አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ቅዱስ ፊቅጦርም በአደገ ጊዜ አባቱ ወደ ንጉሥ አቀረበው ንጉሡም በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛ ማዕርግ አድርጎ ሾመው በዚያን ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበረ። እርሱም የዚህን ዓለም ክብር ናቀ ሥጋ አይበላም ወይን አይጠጣም ዘወትርም ይጾማል ጸሎትንም ባለማቋረጥ በቀንና በሌሊት ይጸልያል።
በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም የታሠሩትን ይጐበኛቸዋል ለድኆችና ለምስኪኖችም ይመጸውታል። የቅዱሳን ቆዝሞስና ድምያኖስ እናት ቅድስት ቴዎዳዳን በገደሉዋት ጊዜ ንጉሡን ስለ መፍራት ሊቀብራት ማንም አልደፈረም። ይህ ቅዱስ ፊቅጦርም መጥቶ ሥጋዋን ወሰደ ከንጉሥ ስለሚመጣው ቅጣት ሳይፈራ ቀበራት። ጣዖት ስለ ማምለኩ አባቱን ዘወትር የሚገሥጸውና ብዙ ጊዜም የሚመክረው ሆነ አባቱም ወደ ንጉሥ ከሰሰው እንጂ አልሰማውም።
ተከሶም ወደ ንጉሥ በአቀረቡት ጊዜ አማልክት ያልሆኑ ርኲሳን ጣዖታትን ለሚያመልክ ሰነፍ ዝንጉ ልብ የለሽ ለሆነ ንጉሥ አላገለግልም። ከዛሬ ጀምሮ ለሕያው ንጉሥ ክርስቶስ እገዛለሁ የሰጠኸኝንም ገንዘብህን ንሣ ብሎ ከፊቱ ትጥቁን ፈትቶ ጣለላት።
አባቱ ኀርማኖስም ወደ እስክንድርያ እንዲልከውና በኄርሜኔዎስ መኰንን ዘንድ በዚያ ፊቅጦር እንዲቀጣ ንጉሡን መከረው። በዚያን ጊዜም ከአደባባይ አወጡት እናቱም በብዙ ልቅሶ ልትሸኘው መጣች።
እርሱም ሲመግባቸው ስለ ነበሩ የታሠሩ ምእመናን ስለ ድኆችና ምስኪኖች ስለ ሙት ልጆችና ስለ ባልቴቶች የሚሹትን በመስጠት እንድትጐበኛቸው አዘዛት ከዚያም አፉን ለጉመው ወሰዱት።
በእስክንድርያ አገር ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስ ዘንድ በደረሰ ጊዜ ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ሰማያት አውጥቶ ስለ ክብራቸው ለመናገር የሚያስጨንቁ የብርሃን ማደሪያዎችን አሳይቶ ወደ መኖሪያው መለሰው።
መኰንኑም በእሳት በአፈሉት በዝፍት በዲን ደግሞ አሠቃየው ከዚያም በብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ። ደግመው ከውሽባ ማንደጃ ውስጥ ጨመሩት በየአይነቱ በሆነ ሥቃይም አሠቃዩት የክብር ባለቤት ጌታችንም ያጸናውና ከሥቃዩ ያስታግሠው መልአኩንም ልኮ ከቁስሉ ይፈውሰው ነበር።
ከዚህም በኋላ ወደ እንዴናው ከተማ ላከው በዚያም ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት ምላሱን ቆረጡ። በእሳት ያጋሉዋቸውን ችንካሮች በጐኖቹ ውስጥ ጨመሩ እግዚአብሔር ግን አጽንቶ አስታግሦ ያለ ጉዳት በደኀና ያነሣዋል።
ከዚህም በኋላ በዚያ በረኃብ እንዲሞት ከዱር ባለ ግምብ ውስጥ አሠሩት። እርሱ ግን መጥረብ የሚያውቅ ስለሆነ ላይዳዎችን በመጥረብና በመሸጥ በየጥቂቱ እየተመገበ የቀረውን ለድኆች እየሰጠ ኖረ።
አንድ መኰንንም መጥቶ በዚያ ግምብ አቅራቢያ አደረ ስለ ቅዱስ ፊቅጦርም እርሱ የንጉሥ የሠራዊት አለቃ የሆነ የኀርማኖስ ልጅ እንደሆነ ነገሩት።
መኰንኑም ወደርሱ አቅርቦ ብዙ ሸነገለው ባልሰማውም ጊዜ ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ ጅማቶቹን መዘዙ አፉን መቱት ቊልቊል ሰቅለው በእጆቹ ላይ ከባድ ደንጊያ አንጠለጠሉ። ከዚያም ከሚነድ እሳት ውስጥ ጨመሩት ሙጫ አደሮ ማርና ዘይትን አፍልተው በላዮ ደፉበት በማበራያም አበራዩት አፉንም በአሞትና በእሬት አመረሩት ዐይኖቹንም አወለቁት ደግመውም ዘቅዝቀው ሰቀሉት። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ተገልጾለት አጸናው አረጋጋው። ሥሮቹንና ሕዋሳቶቹን በቦታቸው መለሰለትና አዳነው።
አንዲት ዓሥራ አምስት ዓመት የሆናት ብላቴና ነበረች ቅዱስ ፊቅጦርን ሲአሠቃዩት በቤቷ መስኮት ታየው ነበር። መላእክትንም በእጆቻቸው አክሊሎችን ይዘው እነርሱም በቅዱስ ፊቅጦር ራስ ላይ ሲያኖሩአቸው አይታ እንዴት እንዳየች ለአሕዛብ ነገረቻቸው እጅግም አደነቁ። ከእርሳቸውም ብዙዎች በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት አረፉ፡፡፡ ያቺም ብላቴና በጌታችን አመነች መኰንኑም ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። የሕይወት አክሊልንም ተቀበለች ሁለተኛም የአመኑትን ሁሉ ራሳቸውን እንዲቆርጡአቸው አዘዘ የሕይወትንም አክሊል ተቀበሉ።
ከዚህም በኋላ የከበረች የቅዱስ ፊቅጦርን ራስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ተጋድሎውንም ፈጽሞ የሕይወትና የድል አክሊልን ተቀበለ።
ምእመናን ሰዎችም ሥጋውን ወስደው በከበሩ ልብሶች በድርብ በፍታ ገነዙት። እናቱ ማርታም ከአንጾኪያ እስክትመጣ በንጹህ ቦታ አኖሩት በመጣችም ጊዜ ከዚያ ወሰደችው። ውብ ቤተ ክርስቲያንም ሠርታ ሥጋውን በውስጥዋ አኖረች ከእርሱም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን።
No comments:
Post a Comment