ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 21 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, April 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 21

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ሃያ አንድ በዚችም ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከሙታን ለይቶ ወደ አስንሳው ወደ አልዓዛር ቤት ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ የሔደበት ነው፣ ተአምረኛው አባት አባ_ሊባኖስ_ዘመጣዕ ዓለምን ፍጹም በመናቅ የመነኑበት ነው፣ የማቱሳላ ልጅ ጻድቁ_ላሜህ መታሰቢያው ነው።


ቅዱስ_ቤተሰብ (አልዓዛር፣ ማርያና ማርታ)
መጋቢት ሃያ አንድ በዚችም ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ለይቶ ወደ አስንሳው ወደ አልዓዛር ቤት ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ሔደ በዚያም ምሳ አዘጋጂለት ማርታም ምግብ በማቅረብ ታገለግላቸው ነበር።
ሁለተኛዋ ማርያም ግን እግሮቹን ሽቱ እየቀባች በጸጕሩዋ ታሸው ነበር። ጌታችንም አመሰገናት እርሷ ከመቀበሪያዬ ጠብቃዋለች በማለት ስለ ቅርብ ሞቱ አመለከተ።
ዳግመኛም ድኆች ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉ እኔ ግን ከእናንተ ጋራ አልኖርም አለ በዚህም ተሰቅሎ የሚሞትበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ዳግመኛም በዚችም ቀን አልዓዛርን ሊገሉት የካህናት አለቆች ተማከሩ ገናና ስለሆነች ምልክት በእርሱ ምክንያት ብዙዎች በጌታችን የሚያምኑ ሁነዋልና።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት ከዐለት ላይ ውኃ እያፈለቁ ድውያንን የሚፈውሱት ተአምረኛውና አባት አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ ዓለምን ፍጹም በመናቅ መንነዋል፡፡ እርሳቸውም የአባታችን የተክለ ሃይማኖት ገዳም ‹‹ደብረ ሊባኖስ›› በስማቸው የተሰየመላቸው ናቸው፡፡ አባ ሊባኖስ አባታቸው አብርሃም እናታቸው ንግሥት ይባላሉ፡፡ እነርሱም በወርቅና በብር እጅግ የበለጸጉ ሮማዊ ናቸው፡፡ ልጃቸውን አባ ሊባኖስን በሃይማኖት በምግባር ኮትኩተው ካሳደጓቸው በኋላ ዕድሜያቸው ሲደርስ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ያጋቧቸው ዘንድ ከቁስጥንጥንያ አገር ሚስት ባመጡለት ጊዜ እርሱ ግን ፈጽሞ እምቢ አለ፡፡ ወደጫጉላቤትም መግባትን እምቢ አለ፡፡ በዚህም ጊዜ ነቢዩ ሳሙኤልን እንደጠራው አባታችንንም እግዚአብሔር ሦስት ጊዜ በስማቸው ጠራቸውና ‹‹ከአባትህ ተለይ አንተ የመንግሥተ ሰማያት ሙሽራ ነህ እንጂ የዚህ ምድራዊ ዓለም ሙሽራ አይደለህም›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ወዴት እሄዳለሁ? ምንስ ላድርግ?›› ባሉ ጊዜ ወዲያው የታዘዘ መልአክ በሌሊት መጥቶ ከአባታቸው ቤት አውጥቶ ታላቁ አባት አባ ጳኩሚስ ዘንድ አደረሳቸው፡፡ ታላቁ አባት አባ ጳኩሚስም ለአባ ሊባኖስ በዓት በመስጠት ገዳመ ሥርዓትን፣ አስኬማ መላእክትን፣ ቅናተ ዮሐንስን አስተምረዋቸው አመነኮሷቸውና ከ8ቱ ቅዱሳን ጋር እንዲገናኙ አደረጓቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ያ ከአባታቸው ቤት ወስዶ አባ ጳኩሚስ ገዳም ያደረሳቸው ያ መልአክ ድጋሚ ተገለጠላቸውና ‹‹ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ሂድና ተጋድለህን በዚያ ፈጽም ዝናህ በስፋት ይነገራል፣ ለብዙዎችም አባት ትሆናቸዋለህ›› አላቸው፡፡ ቀጥሎም ራሱ መልአኩ ወደ ኢትዮጵያ አመጣቸውና በአክሱም ተቀመጡ፡፡ በዚያም ብዙ ከተጋደሉ በኋላ ወደ ሸዋ መጡና ወንጌልን ዞረው አስተምረው ብዙ ድውያንን ፈውሰው ከዓመታት ቆይታ በኋላ ተመልሰው አክሱም ሄዱ፡፡ በአክሱምም 7 የተለያዩ ጸበሎችን ከድንጋይ ላይ በተአምራት አፍልቀው ድውያንን ፈውሰው ዕውራንን አበሩ፡፡ በዓታቸውንም ከአክሱም ጽዮን ፊት ለፊት አድርገው ሲኖሩ ከዕለታት በአንደኛው ቀን አባታችን በተአምራት ከጭንጫ ካፈለቁት ጸበል ‹‹ተራ ውሃ ነው›› ብላ አንዲት ሴት ልጇን አዝላ ልትቀዳ መጣች፡፡ ወዲውም ከቦታው ስትደርስ አድጧት ወደቀችና ልጇም አምልጥጧት ልቡን ድንጋይ መቶት ሞተ፡፡ ሴትዮዋም ስትጮህ አባ ሊባኖስ ፈጥነው ወጡና በልጁ ላይ ጸልየው በመስቀል ምልክት አማትበው ከሞት አስነሥተውታል፡፡ ሕፃኑ ልጅ ከሞት እንደተነሣ ‹‹አምላከ አባ ሊባኖስ›› ብሎ አመሰገነ፡፡
ይህንንም ደግ ሥራቸውንና ተአምራታቸውን ያዩ አንዳንድ እኩይ ካህናት በቅናት ተመልተው ‹‹ምትሃት ነው የሚያሳየው›› ብለው በጻድቁ ላይ ሕዝቡን አሳደሙባቸው፡፡ አባታችንም ካህናቱን ለመምከር ቢሞክሩም አላስቀምጥ አሏቸው፡፡ ይልቁንም ጦር ጦራቸውን ይዘው አሳደዷቸው፡፡ አባታችንም በዚህ እጅግ አዝነው ከአክሱም ተነሥተው ደርቃ ወደምትባል ቦታ ሄዱ፡፡ በዚያም በጾም በጸሎት እየተጋደሉ ሲኖሩ በእነዚያ በጠሏቸውና በክፋት በተነሡባቸው ካህናት አገር ግን ለ3 ዓመት ምንም ዝናብ ሳይዘንብ ቀረ፡፡ አባታችን በተሰደዱባት በደርቃ አገር ግን ብዙ ዝናብ ይዘንብ ነበር፡፡ አባታችን በዚያችም አገር እንደልማዳቸው ከዐለት ላይ ውኃ አፍልቀው በውኃው ብዙ ድውያንን ፈውሰውበታል፡፡ በዚያም ትልቅ በዓት መሥርተው በተጋድሎ ሲኖሩ በክፉ የተነሡባቸው እኩይ የሆኑ ካህናት መጥተው ‹‹አባታችን በከንቱ አምተንሃል በድለንሃልና ይቅር በለን፣ በድርቅ ማለቃችን ነውና ዝናብም እንዲዘንብልን ጸልይን›› ብለው ከእግራቸው ሥር ወደቁ፡፡ አባታችንም ይቅር ብለው ከፈጣሪ አማለዷቸው፡፡ ዝናቡም ወዲያው ዘነበላቸውና በአገሪቱ ጥጋብ ሆነ፡፡
ከዚህም በኋላ አባታችን አስቀድመው ወዳዩአት ወደ ሸዋ ምድር ግራርያ መጡና በዓታቸውን በአሰቦት ጫካ አደረጉ፡፡ ነገር ግን መልአኩ ተገልጦላቸው ‹‹ሊባኖስ ሆይ! ከዚህ ቦታ የአንተ መኖሪያ አይደለም፣ በዚህ ቦታ ላይ እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያገናኝ የሚያስታርቅ ታላቅ ጻድቅ ይወጣበታልና ይህ ቦታ የእርሱ ርስት ነው፣ የብዙ መነኮሳትም መንደር ይሆናል ነገር ግን የቦታው ስም በአንተ ስም ይጠራልሃል›› አላቸው፡፡ በኋላ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ተወልደው በዓታቸውን በዚያ ቦታ ላይ ሲያጸኑ ቦታው ግን ‹‹ደብረ ሊባኖስ›› ተብሎ በመጀመሪያው አባት ስም ተሰየመ፡፡ መልአኩም በሌሊት እየመራ ወደ አክሱም ወሰዳቸው፡፡ ከዚያም ‹‹ታሪክ ወደምትሠራበት ዕጣ ክፍልህ ወደሆነው ቦታ አደርስሃለሁ›› አላቸውና ወደ ኤርትራ አካለ ጉዛይ አውራጃ ልዩ ስሙ መጣዕ ወደተባለው ቦታ ወሰዳቸው፡፡ በዚያም አባታችን ድውያንን እየፈወሱ፣ ለምፃሞችን እያዳኑ፣ ሙታንን እያስነሡ ብዙ ተአምራትን እያደረጉ ወንጌልን እየሰበኩ ‹‹ሊባኖስ ዘመጣዕ›› የሚባለውን ትልቁን ገዳማቸውን መሠረቱ፡፡ በወቅቱ የነበረው ዐፄ ገብረ መስቀልም የመጀመሪያውን ቤተ ክርስቲያን አሠራላቸው፡፡
ቅዱስ ላሊበላ 23 ዓመት ሙሉ ካነጻቸው እጅግ ድንቅ 11 ቤተ መቅደሶች ውስጥ አንደኛውን በአባ ሊባኖስ ስም ሰይሞላቸዋል፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል ያሠራላቸው ሌላኛው ገዳማቸው ትግራይ ተንቤን ውስጥ ይገኛል፡፡ እጅግ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ የሚታወቁት አባታችን እንደ ተስዓቱ ቅዱሳን ከሮም በመምጣት በሀገራችን ላይ ብርሃንን አብርተዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት የማቱሳላ ልጅ የላሜህ መታሰቢያው ነው። እርሱም አንድ መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኑሮ ኖኀን ወለደው ከወለደውም በኋላ አምስት መቶ ስልሳ አምስት አመት ኖረ።
በድምር ሰባት መቶ አርባ ሰባት ዓመት ኖረ። እግዚአብሔርንም አገልግሎት በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages