አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ግንቦት ዘጠኝ በዚች ቀን የጻድቅ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እናት ቅድስት_ዕሌኒ አረፈች፣ ታላቁ አባት አቡነ_ብፁዕ_አምላክ ዕረፍታቸው ነው፡፡
ግንቦት ዘጠኝ በዚች ቀን የጻድቅ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እናት ቅድስት ዕሌኒ አረፈች። ይቺም ቅድስት በፊት የአንድ ነጋዴ ሰው ሚስት ነበረች እርሱም በነገረ ሠሪ ንጽሕት ሁና ሳለች ወደ ባሕር ጣላት። የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ፈቃድም ሮሐ ከሚባል አገር ደርሳ የበራንጥያ ንጉሥ ቊንስጣ አገኛት። ውበቷንና ደም ግባቷንም አይቶ አገባት። ለክርስቲያን ነገሥታት መጀመሪያቸው የሆነውን ቈስጠንጢኖስን ወለደችው ምግባርንና ሃይማኖትን በማስተማር በመልካም አሳደገችው።
ልጇም በነገሠ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሒደሽ የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስን መስቀል ግለጪ የከበሩ ቦታዎችንም ሥሪ የሚላትን በሕልሟ አይታ እንዴት እንዳየች ይህን ለልጇ ነገረችው እርሱም ከብዙ ሠራዊት ጋራ ሰደዳት። በደረሰችም ጊዜ የክብር ባለቤት ስለሆነ ስለ ጌታችን መስቀል መረመረች አዳኝ የሆነ መስቀሉንም ሁለቱ ወንበዴዎች ከተሰቀሉባቸው መስቀሎች ጋራ አገኘችው። የክብር ባለቤት የክርስቶስ መስቀል የትኛው እንደሆነ ታውቅ ዘንድ በወደደች ጊዜ ከራሱ በላይ ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው የሚል በእንጨት የተቀረጸበት ጽሑፍ ያለው እንደሆነ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ቅዱስ መቃርስ ነገራት።
ከዚህ በኋላ ከእርሱ ምልክት ታይ ዘንድ ፈለገች የሞተ ሰውም አግኝታ መስቀሎችን በበድኑ ላይ አኖረች አልተነሣም። ከዚህ በኋላ ሦስተኛውን መስቀል በላዩ አኖረች። ያን ጊዜ ምውት ተነሣ ሃይማኖቷም ጸና ደስታዋም በዛ።
ከዚህ በኋላም ዜናቸው በመስከረም ወር በዐሥራ ሰባት የተጻፈ በከበሩ ቦታዎች ውስጥ አብያተ ክርስቲያናትን ትሠራ ዘንድ ጀመረች። ለአባ መቃርስም በከበሩ ቦታዎች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲሠራ ብዙ ገንዘብ ሰጠችው።
ከዚህ በኋላ ወደ ልጇ ተመልሳ የሆነውን ሁሉ ነገረችው የከበረ መስቀል በመገኘቱ እጅግ ደስ አለው።
ይቺም ቅድስት በጎ ገድሏን ከፈጸመችና እግዚአብሔርንም ከአገለገለች በኋላ ስለ ካህናትም ልብስና ቀለብ ለአብያተ ክርስቲያናትና ለገዳማት ብዙ ጉልቶችና ርስቶችን ለድኆችና ለምስኪኖችም እንዲሁ ከሠራችና ከተከለች በኋላ በሰላም አረፈች መላ ዕድሜዋም ሰማንያ ሆነ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን ታላቁ አባት አቡነ ብፁዕ አምላክ ዕረፍታቸው ነው፡፡ እኚህ ጻድቅ የአባታቸው ስም ቅዱስ አፍቅረነ እግዚእ ሲሆን የእናታቸው ስም ደግሞ ቅድስት ማርያም ዘመዳ ሲባሉ በ1425 ዓ.ም መስከረም አንድ ትግራይ ክልል ልዩ ስሙ መከዳ በተባለ ቦታ ተወለዱ። እስከ ሰባት ዓመታቸው በእናትና አባታቸው ቤት ከኖሩ በኋላ በስምንት ዓመታቸው ወደ ደብረ ቢዘን ገብተው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሲማሩ በገዳማዊ ኑሮ ሲያገለግሩ ቆይ እስከ 25 ዓመታቸው ከቆዩ በኋላ በዛው በደብረ ቢዘን በ25 ዓመታቸው መነኵሰዋል።
ከዚያም ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገብተው ለአምስት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በድጋሚ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ ኤርትራ አገር ወደ መጀመርያ ወደ መሰረቱ ገዳም ደብረ ኰዳዱ ሔደው በአንድ ዋሻ ውስጥ ገብተው ሕማማተ መስቀልን በማሰብ በአንድ ሺህ ችንካሮች እራሳቸው ቸክረው ለ30 ዓመታት ሲጋደዱ ኖሩ። በዛው አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ለአብሃም እንደተገጹ ለእርሳቸውም በአንድነትና በሦስትነት ታኅሣሥ አንድ ቀን ተገለጡላቸው። እርሳቸው ሥላሴ መሆናቸው ለማረጋገጥ የቆሙበት ድንጋይ ለሦስት ቦታ ተከፈለ፤ እንደ ገና ደግሞ ተመልሶ ወደ አንድ ተለወጠ። በዚህ የተገለጡላቸው ሥላሴ እንደሆኑ አረጋገጡ ቃል ኪዳን ከገቡላቸው በኋላ መጨረሻ የሚያርፉበት ቦታ ነግረዋቸው ተሰወሩ ከዚያም ወደ ሁለተኛ ወደ መሰረቱት ገዳም ደብረ ምዕዋን ገብተው ብዙ ከተጋደሉ በኋላ ግንቦት 9 ቀን 1501 ዓ.ም በ76 ዓመታቸው ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለው ዐርፈዋል። አጽማቸውም እስካሁን በዛው በደብረ ምዕዋን ይገኛል።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎትና ምልጃ ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment