አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መጋቢት ዐሥራ አራት በዚህችም ቀን ቅዱስ_ቶማስ ሐዋርያ በአንዲት ሴት ላይ ተአምራትን አደረገ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የቅዱስ_ቄርሎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ፣ ከአረጋውያን ፍጹማን መነኰሳት ውስጥ አንዱ ቅዱስ_አባ_ባጥል አረፈ፣ ቅዱስ_አባት_አባ_ሲኖዳ በሰማዕትነት አረፈ፣ የከበሩ ቅዱሳን_አጋንዮስ_አውንድርዮስና_ብንድዮስ በሰማዕትነት አረፉ፡፡
መጋቢት ዐሥራ አራት በዚህችም ቀን ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ ሰባት ዓመት ያህል የጋኔን ግንኙነት በአስቸገራት በአንዲት ሴት ላይ ተአምራትን አደረገ። ሐዋርያ ቶማስንም የችው ጊዜ የክርስቶስ ሐዋርያው ሆይ እጅግ ከሚያሠቃየኝ ጠላት አድነኝ ብላ ወደርሱ ጮኸች።
እርሱም በምን ምክንያት አገኘሽ አላት እርሷም ከመታጠቢያ ከውሽባ ቤት ስወጣ እንደ ሰው ድው ድው እያደረገ በመታወክ መጣ ድምጡም ሰላላና ቀጪን ነው በሴትና በወንድ ሥራ ሁሉ ነይ እርስበርሳችን አንድ እንሁን አለኝ በተኛሁም ጊዜ በሌሊት መጥቶ ከእኔ ጋራ አንድ ሆነ ብሸሽም አይተወኝም መጥቶ ያሠቃየኛል እንጂ እኔም ከጸሎትህ የተነሣ አጋንንት እንደሚንቀጠቀጡ አውቃለሁና ጸልይልኝ አድነኝም አለችው።
ሐዋርያ ቶማስም ሰምቶ ጸለየ ጋኔኑንም ከእርሷ እንዲወጣ አዘዘው ያንጊዜም በእሳትና በጢስ አምሳል ከሴቲቱ ላይ ወጥቶ ተበተነ ከዚህ በኃላ በክርስቶስ መስቀል በላይዋ አማተበ ሥጋውንና ደሙንም አቀበላት ወደ ዘመዶቿም አሰናበታት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን በእስክንድርያ ለተሾሙ አባቶች ሰባ አምስተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የቅዱስ ቄርሎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። እርሱም በምግባሩ ፍጹም ዐዋቂ ሆነ ሀገሩም ፍዩም ይባላል በእርሷም ቅስና ተሹሞባት ነበር።
ከዚያም ለቆ ወደ አባ ፊቅጦር ገዳም ደረሰ እርሱም ከምስር ከተማ ውጭ የኢትዮጵያውያን ዐዘቅት የዐባይ ግድብ በአለበት ነው። በዚያም ታላቅ ገድልን እየተጋደለ ብዙ ዘመናትን ኖረ። ብዙ መጻሕፍትንም ተምሮ ትርጓሜያቸውንና ምሥጢራቸውን ጠንቅቆ ዐወቀ።
አሸናፊ ወደሚባለውም ንጉሥ አደባባይ ቀርቦ የእስላሞች ታላላቅ ሊቃውንቶቻቸውና ከምሁራኖቻቸው ውስጥ መምህሮቻቸው ተከራከሩት። ጠቃሚ የሆነ ዕውቀት የተመላበትን መልስ አገኙ የሚጠይቁትንም ሁሉ በመልካም አመላለስ ነገራቸው።
ከዚህ በኃላ የዕውቀቱና የቅድስናው ዜና በተሰማ ጊዜ ያለ ፈቃዱ ይዘው በእስክንድርያ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት መንጋውንም ጠበቀ በጸሎትና በቅዳሴ ያገለግሉ ዘንድ ለካህናት ሥርዓትንና መመሪያን ሠራ። ይህም አባት በሊቀ ጵጵስናው ሰባት ዓመታት ከዘጠኝ ወር ከዐሥር ቀኖች ኖረ። ከቀኑም በሦስት ሰዓት አረፈ በምስክርነት አደባባይም ተቀበረ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ከአረጋውያን ፍጹማን መነኰሳት ውስጥ አንዱ አባ ባጥል አረፈ። ይህም ቅዱስ ሰው አባ ዮሐኒ የተባለ አበምኔት በመነኰሳት ላይ ነገረ ሠሪን እንደ ሚቀበል በሰማ ጊዜ በዓቱን ትቶ ወደ እስክንድርያ መጥቶ የሴት አዳሪዎችንና የአመንዝራዎችን ሁሉ ስማቸውን ጻፈ።
ከኪራይ ሠራተኞችም ጋራ ሲሠራ ይውላል። ደመወዙን በተቀበለ ጊዜ የሽንብራ ቂጣ ግዝቶ ይበላል የቀረውንም ገንዘብ ይዞ ወደ አንዲቱ ሒዶ ይሰጣታል በዚች ቀን ከአንቺ ጋራ አድራለሁና ራስሽን ለእኔ አዘጋጂ ይላታል። ከኃጢአትም ሊጠብቃት ከእርስዋ ዘንድ ያድራል ሌሊቱን ሁሉ ተነሥቶ ሲጸልይና ሲሰግድ እግዚአብሔርንም ሲለምን ያድራል ሲነጋም ሥራውን ለማንም እንዳትገልጥ አምሏት ወደ ተግባሩ ይሔዳል።
በየዕለቱም ወደ አመንዝራዎቹ እየሔደ እንዲህ ያደርግ ነበር አንዲቱም ሴት ምሥጢሩን ገለጠች ጋኔንም ይዞ አሳበዳት። ሰዎችም ስለዚህ ክፉ ሽማግሌ ክፉ ሥራ የለበትም ብላ ዋሽታለችና እግዚአብሔር መልካም አደረገባት ተባባሉ። እርሷም እንዳናመነዝር ገንዘብ በመስጠት ከኃጢአት ይጠብቀናል እንጂ ነውር የለበትም ብላ ነበርና።
የቀሩት አመንዝራዎች በእርሷ ላይ የሆነውን በአዩ ጊዜ ደነገጡ እንደርሷም እንዳያብዱ እውነቷን ነው ማለትን ፈሩ። እርሱም ይችስ በእገሌ ዕለት ትጠብቀኛለች ይል ጀመረ ሰዎችም ሁሉ ያሙት ጀመር እርሱም እንደ ሰው ሁሉ ሥጋ የለኝምን ወይስ እግዚአብሔር መነኰሳትን ተቆጥቶ በፍትወት ተቃጥለው እንዲሞቱ ትቷቸዋልን አላቸው።
እነርሱም ልብስህን ለውጠህ ሚስት አግባ ይህ ይሻልሃልና አሉት። እርሱም አዎን ብወድ በሚስቴ እጠነቀቃለሁ በዚህም በክፉ አኗኗር እኖራለሁ እናንተ ግን ከእኔ ዘንድ ሒዱ ምን ትሻላችሁ በእኔ ላይ እግዚአብሔር ፈራጆች አድርጓችኃልን ይልቁንስ እናንተ እንዳይፈረድባችሁ ለራሳችሁ አስቡ ፈራጅ አንድ ነውና ዕለቲቱም አንዲት ናትና አላቸው ይህም ቅዱስ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አገኘ በሰው ዘንድ ግን የተናቀ ሁኖ ኖረ።
ከእርሱ ጥቅም የአገኙ አመንዝራዎችም ዝሙታቸውን ተው። ከእርሳቸውም ሕራዊ ጋብቻ ተጋብቶ የኖረ አለ ወደ ገዳምም ገብቶ መንኵሶ በጾም በጸሎት ተወስኖ የኖረ አለ። በአንዲት ዕለትም ከአንዲት አመንዝራ ቤት ሲወጣ ያቺን ሴት አስቀድሞ የለመዳት አንድ ሰው አገኘውና ይህ ሽማግሌ እስከ መቼ ድረስ በዚህ በክፉ ሥራ ይኖራል ብሎ ፊቱን በጥፊመታው።
ከዚህም በኃላ በአንዲት ቀን በበዓቱ ውስጥ ሰግዶ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጥቶ በቤቱም መድረክ የዚች አገር ሰዎች ጊዜው ሳይደርስ በማንም ላይ አትፍረዱ እንዳይፈረድባችሁ የሚልም ጽሑፍ ተጽፎ ተገኘ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ደግሞ ቅዱስ አባት አባ ሲኖዳ በሰማዕትነት አረፈ። እርሱም በግብጽ አገር ከብሕንሳ ከተማ ነው ወደ መክስምያኖስም ክርስቲያናዊ ሲኖዳ አማልክትን የማያመልክ ነው ብለው ነገር ሠሩበት። እርሱም አስቀርቦ ስለ ሃይማኖቱ ጠየቀው በንጉሡም ፊት በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ እርሱም ዕውነተኛ አምላክ እንደ ሆነም መሰከረ፡፡ መክስምያኖስም ይህን የከበረ አባ ሲኖዳን በምድር ላይ ዘርግተው በበትሮች እንዲደበድቡት አዘዘ። ዐጥንቶቹ እስቲሠነጠቁ ደሙም በምድር ላይ እንደ ውኃ እስቲፈስ እንዲሁ አደረጉበት።
ከዚህም በኃላ እግሩን ይዘው ጎትተው ወስደው ሽታው በሚከረፋ በጨለማ ወህኒ ቤት ጣሉት የእግዚአብሔርም መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ተገለጠለት። ቊስሎቹንም አድኖ ጤነኛ አደረገው አበረታውም በርታ አትፍራ ስለ መከራህም የክብር አክሊል ተዘጋጅቶልሃልና ደግሞም በጽኑዕ ሥቃይ ትሠቃይ ዘንድ አለህ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ እኔም ከአንተ ጋራ እኖራለሁ አለው ከዚያም ከእርሱ ተሠወረ።
በነጋ ጊዜም የነገሥታትን ትእዛዝ የሚተላለፍ ያንን ዐመፀኛ ሒዳችሁ እዩት ሙቶም ከሆነ ለውሾች ጣሉት ብሎ መክስምያኖስ ወታደሮቹን አዘዘ። ወደርሱም በደረሱ ጊዜ ቁሞ ሲጸልይ አግኝተውት ያለምንም ጥፋት ጤነኛ እንደሆነና በሥጋውም ውስጥ የሕማም ምልክት እንደሌለ እርሱም ከቶ ምንም ሥቃይ እንዳላገኘው እንደ ጤነኛና ደስ እንዳለው ሰው ተግቶ እንደሚጸልይ ስለርሱ ለንጉሡ ነገሩት።
ንጉሡም ወደርሱ አስመጣው ከሕይወቱም የተነሣ አደነቀ ልብሶቹንም አስወልቆ ያለጉዳት ጤነኛ እንደሆነ ሥጋውን አየ ደንግጦም ይህ ያየሁት ሥራይ ታላቅ ነው አለ። ከዚያም ዘቅዝቀው ሰቅለው ከበታቹ እሳትን እንዲአነዱ አዘዘ ይህንንም አደረጉበት ደግሞ በመንኰራኩር አሠቃዩት በአለንጋዎችም አብዝተው ገረፉት ደበደቡትም።
ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ቆርጠው ለውሾች እንዲጥሉት አዘዘ ውሾች ግን ፈጽሞ አልቀረቡትም ሌሊትም ሲሆን ምእመናን መጥተው ሥጋውን ወሰዱ በአዳዲሶች ልብሶችና በጣፋጭ ሽቶዎች ገነዙት በሣጥንም አድርገው ቀበሩት።ከሥጋውም ብዙዎች አስደናቂዎች ተአምራቶች ተደረጉ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ደግም የከበሩ አጋንዮስ አውንድርዮስና ብንድዮስ በሰማዕትነት አረፉ። እሊህም ቅዱሳን ከአባቶቻቸው ጀምሮ ክርስቲያኖች ናቸው አምላካዊ ትምህርትንም ሁሉየተማሩ ናቸው።
በእግዚአብሔርም ሕግ ጸንተው ሲኖሩ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አርሞስ መርጦ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ ሾማቸው ግን በታወቁ ቦታዎች ላይ አይደለም በብዙዎች አገሮች ውስጥ እንዲሰብኩ ላካቸው እንጂ። በሀገሮችም ያሉ ከሀዲያን ያዙአቸው ያለርኀራኄም አብዝተው ገረፉአቸው በደንጊያም ወገሩአቸው ነፍሳቸውንም በጌታችን እጅ ሰጡ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment