አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሚያዝያ ሃያ አራት በዚህች ቀን በመጋቢት ዐሥራ ስምንት ቀን የተጻፈ የቅዱስ ኤስድሮስ ባልንጀራ ቅዱስ ፃና በሰማዕትነት አረፈ፡፡
ይህም እንዲህ ነው ባልንጀራው ከኤስድሮስ ጋራ ከአሠቃዩት በኋላ ባልጀራው ኤስድሮስ በሰማዕትነት ሞተ። ቅዱስ ፃናም በእሥር ቤት ቀረ ከአገረ ፈርማ መኰንንም ታሠረ በእርሱም ፈንታ ሌላ መኰንን ተሾመ።
ያንን መኰንንም የክብር ባለቤት የሆነ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሚጠራ ክርስቲያንን ሁሉ እንዳያስቀር ከሀዲው ንጉሥ አዘዘው። ስለ ቅዱስ ፃናም እርሱ ከጭፍሮች ውስጥ እንደሆነ ጽኑዕ ሥቃይም እንዳሠቃዩትና ከአላማውም እንዳልተመለሰ በነገሩ ጊዜ የከበረች ራሱን ይቆርጡት ዘንድ አዘዘና ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ።
የቅዱስ ፃና እናቱም ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት በሆነ ጊዜ አስቀድማ እንዳየች አሁንም ብርሃናውያን መላእክትን የቅዱስ ፃናን ነፍስ ሲያሳርጓት አይታ ለሰው ነገረች። ምዕመናንም ሥጋውን ወስደው ገንዘው ሰምኑድ በሚባል አገር ከባልንጀራው ከኤስድሮስ ሥጋ ጋር አኖሩት። በውስጥዋም እስከ ዛሬ በዓል ይደረግላቸዋል። ወደ እርሳቸው በእምነት ለሚመጣም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ይታያል።
በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስልሳ አምስተኛ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ስንትዩ አረፈ፡፡ ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ መንፈሳዊ ነው። በአስቄጥስም ገዳም በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን በበጎ ሥራ በገድል ተጠምዶ አድጎ በዚያው ገዳም አበምኔት ሁኖ ተሾመ። ከዚህም በኋላም ሕዝቡና ኤጲስቆጶሳቱ መርጠውት በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት። ነገር ግን በዘመኑ ሁሉ ከእስላሞች ነገሥታት ታላቅ ችግርና ኀዘን ደረሰበት። ይኸውም በእርሱ ዘንድ ምንም ምን ያልኖረውን ሊሰጣቸው የሌለውን ብዙ ገንዘብ ይሰጣቸው ዘንድ ፈልገው ይዘውታልና። እግዚአብሔር በእጆቹ ብዙ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ ብዙዎችን ጭንቅ ከሆነ ደዌያቸው አድኖቸዋልና ከሰዎችም ላይ ሰይጣናትና አስወጥቷልና በአገረ መርዩጥ ላይ በጸሎቱ ዝናምን አዝንሞአልና። እርሱም ዝናምን ከማጣት የተነሣ ወንዞቻቸው ጉድጓዶቻቸው ሁሉ ደርቀው ከረኃብና ከውኃ ጥም የተነሣ ለሞት ተቃርበው በታላቅ ረኃብ ሦስት ዓመት ኑረዋልና።
በሰማዕት ቅዱስ ሚናስ ቤተ ክርስቲያን በዓልን ሊያከብር ወደርሳቸው በደረሰ ጊዜ የዚያች አገር ሰዎች ወደ ርሱ ተሰብስበው ውኃ በማጣት እንደ ተቸገሩ ነገሩት እርሱሙ ፈጽሞ አጽናናቸው። የቅዳሴውንም ሥርዓት ከፈጸመ በኋላ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ወዲያውኑ ታላቅ ነጐድጓዶችና ኩሬዎች ሁሉ ሞሉ የተክል ቦታዎች ሁሉ ረኩ። ረኃብ በሆነባቸው በእነዚህ ሦስት ዓመት እንደመላ ኖረ።
አራተኛውም በአስቄጥስ አረቦች በተሰበሰቡ ጊዜ በዚያ የሚኖሩትን መነኰሳት ይገድሉአቸው ዘንድ ከበቡአቸው ይህም አባት መስቀሉን ይዞ ወደእርሳቸው ወጣ መስቀሉንም በአዩ ጊዜ ወደኋላቸው ተመልሰው ሸሹ በማንም ላይ ከቶ ጉዳት አላደረሱም። ደግሞ በትምርቱ ከአገሩና ከመንጋው ውስጥ ክህደትንና ኑፋቄን አስወገደ በዚያን ጊዜ ስለእኛ መከራ የተቀበለው ትብስእት ብቻውን ነው አምላክ አይደለም የሚሉ ነበሩና።
ይህም አባት ስንትዩ በከበረ በታላቁ ጾም ወራት መልክትን ጽፎ ለአገሩ ሁሉ ላከ በውስጥዋም እንዲህ የሚል እያስተማረ "ስለእኛ መከራ የተቀበለ እግዚአብሔር ቃል በሥጋ ነው ከተዋሕዶ በፊት ሁለት የነበሩ በተዋሕዶ አንድ ባሕርይ ስለሆነ አንዲት ሰዓት ወይም የዐይን ጥቅሻ ያህል ከቶ አልተለያዩም በመከራ ጊዜ ወይም በሞት ከመለኮቱ ያልተለየ እርሱ አካላዊ ቃል በሥጋው ስለ እኛ መከራን ተቀበለ"። ይቺም መልእክት በአገሩ ሁሉ በአነበቡአት ጊዜ የክርስቲያን ወገኖች ታላቅ ደስታ ደስ አላቸው እሊያ የሳቱትም ተመልሰው ንስሓ ገቡ። ሁለኛም ደግሞ ምላሳቸውን መቆረጥ የሚገባቸው የተሳሳቱ የመለኮት ባሕርይ ሞተች የሚሉ ሰዎች ተገለጡ እሊህም የብልንያ አገር ሰዎችና ኤጲስቆጶሳቸውም ነው።
ይህም አባት ይህን የእብደትና የስንፍና ነገር በሰማ ጊዜ እጅግ አዝኖ መልእክትን በውስጡ እንዲህ ጻፈ "እግዚአብሔር ባሕርዩ አትመረመርም የማትዳሠሥ የማትታመም ናት እግዚአብሔር ቃል ከእኛ ነሥቶ ያለ መለያየትና ያለ መቀላቀል ከመለኮቱ አዋሐደው ከሰውነቱ ባህርይ በቀር ሕማምን አታስገባም" ሁለተኛም በውስጥዋ እንዲህ አለ "እኛ መከራ ከሚቀበል ከሥጋው እግዚአብሔር ቃልን አንለየውም በመከራውም በሥራው ሁሉ አንድ እንደሆነ እናምናለን እንጂ ሁለተኛም መለኮቱ በባሕርዩ የማይታመም የማይሞት እንደሆነ ከመለኮት ሳይለይ ስለእኛ መከራ ተቀብሎ ሞተ እንጂ"። የመልእክቱም ደብዳቤዎች ወደእነዚህ ሰዎች ደርሰው በአነበቡአቸው ጊዜ ከስሕተታቸው ተመልሰው በእውተኛዪቱ በቀናች ሃይኖት አመኑ። ኤጲስቆጶሳቸውም ጋራ ወደዚህ አባት ወደ ሊቀ ጳጳሳት ስንትዩ ፊት ቀርበው የቀናውን እምነት ተቀብለው አመኑ ታላቅ ስሕተታቸውንና በደላቸውንም ይተውላቸው ዘንድ ለመኑት እርሱም ስሕተታቸውን እያመኑ በኤጲስቆጶሳቱ ሁሉ በካህናቱ በሕዝቡም ፊት እንዲሰግዱ አዘዛቸው እንዳዘዛቸው አደረጉ በደላቸውንም ተወላቸው።
ይህም አባት አብያተ ክርስቲያናትን ስለማነፅ የስደተኞችንም ቦታዎች ስለማዘጋጀት ብዙ የሚአስብ ነው ከዚህ የሚተርፈውንም ለድኆችና ለምስኪኖች ይሰጣል። መልካም ጉዞንም በመጓዝ እግዚአብሔርን አገለገለው ሚያዝያ24 በሰላምም ዐረፈ። የሹመቱም ዘመን ዐሥራ አምስት ዓመት ሆነ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የቅዱሳኑ በረከት ረድኤት በሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ከሥጋና ከነፍስ መከራ ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment