እርሱም በደቡብ ግብጽ በእስሙናይን አውራጃ ለሀገረ ቴርሳ አቅራቢያ ከሆኑ ከሐፂብ ተወላጆች ወገን ነው። ለአንድ ባለጸጋም በጅሮንድ ሆኖ ሳለ ስለ ንጽሕናውና ስለ ቅድስናው በሁሉ ዘንድ ተወዳጅ ሆ። የባለ ጸጋውም ሚስት አባ በአሚንን እጅግ የምትወደውና የምትተማመንበት ሆነች።
እርሱ ግን የዚህን ዓለም ፍጻሜ አሰበ፤ የባለጸጋውንም አገልግሎት ትቶ ወደ ገዳም ሒዶ መነኰሰ። ባለጸጋውም መሔዱን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ። ሚስቱንም ይዞ አባ በአሚን ወዳለበት በአንድነት ሔዱ። ወደ እርሳቸው እንዲመለስም ለመኑት፤ እንዲህም አሉት "ከአንተ እንለይ ዘንድ ከቶ አንችልም ስለዚህ አንተውህም" አሉት።
አባ በአሚንም "እኔ ራሴን ብፅዓት አድርጌ ለእግዚአብሔር ሰጥቻለሁ እኮን" አላቸው። ይህንንም ሲሰሙ ከእርሱ በመለየታቸው እያዘኑ ተትውት ተመለሱ።
ከዚህም በኋላ በአማረ ተጋድሎ ሁሉ ታላቅ ተጋድሎን በመጋደል ብዙ ዘመናት እግዚአብሔርን አገለገለው ። ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ሁኖ ደሙን ሊአፈስ ወዶ ወደ እንዴናው ከተማ ሔደ። ብዙዎች ምእመናንም ሲያሠቃዩአቸው አገኛቸው። እርሱም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመ፣ ጽኑ ሥቃይንም አሠቃዩት፣ ሥጋውን በእሳት ለበለቡ፣ ሕዋሳቱንም ሠነጣጥቀው ከመንኰራኲር ውስጥ ጨመሩት፣ ዳግመኛም በአጋሏቸው የብረት ዘንጎች አቃጠሉት። በዚህም ሁሉ ጸና ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ያለ ጉዳት በጤና ያስነሣው ነበር።
እንዲህም እየተሠቃየ ሳለ ጣዖት የሚመለክበት ወራት አለፈና ጻድቅ ቈስጠንጢኖስ ነገሠ። ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ዲዮቅልጥያኖስ ያሠራቸውን እሥረኞች ሁሉ እንዲፈቷቸው አዘዘ። ጌታችንም ለአባ በአሚን ተገለጠና ከሰማዕታት ጋር እንደቆጠረው አስረዳው።
ንጉሥ ቈስጠንጢኖስም ከእሳቸው ቡራኬ ሊቀበል ሽቶ ከውስጣቸው ሰባ ሁለት እሥረኞችን ወደርሱ ያመጡ ዘንድ አዘዘ። አባ ኖብ ከእርሳቸው ጋር በዚያ ነበረ ከእርሳቸውም አንዱ ይህ አባ በአሚን ነው። ከዚህም በኋላ ከእሥሙናይነረ ውጭ በሆነች ገዳም የሚኖር ሆነ። ጌታችንም ታላቅ ጸጋን ሰጥቶት በሽተኞችን ሁሉ የሚፈውሳቸው ሆነ ዜናውም በቦታው ሁሉ ተሰማ።
በዚያም ወራት የሮም ንጉሥ ሚስት የሆነች አንዲት ንግሥት ነበረች። እርሷም ከእርሷ ጋር ስለሚኖር የወንጌላዊውን ዮሐንስ የራእዩን መጽሐፍ ሁልጊዜ የሚፈራ ስለ አንድ ዲያቆን እጅግ የታመመች ናት። ከንጉሥ ሹሞች አንዱ በቀናበት ጊዜ ወደ ንጉሡ ሒዶ "ጌታዬ ንጉሥ ሆይ ዕወቅ ይህ ዲያቆን ዮሐንስ ሁልጊዜ የዮሐንስ የራእዩን መጽሐፍ በማንበብ እያመካኘ ከእመቤቴ ንግሥት ጋር ይተኛል" አለው።
ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ በዚያንም ጊዜ ተነሥቶ ንግሥቲቱ ወዳለችበት ቤተ መንግሥት ገባ ያንንም ዲያቆን በፊቷ ቁሞ የዮሐንስን የራእዩ መጽሐፍ ሲያነብ አገኘውና ከነመጽሐፉ ወስደው ዲያቆኑን ከባሕር እንዲአሠጥሙት አዘዘ። ሁለት ሰዎችም በታናሽ ጀልባ ጭነው ወስደው ከባሕር መካከል ወረወሩት። ወዲያውኑ ብርሃንን የለበሰ ሰው ከሰማይ ወርዶ ያንን ዲያቆን ከመጽሐፉ ጋር ነጥቆ ወስዶ ከአንዲት ደሴት ላይ አኖረው። እንዚያ ሁለት ሰዎች ሲያዩ ነበር እጅግም እያደነቁ ተመለሱ ያዩትንም ለንጉሡ አልነገሩትም።
ንግሥቲቱም በዲያቆኑ ላይ የተደረገውን በአየች ጊዜ እጅግ አዘነች። በእርሷም ደዌ ጸናባት ሆድዋም ቆስሎ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረች። ወደርሷም ብዙ ጥበበኞች ባለመድኃኒቶች መጥተው ነበር ግን ሊፈውሷት አልቻሉም። አንድ አዋቂ ሰውም እንዲህ ብሎ መከራት በግብጽ አገር ወደሚኖሩ ቅድሳን ብትሔጂ ከደዌሽ በተፈወስሽ ነበር። በዚያን ጊዜ ተነሣች ከእርሷም ጋር ብዙ ሠራዊት አለ። ወደ ግብጽ አገርም ደርሳ ገዳማቱንና አብያተ ክርስቲያንንም ሁሉ ዞረች ግን አልዳነችም።
ወደ እንዴናው ከተማም በደረሰች ጊዜ ስለ መምጣቷ የአገሩ መኳንንት አደነቁ። እርሷም ችግርዋን ሁሉ ነገረቻቸው። እነሱም ወደ ቅዱስ አባ በአሚን እንድትሔድ መከሩዋት። በመርከብም ተሳፍራ ወዲያውኑ ቅዱስ አባ በአሚን ወዳለበት ገዳም ደረሰች። "እነሆ ንግሥት ወዳንተ መጥታለች ከአንተም ልትባረክ ትሻለች" ብለው ነገሩት። እርሱም ከምድር ንግሥት ጋር ምን አለኝ ብሎ መውጣትን እምቢ አለ። መነኰሳትም ወደርሷ እንዲመጣ አጽንተው ለመኑትና ወጣ በአየችውም ጊዜ ከእግሩ በታች ወድቃ ሰገደችለት። እርሱም በዘይት ላይ ጸልዩ ቀባት በዚያንም ጊዜ ዳነች።
ቅዱስ አባ በአሚንም "ንጉሥ ከባሕር በአሠጠመው በዚያ ዲያቆን ምክንያት ይህ ሁሉ እንደደረሰብሽ ዕወቂ፤ እርሱ ግን በአንዲት ደሴት ውስጥ በሕይወት ይኖራል፤ የአቡቀለምሲስ ዮሐንስ የራእይ መጽሐፍም ከእርሱ ጋር አለ" አላት። ንግሥቲቱም ሰምታ እጅግ አደነቀች ደስ አላትም ስለዚያ ዲያቆን በሕይወት መኖርና እርሷም ፈውስ ስለማግኘቷ ለቅዱስ አባ በአሚንም እጅ መንሻ ብዙ ገንዘብ አቀረበችለት። ከንዋየ ቅዱሳት በቀር ምንም ምን ገንዘብ አልተቀበለም።
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔርን እያመሰገነች ወደ ሮሜ አገር ተመለሰች። በእርሷ ላይ የሆነውን ሁሉ፣ ወደ ባሕር ስለ አሠጠሙት ስለዚያ ዲያቆንም፣ እርሱም እስከ ዛሬ በአንዲት ደሴት ውስጥ በሕይወት እንዳለ ለንጉሡ ነገረችው። ንጉሡም ይህን ነገር ሰምቶ እጅግ አደነቀ ይፈልጉትም ዘንድ መልክተኞችን ላከ። በደሴትም ውስጥ በሕይወት አገኙት መጽሐፉም ከርሱ ጋር አለ። ተመልሰውም ለንጉሡ ነገሩት ሁለተኛም ወደርሱ እንዲመጣ እየማለደ ላከ። ከመልክተኞችም ጋር ወደ ንጉሡ መጣ። ንጉሡም በአየው ጊዜ ታላቅ ደስታ አደረገ ከእግሩ በታችም ወድቆ "በአንተ ላይ ስለአደረግሁት በደል ይቅር በለኝ" አለው እርሱም በአንድነት እግዚአብሔር ይቅር ይበለን አለ።
ከዚህም በኋላ ያ ዲያቆን በሮሜ ሀገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ። ያንንም የዮሐንስ አቡቀለምሲስ ራእይ ተረጐመው። ቅዱስ አባ በአሚንም በቀንና በሌሊት ያለማቋረጥ የሚጋደል ሆነ።
በአቅራቢያውም አንድ ደግ ኤጲስቆጶስ አለ። በአንዲት የሰማዕታት ገዳም ከምእመናን ጋር በዓልን ሲያደርግ አርዮሳውያንም ለራሳቸው ሐሰተኛ ኤጲስቆጶስ ይዘው ሕዝብን የሚያስቱ ሆኑ። የሀገሩም ኤጲስቆጶስ ወደ አባ በአሚን መጥቶ ስለ እሊህ ከሀድያን የደረሰበትን ኃዘኑን ሁሉ ነገረው። የሰማዕታትም በዓል በሆነ ጊዜ የእሊህን ከሀድያን ምክር እግዚአብሔር ይበትን ዘንድ ቅዱስ አባ በአሚን ከሕዝብ ጋር በመለመንና በመስገድ ጸለየ። ከዚህም በኋላ የሽመል በትር ያዘ ሕዝቡም ሁሉ እየአንዳዱ በትሮችን ይዘው ወደእነዚያ ከሀድያን ሔዱ። ከሀድያንም በአዩ ጊዜ ተበተኑ ወደዚያ ዳግመኛ አልተመለሱም እግዚአብሔር ምክራቸውን በትኖባቸዋልና።
ቅዱስ አባ በአሚንም ፈጽሞ በአረጀ ጊዜ የሞት ደዌን ታመመ። መነኰሳቱንም ሁሉ ሰብስቦ ዕድሜው እንደ ቀረበ ነገራቸውና አጽናናቸው። እነርሱም ከእርሱ ስለመለየታቸው አዘኑ ከዚህም በኋላ በፈጣሪው እግዚአብሔር እጅ ነፍሱን ሰጠ። መነኰሳቱም እንደሚገባ እያመሰገኑና እየዘመሩ መልካም አገናነዝን ገነዙት ሥጋው በእምነት ወደርሱ ለሚመጣ ሁሉ መጠጊያ ሆነ ወይም በቀናች ሃይማኖት ጸንቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒዶ በስሙ ለሚለምን ሁሉ የለመነው ይሆንለታል።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment