ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 6 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, May 20, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 6

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ግንቦት ስድስት በዚህች ቀን የእስክንድርያ ቄስ የከበረ አባት አባ_መቃርስ አረፈ፣ ከግብጽ ደቡብ ዳፍራ ከሚባል አገር የከበረ አባ_ይስሐቅ ምስክር ሆኖ አረፈ፣ ቅድስት_ዲላጊ ከአራት ልጆቿ ጋራ ምስክር ሆና አረፈች፣ ንጽሕናን ቅድስናን ድንግልናን ገንዘብ ያደረገች ተሐራሚት_ሰሎሜ አረፈች።ግንቦት ስድስት በዚህች ቀን የእስክንድርያ ቄስ የከበረ አባት አባ መቃርስ አረፈ። ይህም ቅዱስ በአባቱ በሚቀድመው በታላቁ በክቡር አባ መቃርስ ዘመን ለአስቄጥስ ገዳም አባት ሁኖ ብዙ ትሩፋትን ሠራ።
ስለእርሱም እንዲህ ተባለ አንዲት ዘመሚት ነክሳው ገደላት ከዚህም በኋላ ተጸጽቶ ነፍሱን ገሠጻት ስለ ዘመሚቷም ሞት በበረሀ ወደአለ ወንዝ ወርዶ ሥጋውንም ለዘመሚት ገልጦ እንደዝልጉስ እስኪሆን በዚያ ስድስት ወር ኖረ። ከዚህ በኋላ ወደበዓቱ ተመለሰ መቃርስ እንደሆነም ማንም አላወቀውም።
አንድ ጊዜም እየጸለየ አምስት ቀን አምስት ሌሊት ቆመ ልቡም ወደ ሰማይ ተመስጦአል ሰይጣናትም እስከ ተቃጠሉ ድረስ ይቺ ትጋትና ተጋድሎ ከሠራው ትሩፋት ሁሉ ትልቃለች አሉ። አንድ ጊዜም የረዓይትን ቦታዎች ሊያይ ወዶ ወደ በረሀ ውስጥ ገባ ዐሥር ቀኖችም እየተጓዘ ኖረ። በሚመለስም ጊዜ ምልክት ሊሆኑት መንገዱን እንዳይስት ለምልክት የሚያኖራቸው ሸንበቆዎች ከእርሱ ጋራ ነበሩና በየመንገዱ ተከላቸው።
በደከመም ጊዜ ጥቂት ሊያርፍ በምድር ላይ ተኛ። ተኝቶ ሳለም እነዚያን ሸንበቆዎች ሰይጣን ነቀላቸው አሥሮም በቅዱስ መቃርስ ራስጌ አኖራቸው። በነቃም ጊዜ አያቸውና ወዲያውኑ አጣቸው አደነቀ እንዲህ የሚልም ቃልን ሰማ።
መቃርስ ሆይ ሃይማኖት ካለህ አታወላውል በሸንበቆዎችም አትታመን የእስራኤልን ልጆች በበረሀ ሲመራቸው የነበረ የብርሃን ምሰሶ እርሱ እንደሚመራህ እመን እንጂ አትጠራጠር። ወዲያውኑ የብርሃን ምሰሶ አይቶ ተመለሰ።
ከዚህም በኋላ በጎዳና ሳለ ተጠማ እግዚአብሔርም ከበረሀ ላሞች አንዲቷን ልኮለት ወተቷን ጠጥቶ ረካ ወደ በዓቱም ተመለሰ።
በአንዲት ቀንም ጅብ ወደርሱ መጥታ ልብሱን ይዛ ትስብ ጀመር እርሱም እስከ ዋሻዋ ተከተላት። ሦስት ልጆቿን አወጣችለት በአያቸውም ጊዜ ዕውሮች ሁነው አገኛቸው ከልቡናዋም አሳብ የተነሣ ያቺን ጅብ አደነቃት። ግልገሎቿንም ይዞ በዐይኖቻቸው ውስጥ ምራቁን ተፋ፡፡ አዳኝ በሆነ በመስቀል ምልክትም አማተበባቸው ያን ጊዜ ድነው ከእናታቸው ኋላ ሮጡ ጡቷንም ጠቡ ከዚህ በኋላም ወደ በዓቱ ተመለሰ እርሷም የበግ አጐዛ አመጣችለት እርሱም ተቀብሎ በላዩ እየተኛ እስከሚአርፍበት ጊዜ በእርሱ ዘንድ አኖረው።
በአንዲት ጊዜም ደግሞ ልብሱን ለውጦ በሕዝባዊ አምሳል ሆኖ ወደ አባ ጳኵሚስ ገዳም ሔደ በታላቁም ጾም ሳይበላ ሳይጠጣ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ቆመ። የሚሠራውንም እንደቆመ ይታታ ነበር እንጂ አይቀመጥም። መነኰሳቱም አባ ጳኩሚስን ይህን ሰው ከእኛ ዘንድ አውጣው ሥጋ የለውምና አሉት አባ ጳኵሚስም ሥራውን ይገልጥልኝ ዘንድ እግዚአብሔርን እስከምለምነው ታገሡኝ አላቸው። በለመነውም ጊዜ የእስክንድርያው መቃርስ እንደሆነ እግዚአብሔር አስረዳው።
በዚያን ጊዜም አባ ጳኵሚስና መነኰሳቱ ሁሉ ወደርሱ ሒደው እጅ ነሱት ከእርሱም ቡራኬ ተቀብለው ደስ ተሰኙበት ወደቤተ መቅደስም ከእሳቸው ጋራ አስገቡት። በገዳሙ ውስጥም በሥራቸው በመመካት በባልንጀሮቻቸው ላይ የሚታበዩ የዚህን ቅዱስ አባት የአባ መቃርስን ጸጋውን አይተው ትሑታኖች ሆኑ። ከዚህ በኋላም ወደ በዓቱ ወደ አስቄጥስ ገዳም ተመለሰ።
በእስክንድርያ አገርም ዝናብ በተከለከለ ጊዜ ዝናብን እንዲያወርድ አንበጣንም እንዲአጠፋ ወደ እግዚአብሔር አብሮት ለመጸለይ ወደርሱ ይመጣ ዘንድ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጢሞቴዎስ እየማለደ ላከበት። ያንጊዜም ተነሥቶ ወደ እስክንድርያ አገር ሔደ ሕዝቡም በታላቅ ደስታ ተቀበሉት በልቡም ጸለየ ብዙ ዝናብም ዘነበ ከዝናብ ብዛት የተነሣ ምድሪቱ ትጠፋለች ብለው እስቲአስቡ ድረስ ሁለት መዓልት ሁለት ሌሊት እየዘነበ ኖረ። እጅግም ፈርተው አባታችን ሆይ ዝናቡን አስወግዶ በልክ ይሆን ዘንድ እንዳንጠፋ ስለ እኛ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ ብለው ለመኑት ያንጊዜም ጸለየ ዝናቡም በርቶ በእግዚአብሔር ቸርነት ፀሐይ ወጣላቸው።
ይህም አባት ብዙ ታላላቅ ትሩፋቶችን ሠርቷል እግዚአብሔርም በእጆቹ ድንቆች ተአምራትን ገለጠ ርኵሳን አጋንንት ያደሩባቸውንና ብዙዎች በሽተኞችን አዳናቸው። ይህ አባትም የሠራቸውን በጎ ሥራዎች ሊቆጥራቸው የሚችል የለም አንድ ሰው በጎ ሥራ እንደሠራ የሰማ እንደሆነ ሰውዬው እንደሠራው እስከሚሠራ አይተኛም።
የክብር ባለቤት ስለሆነ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ክብር ምራቁን ሳይተፋ ስልሳ ዓመት ኖረ። መቶ ዓመት ከሆነውና ተጋድሎውን ከፈጸመ በኋላ በበጎ ሽምግልና አረፈ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን ከግብጽ ደቡብ ዳፍራ ከሚባል አገር የከበረ አባ ይስሐቅ ምስክር ሁኖ አረፈ። ለዚህም ቅዱስ በሌሊት ራእይ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾለት የሰማዕትነትን አክሊል ትቀበል ዘንድ ጣዋ ወደሚባል አገር ሒድ አለው።
ከዚያም በነጋ ጊዜ ከመሔዱ በፊት አባትና እናቱን ሊሰናበታቸው ተነሣ። ሁለተኛም የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ከአገሩ እስከ አወጣውና ሀገረ ጣዋ እስካደረሰው ድረስ እነርሱ በላዩ እያለቀሱ አልለቀቁትም።
በደረሰም ጊዜ መኰንኑን በዚያ ከውሽባ ቤት አገኘው ከዚያም በወጣ ጊዜ በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የማምን እኔ ክርስቲያን ነኝ ብሎ በመኰንኑ ፊት በግልጽ ጮኸ።
ከኒቅዩስ ሀገርም እስኪመለስ ቅዱሱን ወስዶ እንዲጠብቀው ከወታደሮች አንዱን አዘዘው ከዚያ ወታደርም ጋራ ቅዱስ ይስሐቅ አልፎ ሲሔድ በመንገድ ዳር የተቀመጠ አንድ ዕውር የእግዚአብሔር ቅዱስ ሆይ ይቅር በለኝ ዐይኖቼንም አድንልኝ ብሎ ለመነው። አባ ይስሐቅም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለዚያ ዕውር ለመነው ያን ጊዜም ዐይኖቹ ተገለጡ። ይህንንም ድንቅ ተአምር ወታደሩ አይቶ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የክርስቲያን ወገን ሆነ።
መኰንኑም በተመለሰ ጊዜ ያ ወታደር በመኰንኑ ፊት የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ በመታመን ሰማዕት ሁኖ አክሊል ተቀበለ።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ ቅዱስ ይስሐቅን ጽኑ ሥቃይን አሠቃይቶ ወደ ሀገረ ብህንሳ ሰደደው በዚያም አሠቃዩት። በመርከብም ሲወስዱት የጽዋ ወኃን ለመናቸው ከቀዛፊዎችም አንዱ አንድ ዐይኑ የታወረ ውኃን በጽዋ ሰጠው የከበረ ይስሐቅም ያን ውኃ በላዩ ረጨ ዐይኑም ድና እንደ ሌላዪቱ ሆነች።
ጽኑ ሥቃይን የሚአሠቃዩት የብህንሳ ሀገር ሰዎችም ይህን ድንቅ ሥራ በአዩ ጊዜ ወደ መኰንኑ ወሰዱትና ብትገድለውም ብትተወውም አንተ ታውቃለህ አሉት። መኰንኑ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ ወዲያውኑ አዘዘ የከበረች ራሱንም ቆረጡት የምስክርነት አክሊልንም ተቀበለ።
በዚያም ምእመናን ሰዎች ነበሩ የአባ ይስሐቅንም ሥጋ በሠረገላ ጭነው በበሮች እያሳቡ ዳፍራ ወደተባለ አገሩ አደረሱት ያሻግሩትም ዘንድ መርከብ ባላገኙ ጊዜ ተሸክመው አሻግረው ወደ ቤቱ አደረሱት። ቤቱንም አፍርሰው በስሙ ቤተ ክርስቲያን አድርገው ሠሩዋት ሥጋውንም በውስጥዋ አኖሩ ከእርሱም የሚያስደንቁ ብዙዎች ተአምራት ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ቅድስት ዲላጊ ከአራት ልጆቿ ጋራ ምስክር ሆና አረፈች፡፡ እነርሱም ሱርስ ኀርማን ያአፋ ናቸው። ይችም ቅድስት በክብር ባለቤት ክርስቶስ ሃይማኖት የጸናች ናት።
መኰንኑ አርያኖስም ሀገረ አስና በደረሰ ጊዜ ልጆቿን እየነዳች ተቀበለችው በፊቱም ቁማ አርያኖስ ሆይ ሰማይንና ምድርን በውስጣቸው ያለውን በፈጠረ በክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝ አለችው።
ልጆቿም እንደርሷ እኛ ክርስቲያን ነን እያሉ በግልጽ ጮኹ። መኰንኑም ሰምቶ ቁጣን ተመላ ራሳቸውንም በሰይፍ ቆረጠ ምስክርነታቸውንም ፈጽመው ነፍሶቻቸውን ወደ ክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ መላእክት ወሰዱ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት ደግሞ ንጽሕናን ቅድስናን ድንግልናን ገንዘብ ያደረገች ተሐራሚት ሰሎሜ አረፈች። ይችም ቅድስት ወረብ ከሚባል አገር ናት ወላጆቿም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው በበጎ አስተዳደግም አሳደጉዋት። በአደገችም ጊዜ እርሷ ሳትፈቅድ አንድ መኰንን አጭቶ በሠርግ አገባት። ያን ጊዜም አምላካዊ ኃይል ከልክሎት ወደርሷ መቅረብ አልቻለም አባለ ዘሩ ተቀሥፎአልና።
በእንደዚህም እያለች ራሷን ሠውራ በሌሊት ሔደች በእግዚአብሔር ኃይል አመለጠች። ቅዱሳን በአሉበት ሁሉ በመዞር በጾም በጸሎት ተወስና ዕውነተኛ መንገድን ጌታ ይመራት ዘንድ በቀንና በሌሊት ስትማልድ ኖረች።
ጌታችንም ልመናዋን ሰምቶ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም አደረሳት የመላእክት የሆነ አልባሰ ምንኲስናን በአባ ዮሐንስ ከማ እጅ ለብሳ የሰውን ልብ የሚያስደነግጥ ጽኑ ገድልን ተጋደለች።
በጾም በጸሎት በተመሰገነ ገድል ሁሉ የፍጹማን አባቶችን ጐዳና ተጓዘች። በመጽሐፈ ገድሏ እንደ ተጻፈ ብዙዎች ድንቆች ተአምራትንም እስከ ማድረግ ደርሳ ከዚህ በኋላ በሰላም አረፈች።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages