከባሕሩ ዳር ቆመች መኰንኑም ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ ቅዱሳን አባ ኤሲና እኅቱ ቴክላም እጅግ ደስ አላቸው ጸሎታቸውንም ጸልየው በፈጸሙ ጊዜ በሰይፍ ራሶቻቸውን ቆረጧቸው ።
እግዚአብሔርም ስንጡፍ ከሚባል አገር ስሙ ኦሪ የሚባለውን ቄስ የቅዱሳንን ሥጋቸውን እንዲአነሣ አዘዘው እርሱም አንሥቶ ወስዶ አጥኖ በአማሩ ልብሶች ገነዛቸው የመከራውም ወራት እስቲፈጸም በንጹሕ ቦታ አኖራቸው ከእርሳቸውም ታላላቅ ተአምራት ተገለጡ ከእነርሱም ጋር በሰማዕትነት የሞቱ ቁጥራቸው አራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ናቸው ።

በዚችም ቀን በደማስቆ የተከበረ አባት አባ ዮሐንስ አረፈ ። ይህም ቅዱስ ከደማስቆ ከከበርቴዎቿና ከታላላቆቿ ወገን መንሱር ለሚባል ሰው ልጅ ነው በጥበብና በፈሪሀ እግዚአብሔርም አደገ የቀርሊ ፈላስፋ ከሆነ ቅልህፋ ከሚባል ቁልዝማዊ መነኰስ መምህሩ ዘንድ የፍልስፍና ትምህርትን ተማረ ትምርቱንም ሲጨርስ ቁልዝማዊ መምህሩን ተሰናብቶ ወደ ከበረ ሊቅ ሳበ ሰማዕት ገዳም ሔደ ። አባቱም በሞተ ጊዜ ለአገረ ገዢው ጸሐፊ ሆነ ግን ምሥጢሩን አይሠውርም ።
በዚያንም ወራት የከሀዲው ልዮን ልጅ ቁስጠንጢኖስ ተነሥቶ በአምላክ ፈቃድ ስለተሣሉ ሥዕሎች ጸብ በማንሣት አብያተ ክርስቲያናትን አወከ ይህም አባ ዮሐንስ የቤተክርስቲያን ሹመት ሳይኖረው በቀናች ሃይማኖት እያጸናቸው በአምላክ ፈቃድ ለተሣሉ ሥዕሎችም ስግደት እንደሚገባ መስክር ከቅዱሳት መጽሕፍት እያመጣ የሚጽፍና ወደ ምእመናን ሁሉ የሚልክ ሆነ ።
ከሀዲው ቈስጠንጢኖስም በሰማ ጊዜ ጥርሱን አፋጨ በዮሐንስ ብርዕ አምሳል የሚጽፍ ጸሐፊንም ፈልጎ በዮሐንስ ብርዕ አምሳያ እንዲህ ብሎ አጻፈ ከአንተ ዘንድ ያለ ዮሐንስ ከአንተ ጋር ተዋግቼ አገርህን እማርክ ዘንድ ይህን ደብዳቤ ጽፎ ላከልኝ ብሎ በወንጀል ለደማስቆ ገዥ ላከለት በሰማ ጊዜም እውነት ስለ መሰለው የሚጽፍባት ቀኝ እጁን ቆረጠው ።
አባ ዮሐንስም የተቆረጠች እጁን ይዞ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ሒዶ በብዙ ዕንባ እንዲህ ብሎ ለመናት እመቤቴ ሆይ ለሥዕልሽ መስገድ ስለሚገባ በተጣለሁ ጊዜ አይደለምን ይህ መቆረጥ የደረሰብኝ አሁንም በቸርነትሽ ፈውሺኝ አንቺ በሥራው ላይ ሁሉ ችሎታ አለሽና ይህንንም ብሎ ጥቂት አንቀላፋ ። በእንቅልፉም ሳለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገለጸችለትና እጁን እንደ ቀድሞው መለሰችለት በነቃም ጊዜ ድና አገኛት እግዚአብሔርንም አመሰገነው ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምንም አመሰገናት ።
ከዚህም በኋላ ወደ ገዳም ሒዶ መነኰሰ አበ ምኔቱም የምንኩስናን ሥርዓት ያስተምረው ዘንድ ለአንድ ሽማግሌ መንፈሳዊ አባት ሰጠው ሽማግሌውም ልጄ ዮሐንስ ሆይ አፍአዊት ከሆነች ትምርትህ ምንም ምን አታድርግ ግን ዝምታን ተማር አለው ከትሕትናውም ብዛት የተነሣ ሰይጣንን ድል ነሣው ።
ከዕለታትም በአንዲቷ ከመነኰሳቱ አንዱ ሽማግሌ ሞተ መነኰሳቱም ስለ ወንድማቸው ሙሾ እንዲአወጣለት አባ ዮሐንስን ለመኑት አባ ዮሐንስም ከሽማግሌው መምህሬ ትእዛዝ የተነሣ እኔ እፈራለሁ አላቸው ለማንም አይገለጥም አሉት ምልጃንም በአበዙበት ጊዜ ለሚሰማት ሁሉ የምታሳዝን ሙሾ ደረሰ መምህሩም አውቆ በእርሱ ላይ ተቆጣ ከበዓቱም አባረረው እርሱም አባ ዮሐንስ ወደ አረጋውያን ሁሉ ተማጠነ ሽማግሌውንም ይቅርታ እንዲአደርግ ግድ በአሉት ጊዜ የመነኰሳቱን የመፀዳጃ ቤት የጠረገ እንደሆነ እምረዋለሁ አለ አባ ዮሐንስም ሰምቶ መንፈሳዊ መምህሩ እንዳዘዘው አደረገ እርሱም ቅንነቱንና ትሩፋቱን አይቶ በደስታ ተቀብሎ ወደ ማደሪያው አስገባው ።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም አረጋዊ መምህሩን ድርሳናትን መድረስን እንዳይከለክለው አዘዘችው ከዚህም በኋላ ብዙ ድርሳናት ደረሰ የኢየሩሳሌሙም ሊቀ ጳጳሳት ቅስና ሾመው በአምላክ ፈቃድ ስለ ተሣሉ ሥዕሎች ክብር ስለ ቀናች ሃይማኖትም ነገሥታቱንና መኳንንቱን ሲዘልፋቸው ኖረ ወደ ሽምግልናም በደረሰ ጊዜ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ ።

በዚህችም ቀን የደብረ ድማሕ ገዳም አበምኔት ቅዱስ አባት ተክለ አልፋ አረፈ። ዳግመኛም በክርስቶስ የሚታመን የገብረ ማርያም ዕረፍቱ ነው እርሱም የሰማዕታትንና የጻድቃንን በየዕረፍታቸው ቀን ለየአንዳንዱ ርኁባንን በማጥገብ የተራቆቱትን በማልበስ መታሰቢያቸውን የሚያደርግ ነው ።
እንዲህም ባለ ሥራ ላይ እያለ ያንጊዜ እስላሞች ወደ ሸዋ አገር መጡ እርሱም ያማሩ ልብሶችን ለብሶ ወደ ቤተክርስቲያን ሔዶ ገብቶ ጸሎትን ጸለየ ሲጸልይም እስላሞች ወደርሱ መጥተው ራሱን በሰይፍ ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages