ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 26 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, May 6, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 26

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ ሃያ ስድስት በዚህች ቀን የሱሲ ልጅ ቅዱስ_ሱስንዮስ በሰማዕትነት አረፈ፣የጠራቢ ልጅ ቅዱስ_ዮሐንስ በሰማዕትነት አረፈ።


ሚያዝያ ሃያ ስድስት በዚህች ቀን የሱሲ ልጅ ሱስንዮስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም የከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ወዳጅ ነበረ። የእግዚአብሔር መልአክም ተገለጠለትና ሰማዕት እንደሚሆን ነገረው ይህም ነገር በልቡ አደረ።
ከዚህም በኋላ አምልኮ ጣዖትን እንዲአስፋፉና እንዲአድሱ ከሹመት ደብዳቤ ጋራ ንጉሡ ወደ ኒቆምድያ ላከው። ቅዱሱም አይቶ እጅግ አዘነ ከዚያም ወደርሱ አንድ ቄስ አምጥቶ የክርስትናን ትምህርት ተምሮ ተጠመቀ።
ከዚህ በኋላም ወደ አንጾኪያ ተመለሰ ፍጥረቱ ልዩ የሆነ ልጅን ወልዳ እኀቱን አገኛት። ከዚህ በፊት ሴት ልጅ ወልዳ ገድላ ደሟን ጠጥታለች ሰይጣን አድሮባታልና በወፍና በከይሲ አምሳልም ይገለጣል በአገር ውስጥም ልጅ በሚወለድ ጊዜ ወደርሱ ወርዳ በሥራይም ገድላ ደሙን ትጠጣለች።
ቅዱስ ሱስንዮስም ይህን በአየ ጊዜ ጦሩን አንሥቶ ከልጅዋ ጋራ እኀቱን ገደላት ልጅዋ የሰይጣን ልጅ ነውና ሁለተኛም ሥራየኞች ስለሆኑ ባሏንና የባሏን አባቱን ገደላቸው እነርሱ በሥራያቸው ሰውን እያሳመሙ ይገድላሉና።
ከዚህም በኋለ ወደኒቆምድያ ተመልሶ ወደዚያ ወደ አጠመቀው ቄስ ደርሶ ያደረገውን ሁሉ ነገረው። ወደ አገሩ አንጾኪያም በተመለሰ ጊዜ ከእርሱ የሆነውን አባቱ ሱሲ አወቀ መገደሉንም ወዶ ከንጉሥ ዘንድ ነገር ሠራበት። ያን ጊዜም ቅዱስ ሱስንዮስ ወደ ጣዖታት ቤት ሒዶ ወደ ሲኦል ይወርዱ ዘንድ በጌታችን ኢየሱስ ስም አዘዛቸው ያን ጊዜም ምድር አፍዋን ከፍታ ዋጠቻቸው ጣዖታቱንም እንዳጠፋቸው ወሬው ተሰማ።
አባቱም ዳግመኛ በንጉሥ ዘንድ ከሰሰው ታላቅ ሥቃይም ያሠቃዩት ዘንድ ንጉሥ አዘዘ በብረት ዘንጎችም ደበደቡት በመንኰራኲርም አበራዩት በመዶሻም ቀጥቅጠው ሁለተኛ ደግመው እህል በሚአበራዩበት መሣሪያ አበራዩት። ከዚያም በከተማው ውስጥ ጐተቱት።
የክብር ባለቤት ጌታችንም ያጸናውና በሥቃዩም ውሰጥ ያስታግሠዋል ከቁስሉ የሚፈውሰውን መልአኩንም ልኮ ያለ ምንም ጉዳት አነሣው። ብዙ ሰዎችም አይተው በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በርሱ ምክንያት ሰማዕታት ሆኑ።
ንጉሥም ከማሠቃየቱ በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ። በሥቃዩም ወራት በሰማዕትነት የሞቱት ቍጥራቸው አንድ ሺህ አንድ መቶ ዘጠኝ ሆነ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የጠራቢ ልጅ ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ ከነነዌ አገር ነው አባቱ ጣዖትን የሚጠርብና የሚያመልክ ነው። እናቱ ግን ክርስቲያናዊት ናት ልጅ በአጣችም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ለመነች ጌታም ልመናዋን ተቀብሎ ይህን የተባረከ ልጅ ሰጣት ስሙንም በሥውር ዮሐንስ ብላ ጠራችው።
ስምንት ዓመትም በሆነው ጊዜ የጠረበውን ጣዖት እየሸጠለት ኣባቱን ያገለግል ነበር። በአንዲት ዕለትም ጣዖቱን ሊሸጥ ሲሔድ የእግዚአብሔር መልአክ ተገናኘውና ጣዖት የሰይጣን ማደሪያ እንደሆነ ነገረው ጣዖቱንም ከእጁ እንዲጥለው አዘዘው በክብር ባለቤት በክርስቶስ ማመንን አስተማረው።
ወደ አባቱም በተመለሰ ጊዜ ሰማይና ምድርን በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ ከፈጠረ ከክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም እኔ ለሰው እጅ ሥራ አልሰግድም አለው። አባቱም ሰምቶ በእሥር ቤት አሠረው እናቱም መጥታ በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ደሙን ያፈስ ዘንድ አጸናችው።
ከዚህም በኋላ በነገራቸው ሊሸነግሉት የአገር ሰዎች መጥተው የአባትህን አምላኮች ለምን ተውክ አሉት። እርሱም እኔ የሰው እጅ ለሠራቸው ጣዖቶች አልሰግድም አነርሱ የርኲሳን አጋንንት ማደሪያዎች ናቸውና አላቸው አባቱም ይህን በሰማ ጊዜ ምሳር አንሥቶ አንገቱን ቆረጠው በድኑም አልወደቀም በደሙ እስከተጠመቀ ድረስ በእግሮቹ ቆመ እንጂ።
እናቱም በደሙ ተጠምቃ አቤቱ የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የአቤልን መሥዋዕት በምድረበዳ የተቀበልክ ይህንን መሥዋዕት ከእኔ ተቀበል አለች። በዚያን ጊዜ በአባቱ ሰይጣን አደረበትና አበደ። ሚስቱም ወደ ልጅዋ መቃብር ወስዳው ስለርሱ ጸለየች ቅዱስ ዮሐንስም በሌሊት ወደርሱ መጥቶ አባቱን በጦር ወጋው ሰይጣኑም ከእርሱ ወጣ። ከዚህ በኋላም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነና በስሙ ተጠመቀ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages