ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 12 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, April 2, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 12

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ዐሥራ ሁለት በዚች ዕለት እግዚአብሔር ቅዱስ_ሚካኤልን ወደ ጠንቋዩ በለዓም ላከው፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_ድሜጥሮስ ድንግልናው የተገለጠበት ነው፣ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ_ተስፋ_ጽዮን እረፍታቸው ነው፡፡


መጋቢት ዐሥራ ሁለት በዚች ዕለት እግዚአብሔር ቅዱስ ሚካኤልን ወደ ጠንቋዩ በለዓም ላከው።
"የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ። የሴፎር ልጅ ባላቅ እስራኤል በአሞራውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ አየ። ብዙም ነበረና ሞዓብ ከሕዝቡ እጅግ ፈራ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ሞዓብ ደነገጠ። ሞዓብም የምድያምን ሽማግሌዎች። በሬ የለመለመውን ሣር እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ይጨርሳል አላቸው። በዚያን ጊዜም የሴፎር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ ነበረ።
በወንዙ አጠገብ ባለችው በሕዝቡ ልጆች ምድር በፋቱራ ወደ ተቀመጠው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም። እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆም፥ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፈነ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል፤ አሁንም ይህ ሕዝብ ከእኔ ይበልጣልና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ና ርገምልኝ፤ አንተ የመረቅኸው ምሩቅ የረገምኸውም ርጉም እንደ ሆነ አውቃለሁና ብሎ ይጠሩት ዘንድ መልእክተኞቹን ላከ። የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም የምዋርቱን ዋጋ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃል ነገሩት። እርሱም። ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፥ እግዚአብሔርም እንደሚነግረኝ እመልስላችኋለሁ አላቸው፤ የሞዓብም አለቆች በበለዓም ዘንድ ተቀመጡ። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ። እነዚህ በአንተ ዘንድ ያሉ ሰዎች እነማን ናቸው? አለው። በለዓምም እግዚአብሔርን። የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ። እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድርን ፊት ሸፈነ፥ አሁንም ና እርሱንም ርገምልኝ፤ ምናልባት እወጋው አሳድደውም ዘንድ እችል እንደ ሆነ ብሎ ወደ እኔ ልኮአል አለው።
እግዚአብሔርም በለዓምን። ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትረግምም አለው። በለዓምም ሲነጋ ተነሥቶ የባላቅን አለቆች። ከእናንተ ጋር እሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አልፈቀደምና ወደ ምድራችሁ ሂዱ አላቸው። የሞዓብ አለቆች ተነሡ፥ ወደ ባላቅም መጥተው። በለዓም ከእኛ ጋር ይመጣ ዘንድ አልፈቀደም አሉት። ባላቅም ደግሞ ከፊተኞች የበዙና የከበሩ ሌሎችን አለቆች ሰደደ። ወደ በለዓምም መጥተው። የሴፎር ልጅ ባላቅ። ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የተናገርኸውንም ሁሉ አደርግልሃለሁና እባክህ፥ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ ምንም አይከልክልህ፤ እባክህ፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ አለ ብለው ነገሩት። በለዓምም መልሶ የባላቅን ባሪያዎች። ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ በትንሹ ወይም በትልቁ ቢሆን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ አሁንም እግዚአብሔር ደግሞ የሚነግረኝን አውቅ ዘንድ፥ እባካችሁ፥ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ አላቸው። እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ። ሰዎቹ ይጠሩህ ዘንድ መጥተው እንደ ሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ አለው።
በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ። እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሊቋቋመው በመንገድ ላይ ቆመ። እርሱም በአህያይቱ ላይ፥ ሁለቱም ሎሌዎቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ።
አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ ከመንገዱም ፈቀቅ ብላ ወደ እርሻው ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገድ ይመልሳት ዘንድ አህያይቱን መታት። የእግዚአብሔርም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ። አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አየች፥ ከበለዓምም በታች ተኛች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጣ፥ አህያይቱንም በበትሩ ደበደባት። እግዚአብሔርም የአህያይቱን አፍ ከፈተ፥ በለዓምንም። ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌብህ ነው? አለችው። በለዓምም አህያይቱን። ስላላገጥሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር አላት።
አህያይቱም በለዓምን። ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ እንዲህ አደርግ ዘንድ ልማዴ ነበረን? አለችው። እርሱም። እንዲህ አላደረግሽብኝም አላት። እግዚአብሔርም የበለዓምን ዓይኖች ከፈተ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደቀ። የእግዚአብሔርም መልአክ። አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና እቋቋምህ ዘንድ ወጥቼአለሁ፤ አህያይቱም አይታኝ ከፊቴ ሦስት ጊዜ ፈቀቅ አለች፤ ከፊቴስ ፈቀቅ ባላለች በእውነት አሁን አንተን በገደልሁህ፥ እርስዋንም ባዳንኋት ነበር አለው። በለዓምም የእግዚአብሔርን መልአክ። በድያለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ በፊቴ እንደቆምህብኝ አላወቅሁም፤ እንግዲህም አሁን አትወድድ እንደ ሆነ እመለሳለሁ አለው።
የእግዚአብሔርም መልአክ በለዓምን። ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምናገርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ አለው። በለዓምም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ። ባላቅም በለዓም እንደ መጣ በሰማ ጊዜ በአርኖን ዳር ዳርቻ በመጨረሻ ወዳለችው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊገናኘው ወጣ። ባላቅም በለዓምን። በውኑ አንተን ለመጥራት አልላክሁብህምን? ለምንስ ወደ እኔ አልመጣህም? በውኑ አንተን ለማክበር እኔ አልችልምን? አለው። በለዓምም ባላቅን። እነሆ፥ ወደ አንተ መጥቼአለሁ፤ በውኑ አሁን አንዳችን ነገር እናገር ዘንድ እችላለሁን? እግዚአብሔር በአፌ የሚያደርገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ አለው። በለዓምም ከባላቅ ጋር ሄደ፥ ወደ ቂርያት ሐጾትም መጡ። ባላቅም በሬዎችንና በጎችን አርዶ ወደ በለዓም ከእርሱም ጋር ወዳሉት አለቆች ላከ። በነጋውም ባላቅ በለዓምን ይዞ ወደ በኣል ኮረብታ መስገጃ አወጣው፤ በዚያም ሆኖ የሕዝቡን ዳርቻ አየ።
..... በለዓምም መርገሙን ወደ በረከት መለሰው።
(ሙሉ ታሪኩን ለማንበብ ኦሪት ዘኁልቁ ምዕራፍ ፳፪፣ ፳፫፣ ፳፬ እስከ ፍጻሜ)
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የከበረና የተመሰገነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ዐሥራ ሁለተኛ ተሿሚ የሆነ የድሜጥሮስ ድንግልናው የተገለጠበት ሆነ።
የመገለጡ ምክንያትም እንዲህ ነው ከእርሱ በፊት ሊቀ ጳጳሳት ለነበረው ለቅዱስ ዮልያኖስ መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገልጦለት አንተ ወደ ክብር ባለቤት ወደ ክርስቶስ ትሔዳለህ የወይን ዘለላ ይዞ ነገ ወደ አንተ የሚገባ ሰው ከአንተ በኋላ ሊቀ ጳጳስ ሊሆን የሚገባው እርሱ ነው አለው።
ማግስት በሆነ ጊዜም የከበረና የተመሰገነ ድሜጥሮስ የወይን ዘለላ ይዞ ወደ ከበረ ዮልያኖስ ዘንድ ገባ ቅዱስ ዮልያኖስም ያዘው ከእኔ በኋላ ሊቀ ጳጳሳታችሁ እነሆ ብሎ ለሕዝብ አስረከባቸው ስለእርሱም የእግዚአብሔር መልአክ እንደተገለጠለት ነገራቸው።
አባ ዮልያኖስም በአረፈ ጊዜ በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ከእርሱ በቀር ሚስት ኑራው የተሾመ የለም። ሰይጣንም በሰዎች ልቡና አደረ። በእርሱ ላይም በመናገር የሚአሙት ሆኑ።
ስለዚህም ነገር ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለቅዱስ ድሜጥሮስ ተገልጦ እንዲህ አለው ከሕዝቡ የሚአሙህ አሉና ከልባቸው ጥርጥርን ልታርቅ ይገባሃል። ከሚስትህም ጋር ያለውን የገድልህን ምሥጢር ልትገልጥላቸው ይገባሃል አንተ ራስህን አድነህ በአንተ ምክንያት ሌሎች ይጠፉ ዘንድ አይገባህም ቸር ጠባቂ ከሆንክስ ወገኖችህን ለማዳን ታገል።
ማግስት በሆነ ጊዜም ይህም መጋቢት ዐሥራ ሁለት ቀን ነው የቍርባንን ቅዳሴ ቀደሰ፡፡ ሕዝቡንም እንዲጠብቁ እንጂ ከቤተ ክርስቲያን እንዳይወጡ አዘዛቸው። ደግሞ እሳትን እንዲአነዱ አዘዛቸው ወደ ሴቶች መቆሚያም ልኮ ሚስቱን አስመጣት ከሥራው የተነሣ ሕዝቡ ያደንቁ ነበር ምን ሊሠራ እንደፈለገ ሕዝቡ አላወቁምና ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ ተነሥቶ ተንቀሳቀሰ ከእሳቱ መካከል ገብቶ በመቆም እሳቱ እየነደደ በውስጡ ጸለየ ከእሳቱም ፍም በእጁ ዘግኖ በልብሰ ተክህኖው ላይ አኖረ በእሳቱ ውስጥም ቁሞ ለረጅም ጊዜ ጸለየ በልብሰ ተክህኖው ውስጥ ያለ እሳትም አይቀጣጠልም።
ከዚህም በኋላ ሚስቱን ጠርቶ ያንን እሳት በመጐናጸፊያዋ ውስጥ ጨመረ ረጅም ጸሎትም ጸለየ እሳቱም ከልብሶቻቸው ምንም ምን አላቃጠለም። ሕዝቡም አድንቀው እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ሕዝቡም ይህን ሥራ በምን ምክንያት እንደሠራ ያስረዳቸው ዘንድ የከበረ ድሜጥሮስን ለመኑት።
እርሱም ከሚስቱ ጋራ ያለውን ገድሉን ገለጠላቸው ያለውዴታው እርሷም ጋብቻን ሳትሻ እንዳጋቡት እንዲህም አለ እነሆ በአንድነት እኛ ሠላሳ ስምንት ዓመት ስንኖር በጋብቻ ሥርዓት ከተገናኘንበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ አልጋ አንድ ልብስ ለብሰን እንተኛለን። ግን ወንዶች ሴቶችን በግብር እንደሚአውቋቸው ሴት እንደሆነች አላውቃትም።
በዚህ ሁሉ ዘመን በየሌሊቱ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ እየወረደ በክንፎቹ ይሸፍነናል። ይህንንም በዚህ ሁሉ ዘመን ከሰው ወገን ለማንም ከቶ አልገለጥኩም። ልገልጠውም ከቶ አልሻምና ግን እናንተ ከበደል ትድኑ ዘንድ እርሱ እግዚአብሔር አዘዘኝ እንጂ አላቸው። ከአዩትና ከሰሙት የተነሣ ሕዝቡ እጅግ አደነቁ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት እርሱን ስለማማታቸውም የበደሉትን በደል ይቅር ይላቸው ዘንድ እያለቀሱ ቅዱስ ድሜጥሮስን ለመኑት።
እርሱም ስሕተታቸውን ይቅር ብሎ በጎ ሥራን ከሚጠላ ከሰይጣን እንጂ ከእናንተ አይደለምና አትዘኑ አላቸው። ከዚህም በኋላ ባረካቸው ወደ ቤታቸውም ይገቡ ዘንድ በሰላም በፍቅር አሰናበታቸው ከሊቀ ጳጳሳቱ ከቅዱስ ድሜጥሮስ ከአዩት ተአምራት የተነሣ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደ ቤታቸው ገቡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች እለት አቡነ ተስፋ ጽዮን እረፍታቸው ነው፡፡ ጻድቁ ሀገራቸው ሸዋ ሲሆን የንጉሡ የዐፄ ዳዊት ልጅና የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ወንድም ናቸው፡፡ ስንክሳሩ ‹‹መናኔ መንግሥት ወብእስት›› በማለት ይጠራቸዋል፡፡ አቡነ ተስፋ ጽዮን በመጀመሪያ ‹‹በዓለም ነግሦ መኖርን አልፈልግም›› በማለት የዓለምን ጣዕም ንቀው በመተው ገዳም ገብተዋል፡፡ በታላቅ ተጋድሎ እየኖሩ አጠቃላይ የመርሐ ቤቴ ገዳማትን ሲመሩና ሲያስተዳድሩ ነበር፡፡
ጻድቁ በመስቀላቸው በመባረክ በሐምሌ ወር የዠማን ወንዝ አቆመው የተሻገሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ብዙ ሙታንን በማስነሣትና ታላላቅ ተአምራትን በማድረግ ነው ወንጌልን ሲሰብኩ የነበረው፡፡ አበታችን ከመላእክት ጋር በማዕድ አብረው ይቀመጡ የነበሩ ናቸው፡፡ በተለያየ ሀገር የሚኖሩ ቢሆኑም ከወለቃው አቡነ ዘአማኑኤል ጋር በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እየተገናኙ ስለ ገዳማት ይወያዩ ነበር፡፡ አቡነ ተስፋ ጽዮን በትግራይ ትልቅ ገዳም ያላቸው ሲሆን በደብረ በግዕና በዜና ማርቆስ ገዳም ደግሞ ቅዱስ ገድላቸው ይገኛል፡፡ ጻድቁ ከብዙ ተጋድሎ በኋላ ጌታችን ተገልጦላቸው ታላቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸው በዛሬዋ ዕለት መጋቢት 12 በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages