ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 20 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, April 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 20

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ሃያ በዚህችም ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ጻድቅ_አልዓዛር ከሞተ በኋላ በአራተኛው ቀን ከሙታን ለይቶ ላስነሳበት መታሰቢያ ነው፣ የእስክንድርያ ሃምሳ ሰባተኛ ሊቃነ ጳጳሳት የሆነ ሊቀ_ጳጳሳት_አባ_ሚካኤል አረፈ፣የተመሰገነችና የከበረች ተጋዳይም የሆነች ቅድስት_አስጠራጦኒቃ ስለ ክርስቶስ ምስክር ሁና ሞተች።


መጋቢት ሃያ በዚህችም ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅ ሰው አልዓዛርን ከሞተ በኋላ በአራተኛው ቀን ከሙታን ለይቶ አስነስቶት ነበርና ስለዚች ምልክት ገናናነት ብዙዎች አመኑበት።
ይህም ጻድቅ ሰው ከእስራኤል ልጆች ውስጥ ነው ማርያና ማርታ የተባሉ ሁለት እኅቶች አሉት። ማርያም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሸቱ የቀባችው ናት። እነርሱም ለጌታ ደቀመዛሙርቶቹ ናቸው ስለ ምግባራቸውም ጌታችን ይወዳቸዋል ሁሉም ያላገቡ ድናግል ናቸው። በሰው ወገን ሁሉ ላይ የተቆረጠና የተወሰነው ሰዎችም ሊጠጡት ያላቸው የሞት ጻዋን የሚጠጣበትና እጁን ለሞት የሚሰጥበት ለዚህ ጻድቅ ጊዜው ሲደርስ እርሱም እጁን በመስጠት አረፈ።
የክብር ባለቤት ጌታችን ግን የሚሠራውን ያውቃልና መጀመርያ ከሞት አላዳነውም ጠርቶ እስከሚአሥነሣው ድረስ ሙቶ በመቃብር አራት ቀን እንዲኖር በዚህ በአራት ቀንም የጻድቃንን ማደሪያዎችንና የኃጥአንን የሥቃይ ቦታዎች እንዲያይ ተወው እንጂ አላዳነውም ያን ጊዜም ታላቅ ምልክት ትሆናለች።
ከአራት ቀኖችም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጥቶ አልዓዛር አልዓዛር ና ውጣ ብሎ ከመቃብር ውስጥ ጠራው ያን ጊዜ አጆቹና እግሮቹ እንደታሠሩ ሙታኖችንም እንደሚጠቀልሏቸው በሰበን ፊቱ ተጠቅልሎ ወጣ።
እጆቹና እግሮቹ እንደ ተጠቀለሉና እንደ ታሠሩ ከመቃብር የመውጣቱ ምክንያት ሰዎች ሁሉ መሞቱን እንዲረዱ ሌሎችም ይህ በመካከላቸው በስምምነት የሆነ ነው ብለው እንዳያሰቡ። ስለዚህም እንደ ገነዙት ሁኖ እንዲወጣ ጌታችን አዘዘው ይችም ምልክት እንድትሆን።
ከሀዲዎችም በመቃብር ውስጥ ሕያው እንደ ነበር ቢያስቡም እጆቹና እግሮቹ ፊቱም እንደ ተጠቀለሉ እንዴት ይወጣ ነበር እኛ የክርስቲያን ወገኖች ግን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአራት ቀኖች በኋላ አልዓዛርን ያስነሣው እርሱ እንደሆነ እናምናለን። እንታመናለንም እርሱ በሥራው ሁሉ ላይ ችሎታ አለውና።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን በእስክንድርያ ከተሾሙ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃምሳ ሰባተኛ የሆነ የከበረ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል አረፈ።
ይህም አባት በሹመቱ ወራት ብዙ ኀዘንና መከራ ደረሰበት ጎሕ በሚባል አገር የተሾመ የዚህን የኃላፊውን ዓለም ክብር የሚወድ አንድ ክፉ ኤጲስቆጶስ ነበረ። በሀገረ ስብከቱም ውስጥ ደነውስር በሚባል አገር ያሉ ምእመናን የቤተ ክርስቲያናቸውን ሕንፃዋን አደሱ ሊአከብሩዋትም በፈለጉ ጊዜ የአገር ታላላቆች ከእርሳቸው ሊባረኩ ወደው ሊቀ ጳጳሳቱና በአገሩ ዙሪያ ያሉትን ኤጲስቆጶሳት ልኮ እንዲአስመጣቸው ይህን ክፉ ኤጲስቆጶስ ለመኑት እርሱ ግን እምቢ አላቸው ልመናቸውን መቀበል አልወደደም።
እነርሱም በራሳቸው ፈቃድ ይህ ክፉ ኤጲስቆጶስ ሳይፈቅድ ሊቀ ጳጳሳቱንና ኤጲስቆጶሳቱን ሁሉ ልከው አስመጡአቸው። ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤልና ኤጲስቆጶሳቱ ሁሉ በመጡ ጊዜ ምሳ አዘጋጅላቸዋለሁ ብሎ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትቶአቸው ሔደ። ማርታ ማርታ ብዙ በማዘጋጀት ብዙ ትደክሚያለሽ ግን ጥቂቱ ይበቃል ያለውን የጌታችንን ቃል አላሰበም።
የቍርባን ጊዜ ሊያልፍ ስለሆነ ሊቃውንቱና ኤጲስቆጶሳቱ የቅዳሴውን ሥርዓት ይጀምር ዘንድ ሊቀ ጳጳሳቱን ለመኑት ግድ ባሉትም ጊዜ በሊቀ ጵጵስና ማዕረግና ክብር ተሠይሞ ተነሣ እርሱ ለሁሉ አባት የሆነ ሥልጣኑም ከሥልጣናቸው በላይ ነውና የቅዳሴውንም ሥርዓት ጀመረ።
ያ ክፉ ኤጲስቆጶስም በሰማ ጊዜ በልቡ ሰይጣን አደረበትና ተቆጥቶ መጣ። መሥዋዕቱንም ከመቅደስ ገብቶ ከጻሕሉ ውስጥ ነጥቆ ወደ ምድር ወረወረው ሊቀ ጳጳሳቱም ሌላ መሥዋዕት አምጡ ብሎ አዘዘ አምጥተውለትም ቀድሶ ለሕዝቡ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸውና አሰናበታቸውም።
በማግሥቱም ይህ አባት አባ ሚካኤል ሕዝቡን ሰበሰበ ከእርሱ ጋራ ያሉትንም ኤጲስቆጶሳት ካህናቱንና የምእመናንን አንድነት ሰብስቦ ይህን ክፉ ኤጲስቆጶስ ከሹመቱ ሽረው በእርሱ ፈንታ ሌላ ኤጲስቆጶስ ሾሙ።
ይህም ለአስቆሮቱ ሰው ለይሁዳ ሁለተኛው የሆነ የምስርን አገር ወደ ሚገዛ ስሙ አሕመድ ወልደ በጥሎን ወደተባለው ሹም ሔደ ይህን አባት አባ ሚካኤልን እንዲህ ሲል ነገር ሠራበት። በሊቀ ጳጳሳቱ ዘንድ ብዙ የወርቅና የብር ገንዘብ እንዳለ እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናት የወርቅና የብር ንዋየ ቅድሳትን የተመሉ እንደሆኑ መኰንን ሆይ ዕወቅ አለው።
መኰንኑም ይህን አባት ወደርሱ አስቀርቦ ንዋየ ቅድሳቱን እንዲሰጠው ፈለገ እርሱም ሥጋዬን እንደፈለግህ አድርግ ነፍሴ ግን በእግዚአብሔር እጅ ናት በሎ ከለከለው። እጆቹንና እግሮቹን አሥረው በእሥር ቤት እንዲጥሉት አዘዘ በእሥር ቤትም ከአንድ ዓመት በላይ ኖረ በእሥር ቤት ውስጥ በኖረበት መጠን ከለምለም እንጀራና ከጨው ከበሰለ አተር በቀር ሳይበላ ሁል ጊዜ ይጾም ነበር።
ከዚህም በኋላ አንድ ጸሐፊ ምእመን ዮሐንስ የሚባል መጥቶ ለዚህ ለከበረ አባት አባ ሚካኤል ዋስ ሆነው ለመኰንኑ አባ ሚካኤል ሃያ ሽህ የወርቅ ዲናር እንዲሰጠው ሁኖ ከወህኒ ወጥቶ ወደ ቤቱ ሔደ ጥቂት ቀን ተቀመጠ ታላላቆች ምእመናንና የአስቄጥስ ገዳም መነኰሳት ዐሥር ሽህ የወርቅ ዲናር ሰበሰቡ ደግሞ የእስክንድርያ አገር ሰዎች ከምድራቸው አንዱን ለዐሥር ሽህ ዲናር ሸጡ ሃያ ሽህ እስከሚሞላ ሰበሰቡ።
ሊቀ ጳጳሳቱም ለመኰንኑ ይህን ሃያ ሽህ የወርቅ ዲናር ሰጠው መኰንኑም ዐሥር ዐሥር ሽህ የወርቅ ዲናር እንደ ግብር ሁኖ በየዓመቱ እንዲከፈል ጽፎ አስፈረመው።
ጊዜውም ሲቀርብ ይህ አባት አባ ሚካኤል ከምእመናን ሊለምን ተነሥቶ ወጣ በልበይስ ወደተባለም አገር ደርሶ አንዲት ቀን ዋለ ወደርሱም አንድ ምስኪን ድኃ መነኰሴ ገባ። ከሊቀ ጳጳሳቱም ቡራኬ ተቀብሎ ተመልሶ በበር አጠገብ ከረድኡ ጐን ቆሞ አትዘን በልብህም አትተክዝ ከዛሬዪቱ ዕለት እስከ አርባ ቀኖች ትድናለህ በላይህ ያለውን የዕዳ ደብዳቤ ትቀበላለህና ለመኰንኑ ምንም አትሰጠውም ብለህ ለአባት ሊቀ ጳጳሳት ንገረው አለው ያ ረድኡም እንዳለው ነገረው ድኃውን መነኲሴ ፈለጉት ግን አላገኙትም።
አርባ ቀኖችም ሳይፈጸሙ ያ መኰንን በክፉ አሟሟት ሞተ በእርሱ ፈንታም ልጁ ተሾመ ለዚህም አባት ያንን የዕዳ ደብዳቤ መለሰለት ይህም አባት ድኃው መነኰስ ትንቢት እንደ ተናገረ ደብዳቤውን ተቀብሎ ቀደደው ከዕዳም ዳነ። ይህም አባት በታላቅ መከራና በኀዘን በሹመቱ ዘመን ሃያ ዘጠኝ ዓመት ከኖረ በኋላ በፍቅር በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የተመሰገነችና የከበረች ተጋዳይም የሆነች አስጠራጦኒቃ ስለ ክርስቶስ ምስክር ሁና ሞተች። የዚች ቅድስት አባቷ ጣዖት አምላኪ ነው እርሷ ግን በክብር ባለቤት በክርስቶስ የምታምን ናት ሥጋዋም እስቲከሣና እስቲደርቅ መልኳም እስቲለወጥ ድረስ በሥውር ትጾማለች ትጸልያለችም።
ዐሥራ አምስት ዓመት በሆናት ጊዜ እናትና አባቷ ምን ያከሣሻል አሏት እርሷም እኔስ ኃጢአቴን ይቅር ይለኝ ዘንድ የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እጸልያለሁ አለቻቸው። አባቷም በሰማ ጊዜ ወደ ጢባርዮስ ሒዶ የልጁን ሥራ ነገረው እርሱም ወታደሮች ልኮ ወደ ርሱ አስመጣት። ለጣዖትም እንድትሰግድ መኰንኑ አባበላት እምቢ በአለችም ጊዜ ወደ ወህኒ ቤት አስገቧት እናቷም ክርስቲያናዊት ናት እየመጣች በክብር ባለቤት በክርስቶስ እምነት ታበረታታት ነበር።
ከዚህ በኋላ የብረት የሆነ የሰሌዳ ክርታስ ይሠሩላት ዘንድ በእሳትም አግለው ክንዶቿ ከወገቦቿ ጋራ አንድ እስቲሆኑ እንዲአጣብቋት አዘዘ ይህንንም በአደረጉባት ጊዜ ያንን የብረት ክርታስ ሰብራ በደኅና ወጣች ሕዝቡም ይህን አይተው በክብር ባለቤት በክርስቶስ አራት ሺህ ሰባት መቶ ያህል አምነው በሰማዕትነት ሞቱ የሰማዕታትንም አክሊል ተቀበሉ።
ሁለተኛም ደግመው ከእሥር ቤት አስገቧት ጥፍሮች ያሉት የብረት በሬ ሠሩላት ሆዷን ያስወጓት ዘንድ ሊሰቅሏትም ወደርሷ አቀረቡት ይህንንም በአደረጉባት ጊዜ በጌታ ኃይል በሬው ወዲያና ወዲህ ተከፈለ ሕዝቡም ይህን በአዩ ጊዜ በክብር ባለቤት በጌታችን ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አምስት ያህል ሰው አምነው በሰማዕትነት አረፉ።
ከዚህም በኋላ መርዝን ከተመሉ እባቦች ጉድጓድ ውስጥ ጨመሩዋት በጸለየችም ጊዜ እንደ ትቢያ ሆኑ። ሁለተኛም አራት ሰዎች የሚሸከሙትን ከባድ ደንጊያ አምጥተው በአንገቷ ላይ ሰቀሉ በጸለየችም ጊዜ ደንጊያው ወደ ሦስት ተከፈለ። ብዙዎች አረማውያንም በክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት አረፉ።
ለቅድስቲቱ ግን የብረት ምንቸት አዘጋጁላት በውስጡ የፈላ እርሳስ በላይዋ ያፈሱባት ዘንድ በነኩት ጊዜ በላያቸው ተሰብሮ የሚያሠቃዩአትን ገደላቸው። ንጉሡም አይቶ ተቆጣ ራሷንም በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ።
ምስክርነቷን ከምትፈጸምበት ቦታም በደረሰች ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች አስጠራጢኒቃ ሆይ አንቺ ብፅዕት ነሽ ስምሽ በሕይወት መጽሐፍ ተጽፏልና የሚል ቃል መጣላት ከዚያም በኋላ በሰይፍ ተቆረጠች።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages