ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 16 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, April 24, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 16

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሚያዝያ ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን የበአርማ አገር ኤጲስቆጶስ ቅዱስ አንቲቦስ በሰማዕትነት አረፈ። እርሱም የመለኮትን ነገር ለሚናገር ለወንጌላዊው ዮሐንስ ረድኡ ነው። እርሱም ከአይሁድ ወገን በግዛቱ ውስጥ አንድ ሰው የሚታይ እስከ አልሆነ ድረስ አይሁድን ያጠፋቸውና ኢየሩሳሌምንም በአፈረሳት በአስባስያኖስ ልጅ በግማትያኖስ ዘመን ነበረ። ከእስራኤል መንግሥት ትውልድ ያላቸውንም ብዙዎችን ገደላቸው ለመንግሥቱና ለራሱ ስለ ፈራ ነው።
የክብር ባለቤት ክርስቶስ አምላካቸውና ንጉሣቸው ድል አድራጊና እነርሱም ወገኖቹ እንደሆኑ ክርስቲያኖች ይናገራሉና ስለዚህ ከአማንያን ብዙዎችን ገደለ። ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሱ ሸሸ የዮሴፍ ልጅ በሮሜ ከተማ ታሥሮ ሳለ ወደ ኢየሩሳሌም ጭፍራ ልኮ የይሁዳን ተወላጆች ወደርሱ አስመጣቸው የክብር ባለቤት ስለሆነ ክርስቶስ መንግሥት በጠየቃቸው ጊዜ ክርስቶስ ሰማያዊ ንጉሥና በሰማያት የሚኖር እንደሆነ በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ለሁሉም እንደየሥራው ሊከፍለው ዳግመኛ ይመጣ ዘንድ እንዳለው አስረዱት።
ይህንንም ሰምቶ እጅግ ፈራ ክርስቲያኖችንም ማሠቃየቱን ተዋቸው። ቅዱስ አንቲቦስን ግን የክብር ባለቤት ክርስቶስን ሊአስክደው ሽቶ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው እርሱም በሥቃዩ ውስጥ በመታመን ጸና ፣ ከዚህም በኋላ ከናስ በተሠራ በላመ ፈጅ ጋን ውስጥ አድርገው ከበታቹ እሳትን አነደዱ እርሱም በውስጧ ሁኖ ስለከበረ ስሙ ምስክር ሊሆን ያደለው እግዚአብሔርን ፈጽሞ ያከብርና ያመሰግን ነበር።
ከዚህም በኋላ ስሙን ለሚጠሩና መታሰቢያውን ለሚያደርጉ ከነፍስ ከሥጋ ደዌ ሁሉንም ይፈውሳቸው ዘንድ ከእግዚአብሔር ፈለገ። ከዚህም በኋላ ከነሐስ በተሠራው በላመ ፈጅ ውስጥ የምስክርነቱን ተጋድሎ ፈጽሞ ነፍሱን ሰጠ። በድኑንም ሲጥሉት ምእመናን አንሥተው በታላቅ ክብር ፈጽሞ እያመሰገኑ ወስደው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት።
እርሱም አስቀድሞ በግዞት ቤት ሳለ ከወንጌላዊ ዮሐንስ ዘንድ የሚያጽናናውና የሚአረጋጋው ቸር ጠባቂ እረኛና ታማኝ አገልጋይ ካህን የሚለው መልእክት ወደርሱ መጣ። እንዲህም ብሎ ሁለተኛ ነገረው በሰማዕትነት እንደሚሞት አንተ ከከበሩ ሐዋርያትና ከሰማዕታት ጋራ ተቆጥረሃል። ደግሞ ከሥጋው ጣፋጭ የሽቱ ቅባት እንደሚፈስ ስለርሱ ተነገረ እርሱም መዓዛው እጅግ ጣፋጭ የሆነ በእምነት ለሚሻው ሁሉ እስከ ዛሬ ጠቃሚ የሆነ ነው በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን።
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages