ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 8 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, May 20, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት 8

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ግንቦት ስምንት በዚህች ዕለት የክብር ባለቤት የጌታችንና_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በዓለ_ዕርገት ሆነ፣ ስንሑት ከሚባል አገር ቅዱስ_ዮሐንስ በምስክርነት አረፈ፣ የአስቄጥስ ገዳም አበምኔት አባ_ዳንኤል አረፈ።


ግንቦት ስምንት በዚህች ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ በነሣው ሥጋ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ወደአለው የአንድነት አኗኗሩ ከሰማያት በላይ ያረገበት ሆነ።
እርሱም በረቀቀ ጥበቡ በመከራው በሞቱና በመነሣቱ ሥራውን ከፈጸመ በኋላ አርባው ቀን ሲፈጸም በነፋሳት ክንፍ ላይ ሆኖ ዐረገ።
ያን ጊዜ በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ ወጣ በነፋሳትም ክንፎች ላይ ሁኖ ወጣ ያለው የዳዊት ትንቢት ተፈጸመ። በዚህም ዕርገቱ ለሚያምኑበት በልዕልና ወደሚኖሩበት የሚዐርጉ መሆናቸው ተረዳ ተረጋገጠ ራስ በአለበት ሕዋሳት ሊኖሩ ይገባልና ።
አዳም አስቀድሞ በምድራዊ ርስቶች በሲኦልም እንደኖረ መኖርንም እንደ ቀደመ እንዲሁ ዳግማዊ አዳም ጌታ በመንግሥተ ሰማያት ርስት መኖርን ቀደመ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዕርገቱን ከትንሣኤው አከታትሎ ወዲያውኑ አላደረገም መናፍቃን ዕርገቱ ምትሐት ናት ብለው እንዳያስቡ።
ጌታችንም በረቀቀ ጥበቡ የደቀ መዛሙርቱን ተሸብሮ የነበረ ልቡናቸውን እያጽናና መነሣቱንም እያስረዳቸው ከትንሣኤው በኋላ አርባ ቀን ኖረ። በጌታችንም ዕርገት የዳንኤል ትንቢት ተፈጸመ እንዲህ የሚል ሌሊት በራእይ አየሁ እነሆ ታላቅ እንደ ሰው ልጅ የሆነ መጣ ዘመናትን ወደሚያስረጃቸው ደረሰ ከፊቱም አቀረቡት።
የዘላለም አገዛዝ ጌትነት መንግሥት የዘላለም ሥልጣን ተሰጠው ሕዝቡና አሕዛቡ ሁሉ መንደር መንድረው የሚኖሩትና ነገዱም ነገሥታቱም ሁሉ ይገዙለታል አገዛዙም የዘላለም አገዛዝ ነው መንግሥቱም የማያልፍ የማይጠፋ ነዋሪ ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን ስንሑት ከሚባል አገር ቅዱስ ዮሐንስ በምስክርነት አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም መቃርስ የእናቱም ስም ሐና ነው። እርሱም የአባቱን በጎች ሲጠብቅ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ የብርሃን አክሊልን አሳየው። እነሆ ተጋድሎ ተዘርግቶ በክርስቶስ ስም ለሚጋደል አክሊላት ተዘጋጅተው ሳሉ አንተ ለምን ከዚህ ተቀመጥክ። አሁንም ወደ ሀገረ አትሪብ ሒድ የክብር ባለቤት ስለሆነ ስለ ክርስቶስ ስም ተጋደል አለው። ከዚያም ሰላምታ ሰጥቶት ከእርሱ ዘንድ ሔደ።
በዚያም ወቅት ቅዱስ ዮሐንስ ተነሣ እናቱንና አባቱንም ተሰናብቶ ወደ አትሪብ ከተማ ሔደ መኰንኑንም በውሽባ ቤት አገኘውና በወጣ ጊዜ በፊቱ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ። መኰንኑም ለአንድ ወታደር ሰጥቶት ምናልባት ከምክሩ ተመልሶ ቢታዘዝለት አስቦ እንዲአባብለው ወታደሩን አዘዘው።
ከዚህ በኋላ መኰንኑ ወደ ሥራው ሔደ ወታደሩም ቅዱስ ዮሐንስን ወደ ቤቱ ወሰደው። ቅዱሱም ተአምራትን አደረገ ያ ወታደርም በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ። መኰንኑም በተመለሰ ጊዜ ያ ወታደር በክብር ባለቤት በጌታችን በመኰንኑ ፊት ታመነ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበለ።
ከዚህ በኋላም ቅዱስ ዮሐንስን እንዲአሠቃዮት መኰንኑ አዘዘ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይም አሠቃዩት። እግዚአብሔርም ያጸናውና ያስታግሠው መልአኩንም ልኮ ቊስሎቹን አድኖ ያለ ጉዳት በደኀና ያነሣው ነበር።
ከዚህም በኋላ ወደ እንዴናው ከተማ ላከው በዚያም ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት። መኰንኑም ማሠቃየቱን በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበለ።
የአቅፍሐሲ ዮልዮስም ሥጋውን ወስዶ ገነዘው ወደ ሀገሩ ስንሑትም ላከው። የሀገሩ ሰዎች ሁሉም ወጥተው በፍጹም ደስታ ተቀበሉት ከማዕጠንት ጋራ እየዘመሩና እያመሰገኑ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከሥጋውም ብዙዎች ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የአስቄጥስ ገዳም አበምኔት አባ ዳንኤል አረፈ። ይህም ቅዱስ ዕውነተኛ ንጹሕ ፍጹም ነው ዜናው በሁሉ ቦታ በተሰማ ጊዜ ሹመት ያላት አንስጣስያ የመኳንንቶችን ልብስ ለብሳ ወደርሱ መጥታ ከእርሱ መነኰሰች። በእርሱ አቅራቢያም ሃያ ስምንት ዓመት በበዓት ውስጥ ኖረች እርሷ ሴት እንደሆነችም ማንም አላወቀም።
ይህም ቅዱስ ስሙ አውሎጊስ የሚባለውን ሰው አየው ይህም አውሎጊስ የወፍጮ ድንጋይ እየወቀረ ለግርሽ እየሸጠ ሁል ጊዜ በመጠኑ እየተመገበ ድኆችንና ጦም አዳሪዎችን ይመግባቸዋል የተረፈውንም ፍርፋሪ ለውሾች ይጥላል ለነገ ብሎ ምንም አያሳድርም።
አባ ዳንኤልም ይህን መልካም ሥራውን አይቶ በርሱ ደስ አለው እጅግም አማረው ለአውሎጊስም የዚህን ዓለም ብልጽግና እንዲሰጠውና ለድኆች የሚመጸውተው እንዲጨመርለት ወደ እግዚአብሔር ለመነ።
ለአውሎጊስም ዋስ ሆነው የሚወቅረውንም ደንጊያ ሲፈነቅል በሸክላ ዕቃ የተደፈነ ወርቅን አገኘ ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ ሒዶ የንጉሥ የሠራዊት አለቃ ሆኖ ተሾመበት የሚሠራውንም የቀደመ በጎ ሥራውን ተወ። አባ ዳንኤልም ስለርሱ ሰምቶ ወደርሱ በሔደ ጊዜ የንጉሥ ሠራዊት አለቃ ሆኖ በፈረስ ላይም ተቀምጦ ብዙ ሠራዊት አጅቦት እርሱም በትዕቢት ተመልቶ የቀድሞ በጎ ሥራውንና ለድኃ መመጽወቱንም ትቶ አገኘው።
አባ ዳንኤልም አይቶ አዘነ ስለርሱ በመለመኑም ተጸጸተ። ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ እንደ መጣ አባ ዳንኤልንም እንዲሰቅሉት ሲያዝ የአውሎጊስንም ነፍስ ከእርሱ እንዲሹ በእርሱ ምክንያት ጠፍቷልና የከበረች ድንግል እመቤታችን ማርያምም የክብር ባለቤት ጌታችንን ልጅዋ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ አባ ዳንኤል እንደ ለመነችው በሌሊት ራእይ አባ ዳንኤል ራሱ አየ።
በነቃም ጊዜ ደነገጠ አውሎጊስንም ወደ ቀድሞ ሥራው ይመልሰው ዘንድ በጸሎትና በምሕላ በመትጋት ወደ እግዚአብሔር እየለመነ ግብር ገባ ሱባኤ ያዘ።
ከዚህ በኋላም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለት በፍጥረቱ ላይ በሚያደርገው በእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ ለመግባት በመድፈሩ ገሠጸው። በዚያንም ወቅት አውሎጊስን የሾመው ንጉሥ ሞተ ሌላ ንጉሥም ነገሠ በአውሎጊስም ላይ ተነሥቶ ገንዘቡን ሁሉ ወረሰ። ደግሞም ሊገድለው ፈለገው አውሎጊስም ነፍሱን ለማዳን ከንጉሡ ሸሽቶ ወደ አገሩ ደረሰ እንደ ቀድሞውም ደንጊያ ይወቅር ጀመረ አባ ዳንኤልም ወደርሱ ተመልሶ ስለርሱ ያየውን ሁሉ ስለ ርሱም እንደሰቀሉትና ነፍሱንም ከእርሱ እንደፈለጉ ነገረው።
በዚህ በአባ ዳንኤልም የትንቢት መንፈስ አድሮበት ነበር ከእርሱም ብዙዎች ታላላቅ ታአምራት ተገለጡ። መናፍቃን አርዮሳውያንም ከቀናች ሃይማኖት ሊአወጡት በፈለጉ ጊዜ እንቢ አለ። ያቺንም የክህደት ደብዳቤ ተቀብሎ ቆራረጣት የአርዮሳዊ ንጉሥ ወታደርም ይዞ ብዙ ሥቃይን አሠቃየው። በአንዲት ዕለትም ቅዱሳት ደናግል ወደ ሚኖሩበት ወደ ሲሐት ገዳም አባ ዳንኤልን ተመስሎ ሽፍታ ገባ። ደናግሉም በደስታ ተቀብለው እግሮቹን አጠቡ። እነርሱም አባ ዳንኤል እንደሆነ አምነው የወንበዴውን የእግር እጣቢ ውኃ በረከቱን ለማግኘት በላያቸው ረጩት። በዚያም አንድ ዐይኗ የታወረ ነበረች ውኃው በነካት ጊዜ ዐይኗ በርቶላት አየች።
ወንበዴውም አይቶ ደነገጠ ሥራውንም ገለጠ ንስሓ ገብቶም መነኰሰ በበጎ ገድል ሁሉ ተጠምዶ እግዚአብሔርን አገለገለው። ጌታችንም ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው በወደደ ጊዜ መልአኩን ልኮለት ከዓለም የሚወጣበትን ጊዜ አስረዳው። መነኰሳቱንም ሰብስቦ በበጎ ሥራ እንዲጸኑ አዘዛቸው አጽናናቸው አረጋጋቸውም ከዚህም በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎትና ምልጃ ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages