ሐዲስ ኪዳኑ ሐሙስ
ምሴተ ሐሙስ
ከስቅለትና ከትንሣኤ በፊት ያለው ሐሙስ በቤተክርስቲያናችን 5 የተለያዩ ስያሜዎች አሉት።
1. ሕጽበተ እግር ይባላል።
ይህ ስያሜ የተሰጠው ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት ነው። ይህም የሚያሳየው የዓለምን ኃጢአት
ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው። ይህንን ለማስታወስ ዛሬ ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳት በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝቡንብ ኃጢአት እጠብ ሲሉ ሲሉ በቤተ ክርስቲያናችን የተገኙትን ምእመናን
እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ሲያጥቡ ያረፍዳሉ። / ዮሐ.13:4-15/
2. የጸሎት ሐሙስ ይባላል።
የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚደክም ሥጋን የተዋሐደ አምላክ ፍፁም ሰው መሆኑን ለመግለጽና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ በጌቴሴማኒ ሲጸልይ በመቆየቱ ነው /ማቴ26:36 ፤ ዮሐ 17:1/
3. የምስጢር ቀንም ይባላል።
ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አንዱ በዚህ ዕለት ተመስርቷል። ይኸውም ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ስጋዬ ነው፤ እንካችሁ ብሉ ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ ይህ ስለ እናንተ ነገ
በመስቀል ላይ የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ በማለት እኛ ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበትን መንገድ ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው።
~ በዚህ ዕለት ቅዳሴ ይቀደሳል። የሚቀደሰውን በለሆሳስ /በዝግታ/ ሲሆን እንደ ቃጭል በመሆን የሚያገለግለውም ጽናጽል ነው። ይህም
አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ ሲመጡ ድምፃቸውን ዝግ አድርገው በለሆሳስ እየተነጋገሩ መምጣታቸውን ለማሰብ ነው።
~ በቅዳሴውም ኑዛዜ አይደረግም። ሥርአተ ቁርባን ግን.ይፈጸምበታል። ይህም ጌታችን የሰጠውን ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ለማሰብ ነው። በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሀ ታጥቦ
ተዘጋጅቶ ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይኖርበታል።
4. የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል።
ምክንያቱም መስዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንሰሳ ደም የሚቀርበው መስዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኀነቱ ዓለም ራሱን የተወደደ መስዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው። /ሉቃ 22:18-20/
ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚሆን የአዲስ ኪዳን ነው።
ከእርሱም ጠጡ በማለቱ ይታወቃል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘላለማዊ ቃል ኪዳን በራሱ ደም
የፈጸመበት ዕለት መሆኑን በማሰብ የቃል ኪዳኑ ፈጻሚዎች ጠባቂዎች መሆን እንደሚገባን እንማራለን።
5. የነጻነት ሐሙስ ይባላል።
ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባርያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው። ራሱም
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ ነፃነት ሲናገር ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚደርገውን
አያውቅምና፤ ወዳጆቼ ግን ብያችኋለሁ በማለቱ /ዮሐ 15:15/ ከባርነት ነፃ የወጣንበት ቀን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ.ያስረዳል። ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከኃጢአት ባርነት በመራቅ
ከእግዚአብሔር ሕይወቱን በቅድስና መምራት ይኖርበታል። እርሱ
ጠላቶቹ ስንሆን ወዳጆቹ አድርጎናል። /ማቴ 26:17-19/
6. አረንጓዴው ሐሙስ ይባላል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአትክልት ቦታ ስለ ጸለየ።
ዝቅ ብሎ ትህትናንና አክብሮትን ያስተማረን ጌታ ልባችንን
ይስበርልን አሜን ።
No comments:
Post a Comment