ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 13 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, April 2, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 13

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ዐሥራ ሦስት በዚህችም ቀን የታላቁ አባት የቅዱስ_መቃርስ እና የቅዱስ_መቃርዮስ_ዘእስክንድርያ የስደታቸውን መታሰቢያ ነው፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_ዲዮናስዮስ አረፈ፣ የከበሩ ቅዱሳን_አርባ_ሐራ ሰማይ በሰማዕትነት አረፉ፡፡


መጋቢት ዐሥራ ሦስት በዚህችም ቀን ኦርቶዶክሳውያን ሰዎች የታላቁ አባት የመቃርስን የእስክንድርያው የመቃርዮስን የስደታቸውን መታሰቢያ ያከብራሉ። ይህም በሮም መንግሥት ከወንድሙ ከዋልጥስ በኋላ በነገሠ ጊዜ በኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ላይ ስደትንና መከራን አመጣ።የረከሰ የማኒንና የከሀዲው አርዮስን እምነት ስለሚከተል ነው ለእስክንድርያም ሉክዮስን ሊቀ ጳጳሳት አድርጎ ሹሞ ሐዋርያዊ አትናቴዎስን አሳደደው።
ይህም ከሀዲ ሉክዮስ ታላቁን አባት አባ መቃሪን እስክንድርያዊውን አባት መቃርዮስን ፈልጎ በንጉሥ ትእዛዝ ወደርሱ ከገዳማቸው አስመጣቸው። ወደርሱም በደረሱ ጊዜ ለያይቶ በለሰለሰ አንደበት በመሸንገል ወደረከሰ የአርዮስ ሃይማኖት ይገቡ ዘንድ አግባባቸው። እነርሱ ግን ወደ ነገሩ አልተመለሱም ሳይፈሩትም መለሱለት በቅንነትና በትዕግሥትም መከሩት ገሠጹት እንጂ የአርዮስንም ሃይማኖት ብላሽነት የባህሉንም አስከፊነት ከቅዱሳት መጻሕፍት ለይተው አስረዱት።
በዚያን ጊዜም ተቆጣ ከቊስጥንጥንያ መካከል ወደምትርቅ ደሴት አጋዛቸው ከእስክንድርያም መርከብን የሚጠብቋቸውንም ወታደሮችን በእነርሱ ላይ በሚያደርጉት ሥራ ሁሉ አጫንቀው በብረት አሥረው ይወስዱአቸው ዘንድ አዘጋጁ። ወደዚች ደሴት በደረሱ ጊዜ በደሴቱ ንጉሥ ፊት አቆሙአቸው ንጉሡም ሰይጣንን የሚያመልክ የከፋ ሰው ነበር የደሴቱም ሰዎች አምላክ ነው ብለው እስቲ አምልኩትና እስቲሰግዱለት ድረስ በሥራዩ አስቷቸው ነበር።
እሊህ አባቶቻችንም ከስሕተቱ እንዲመለስ አስተማሩት ለመኑትም አልሰማቸውም ከብዙ ሥቃይ ጋር በወህኒ ቤት ዘጋባቸው እንጂ በጽኑዕ ሥቃይም አሠቃያቸው ጌታችንም ተገልጦ የሚያጸናቸውና የሚያስታግሣቸው ሆነላቸው። የክብር ባለቤት ጌታችንም ጽድቃቸውንና ትሩፋታቸውን ሊገልጥ በወደደ ጊዜ የንጉሡን ልጅ ሰይጣን ያዛት። አባትና እናቷም በታላቅ ኀዘን ላይ እስቲሆኑ አብዝቶ አሠቃያት በከተማ ውስጥም ሰይጣናት ተገልጠው መቃርስና ባልንጀራው ሆይ እኛ ከእናንተ እናንተ ከኛ ምን አላችሁ ከአገራችሁ ያሰደዳችሁን እያሉ ተገልጠው ይጮኹ ጀመር።በንጉሡ ልጅ ያደረውም ሰይጣን ንጉሥ ሆይ መቃርስና ባልንጀራው ካልመጡ ከልጅህ ላይ አልወጣም ብሎ ጮኸ ንጉሡና አብረውት ያሉ አደነቁ ወደ ንጉሡም ቅዱሳንን አመጡአቸው።
እሊህ ቅዱሳን መቃርስና ባልንጀራው ወደ ንጉሥ በደረሱ ጊዜ በንጉሡ ልጅ ያደረ ሰይጣን እንዳያሠቃዩት ለመነ። ንጉሡና አብረውት ያሉትም ስለ ሥራቸው ቅዱሳንን መረመሩአቸው፡፡ እነርሱም የሆነውን ሁሉ ነገሩአቸው ስለ ንጉሡም ልጅ ያድኑዋት ዘንድ ለመኑዋቸው። እነርሱም ንጉሡን ገሠጹት እንዲህም አሉት አንተ ሰው ስትሆን ለምን ራስህን አምላክ ታደርጋለህ ዓለምን የፈጠረ አምላክ ከሆንክ ራስህንና ልጅህን ማዳን ይገባህ ነበር። ያን ጊዜም ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ጸልየው ጋኔኑም በወጣ ጊዜ ስለ ክፉ ሥራቸው ንጉሡንና የዚያችን ደሴት ሰዎች ዘለፋቸው።
ንጉሡና በዚያ የተሰበሰቡት ይህን አይተው በእሊህ ቅዱሳን አምላክ እናምናለን ከእሊህ ቅዱሳን አምላክ ከእግዚአብሔር በቀር በሰማይና በምድር ሌላ አምላክ እንደሌለ ተረድተናልና እያሉ ጮኹ። የከበሩ አባቶቻችንም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን አሰተማሩአቸው እነርሱም በሽተኞቻቸውን ሁሉ ሰበሰቡ አባቶቻችንም በዘይት ላይ ጸልየው በመስቀል ምልክት አማትበው ቀብተው በሽተኞችን ሁሉ አጋንንት ያደሩባቸውንም ሁሉንም አዳኑአቸው እንዲሁም እያደረጉ እያስተማሩዋቸውም ብዙ ቀን ኖሩ።
ከዚህም በኋላ የሀገሩን ምኵራብ አስፈርሰው ቦታውን አጸዱ አነፁ ቦታውም እጅግ ስፋት ያለው መልካም ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን አሳነፁ ንጉሡም ስፍር ቁጥር የሌለው ወርቅና ብር የሐር ልብሶችንም ለእግዚአብሔር መቅደስ ለሚአሻውም ሁሉ አመጣ። የከበሩ አባቶቻችንም ጥበብ ያላቸው አንጣሪዎችን ሚዛኑ ለየአንዳንዱ ዘጠኝ ልጥር የሚሆን አሥራ ሁለት ጻህሎችን ሠርተው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንና የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ሥዕል የሁለቱንም የመላእክት አለቆች የሚካኤልንና የገብርኤልን ሥዕል በውስጡ እንዲሥሉ ደግሞ አሥራ ሁለት መንበሮችን ለመሠዊያ የሚፈለገውንም ሁሉ አሥራ ሁለት ጽዋዎችና አሥራ ሁለት ዕርፈ መስቀልም እያንዳንዱ ሦስት ሦስት ልጥር የሆኑ ሃያ አራት መስቀሎችን እንዲሠሩ ሦስቱንም የመቅደስ ግድግዳ እንዲሥሉ አዘዙ።
የቤተ ክርስቲያኒቱ የሕንፃዋ ሥራ ተፈጸመ። የተረፈውንም ገንዘብ ለድኆችና ለችግረኞች በተኑ። ጌታችን የተጠመቀባት ጥር ዐሥራ አንድ ቀን በሆነች ጊዜ ወደ ባሕር አጠገብ እንዲወርዱና እንዲሰበሰቡ የአገሩን ሰዎች አዘዙዋቸው። ከእስክንድርያም በተሰደዱ ጊዜ እግረ መንገዳቸውን የያዙትን የከበረ ሜሮንን አመጡ። ይህም ከሐዋርያዊ አትናቴዎስ ጊዜ ጀምሮ የተጠበቀ ሉክዮስም ያላገኘው ጌታችንም በዘመናት ሁሉ የጠበቀው ጥፋት ያላገኘው ነው።ይህ በመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ ሆኖአልና።
በዚያንም ጊዜ አባት መቃሪ በከበረ ሜሮን በጥልቁ ባሕር ላይ ባረከ ባሕሩም ከእሳት ኃይል የተነሣ በድስት እንደሚያፈሉት ውኃ የሚፈላ ሆነ ዘይቱና ሜሮኑም በውኃው ላይ ተንሳፈው እንደሚያበሩ ከዋክብት ሆኑ ከእርሳቸውም እንደ ፀሐይ የሆነ ታላቅ ብርሃን ታየ። ንጉሡና የተሰበሰቡት ሕዝብ አይተው ፈሩ። የክብር ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠ። አጥማቂው ዮሐንስና ቅዱሳን መላእክትም ውኃው በመከብርበትና በሚለወጥበት ጊዜ ተገለጡ። ሕዝቡም ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠመቁ ያንጊዜ ከሽቱ ሁሉ መዓዛው የሚጣፍጥ ሽታ ሸተተ።
በዚያን ጊዜም የከበሩ አባቶቻችን ይህን አይተው በምድር ላይ ወድቀው ሰገዱ በስግደታቸው እዚያው ዘገዩ። አባት መቃርስም ሰግዶ ሳለ ጌታችንን እንዲህ ሲል ለመነው። ጌታዬ እለምንሃለሁ ቸርነትህ ትድረሰኝ የዚች ታቦትና ንዋየ ቅድሳቷ ቡራኬ በአምላካዊት እጅህ እንዲሆን አለው።ጌታም እሺ በጎ ብሎ ሜሮኑን ከአባ መቃሪ እጅ ተቀብሎ ታቦቱንና ንዋየ ቅዱሳቱን አከበረ።
ከዚያም በኋላ አባት መቃርስን ሦስቱን ደርብ ትባርክ ዘንድ እኔ አዝሃለሁ እኔም ካንተ ጋራ አለሁ ይህንንም ንጹሕና ክቡር የሆነ አገልግሎት ባልንጀራህ አብሮህ ያገልግል። በመጀመሪያም የመካከለኛውን ደርብ በሥጋ በወለደችኝ በድንግል ማርያም ስም ለይተህ አክብር ደግሞ በቀኝ በኩል ያለውን በከበረ መስቀል ስም ለይተህ አክብር በግራ በኩል ያለውን ደርብ በስምህ ለይተህ አክብር በከሀዲ ሉክዮስ እጅ ስለ ስሜ በዚች ደሴት ውስጥ ደምህን አፍሰሃልና አለው።
እሊህም የተባረኩ አባቶች ጌታችን እንደ አዘዘ ሊሠሩ በጀመሩ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት በመዝሙር ሊያመሰግን ጀመረ መላእክትም በመልካም ቃላት በቋንቋቸው ያመሰግኑ ጀመር ሕዝቡም አድንቀው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
ዳግመኛም ጌታችን አባ መቃርስን መሥዋዕቱን ተሸክሞ በመሠዊያ ላይ ይቀድስ ዘንድ አዘዘው አባ መቃርስም ጌታችንን የሐዋርያት አለቃ አባታችን ጴጥሮስን እንዲቀድስ እዘዘው ይኽቺ ዕለት በከበረ ስምህ በዚች ደሴት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሥዋዕት የተሠዋባት ናትና አለው።
ጌታም ላንተ ይገባል አንተ በዚች ደሴት ዘርተሃልና እኔም አሳደግሁ በደቀ መዝ ሙሬ በጳውሎስ አድሬ የተናገርኩትን አላስተዋልክምን የዘራና የደከመ እርሱ አስቀድሞ ፍሬውን ይብላ ያልሁትን አለው።
አባት መቃርስም የቅዳሴውን ሥርዓት ከጌታ ተባርኮ በጀመረ ጊዜ ከእስክንድርያዊ መቃርዮስ ጋራ ይራዱት ዘንድ ጴጥሮስ በቀኙ ማርቆስ በግራው ሁሉም ሐዋርያት በዙሪያው ቆሙ።ጳውሎስና ዮሐንስም የየራሳቸውን መልእክት አነበቡ ሉቃስም የሐዋርያትን ሥራ አነበበ ዳዊትም መዝሙሩን ዘመረ ለስም አጠራሩ ምስጋና ገንዘቡ የሆነ ጌታችንም ወንጌሉን አነበበ።በነጭ ርግብ አምሳልም መንፈስ ቅዱስ በኅብስቱና በውይኑ ላይ ወርዶ የጌታችን ክርስቶስን ሥጋና ደም ወደመሆን ለወጣቸው።
አባት መቃርስም ወደ ጽዋው ጣቱን በአስገባ ጊዜ ጣቱ በደም ታለለ።የመላእክት ሠራዊት ሁሉ በመሠዊያው ላይ ክንፋቸውን ዘርግተው ይራዱት ነበር ሚካኤልና ገብርኤልም መጡ የመላእክት አንድነት ሁሉም በእርሱ በአባት መቃርስ አምሳል ሁነው እየተራዱት ለሕዝቡ የከበረ ሥጋውንና ደሙን አቀበለ። ከቁርባን ሥርዓት ፍጻሜ በኃላ ጌታችን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመቃርስ አምሳል ሁኖ ወንጌል በሚነበብበት አትሮንስ ላይ ተቀመጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ ይበራ ነበር ለሕዝቡም ቡራኬ ሰጥቶ ወደ መሠዊያው ተመለሰ ሐዋርያትም ከርሱጋራ።
ዳግመኛም ከሰባት ቀኖች በኃላ አባታችን መቃርስ ስለ ቤተ ክርስቲያን የሹመት ማዕርግ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ የክብር ባለቤት እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስም ተገልጦ በእኔ ዘንድ ለዚህ ታላቅ ክብር የምትገባ አንተ ነህና አለው።
ሽማግሌውም ሰምቶ አለቀሰ በእግዚአብሔርም ፊት ሰገደ አቤቱ በሲሐት ገዳም ወዳሉ መነኰሳት ልጆችህ ጊዜው ሲደርስ እመልስሃለሁ ከዚህ ከሥጋህ ሳትለይ ያልከኝን አስብ።ይህ ካልሆነ መቃራ የምንኲስናውን ሥራ ትቶ ፓትርያርክ ሆነ ይላሉ አለ። ጌታችንም የመረጥኩህ መቃርስ ሆይ እኔ የልብህን ፍላጎት ሁሉ እፍጽምልሃለሁ ግን ፓትርያርክ ትሾም ዘንድ ከልጆችህ የመረጥከውን አንድ አቅርብ አለው። ቅዱስ መቃርስም አቤቱ አንተ ልብ ያሰበውን የምታውቅ ነህ እኔ ግን ወደዚህ አንጥረኛ ሽማግሌ ሰው ተመለከትኩ። እርሱ በቀናች ሃይማኖት የጸና ከሴቶችም ጋር ግንኙነት የማያውቅ ነው አለው ጌታችንም አንተ እንዳልክ ደግ ነው አለ። ቅዱስ መቃርስም ያንን አንጠረኛ ጠርቶ ወደ ታቦተ ሕጉ አቀረበው ያን ጊዜም ወንጌላዊው ማርቆስ መጣ እጁንም በአንጠረኛው ራስ ላይ ጭኖ ዲቁና ሾመው። ደግሞ ቅስና ሾመው ከዚያም የሊቀ ጵጵስና ሹመት እስከ ሚፈጽም በየመዐርጉ ሾመው ስሙንም ዮሐንስ አለው የሰማይ ሠራዊትም ሁሉም የወንጌላዊ ማርቆስ አዲስ ተክል የሆነ ለመቃርስ ልጅ ለዮሐንስ ሊቀ ጵጵስና ይገባዋል ይገባዋል ይገባዋል እያሉ ሦስት ጊዜ ጮኹ በዚያ ያሉ ሕዝብም እሊህን ቃሎች ይሰሙ ነበር።
ጌታችንም የሊቀ ጳጳሳት የዮሐንስን ዓይነ ልቡናውን ገልጦለት በሚቻለው መጠን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አየው።ብዙ ቃላትንም ተናገረ ደግሞ ረቂቃን በሆኑ በሰማይ ሠራዊት ቤተ መቅደሱ ተመልቶ አየ የከበሩ ነቢያትና ሐዋርያትም በዚያ አሉ።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቁ አባ መቃራንና የእስክንድርያውን አባ መቃራን ጠራቸው እንዲህም አላቸው በምድር ሳሉ መታሰቢያችሁን የሚያደርጉ ሰዎች የተመሰገኑ ናቸው የዘላለም ሕይወትን ይወርሳሉና በራሴ እምላለሁ ስለ ስሜ የተቀበላችሁትን መከራ በትጋት የሚአስበውና የሚጽፈው የሚሰማው ሁሉ ያመሰግነኝ ዘንድ በቤተ ክርስቲያን የሚያነበው እኔ በጎ ነገርን ሁሉ እሰጠዋለሁ። ከበጎ ነገርም ምንም አላሳጣውም ከመከራውም ሁሉ አድነዋለሁ ኃጢአቱንም ሁሉ አስተሠርይለታለሁ። ከዚህ ዓለምም በሚለይለት ጊዜ ነፍሱን ወደ ዘላለም ተድላ ደስታ ይወስዱ ዘንድ እናንተ ወደም ታስቡትም መንግሥቴ ሊአስገቡት የምሕረት መላእክትን እልካለሁ።
በገዳም ወይም በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ወይም በአገር ውስጥ ይህ ዜናችሁ በሚነበብበት እኔ አድራለሁ በረከቴንና ሰላሜንም እስከ ዓለም ፍጻሜ በውስጥዋ አደርጋለሁ። ለዚህ ለስደታችሁ ዜና ተቃራኒ የሚሆን ባልተወለደ በተሻለው ነበር። በእውነት እነግራችኋላሁ በሰው ፊት እንደአመናችሁብኝ በሰማያት በአለው አባቴ ፊትና በከበሩ መላእክቶቼ ፊት አምንባችኋለሁ። አሁን ግን ወደ ሀገራችሁ የምትመለሱበት ጊዜ ደረሰ ይህንንም ብሎ ሰላምታ ሰጥቷቸው ወደ ሰማይ በክብር ዐረገ።
ከዚህ በኋላ ሕዝቡን ሁሉ ንጉሡንም ሰበሰቧቸው ወደ አገራቸውም እንደሚመለሱ ነገሩአቸው የክርስቶስንም ሕጉን ሁሉ እንዲጠብቁ ለሊቀ ጳጳሳቱ ዮሐንስም እንዲታዘዙ አዘዙአቸው።ከቀናች ሃይማኖት ወደ ቀኝም ቢሆን ወደ ግራም ፈቀቅ እንዳይሉ በብዙ አማፀኑአቸው አስጠነቀቋቸውም። ሕዝቡም ሰምተው ደነገጡ መሪር ልቅሶንም አለቀሱ ቅዱሳን አባቶቻችንም ከእሳቸው ጋራ በአንድነት አለቀሱ ከእዚህም በኋላ እየአንዳንዳቸውን ባረኳቸውና ተሰናበቷቸው።
ያን ጊዜም ከኪሩቤል ወገን የሆነ መልአክ መጣ አውጥቶም በክንፎቹ ተሸከማቸው ወደ እስክንድርያም አድርሶ በሊቀ ጳጳሳቱ ደጅ እሑድ ጥዋት አወረዳቸው።ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ጢሞቴዎስም ሰምቶ እጅግ ደስ አለው።ሁለተኛም በአያቸው ጊዜ አለቀሰ ሰገደላቸውም እነርሱም ሰገዱለት እርስ በርሳቸውም እጅ ተነሣሥተው ሰላምታ ተለዋወጡ። ጤንነታቸውንም ተነጋገሩ ደግሞም ልዩ የነበሩ የአሕዛብን ወደ እግዚአብሔር ስለመመለሳቸውና ስለ ተደረጉት ድንቆች ተአምራት ነገሩአቸው።ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ጢሞቴዎስና ይህን የሰሙ ሁሉም ሕዝብ አደነቁ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት አባቶቻቸንም በዚያ ስምንት ቀን ተቀመጡ።
ከዚህም በኋላ ያ መልአክ ተገልጦ በክንፎቹ ደግሞ ተሸከማቸው ወደ ደብረ ሲሐትም አደረሳቸው አንዱ ኪሩብም ከአየር ሁኖ የአባት መቃርስ ልጆች ሆይ አባታችሁ የመንፈስ ቅዱስን ፍሬዎች ተሸክሞ ከስደት ተመልሶ መጥቷልና ወጥታችሁ ተቀበሉ እያለ ጮኸ፡፡ ይህንንም በሰሙ ጊዜ ከታላላቆች እስከ ታናናሾች ወጡ ቁጥራቸውም አምሳ ሺህ መነኰሳት ሆኑ። ከውስጣቸውም በዚያን ጊዜ አባ ዮሐንስ ሐፂርና አባ ብሶይ አሉ የደረሰባቸውንም ሥቃይ በነገራቸው ጊዜ እጆቹንና እግሮቹን እየሳሙ መሪር ዕንባ አለቀሱ። ደግሞ ፊቱን ስለአዩ ደስ አላቸው እርሱም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ባረካቸው።
የክርስቶስ ወገን የሆናችሁ በዓለሙ ሁሉ የምትገኙ ምእመናን ሆይ በዘመናት ሁሉ በዓል እያደረጋችኋት በዚች ዕለት ደስ ሊላችሁ ይገባል።ይህም ለአምላካችን ክርስቶስ ስለ ስሙ ደማቸውን እንዳፈሰሱ እንደ ጴጥሮስና እንደ ጳውሎስ መታሰቢያ ለእሊህ ታጋዮች አባቶች ለመከራቸው መታሰቢያ እንዲሆን።
እሊህም ታላቁ አባ መቃርስና ባልንጀራው የእስክንድርያው አባ መቃርስ ናቸው በዚች በመጋቢት ወር በዐሥራ ሦስተኛ ቀን ሉክዮስ ከእስክንድርያ አስቀድመን ወደ አወሳናት ደሴት አጋዛቸው ደግሞ በዚሁ ቀን ተመልሰው ወደ እስክንድርያ ደረሱ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት ደግሞ በእስክንድርያ ሊቀ ጵጵስና ለተሾሙ አባቶች አሥራ አራተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ዲዮናስዮስ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ እምነት የሌላቸው አረማውያን ናቸው እርሱ ግን ብዙ ትምርቶችን ተማረ አባቱ በዘመድ የከበረ ስለነበረ ከታናሽነቱ ጀምሮ አስቦለት ለአረማውያን መምህራን መምህራቸው እስኪሆን ጥበብን ሁሉ አስተማረው።
በአንዲት ቦታ ተቀምጦ ሳለ አንዲት አሮጊት ክርስቲያን ሴት በፊቱ አለፈች። ከሐዋርያ ጳውሎስ መጽሐፍም አንድ ጥራዝ ይዛ ነበር እርሱም እስቲ ስጪኝ ልየው አላት እርሷም ሰጠችውና አነበባት በውስጧም ልዩ የሆነ ቃልንና የሚያሰደንቅ ዕውቀትን አገኘ በምን ያህል ትሸጪዋለሽ አላት።
በአንድ አላድ አለችው እርሱም ከዚህ መጽሐፍ የቀረ አለ ከአገኘሽ ሒደሽ አምጭልኝ አላት እርሷም ሒዳ ሌሎች ሦስት ጥራዞች አመጣች እርሱም አራት የወርቅ አላድ ሰጣት በአነበባቸውም ጊዜ መጽሐፉ ጐደሎ ሆኖ አገኘው።
ዳግመኛም ከዚህ መጽሐፍ የቀረ አለ ብታገኚ ሒደሽ ፈልጊ አላት እርሷም በአባቶቼ መጻሕፍት ውስጥ እሊህን ብቻ አገኘሁ ምሉውን የጳውሎስን መጽሐፍ ከፈልግህ ወደዚያች ቤተ ክርስቲያን ሒደህ ጠይቅ አለችው። እርሱም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ብፈልግ ከእርሷ ይሰጡኛልን አላት አዎን ይሰጡሃል አለችው።
ሒዶም ወደ ቤተ ክርስቲያን ጠየቀ እነርሱም የጠየቀውን መጽሐፍ ሰጡት አነበበውም በልቡም አጸናው።ያለ መጽሐፍም በቃሉ ያነበው ነበር በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አመነ።
ከዚህ በኋላ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ድሜጥሮስ ዘንድ ሒዶ ያጠምቀው ዘንድ ለመነው እርሱም ሕግና ሥርዓትን ትምህርትን ሁሉ አስተምሮ ከዚያ በኋላ አጠመቀው አባ ድሜጥሮስም ለቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ አስተማሪ አደረገው።
አባ ያሮክላ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ይህን አባት ዲዮናስዮስን በእስክንድርያ አገር ውስጥ በወንዶችም በሴቶችም ምእመናን መካከል እንዲፈርድላቸው እንደ ራሴ አድርጎ ሾመው በሊቀ ጵጵስናው ሥራ ላይ ሁሉ ሥልጣን ሰጠው።
አባ ያሮክላም በአረፈ ጊዜ ሕዝቡና ካህናት ሁሉም ተስማምተው በእስክንድርያ ላይ ይህን አባት ዲዮናስዮስን ሊቀ ጵጵስና ሾሙት መንጋውንም በበጎ አጠባበቅ ጠበቀ ነገር ግን በሹመቱ ዘመናት ብዙ መከራና ኀዘን አገኘው።
በዘመኑም ከሀዲው ዳኬዎስ ተነሥቶ ክርስቲያንን ከሚወድ ከፊልጶስ ጋራ ተዋጋ ድል አድርጎም ፊልጶስን ገደለው ።በእርሱ ፈንታም ነገሠ በክርስቶስ የሚያምኑትን ምእመናንን ሁሉ አሠቃያቸው። ከጳጳሳትና ከምእመናንም ብዙዎች ሰማዕታትን ገደላቸው ከፍርሃትና ከድንጋፄም የተነሣ ወደ በረሃ ወደ ገዳም ሸሽተው በዚያው የሞቱ አሉ የዚህም የዳኬዎስ ጭፍሮች ይህን አባት አግኝተው ያዙት ለብዙ ጊዜ አሠሩት።
ከዚህ በኋላ በአምላክ ፈቃድ ይህ ከሀዲ ጠፋ በእርሱም ፈንታ ግርላዎስ ነገሠ ከክርስቲያንም ልጆች መከራው ጸጥ አለ በዘመኑም ሰላም ሆነ። ከዚህ በኋላም ግርላዎስ ሞተ በእርሱ ፈንታም ዋርልዮስ ነገሠ እርሱም ሁለተኛ በክርስቲያን ወገኖች ላይ መከራ አሥነሣ የዚህ ከሀዲ ንጉሥም መኳንንቶች ይህን አባት ይዘው አሠሩት ታላቅ ሥቃይም አሠቃዩት እጅግም አስጨነቁት። ንጉሡም ይህ አባት ለጣዖት እንዲሰግድ ፈለገ እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት እኛስ ለክብር ባለቤት ለእግዚአብሔር አብ ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ለመንፈስ ቅዱስ አንዲት ስግደትን እንሰግዳለን። ንጉሡም ሰምቶ እጅግ ተቆጣ ሊአስፈራራውም በፊቱ ብዙ ሰዎችን ገደለ ቅዱሱ ግን አልፈራውም ወደ ደሴትም አጋዘው በዚያም ብዙ ዘመናት ኖረ።
ከዚህም በኋላ ከግዞት መልሶ አንተ በሥውር ለብቻህ እንደምትቀድስ ስለ አንተ ሰማሁ አለው ቅዱሱም አባት መልሶ እኛ ጸሎታችንን ምስጋናችንን ቅዳሴያችንን በቀንም በሌሊትም ቢሆን አንተውም ከእርሱ ጋርም ወደሆኑ ወገኖች ዘወር ብሎ ሒዱ ቀድሱ በሥጋ ከእናንተ የራቅሁ ብሆን በመንፈስ ከእናንተ ጋራ ነኝ አላቸው ።ንጉሡም ተቆጥቶ ወደ ስደት መለሰው።
እግዚአብሔርም በዚህ በከሀዲ ንጉሥ ላይ የበርበርን ሠራዊት አስነሳበት ከእርሳቸውም የተነሣ ፈራ ገደሉትም መንግሥቱንም ብልህና አዋቂ የሆነ ልጁ ወረሰ።አባቱ ያሠራቸውን ሁሉ ፈታቸው ከተሰደዱበትም መለሳቸው ወደ ሊቃነ ጳጳሳትና ወደ ኤጲስቆጶሳት ሁሉ ቤተ ክርስቲያናችሁን ክፈቱ መብራቶቻችሁንም አብሩ በእናንተ ላይ ምንም ምን የሚደርስባችሁ ክፉ ነገር የለም ብሎ ደብዳቤዎችን ጻፈ።
ይህም አባት ቀሪ ዘመኑን በጸጥታና በሰላም ኖረ ። ደግሞ በዚህ አባት በዲዮናስዮስ ዘመን ከዓረቢያ አገር በኵል የመጡ ነፍስ ከሥጋ ጋር ትሞታለች ከዚያም በትንሣኤ ቀን ትነሣለች በማለት የሳቱ ዝንጉዎች ሰዎች ተነሡ።በእነርሱ ላይም የኤጲስቆጶሳትን ጉባኤ ሰብስቦ አውግዞ ለያቸው ሌሎችም የረከሱ የአርዮስንና የሰባልዮስን እምነት ይዘው የተነሡ አሉ።
ይህም አባት ፈጽሞ በአረጀ ጊዜ ወልድን የካደ ሳምሳጢ ጳውሎስ ተነሥቶ አሳተ።በአንጾኪያም ኤጲስቆጶሳት በአንድነት ተሰበሰቡ ይህ አባት ግን ስለ እርጅናው አብሮ አልተሰበሰበም በውስጥዋ የቀናች ሃይማኖትን የምትገልጥ ሀብቱ የሆነ ጥበብን ዕውቀትን የተመላች መልካም ምክርን የያዘ ደብዳቤ ጽፎ ላከ ወደ በጎ ሽምግልናም ደርሶ ወደ ወደደው እግዚአብሔር ከዓለም ተለይቶ መሔድን አገኘ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን ልብጥያ በሚባል አገር የከበሩ አርባ ሐራ ሰማይ በሰማዕትነት አረፉ፡፡ እሊህ ቅዱሳንም በአልፊያኖስ ዘመን ተጋደሉ እርሱም ከንጉሠ ነገሥት ቈስጠንጢኖስ ከመኳንንቶቹ አንዱ ነው። ከአይሁድ አገሮችም በአንዱ ላይ አነገሠው ክርስቲያኖችንም እንዲጠብቃቸውና እንዲያከብራቸው አዝዞት ነበር።
እርሱ ግን ወደዚያ አገር በደረሰ ጊዜ ጣዖትን አመለከ ሰዎችንም ሁሉ ጣዖት እንዲአመልኩ አስገደዳቸው ብዙዎች ምእመናንም ተነሥተው እርሱንና የረከሱ ጣዖቶቹን ረገሙ። በዚያችም ሌሊት እሊህ አርባ ጭፍሮች ወደ መኰንኑ ደርሰው በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ምስክር ይሆኑ ዘንድ እርስ በርሳቸው ተስማሙ።
በእንቅልፋቸውም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ ለሰውነታቸው ብርታትን ሰጣቸው በጥዋትም ተነሥተው የጭፍራ አለቃ በሆነ በአግሪጎላዎስ ፊት ቁመው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመኑ። በላያቸውም ተቆጥቶ አስፈራራቸው እነርሱ ግን አልፈሩም በደንጊያም እንዲወግሩአቸው አዘዘ ። በአቅራቢያቸውም የውሽባ ቤት በአጠገቧ ያለ የውኃ ጒድጓድ ነበረች ከውርጭ ጽናትም የተነሣ ትረጋለች በውስጥዋም ይጥሏቸው ዘንድ መኰንኑ አዘዘ።
በውስጥዋም በጣሉአቸው ጊዜ ከውርጭ ጽናት የተነሣ ሕዋሳታቸው ተቆራረጠ ከእርሳቸውም አንዱ ፈራ ከዐዘቅቱም አውጡኝ ብሎ ወጣ ወደ ወሽባው ቤትም ገባ ፈጥኖም ሞተ ዋጋውንም አጠፋ የፈለገውንም አላገኘም። አርባ አክሊላትም ከሰማይ ሲወርዱ በሠላሳ ዘጠኙ ሰማዕታት ላይም ሲቀመጡ አንዱ አክሊልም በመልአኩ እጅ ተንጠልጥሎ ሲቀር ከወታደሮች ይህን ያየ ከዚያ ተነሥቶ በጌታ አምኖ ልብሶቹንም አውልቆ ቅዱሳን ወደአሉበት ወደ ዐዘቅቱ ወረደ በመልአኩ እጅ ተንጠልጥሎ የቀረውንም አክሊል ወሰደ።
እሊህም ጐልማሶች ሰማዕታት በዚያች ዐዘቅት በነበሩበት ጊዜ እናቶቻቸው ያጽናኗቸውና ያስታግሡአቸው ነበር። እነርሱም ብዙ ጊዜ ቆዩ እንጂ ቶሎ አልሞቱም። ከሀድያንም ጭኖቻቸውን ሊሰብሩ ፈለጉ ፈጥነው እንዲሞቱ እግዚአብሔርም ወዲያውኑ ነፍሳቸውን ወሰደ ጭኖቻቸውን መስበር አልተቻላቸውም።
ከዚህ በኋላም በእሳት ሥጋቸውን እንዲአቃጥሉ በተሽከረካሪም ጭነው ወስደው ወደ ባሕር እንዲጥሏቸው መኰንኑ ወታደሮችን አዘዘ። ሲጭኑአቸውም ያልሞተ ሕፃን አገኙና ተዉት እናቱም ከሠረገላው ውስጥ ልትጥለው ተሸክማው ሮጠች ወታደሮችም ስለአልሞተ ከለከሉአት ወዲያውኑ በጫንቃዋ ላይ ሙቶ ከቅዱሳን ጋር እንዲሆን ወደ ተሽከርካሪው ጣለችው። ወደ ስብስጥያ ከተማ ጭነው ወስደው በእሳት አቃጠሉአቸው ወደ ባሕርም ጣሉአቸው።
ከዚህም በኋላ በሦስተኛ ቀን ለስብስጥያ አገር ኤጲስቆጶስ ተገለጡለተ። እንዲህም አሉት ወደዕገሌ ወንዝ ሒድ ሥጋችንንም ታገኛለህና አሸክመህ አምጣው ኤጴስቆጶሱም ከካህናት ጋራ በሌሊት ተነሥቶ ወደ ወንዙ ሔዱ የቅዱሳንንም ሥጋቸውን በአንድ ቦታ ተሰብስቦ እንደ ከዋክብት እያበራ አገኙት ከእርሳቸውም አንድ እንኳን አልጐደለም በክብር ተሸክመው ወስደው በመልካም ቦታ በክብር አኖሩአቸው። ዜናቸውም በአራት ማእዘን ተሰማ መታሰቢያቸውንም አደረጉ በዓለም ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ታነፀላቸው ከሥጋቸውም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages