ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 11 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, April 2, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 11

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ዐሥራ አንድ በዚህች ዕለት ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ አባ_አሌፍ አረፈ፣ ተጋዳይ የሆነ ኤጲስቆጶስ አባ_ባስሊዖስ በማዕትነት አረፈ፣ በንጉሥ መክስምያኖስ ዘመን ቅዱስ_ቴዎቄጤኖስ በሰማዕትነት አረፈ።


መጋቢት ዐሥራ አንድ በዚህች ዕለት ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ አባ አሌፍ አረፈ፡፡ ተሰዓቱ ቅዱሳን በፈቃደ እግዚአብሔር ተሰባስበው በአንድ ላይ አገልግሎታቸውን ይፈጽሙ እንጂ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ናቸው፡፡ እነርሱም የቁስጥንጥንያው አባ ሊቃኖስ፣ የሀገረ ቁስያው (ኢጣሊያ) አባ ይምአታ፣ የአንጾኪያው (ሶሪያ) አባ ጽሕማ፣ የቂልቅያው (ግሪክ) አባ ጉባ፣ የእስያው አባ አፍጼ፣ የሮምያው ጰንጠሌዎን፣ የቂሣርያው አባ አሌፍ ናቸው፡፡
ሁሉም የነገሥታት ልጆች ቢሆኑም ዓለምን ፍጹም ንቀው በአባ ጳኩሚስ እጅ ከመነኮሱ በኋላ ሮምን ወደ ቀናች ሃይማኖት መልሰዋት ነበር፡፡ በሮም ሣሉ በምድረ አዜብ ብሔረ ኢትዮጵያ ስለሚኖሩ ሰዎች ዝና ስለ ነገሥታቶቻቸውም ቅድስናና ሀገሪቱም የእመቤታችን አሥራት መሆኗን ከመጻሕፍት ተረዱ፡፡ አባ ዘሚካኤልም ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቶቹ ጋር በሌሊት ወጥቶ ወደ ኢትዮጵያ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እየመራው መጥቶ አክሱም ደረሰ፡፡ በዚያም ጥቂት ጊዜ በመቀመጥ ተመልሶ ወደ ሮምያ ሄዶ ስለ ኢትዮጵያ ያየውንና የሰማውን በሙሉ ሁሉ ለሌሎቹ ቅዱሳን ሲነግራቸው እነርሱም ‹‹ይህችን ሄደን ማየት አለብን›› ተባበብለው ያላቸውን ሁሉ ይዘው ታቦቶቻቸውን፣ ካህናቶቻቸውን፣ ንዋየ ቅድሳቶቻቸውን፣ መጻሕፍቶቻቸውን ሁሉ ይዘው በዘሚካኤል መሪነት በመምጣት በ460 ዓ.ም ጳጳሱና ንጉሡ ካሉበት አክሱም ከተማ ገቡ፡፡
ተሰዓቱ ቅዱሳን ከአብርሃ ወአጽብሐ 6ኛ ንጉሥ በሚሆን በአልሜዳ ዘመነ መንግሥት ከአውሮፓና ከእስያ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አክሱም ከተማ ካረፉ በኋላ ሀገረ ስብከታቸውን ተከፋፍለው ገዳም እየገደሙ፣ በዓት እያበጁ፣ ከሣቴ ብርሃን አባ ሰላማ የመሠረተውን የክርስትና ሃይማኖት በከፍተኛ ሁኔታ አስፋፍተዋል፡፡ ገዳማትን አስፋፍተው የወንጌልን ብርሃን በሀገራችን ላይ አብርተዋል፡፡
ተሰዓቱ ቅዱሳን የነገሥታት ወገን ስለሆኑ በሮም ነግሦ የሚገኘውን ወንድማቸውን ይስሐቅን ላኩበት፡፡ ንጉሡ ይስሐቅ ለአባ ዘሚካኤል የእኅት ልጅ ነው፡፡ እርሱም መልእክቱ እንደደረሰው 7 ዓመት በሮም ከነገሠ በኋላ መንግሥቱን ትቶ በሌሊት ተነሥቶ በመውጣት ወደ ሀገራችን በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል መሪነት መጣና ከወንድሞቹ ጋር ተቀላቀለ፡፡ እነርሱም አመነኮሱትና ስሙን ገሪማ አሉት፡፡ ሁሉም በአንዲት የጸሎት ቤት በምንም ሳይለያዩ በአንድነት እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነው ለጸሎት ቆመው ውለው ያድሩ ነበር፡፡ እነዚህም እጅግ የከበሩ ቅዱሳን ድውያንን እየፈወሱና ሙታንን እያስነሱ እጅግ በጣም አስገራሚ የሆኑ ድንቅ ድንቅ ብዙ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡ ከሰንበት በቀር እህል የሚባል ነገር የማይቀምሱት እነዚህ ቅዱሳን ኢትዮጵያን በኪደተ እግራቸው ባርከዋታል፣ ጌጦቿ ሆነውላታል፣ በትምህርታቸው የእምነቷን መሠረት አጽንተውታል፣ የልዕልናዋንም ታሪክ ለዓለም መስክረውላታል፡፡
ለ12 ዓመታትም በፍጹም አንድነት አብረው ከተቀመጡ በኋላ ‹‹እርስ በራሳችን እየተያየን ብንኖር ተድላ ደስታ ይሆንብናልና ተለያይተን እንቀመጥ›› ብለው ተማከረው በተለያየ በዓት አባ ሊቃኖስ በደብረ ቁናጽል፣ አባ ጰንጠሌዎንም በእርሱ ትይዩ በሆነ ቦታ፣ አባ ገሪማ በደብረ መደራ፣ አባ ጽሕማ በደብረ ጸድያ፣ አባ ይምአታ በደብረ ገረዓልታ፣ አባ አፍጼ በደብረ ይሐ፣ አባ አሌፍ በደብረ አኅድአ፣ አባ አረጋዊ በደብረ ዳሞ መኖር ጀመሩ፡፡ በዋሻና በፍርኩታ ውስጥ በተራራም ላይ መኖር ጀመሩ፡፡ እናንተ የከበራችሁ ቅዱሳን ሆይ! የነገሥታት ልጆች ስትሆኑ ላባችሁን እያንጠፈጠፋችሁ በዱር በገደል መንከራተታችሁ፣ በቀበሮም ጉድጓድ መቀመጣችሁ፣ የምትለብሱት ሳታጡ በበርድ በቁር መራቆታችሁ ምንኛ ድንቅ ነው!? የምትበሉት የምትጠጡት ሳታጡ የነገሥታት ልጆች ስትሆኑ መራብ መጠማታችሁስ እንደምን ያለ ነው!?
አቡነ አሌፍ ኤርትራ ጠረፍ አካባቢ ወደሚገኘው በዓታቸው ወደ ደብረ አኅድአ በሄዱ ጊዜ በቦታው ላይ ታላቅ ዘንዶ ሰፍሮ ይኖር ነበር፡፡ ይህንንም ታላቅ ዘንዶ ቦታውን አስለቅቀው በዋሻ ውስጥ ገብተው ብዙ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ሕዝቡንም የከበረች ወንጌልን እያስተማሩ በተአምራት ከደዌ እየፈወሱ በጸሎታቸውም አጋንንትን እያስወጡ፣ ድውያንን እየፈወሱ፣ ዕውራንን እያበሩ፣ ሙታንን እያስነሡ ብዙ ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽመዋል፡፡ መላእክትም ዘወትር ባለመለየት አባ አሌፍን ይጎበኙዋቸው ነበር፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዘወትር እየተገለጠላቸው ይባርካቸውና ቃልኪዳን ይሰጣቸው ነበር፡፡
የአቡነ አሌፍ ገዳማቸው ከአዱዋ በስተሰሜን አቅጣጫ ወደ ኤርትራ ጠረፍ አቅራቢ ልዩ ስሙ ብህዛ በሚባለው ተራራማ ቦታ ላይ ይገኛል፡፡ የአባታችን በዓለ ዕረፍታቸው መጋቢት 11 ነው፡፡ ነገር ግን ቀደምት ቅዱሳን አባቶቻችን በደነገጉት መሠረት ይህ ወቅት ዐቢይ ጾም ላይ ስለሚውል በዚህ ወቅትም ምንም ዓይነት በዓል ማክበር ሥርዓት ስላልሆነ በጻድቁ ገዳም ውስጥ የአባታችን በዓላቸው በስፋት የሚከበረው ታህሳስ 11 ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ደግሞ ተጋዳይ የሆነ ኤጲስቆጶስ አባ ባስሊዖስ በማዕትነት አረፈ። ይህንንም ቅዱስ የኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳት አባ አርሞን ከሌሎች ኤጲስቆጶሳት ጋራ ሾመው። በታወቀና በተወሰነ ቦታ ላይ አይደለም። እምነት በሌላቸው በአረማውያን አገር ይሰብክ ዘንድ ላከው እንጂ።
ይህም ቅዱስ ወደ ከሀድያን አገር ገብቶ የከበረ ወንጌልን ሰበከ። እነርሱም እየደበደቡ በአገራቸው ሁሉ አዞሩት። ደግሞ ወደ ሠርዑና አገሮች ገብቶ የከበረ የወንጌል ትምህርትን ስተማረ። እኩሌቶቹ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ።
ያላመኑት እኩሌቶቹ ከሀድያን ግን አሳደዱት ከከተማው ውጭ ወጥቶ በዋሻ ውስጥ ተቀመጠ። የዚያች አገር ሰዎች እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ይመለሱ ዘንድ በአንድ ልጁም ያምኑ ዘንድ ስለዚያች አገር ሰዎች አዘውትሮ እግዚአብሔርን ማለደ።
በዚያንም ሰሞን ለእርሱ ለአባቱ አንድ ብቻውን የሆነ የመኰንኑ ልጅ ሞተ። አባቱም ታላቅ ኀዘንን አዘነ መኰንኑ አባቱም በሕልሙ ልጁን አየው። እርሱም በፊቱ ቁሞ አባቴ ሆይ እነሆ እኔ በታላቅ ጨለማ ውስጥ ነኝና ወደ ክርስቶስ ስለ እኔ ይጸልይ ዘንድ ኤጲስቆጶሱ አባ ባስሊዖስን ጠርተህ ለምነው ሲለው ነበር።
ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ደንግጦ ተነሣ ከእርሱም ጋራ የአገር ታላላቆችን ይዞ ወደ ቅዱስ ባስሊዖስ በዓት ሔደ። ከእርሱ ጋራም ወደ ከተማ ገብቶ ስለ ልጁ እንዲጸልይ ለመነው።
እርሱም ልመናውን ተቀብሎ ወደ ከተማ ገባ በመኰንኑ ልጅ መቃብር ላይም ጸለየ ያንጊዜም የመኰንኑ ልጅ ድኖ በሕዝብ ሁሉ ፊት ተነሣ መኰንኑ ሕዝቡም ሁሉ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ።
ከአገርም ሰዎች ብዙዎች አምነው የክርስትና ጥምቀትን በቅዱስ ባስሊዖስ እጅ ተጠመቁ በዚያቺም አገር ታላቅ የክርስቲያኖች ጉባኤ ሆነ።
ክፍዎች ሰዎችም ቀንተውበት በጠላትነት ተነሡበት በክርስቶስ ከማያምኑ ጋራ ተሰባስበው ወደ ሸንጓቸውም አደረሱት ይህን ቅዱስ ባስሊዖስን ታላቅ ግርፋትን ገረፉት ነፍሱንም በጌታችን እጅ እስከሰጠ ድረስ እያሠቃዩ በዚያች አገር አዋሉት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን በንጉሥ መክስምያኖስ ዘመን ቅዱስ ቴዎቄጤኖስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህ ቅዱስ አስቀድሞ ወታደር ነበር ትጥቁን በንጉሡን ፊት ጥሎ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ ከርሱም ጋራ ብፅዕት እስክንድራ አለች።
ንጉሡም ሰምቶ ተቆጣ ልብሱን አስወለቀው የሴቶች ልብስ አልብሰው ከሚፈትሉ ሴቶች ጋራ እንዲጨምሩት። ከዚያም የጋለ የብረት መንኰራኲር በላዩ አድርገው ዘቅዝቀው ቊልቊል እንዲሰቅሉት አዘዘ።
ሁለተኛም እንዲህ ብሎ አዘዘ የፈላ ቅጥራን የተመላ ወጭት አምጥታችሁ ወደ ጆሮው እስቲደርስ በራሱ ላይ ድፉበት ደግሞ ከተሰቀለበት አውርደው ከእሥረኛዋ እስክንድራ ጋር በፊቱ እንዲአቆሙት አዘዘ።
ከዚህም በኋላ ምላሱን እንዲቆርጡ አዘዘ በእሊህ ቅዱሳን በአንገቶቻቸው የሚካበዱ ደንጊያዎችን አሥረው በኤፍራጥስ ወንዝ ውስጥ እንዲጥሉአቸው አዘዘ። በዚያም ተጋድሎአቸውንና ምስክርነታቸውን ፈጸሙ ሥጋቸውንም ምእመናን አግኝተው በሥውር ቦታ ቀበሩት፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages