አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሚያዝያ ዐሥራ አምስት በዚህች ዕለት የመጥምቁ_የቅዱስ_ዮሐንስ ነፍሱ ከተቆረጠች ራሱ ጋራ በአየር ውስጥ እየዞረች ዐሥራ አምስት ዓመት ካስተማረች በኋላ ተለይታ የወጣችበት ሆነ፣ የከሃዲው ንጉሥ የዱድያኖስ ሚስት ቅድስት_እለእስክንድሪያ በሰማዕትነት ዐረፈች፣ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የአንዱ ሐዋርያ ቅዱስ_አጋቦስ መታሰቢያው ነው፣ የአገረ ሜራ ኤጲስቆጶስ በሆነ በቅዱስ_ኒቆላዎስ ስም ለያዕቆባውያን ወገን በግብጽ አገር ያለች ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት መታሰቢያ ሆነ።
ሚያዝያ ዐሥራ አምስት በዚህች ዕለት የመጥምቁ የቅዱስ ዮሐንስ ነፍሱ ከተቆረጠች ራሱ ጋራ በአየር ውስጥ እየዞረች ዐሥራ አምስት ዓመት ካስተማረች በኋላ ተለይታ የወጣችበት ሆነ፡፡ የመጥምቁ ዮሐንስ ቅድስት ነፍሱ ከተቆረጠች ራሱ ጋራ በአየር ውስጥ እየበረረች 15 ዓመት ስታስተምር ከኖረች በኋላ ጥቅምት 30 ቀን በዐረቢያ ምድር በግልጽ ታይታለች፡፡ ይኸውም የሆነው እንዲህ ነው፡- ሄሮድያዳ ልጅ ርጉም የሆነ ንጉሥ ሄሮድስን በዘፈኗ በጣም አድርጋ አስደሰተችው እርሱም በተራው ሊያስደስታት ፈለገና እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን የለመነችውን ይሰጣት ዘንድ በሕዝቦቹና በመኳንንቱ ሁሉ ፊት እንዳይከዳት በፅኑ ቃልኪዳን ማለላት፡፡ እርሱም አስቀድሞ ‹‹የፈለግሽውን ጠይቂኝ፣ የመንግሥቴንም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሻለሁ ምን ላድርግልሽ?›› እያለ በመሐላ ባላት ጊዜ በእናቷ ምክር የዮሐንስን አንገት ቆርጦ ይሰጣት ዘንድ ለመነችው፡፡ እርሱም ስለማሐላው የዮሐንስን አንገት እንድትቆረጥ አደረገ፡፡ በመጀመሪያም የሄሮድስ ወታደሮች ሠይፍ ይዘው የዮሐንስን አንገት ይቆርጡ ዘንድ ወደ መኅኒ ቤት ሲሄዱ ቅዱስ ዮሐንስም የሄሮድስ ጭፍሮች ሊገድሉት እንደመጡ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ስላወቀ ከጨለማው ቤት ውስጥ አንገቱን በመስኮት አውጥቶ እንደሚመቻቸው አድርጎ ጠበቃቸው፡፡ የንጉሡም ጭፍሮች የመጥምቁን ራስ በወጪት አድርገው ለንጉሣቸው ሄሮድስ ሰጡት፡፡ ሄሮድስም ለሄሮድያዳ ልጅ ሰጣት፡፡ የመጥምቁ ዮሐንስ ግን በወጪት ላይ ሆና ሕዝቦቹና የመንግሥቱ ታላላቅ ሰዎች እየሰሟት በየመኳንንቱ ፊት ንጉሥ ሄሮድስን ‹‹የወንድምህን የፊሊጶስን ሚስት ማግባት አይገባህም›› እያለች መጀመሪያ ትዘልፈው እንደነበረው ሁሉ አሁንም ዘለፈችው፡፡ መዓዛዋም እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነበር፣ ዐይኖቹም እንደፀሐይ ያበሩ ነበር፡፡
የሄሮድያዳም ልጅ የመጥምቁን ራስ ወስዳ ለእናቷ ልትሰጣት ስትል ዐይኖቹ እንደፀሐይ ሲያበሩ ብታየው ‹‹ንጉሡን አትፈራውምን?›› በማለት ተቆጣች፡፡ በመቀጠልም ‹‹እነዚህን ዐይኖቹን በወስፌ እያወጣሁ እጥላቸዋለሁ፣ ምላሱንም ደግመኛ እንዳይገሥጽ ቆርጨ እጥላቸዋለሁ›› በማለት ፊቱን በጥፊ ለመምታት እጇን ስታነሣ ያንጊዜ የዮሐንስ ራስ ክንፍ አውጥታ በረረች፡፡ በአየር ላይ ሳለችም ዳግመኛ ‹‹የተረገምሽ ሄሮድያዳ የባልሽን ወንድም ሄሮድስን ማግባት አይገባሽም፣ ቀድሞ የምዘልፍሽ አሁንም የምዘልፍሽ እኔ ነኝ›› እያለች የዮሐንስ ራስ የቤቱን ጣሪያ ሰንጥቃ እንደንሥር በአየር በራ ሄደች፡፡
ከዚህም በኋላ ለጥፊ የዘረጋቻቸው የሄሮድያዳ እጆቿ ከትከሻዋ እየተቆረጡ መሬት ላይ ወደቁ፤ እውነቷንም መሬት አፏን ከፍታ ዋጠቻት፡፡ ዘፋኟ ልጇም አብዳ የቤተ መንግሥቱን ዕቃ ሁሉ መሰባበር ጀመረች፡፡ የንጉሡ አንዱ ጭፍራም የሄሮድያዳን በእሳት እንደተለበለበ የግንድ እሳት የመሰለና የተቆረጠ እጇን አምጥቶ ለሄድሮስ ሰጠውና የሆነውን ነገረው፡፡ ንጉሡም ነገሩ እውነት መሆኑን ሄዶ ባየ ጊዜ በሀፍረት እጅግ ተሸማቀቀ፡፡ ዘፍና በማስደሰት የዮሐንስን ራስ እንዲያስቆርጠው ያደረገችው የሄሮድያዳ ሴት ልጅም አብዳ በቤተ መንግሥቱ ስትለፈልፍ አገኛት፡፡ ሄሮድስም መኳንንቶቹን ‹‹በቤተ መንግሥቴ የተደረገውን ይህን ነገር ለማንም አትንገሩ›› ብሎ አማላቸው ነገር ግን ያበደችው የሄሮድያዳ ሴት ልጅ ራሷ ሄዳ ሄሮድስን ‹‹የወንድምህን የፊሊጶስን ሚስት ማግባት ፈጽሞ አይገባህም›› እያለች በመኳንንቶቹ ፊት ገሠጸችው፡፡ ንጉሥ ሄሮድስም ይህን ቃል ከእርሷ በሰማ ጊዜ እጅግ ተናደደና ‹‹ቀደሞ ያልሆነ ሥራ ታሠራ በኋላ ደግሞ ምሥጢር ታወጣ ንሣ በሰይፍ ቁረጣት›› ብሎ አንገቷን በሰይፍ አስቆረጣት፡፡ ሥጋዋንም ዓሣ አንበሪ ተቀብሎ ዋጣት፡፡ ሄሮድም የወንደሙን ሚስት ሲያገባ አስቀድሞ አግብቷት የነበረችውን ሚስቱን በግፍ አባሯት ነበር፡፡ እርሷም ይህንን ሄሮድስ ያደረሰባትን ግፍ ለአባቷ አርጣ ብትነግረው አባቷ ብዙ ጦር ሰብስቦ መጥቶ ምድረ ገሊላን በኃይል አፈራረሳት፡፡ የበላዩ ንጉሥ ቄሳርም የገሊላን መፍረስና መውድም ሲሰማ ምክንያቱን ቢጠይቅ ሄሮደስ ባደረገው ግፍ ምክንያት መሆኑን ነገሩት፡፡ ቄሳርም ሄሮድስን ከሥልጣኑ ሽሮ አጋዘውና በወህኒ ጣለው፡፡ ሄሮድስም በወህኒ ቤት ሳለ አብዶ ራሱን ስቶ የገዛ አካሉን እየነጨ እየበላ ቷ ብሎ ፈንድቶ ተልቶ ሸቶ እጅግ ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡
የኃጢአት መጨረሻው ይህ ነው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስን ራስ ካስቆረጡ በኋላ ሦስቱም የደረሰባቸውን ተመልከቱ፡፡ በሥጋም በነፍስም ጽኑ ቅጣት አገኛቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በምድርም በመንግሥተ ሰማያትም ለዘለዓለም ከብሮ ይኖራል፡፡ የተቀደሰች ራሱም በሰማይ ላይ እየበረረች ወደ ደብረ ዘይት ሄደች፡፡ ጌታችንም በደብረ ዘይት እያስተማረ ሳለ ወደ እርሱ ሄደችና ከእግሩ በታች ወድቃ ሰገደች፡፡ ጌታችንም የዮሐንስን ራሱ በእጆቹ አቅፎ ይዙ በመለኮት አፉ አክብሮ ሰማት፡፡ እመቤታችንም የዮሐንስን ራስ በጌታን እጅ ላይ ሆና ባየቻት ጊዜ በሀዘን እጅግ አምርራ አለቀሰች፡፡ ጌታችንም ቅድስት እናቱን ካረጋጋት በኋላ ‹‹ክብርት እናቴ ሆይ! አታልቅሺ እነሆ ዮሐንስ ሙቶ እንዳየሽው እኔም ደግሞ እሞታለሁኝ እገደላለሁኝ፡፡ ነገር ግን የእኔ ሞት እንደ ዮሐንስ አንገቴን በሰይፍ ተቆርጨ አይደለም እጅና እግሬን በብረት ተቸንክሬ በመስቀል ላይ ተሰቅዬ ነው፣ ቀኝ ጎኔንም በጦር እወጋለሁ ደምና ውኃም ከጎኔ ይፈሳል›› አላት፡፡ ሌላም ብዙ ምሥጢርን ነገራትና አጽናንቶ አረጋጋት፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ራስ መለስ ብሎ እንዲህ በማለት ሥልጣን ሰጣት፡- ‹‹እነሆ መንፈስሽን በራስሽ ውስጥ አድርጌልሻለሁ በሰማይም የምትበሪበት እንደ ንሥር ክንፍ ሰጥቼሻለሁና እንደንስር በሰማይ እየበረርሽ በዓለም ሁሉ እየዞርሽ የሄሮድስንና የሄሮድያዳን ኃጢአት ግለጭባቸው፤ እስከ 15 ዓመት ድረስ ገቢረ ተአምራት የምታደርጊበት ኃይሌን መንፈሴን በእራስሽ ውስጥ አድርጌልሻለሁ›› አላት፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ዮሐንስን ‹‹እኔም ከ3 ዓመት በኋላ ለአዳም የሰጠሁትን ተስፋ ፈጽሜ በሞቴ ወደ ሲኦል ወርጄ ነፍሳትን ከዲያብሎስ እጅ ማርኬ በ3ኛው ቀን ከሙታን ተለይቼ ተነሥቼ ወደ ባሕርይ ክብሬ ተመልሼ ወደ ሰማይ አርጌ ባባቴ ቀኝ በተቀመጥኩኝ ጊዜ ከ15 ዓመት በኋላ ርጉም ሄሮድስ ካስፈጃቸው ከትንንሾቹ ሕፃናት ጋራ ትሆን ዘንድ በአባቴ ፈቃድ እራስህን ተሸክመው ወደ አባትህ ወደ ዘካርያስ ያመጧት ዘንድ እኔ መላእክትን አዛቸዋለሁ፡፡ ዛሬ ግን ነፍስህን በእኔ ቀኝ ባባትህ በዘካርያስ አጠገብ አኑሬያታለሁ መንፈስህንም እስከ 15 ዓመት በእራስህ ውስጥ እንድትኖር አዝዣታለሁ፣ ሥጋህም ከነቢዩ ከኤልሳዕ ጋር እንዲቀመጥ አድርጌያለሁ›› አለው፡፡
ከዚህም በኋላ ጌታችን እንዳዘዛት የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ እራስ እንደንስር በአየር ላይ እየበረረች የምታስተምር ሆነች፡፡ በምሥራቅ በኩል ሄዳ በዐረብ አገር ውስጥ በሰማይ ላይ ስታስተምር በዚህች ዕለት ጥቅምት 30 ቀን በግልጽ ታየች፡፡ ነጋዴዎች ድምጹዋን ሰምተውና አይተዋት እጅግ ተደስተው ገንዘባቸው ሁሉ ጥለው የቅዱስ ዮሐንስን እራስ ለመያዝ ሰውነታቸውን ብዙ አደከሙ፡፡ ነገር ግን ለመያዝ አልተቻላቸውም፡፡ ከዚህም በኋላ ከሰማይ ‹‹የምትያዝበት ጊዜ ስላልደረሰ ሰውነታችሁን አታድክሙ›› የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣላቸው፡፡ መፈለጋቸውንም ተው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስም እራስ 15 ዓመት ስታስተምር ኖራ ሚያዝያ 15 ቀን በዐረብ ሀገር ዐረፈች፡፡ የታዘዙ ቅዱሳን መላእክትም መጥተው ከቅዱስ ዮሐንስ እራስ ከተባረኩ በኋላ በታላቅ ዝማሬ እያመሰገኑ የቅዱስ ዮሐንስን አንገት ወስደው በነቢዩ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ አብረው ቀበሯት፡፡ ቅድስትን ነፍሱንም እያመሰገኑ ወደ ሰማይ አሳረጓት፡፡ በዚያም በሥሉስ ቅዱስ ዙፋን ፊት ወድቃ ከሰገደች በኋላ አባቷ ዘካርያስንና እናቷ ኤልሳቤጥን እጅ ነሳቻቸው፡፡ ከዚህም በኋላ በ3ኛው ሰማይ ውስጥ ተቀመጠች፡፡ ጌታችን ሦስቱን ሰማየ ሰማያት ርስት ጉልት አድርጎ ሰጥቶታልና፡፡
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ መላ ዘመኑ 45 ዓመት ከ8 ወር ነው፡፡ 2 ዓመት በእናት በአባቱ ቤት ተቀመጠ፣ 28 ዓመት በበረሃ ብቻውን ኖረ፣ 8 ወር ርጉም ሄሮድስ አንገቱን ከማስቆረጡ በፊት ሲያስተምር ቆየ፣ 15 ዓመት አንገቱ ከተቆረጠች በኋላ በዓለም ዞሮ ሲያስተምር ኖረ፡፡
ይህች እጅግ የከበረች የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ እራስ እኛው ሀገር ኢትዮጵያውያ ውስጥ ነው የምትገኘው፡፡ ይህንንም መጽሐፈ ጤፉት በደንብ ይገልጸዋል፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግውና የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ መስቀሉን በተአምራት አባቶቻችን ወደ ሀገራችን እንዲያመጡት ሲያደርግ የብዙ ቅዱሳንን ዐፅንም አብሮ ሰጥቶናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ የከበረች እራሱ አንዷ ናት፡፡ እርሷም በግሸን ደብረ ከርቤ በእግዚአብሔር አብ ቤተ መቅደስ ውስጥ በክብር ተቀምጣ ትገኛለች፡፡
የአመጣጧም ነገር እንዲህ ነው፡- የቅዱስ ዮሐንስ እራስ 15 ዓመት ስታስተምር ኖራ ሚያዝያ 15 ቀን በዐረብ ሀገር ካረፈች በኋላ የታዘዙ ቅዱሳን መላእክት ወስደው በነቢዩ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ አብረው ቀበሯት፡፡ ከብዙ ዘመን በኋላ በገንዘብ ድኆች በሃይማኖት ግን ባለጸጎች የሆኑ ሁለት ደጋግ ክርስቲያኖች ለአርባ ጾም ስግደት ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ሳለ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ለአንደኛው በራእይ ተገለጠለትና የከበረች ራሱ ያለችበትን ቦታ ነገረው፡፡ እርሱም ወዳመለከተው ቦታ ቢሄድ የቅዱስ ዮሐንስን ራስ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አገኛት፡፡ መዓዛዋም እጅግ የሚመስጥ ነው፡፡ ሰውየውም ከእርሷ ከተባረከ በኋላ ከእርሱ ጋራ ወደቤቱ ወስዶ በፊቷ መብራት እያበራ ዕጣን እያጠነ በታላቅ ክብር አኖራት፡፡ እርሱም በሞት ባረፈ ጊዜ ለእኅቱ ምሥጢሩን ነግሯት እርሷም በክብር ስትብቃት ኖረች፡፡ የቅዱስ ዮሐንስም ራስ በአንድ አርዮሳዊ ሰው እጅ እስከገባች ድረስ ከአንዱ ሰው ወደ አንዱ ሰው የምትፋለስ ሆነች፡፡ አርዮሳዊውም ሰው ከሞተ በኋላ በኢየሩሳሌም፣ አባ አንያኖስ በሀገረ ኀምዳ ኤጲስቆጶስነት ተሹመው ሳለ ቅዱስ ዮሐንስ ለአባ አንያኖስ ተገለጠለትና የከበረች ራሱ ያለችበትን ነገረው፡፡ አባ አንያኖስም ሄዶ እንደዛሬው ባለ ዕለት ግንቦት 30 ቀን ከዚያ አወጣት፡፡ ይህም የካቲት 30 ቀን ከአገኟት በኋላ ዳግመኛ ያገኙበት ነው፡፡ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስንም ራስ በነቢዩ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ አብረው ካኖሯት ከብዙ ዘመን በኋላ የነቢዩ ኤልሳዕና የመጥምቁ ዮሐንስ ዐፅም ሰኔ 2 ቀን ፍልሰተ ዐፅማቸው ሆነና በፈቃደ እግዚአብሔር በተአምር ወደ እስክንድርያ ሄደ፡፡ የቅዱሳኑም ዐፅም እስክንድርያ እንደደረሰ ቅዱስ አትናቴዎስ ሕዝቡን ይዞ ወጥቶ በታላቅ ክብር ተቀበላቸው፡፡ በዓላቸውንም በደስታ አከበረላቸው፡፡ በስማቸውም ቤተ ክርስቲያን አነጸላቸውና ዐፅማቸውን በክብር አስቀመጠው፡፡ የቅዱሳኑም ዐፅም በእስክንድርያ እጅግ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን እያደረጉ ብዙ ዘመን ኖሩ፡፡
ከዓባይ ወንዝ ውጭ ሕይወት የሌላቸው ግብጾች አምጸው በሀገሪቱ ያሉትን ክርስቲያኖች ያሠቃዩአቸው ጀመር፡፡ ሊቀ ጳጳሳቱን አባ ሚካኤልንም አሠሯቸው፡፡ ይህንንም ሲሰሙ ዐፄ ዳዊት ሱዳን ድረስ ዘምተው የዓባይን ወንዝ አቅጣጫውን በማስቀየር ግብጻውያንን በረሀብ ሊፈጇቸው ሲሉ እስላሞቹ የግብጽ መሪዎች ሊቀ ጰጳሳቱን ከእስር ፈቷቸውና አከበሯቸው፡፡ ዐፄ ዳዊትም የግብጹን ሊቀ ጳጳሳት ከእስላሞች የግዞት እስራት ካስፈቷቸው በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱና ክርስያኖቹ ተመካክረው ብዙ ወርቅ እጅ መንሻ አድርገው ቢሰጧቸው ንጉሣችን ግን ‹‹የዳነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው እንጂ በሰው ነውን? እኔስ ወርቅና ብር አልሻም የጌታዬን ቅዱስ መስቀሉን ስጡኝ እንጂ›› ብለው መልእክት ጽፈው እጅ መንሻቸውን መልሰው ላኩላቸው፡፡ ዐፄ ዳዊትም የዓባይን ወንዝ አለቀቀላቸውም ነበርና ገዥዎቹ እስላሞች እጅግ ተጨንቀው ሊቀ ጳጳሳቱንና ኤጲስቆጶሳቱን ካህናቱንም ሁሉ ሰብስበው የኢትዮጵያዊውን ንጉሥ ፈቃዱን እንዲፈጽሙለት ነገሯቸው፡፡ የግብጹ ሊቀ ጳጳሳትና ክርስያኖቹም በጉዳዩ ከተመካከሩ በኋላ ‹‹እርሱስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚወድ ሃይማኖቱ የቀና ደገኛ ንጉሥ ነውና ቅዱስ መስቀሉን ከሌሎች ቅዱሳን ዐፅም ጋር እንስደድለትና ደስ እናሰኘው›› ብለው ተማሩ፡፡
በመጨረሻም በፈቃደ እግዚአብሔር በግብጽ ያሉ የከበሩ ቅዱሳት ንዋያትንና የብዙ ቅዱሳንን ዐፅም ከቅዱስ መስቀሉ ጋር ለዐፄ ካሌብ ላኩለት፡፡ ከእነዚህም ቅዱሳን ዐፅም ውስጥ እጅግ የከበረች የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ እራስ አንዷ ናት፡፡ ጥንቁቅ የሆኑ አባቶቻችን የጌታችንን ቅዱስ መስቀል በዕንጨት፣ በብረት፣ በነሐስና በወርቅ ሣጥን ደራርበው በክብር ሲያስቀምጡ የመጥምቁ ዮሐንስን ዐፅም ከሌሎቹ ቅዱሳን ዐፅም ጋር አብረው በግሸን እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ክብር አስቀምጠውታል፡፡ ይህንንም መጽሐፈ ጤፉት በዝርዝር ይገልጸዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት ቅዱስ ጊዮርጊስ በተአምራቱ ያሳመናት የከሃዲው ንጉሥ የዱድያኖስ ሚስት እለእስክንድሪያ በሰማዕትነት ዐረፈች፡፡ ይህችውም ቅድስት እለእስክንድርያ የሰማዕታት አለቃ ታላቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ በትምህርቱና በተአምራቱ ያሳመናትና በጌታችን ስም ሰማዕትነትን የተቀበለች የንጉሡ የዱድያኖስ ሚስት ናት፡፡ ከሃዲውና ጣዖት አልምላኪው ባሏ ንጉሥ ዱድያኖስ ከ70 ነገሥታት ጋር ሆኖ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሦስት ጊዜ ገድሎት ጌታችን ከሞት ካስነሣው በኋላ ንጉሡ መልሶ ያባብለው ጀመር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ንጉሡን ዱድያኖስን ከነጣዖታቱ በሰው ሁሉ ፊት ሊያዋርደው ፈልጎ እንዲህ አለው፡- ‹‹ለጣዖትህ ከሰገድኩና ከሠዋሁለት በመንግሥትህ ሁሉ ሁለተኛ አድርገህ እንደምትሾመኝ የነገርከኝ ነገር ደስ አሰኝቶኛልና በሰው ሁሉ ፊት ለምታመልከው ለአጵሎን እሰግድ ዘንድ ሕዝቡም ሁሉ ለጣዖትህ ስሠዋ ይመለከቱ ዘንድ እንዲሰበሰቡ በአዋጅ ነገር›› አለው፡፡ ንጉሡም ቅዱስ ጊዮርጊስ የነገረው እውነት መስሎት እጅግ ተደስቶ እስኪነጋ ድረስ ብሎ ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ሚስቱ እልፍኝ አስገባው፡፡ የንጉሡም ሚስት እለእስክንርያ ብቻዋን ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተገናኘች ጊዜ ሰማዕቱ የዳዊትን መዝሙር ሲጸልይ ሰማችው፡፡ ጸሎቱንም ሲጨርስ ይጸልይ ስለነበረው ነገር ጠየቀችው፡፡ ‹‹ክርስቶስ ብለህ የጠራኸ እርሱ ማነው?›› አለችው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ይህን ጊዜ ስለ ጌታችን ለንግሥቲቱ አስተማራት፡፡
ከብሉይና ከሐዲስም መጻሕፍትን እየጠቀሰ ከዓለም መፈጠር ጀምሮ እነርሱ እስካሉበት ዘመን ድረስ ያለውን የሃይማኖትን ነገር በሚገባ አስተማራት፡፡ ንግሥቲቱም ‹‹በአምላክህ አምኛለሁና ስለ እኔ አምላክህን ለምንልኝ›› አለችው፡፡ ስለ ክፉው ባሏ ስለ ንጉሡ እንዳትፈራ አጽናናትና ሲሰግድ ሲጸልይ አደረ፡፡ በነጋም ጊዜ ነጉሡ አስቀድመው በተነጋገሩት መሠረት መጥቶ ለጣዖቱ እንዲሰግድና እንዲሠዋ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መልዕክት ላከበት፡፡ ንጉሡም ‹‹ገሊላዊው ጊዮርጊስ ለጣዖቴ ሊሰግድ ነውና ኑ ተመልከቱ›› ብሎ 70ውን ነገሥታትና ሕዝቡን ሁሉ በአዋጅ ሰብስቦ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም አስቀድሞ ፈውሶት የነበረውን አንዱን ሕፃን ጠርቶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሄዶ ጣዖቱን እንዲጠራው ላከው፡፡ ‹‹የማታውቅ ዕውር የሆንክ ዲዳ ደንቆሮ አጵሎን ሆይ የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ ጊዮርጊስ ይጠራሃል›› ብሎ በላከበት ጊዜ በጣዖቱ ላይ አድሮ ራሱን ያስመልክ የነበረ ሰይጣን እጅግ ደነገጠ፡፡ ሮጦም ወጥቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ፊት በፍርሃት ቆመ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሰይጣኑ ያደረበትን ጣዖት ‹‹አንተ በምስል ውስጥ የምትናገረው በእውነት የእነዚህ የከሃዲዎቹ አምልክ ነህን?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ በምስል ውስጥ ያለው የሰይጣን መንፈስም ‹‹ጌታዬ ሆይ ተወኝ አታጥፋኝ፣ እኔስ አምላክ አይደለሁም…›› እያለ ከአዳም ጀምሮ የሰው ልጆችን እንዴት እንደሚያስት በነገሥታቱና በሕዝቡ ሁሉ ፊት መሰከረ፡፡ አሁንም በጣዖቱ ውስጥ አድሮ ራሱን እያስመለከ መሆኑንና ወደፊትም የሰው ልጆችን ሁሉ በልዩ ልዩ መንገድ ከፈጣሪያቸው እየለየ ወደ ሲኦል እንደሚያወርዳቸው ተናገረ፡፡ በጣዖቱ ያደረው ሰይጣን በሰው ሁሉ ፊት ይህን ሁሉ ከተናገረ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስም ወደ አምላኩ ከጸለየ በኋላ ምድር አጵሎንን አፏን ከፍታ እንድትውጠው አደረገ፡፡ ሕዝቡም ሁሉ ‹‹በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ አምናል›› እያሉ ጮኹ፡፡
ንጉሡም ይህን ሲያይ በንስሓ ተመልሶ ከማመን ይልቅ እጅግ ተቆጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስን ካሰረው በኋላ ‹‹የተነጋገርነው ለጣዖቶቼ እንድትሠዋላቸው አልነበረምን? ለምን ቃልህን ለወጥክ?›› እያለ በታላቅ ቁጣ ተናገረው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ‹‹አንተ ሰነፍ ጎስቋላ የአእምሮ ድሃ የሆንክ ራሱን ሊረዳ ያልቻለው አምላክህ የሌሎቹን ነፍስ ሊረዳ እንዴት ይችላል? ጌታችን በጌትነቱ ለፍርድ በመጣስ ጊዜ ምን ታደርግ ይሆን?›› አለው፡፡ ንጉሡም እጅግ ተቆጥቶ ልብሱን ቀዶ ተነሥቶ ወደ ንግሥቲቱ ወደ እለእስክንድርያ ገባና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገበትን ነገራት፡፡ እርሷም ‹‹ቅዱስ ጊዮርጊስን ከማሠቃየት ይልቅ የሚጠቅምህን ዕወቅ፣ አምላኩ እውነተኛ አምላክ ነውና በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ እመን›› አለችው፡፡ ንጉሡም ‹‹ሚስቴ እለእስክንድርያ ሆይ ይህ ጊዮርጊስ አስማቱን አደረገብሽ እንዴ?›› ሲላት እርሷም ‹‹የቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቃል ጠርቶኛል በእርሱ አምኛለሁ›› አለችው፡፡ እርሱም ከአንደበቷ የክርስቶስን ስም በሰማ ጊዜ ጠጉሯን ይዞ እየጎተተ ወደ ነገሥታቱ ወስዶ ከመካከላቸው አቆማትና የሆነውን ነገራቸው፡፡ ከዚህም በኋላ እጅግ አስፈሪ የሆኑ ሥቃዮችን ካሳያት በኋላ ራቁቷን አድርጎ በራስ ጸጉሯ ሰቀላት፤ ደሟም በምድር ላይ እስኪፈስ ድረስ ሥጋዋን ቆራረጠው፡፡
በመከራዋ ውስጥ ሆና ቅዱስ ጊዮርጊስን ባየችው ጊዜ ‹‹የእግዚአብሔር ቅዱሱ ሆይ በታላቅ ሥቃይ ውስጥ ነኝና ወደ መሐሪው አምላክህ ለምንልኝ›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ከጌታችን የማይጠፋውን የሕይወትን አክሊል እንድትቀበይ ጥቂት ታገሺ›› አላት፡፡ ከዚህም በኋላ ከተሰቀለችበት አውርደው በመሬት ካስተኟት በኋላ አራት ጎልማሶች ሊያነቃንቁት የማይችሉትን ትልቅ ድንጋይ አንከባለው በሁለቱ ጡቶቿ ላይ ጫኑባት፡፡ ዝፍጥም አፍልተው በጡቶቿ ላይ ጨመሩባትና እጅግ አሠቃዩአት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስንም ዳግመኛ ‹‹ጌታዬ ሆይ ምን ላድርግ? በክርስቶስ ስም የምትሰጠውን የጥምቀት ጸጋ ባለመቀበሌ እኔ አዝኛለሁ ልቤም ልትፈርጥ ደርሳለችና አንተ እንደመራኸኝ ተስፋ ያደረኩትን ክብር እንዳላጣ የመንግሥተ ሰማይ ደጃፍ የገነት በሮች እንዳይዘጉብኝ እፈራለሁ›› አለችው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም መልሶ ‹‹ስለዚህ ነገር አትዘኝ፣ እነሆ በደምሽ ተጠምቀሻልና ጥምቀትንስ አግኝተሻል፡፡ እነሆ ቅዱሳን መላእክት ሊያጠምቁሽ የሕይወትንም አክሊል ሊያቀዳጁሽ ሰላምንም ሊሰጡሽ ይጠብቁሻል›› አላት፡፡ በዚህም ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተናዶ አንገቷን በሰይፍ አስቆረጣት፡፡ ቅድስት እለእስክንድርያም በዓለም ላይ ስላሉ ኃጥአን ሁሉ እየለመነች ሰማዕትነቷን ሚያዝያ 15 ቀን ፈጽማ መላእክት ቅድስት ነፍሷን ወደ ገነት አስገቧት፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት ከሰባ ሁለቱ አርድእት የአንዱ ሐዋርያ ቅዱስ አጋቦስ መታሰቢያው ነው። ይህም ቅዱስ ጌታችን ከመረጣቸውና ይሰብኩ ዘንድ ከመከራው በፊት ከላካቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ ነው።
በጽርሐ ጽዮንም አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋር ስጦታውን ተቀብሏል። እግዚአብሔርም የትንቢትን ሀብት ሰጠው ስለርሱ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደ ተናገረ የቅዱስ ጳውሎስን መታጠቂያ አንሥቶ ራሱ እግሮቹን አሠረባትና የዚችን መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም አይሁድ እንዲህ ያሠሩታል አለ መንፈስ ቅዱስ ብሎ ትንቢት ተናገረ ትንቢቱም ተፈጸመች።
ከዚህም በኋላ ሕይወት በሆነ በወንጌል ትምህርት ሊአስተምር ከሐዋርያት ጋር ወጣ እያስተማረና ቀና የሆነ የእግዚአብሔርን መንገድ እየመራ ብዙ አገሮችን ዞረ ከአይሁድና ከዮናናውያንም ብዙዎችን የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅን ሃይማኖት አስገባቸው በከበረች በክርስትና ጥምቀትም አነፃቸው።
ቅናትን የተመሉ አይሁድም ብቻውን በኢየሩሳሌም በድንገት ያዙትና ታላቅ ግርፋትንም ገረፉት ከዚህም በኋላ በአንገቱ ገመድ አስገብተው እስከ ከተማ ውጭ ጐትተው በዚያም ነፍሱን እስከአሳለፈ ድረስ በደንጊያ ወገሩት። በዚያንም ጊዜ ከሰማይ ብርሃን ወርዶ በሥጋው ላይ እንደ ምሰሶ ተተከለ ወደ ሰማይም ደርሶ አሕዛብ ሁሉ ወደርሱ ሲመለከቱ ነበር።
እግዚአብሔርም የአንዲት አይሁዳዊት ሴት ልቡናዋን ገለጠላት እርሷም በውስጥዋ ሽንገላና ቅናት ጠብ የሌለባት ናት የኦሪትንም ሕግ የምትጠብቅ ነበረች እርሷም ይህን ብርሃን አይታ ይህ ሰው እውነተኛ ነው አለች። ያን ጊዜም በላይዋ ብርሃን ወረደ እንዲህ ብላ ጮኸች እኔ በቅዱስ አጋቦስ ፈጣሪ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነ በጌታ ኢየሱስ የማምን ክርስቲያን ነኝ እግዚአብሔርንም ከፍ ከፍ እያደረገች ስታመሰግነው በደንጊያ ወገሩዋት ነፍሷንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የአገረ ሜራ ኤጲስቆጶስ በሆነ በኒቆላዎስ ስም ለያዕቆባውያን ወገን በግብጽ አገር ያለች ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት መታሰቢያ ሆነ። አባ ኒቆላዎስ አባቱ ኤጲፋንዮስ እናቱ ዮና ይባላሉ፡፡ እርሱም ሜራ በምትባል አገር እጅግ ባለጸጎች ሆነው የሚኖሩ ደጋግ ሰዎች ናቸው፡፡ እጅግ ባለጸጎች ቢሆኑም ልጅ ስላልነበራቸው እያዘኑ እግዚአብሔርን በመለመን ብዙ ዘመን ኖሩ፡፡ የመውለጃ ጊዜአቸውም ባለፈ ጊዜ ስለ ልጅ መለመናቸውን አቆሙ፡፡ እግዚአብሔር ግን በመጨረሻ ዘመናቸው የተባረከ ይህን ኒቆላዎስን ሰጣቸው፡፡ እግዚአብሔርም በልጃቸው ላይ የጽቅን ሥራ ገለጠ፡፡ ልጁ ገና እንደተወለደ ተነሥቶ በእግሮቹ ቆሞ በሰዎች መካከል ለሁለት ሰዓት ያህል ቆመ፡፡ ይህም ለመንደሳዊ ሥራ የተነሣ ቅዱስ መሆኑን ያጠይቃል፡፡ በሕፃንነቱም የሐዋርያትን ትምህርት ፈጽሞ ረቡንና ዓርብን በመጾም እስከ ዘጠኝ ሰዓት የእናቱን ጡት አይጠባም ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ ወላጆቹ ለመምህር ሰጥተውት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ ተማረ፡፡ ወደ ገዳምም ገብቶ ማንም እንደ እርሱ ሊሠራው የማይችለውን ጽኑ ገድል ተጋደለ፡፡ ዘጠኝ ዓመትም በሆነው ጊዜ ቅስና ተሾመና ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ማድረግ ጀመረና ሕመምተኞችን ሁሉ የሚፈውሳቸው ሆነ፡፡ አንድ ባለጸጋ በሀገሩ ነበር፡፡ እርሱም የዕለት እራት እስኪያጣ ድረስ ፈጽሞ ድኃ ሆነ፡፡ አራት ሴት ልጆችም ነበሩትና እነርሱን ስለድኅነቱ የሚያገባቸው ጠፋ፡፡ ባለጸጋ የነበረውም ሰው የዝሙት ሙት ሠርቶ በዚያ ልጆቹ እያመነዘሩ በዝሙት ዋጋ ይኖሩ ዘንድ ይህንን የረከሰ ሀሳብ ሰይጣን አሳሰበው፡፡
እግዚአብሔር ግን የዚያን ባለጸጋ የነበረ ሰው ክፉ ሀሳብ ለአባ ኒቆላዎስ ገለጠለት፡፡ አባ ኒቆላዎስም ከአባቱ ገንዘብ ላይ መቶ የወርቅ ዲናር ወስዶ በሌሊት ማንም ሳያየው ወደዚያ ባለጸጋ ወደነበረው ሰው ቤት ሄዶ በበሩ ሥር አስቀምጦለት ተመለሰ፡፡ ባለጸጋ የነበረውም ሰው ወርቁን ወስዶ እጅግ ደስ ብሎት ታላቂቱን ልጁን አጋባት፡፡ አሁንም ለ2ኛ ጊዜ አባ ኒቆላዎስ መቶ የወርቅ ዲናር አስቀመጠለትና ሰውየውም ሌላኛዋን ታላቅ ልጁን ዳራት፡፡ አባ ኒቆላዎስም ለ3ኛ ጊዜ እንዲሁ አደረገ፡፡ ባለጸጋውም በስተመጨረሻ ‹‹ይህን የሚያደርግልኝ የእግዚአብሔርን ሰው ማየት አለብኝ›› ብሎ ቁጭ ብሎ እያደረ በሌሊት የሚመጣውን መጠበቅ ጀመረ፡፡ አባ ኒቆላዎስም ለ4ኛ ጊዜ ወርቁን ሲያኖርለት አገኘውና ወድቆ ሰገደለት፡፡ ‹‹ከገንዘብና በኃጢአት ከመውደቅ አድነኸኛልና ዋጋህ ፍጹም ነው›› ብሎ አመሰገነው፡፡ አባ ኒቆላዎስ በአካባቢው ባለው ዛፍ ላይ አድረው በሰውየው ላይ መከራ ያመጡበትን አጋንንት አባረራቸው፡፡ በዚያ የነበሩ ሕመምተኞችንም አዳናቸው፡፡ ዳግመኛም ጥቂት እንጀራን አበርክቶ ብዙ ሕዝቦችን አጠገባቸው፡፡ እጅግ የበዛ ትራፊም ተመልሶ ተነሣ፡፡
ከዚህም በኋላ አባ ኒቆላዎስ ኤጲስቆጶስነት ከመሾሙ አስቀድሞ የክህነት ልብስንና ብርሃንን የለበሰ ሰው በዙፋን ላይ ተቀምጦ በራእይ አየና ‹‹ይህንን የክህነት ልብስ ለብሰህ በዙፋኑ ተቀመጥ›› የሚል ድምጽ ሰማ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜም እመቤታችን ተገልጣለት የክህነትን ልብስ ስትሰጠው ጌታችንም የከበረች ወንጌልን ሲሰጠው አየ፡፡ ከዚህም በኋላ የሜራ አገር ኤጲስቆጶስ በሞት ባረፈ ጊዜ የታዘዘ መልአክ ለሮሜው አገር ሊቀ ጳጳስ ተገለጠለትና ስለ አባ ኒቆላዎስ መልኩንና ስሙን በዝርዝር ነገረው፡፡ እርሱም ለሕዝቡ ሁሉ ነገራቸው አባ ኒቆላዎስን ወስደው በሜራ አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት፡፡
ከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ አምለኮ ጣዖትን በግዛቱ ሁሉ ሲያውጅና የክርስቲያኖችን ደም እንደውኃ ሲያፈስ አባ ኒቆላዎስ ደግሞ ክርስቲያኖችን ያስተምራቸውና በሃይማኖት ያጸናቸው ነበር፡፡ ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ አባ ኒቆላዎስን ይዞ እጅግ ብዙ አሠቃየው፡፡ ነገር ግን ጌታችን ከመከራው ሁሉ እያዳነው ከቁስሉም ይፈውሰው ነበር፡፡ ንጉሡም እጅግ ቢያሠቃየውም ቅዱሱ ደግሞ መልሶ ጤነኛ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ በዚህም ማሠቃየት ቢሰለቸው ወደ እሥር ቤት ጨመረው፡፡ እግዚአብሔርም ዲየቅልጥያኖስን አጥፍቶት ጻደቁን ቆስጠንጢኖስን እስካነገሰው ድረስ አባ ኒቆላዎስ በእሥር ቤት ብዙ ዓመታት ኖረ፡፡ ቆስጠንጢኖስም የታሰሩትን ቅዱሳን ሁሉ በፈታቸው ጊዜ አባ ኒቆላዎስ ከእሥር ወጥቶ ወደ መንበረ ጵጵስናው ተመለሰ፡፡ ሕዝቡንም ስለቀናች ሃይማኖት አስተማራቸው፡፡ ሃይማኖታቸው የቀና እጅግ የከበሩ 318 ቅዱሳን በአርዮስ ጉዳይ በተሰበሰቡ ጊዜ ይህ ቅዱስ አባት አባ ኒቆላዎስ ከእነርሱ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እርሱም ከሌሎቹ ቅዱሳን ጋር ሆኖ አርዮስን አሳዶ የቀናች ሃይማኖትን ደነገገልን፣ ሥርዓትን ሠራልን፡፡ እርሱም ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን።
No comments:
Post a Comment