ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 28 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, June 6, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 28

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ግንቦት ሃያ ስምንት በዚህችም ዕለት ተጋዳይ የሆነች ዓለምን ንቃ የተወች ድስት ዓመተ ክርስቶስ አረፈች፣ ከአባ ጳኵሚስ ገዳም አባ መርቆርዮስ አረፈ፣ የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሥጋ ወደ ቆጵሮስ ደረሰ።


ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
ግንቦት ሃያ ስምንት በዚህችም ዕለት ተጋዳይ የሆነች ዓለምን ንቃ የተወች አባ ዳንኤል ስለርሷ እንደተናገረ የዓለምን ፍላጎት ሁሉ ድል የነሣች ቅድስት አመተ ክርስቶስ አረፈች። ሀገሯ ልዩ ስሙ ተጉለት ሲሆን በተጋድሎዋ በእጅጉ ትታወቃለች፡፡ መጽሐፍ ተሐራሚት ገዳማዊት ይላታል፡፡ በበረሃ ውስጥ በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ 38 ዓመት ብቻዋን ማንም ሳያያት የኖረች ታላቅ እናት ናት፡፡ አባ ዳንኤል ስለርሷ እንዲህ አለ በበረሀም ሳለሁ በሌሊት ተነሥቼ በጨረቃ ብርሃን ተጓዝኹ በተራራ ላይ የተቀመጠ ሰውንም አየሁ ጠጉሩም ሁለመናውን ሸፍኖታል በልቤም ወደርሱ ሔጄ ይህ ምን እንደሆነ ልወቅ ብዬ ወደርሱ ሔድሁ።
በአየችኝም ጊዜ ወደ ተሠነጠቀ አለት ውስጥ ገባች ሰው እንደሆነ አውቄ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ በረከትህን እንድቀበል እማልድሃለሁ አልሁ እጅግም አብዝቼ ለመንሁ። ከዚህም በኋላ አባት ሆይ አልወጣምና ይቅርታ አድርግልኝ አለችኝ። ስለምን አልኋት እኔ ሴት ነኝ ራቁቴን ስለሆንኩ አለችኝ። ይህንን ሰምቼ የለበስኩትን ዐጽፍ ጣልሁላት ለብሳም ወጣች በአንድነትም ጸለይን።
ከዚህ በኋላ እናቴ ሆይ ከዓለም ወደዚህ ስለመውጣትሽ ይኸንን የተሠነጠቀ ዐለት እንዴት እንዳገኘሽ ንገሪኝ አልኋት። እርሷም እንዲህ ብላ መለሰችልኝ በወላጆቼ ቤት ድንግል ሁኜ በኢየሩሳሌም የምኖር ነኝ ሁል ጊዜ የሚጎበኘኝና ከእኔ ጋራ የሚነጋገር አንድ መነኰስ ነበረ።
ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ወደርሱ ሔድኹ በእግዚአብሔር ፊትም ኃጢአቱን እየታመነ ሲአለቅስ አገኘሁት። ደጁንም በአንኳኳሁ ጊዜ አልከፈተልኝም እየተጸጸተ ልቅሶን አበዛ እንጂ። በዚያን ጊዜ በልቤ እንዲህ እልኩ እኔስ ስለ ጕስቊልናዬና ስለ ኃፍረቴ የማላለቀስና የማልጸጸት ለምንድነው ወደ ማደሪያዬም ፈጥኜ ሔድኹ ማቅ ለበስኩ በዘንቢልም ሽምብራ በጽዋ ውኃን ያዝሁ። በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ዘንድ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ አቤቱ ጽኑዕ ኃያል ለዘላለሙ ድንቅ የሆንክ የጠፉትን የምታድን የወደቁትንም የምታነሣቸው ወደ አንተ የሚጮኹትንም የምትሰማቸው የታመነችብህ ባሪያህን ታድናት ዘንድ ይቅርታህንና ምሕረትህን ላክ። ከምግባር ድኃ የሆንኩ ባሪያህን ጐብኘኝ ንስሓዬንም ተቀበል። ለረጅም ዘመን ስንቅ ይሆነኝ ዘንድ ይህን ሽምብራና ይህን የጽዋ ውኃ ባርከው ስለ ነፍሴ ድኅነት የአሰብኩትን እንዳላቃልል ለሆዴ ምግብ ስለሚአሻኝ።
ከዚህ በኋላም ነፍሴን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል ወጥቼ ወደ በረሀ ሔድኹ እስከ ኤርትራ ባሕርም ደረስኩ። ከዚያም ወደዚህ በረሀ መጥቼ ይህን የተሠነጠቀ ዐለት አገኘሁ ይህ እግዚአብሔር ያዘጋጀልኝ መኖሪያዬ ነው አልሁ።
እነሆ በዚህ በረሀ ውስጥ ሠላሳ ስምንት ዓመት ሆነኝ ያለ አንተ ሰው አላየሁም። ይህም የዘንቢል ሽምብራና የጽዋ ውኃ ሠላሳ ስምንት ዓመት ከእሳቸው ስመገብ አልጐደሉም ልብሴ ግን አለቀ ነገር ግን ይህ ቦታ ስለ ልብስ መከለያ ሆነኝ። የበጋ ፀሐይ ትኩሳትም አላስቸገረኝም ቁር ቢሆንም በዕድሜዬ ዘመን ሁሉ አላስጨነቀኝም።
ከዚህ በኋላም ከዘንቢል ካለው ሽምብራ እንድመገብ ማለደችኝ ከሽምብራውም በላሁ ከውኃውም ጠጣሁ። ግን አልጎደለም እግዚአብሔርንም አመሰገንሁት ልብሴንም ልተውላት ወደድሁ እርሷም ከዚህ የተሻለ አምጣልኝ ብላ ይህን እምቢ አለችኝ።
ከዚህ በኋላም ከእርሷ ዘንድ ሔድኩ ወደ ገዳም ደርሼ ስለርሷ ለአበ ምኔቱ ነገርኩት። እርሱም ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው አንዱን ይስጥ ብሎ ጮኸ ፈቃደኞች የሆኑም አመጡለት ያን ጊዜም ይዤ ሔድኩ ለአመተ ክርስቶስ ልስጣት ብዙ ደከምኩ እርሷን በመፈለግ ዞርኩ አላገኘኋትም።
ከጥቂት ቀኖች በኋላም አረጋውያን ወደ እኔ መጡ እንዲህም አሉኝ ወደ ኤርትራ ባሕር የሚያደርሰውን መንገድ ይዘን በጣኔዎስ በረሀ ስንጓዝ ከዋሻ ዘንድ ሴት ተቀምጣ አይተን ከእርሷ በረከት ለመቀበል ሮጥን ሸሽታ ከዋሻው ገባች ወደ ዋሻውም አፍ ቀረብን ግን አላየናትም። ሽምብራ በዘንቢል ውኃም በጽዋ አግኝተን በላን ጠጣን ያን ጊዜም አለቀ እስከ ንጋትም አደርን።
በነጋም ጊዜ በረከቷን ለመቀበል ቅድስቲቱን ፈለግናት ሙታም አገኘናት ጠጉሯም ሥጋዋን ሁሉ ሸፍኖአል። በዚያም ሰገድን በበዓቷም ውስጥ ቀበርናት የዋሻውንም አፍ በደንጊያ ዘጋን የቅድስቲቱን በረከት እንድንቀበል አድሎናልና እግዚአብሔርን እያመሰገን ወደ በዓታችን ገባን።
በሰማሁም ጊዜ አስቀድሜ ያገኘኋት እንደሆነች አወቅሁ የነገረችኝንም ሁሉ ነገርኳቸው። ጠላት ዲያብሎስን ድል ያደርገው ዘንድ ክፉዎች አጋንንትንም ደካማውን ድኃ የሚረዳ የተመሰገነ እግዚአብሔርን ፈጽመን አመሰገን ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ መርቆርዮስ ገዳማዊ
በዚችም ዕለት ከአባ ጳኵሚስ ገዳም አባ መርቆሬዎስ አረፈ። እንጦንዮስም እንዲህ አለ ለእኔ ገዳም አለኝ ይኸውም የወንድማችን የመርቆሬዎስ ዕረፍቱ ቀረበ እያሉ ወደእኔ መነኰሳት የመጡበት ነው እኔም በረከቱን ለመቀበል ወደርሱ በሔድኩ ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው ሳትለይ በተመሥጦ ላይ አገኘሁት።
ከመነኰሳቱ ጋራ በእርሱ ዘንድ ሦስት ሌሊቶች ኖርን በሦስተኛዪቱም ዕለት ነፍሱ ተመልሳ ዐይኖቹን ገለጠ በአየንም ጊዜ ከእኔ ዘንድ ምን ሰበሰባችሁ አለን። እኛም የሆነውን ሁሉ ነገርነውና ከዚህም በኋላ ያየውን እንዲነግረን ለመንነው እርሱም የሚአስፈራ ሰው ወደርሱ መጥቶ ነፍሱን እንደወሰደ የኃጥአንን ሥቃይ እንዳሳየው የጻድቃንንም ዋጋቸውንና ተድላቸውን እንዳሳየው ነገረን።
ከዚህ በኋላ ወዮ ብሎ በማልቀስ በግምባሩ ከምድር ላይ ተደፋ እንዲህም አለን ወንድሞቼ ሆይ ወደ ሐራጺት ገዳም ወደ አባ ጊዮርጊስ ማደሪያ ሒዱ። ከእኔ ጋራ የነበረውን መልአክ መርቆሬዎስን መልሳችሁ በትንሽ በዓት ውስጥ ሲጋደል የኖረ ጊዮርጊስን አምጡት ሲል ሰምቼዋለሁና ይቺም ሥጋው እስቲቋጠር የተጋደለባት የጨው በረሀ ናት።
ወንድሞች መነኰሳትም በሔዱ ጊዜ ሙቶ አገኙት ወደዚህ ገዳምም አምጥተው ቀበሩት። ይህም ወንድም መርቆሬዎስ እንደ ደረቀ እንጨት እስቲሆን ሥጋውን እጅግ አሠቃየ።
ከዚህም በኋላ ወደ ገዳም ይሔድ ዘንድ ተሰናበተኝ። ደግሞ ግንቦት ሃያ ስምንት ቀን ወደኔ ና ታገኘኛለህና አለኝ። በቀጠረኝም ቀን ወደርሱ ሔጄ አገኘሁትና እኔ ወደ አባቶቼ እሔዳለሁ። ወደ አንተም ሦስት አጋዘኖች ይመጣሉ ሥጋዬንም በጀርባቸው ላይ ጫን እነርሱም ወደ ቦታዬ በእግዚአብሔር ፈቃድ ይመሩሃል።
በዚያም በማደሪያዬ ውስጥ ድፈኑኝ አለኝ። እንደ ቃሉም ሆነለት ከመቃብሩም ቁጥር የሌላቸው ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ኤጲፋንዮስ
በዚህችም ዕለት የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሥጋ ወደ ቆጵሮስ ደረሰ። ይህም እንዲህ ነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ወደ መንበረ ሢመቱ እንደማይደርስ ትንቢት እንደተናገረበት ወደ ቆጵሮስ ሳይደርስ በመርከብ ውስጥ ሳለ ግንቦት ዐሥራ ስድስት ቀን አረፈ።
በአረፈም ጊዜም በመርከብ ጭነው ወደ ቆጵሮስ ከተማ አደረሱት። ካህናቱና ሕዝቡ ሁሉ መጡ ከሳቸውም ጋር ወንጌሎች መስቀሎች መብራቶችና ማዕጠንቶችም ይዘው ነበር የሐዋርያት ጉባኤ ከታላቂቱ ቤተ ክርስቲያን እስኪያደርሱት በዝማሬና በማኅሌት በሚገቡት ጸሎቶች ሁሉ እያመሰገኑ ሥጋውን ተሸከሙ። ካህናቱም መቃብሩን በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሊያዘጋጁ ወደዱ። ቀድሞ ስለ ክፉ ሥራቸው ቅዱስ ኤጲፋንዮስ አውግዞአቸው የነበሩ ሁለት ዲያቆናት ተቃወሟቸው።
ስለዚህም አርባ ቀን ተቀመጠ ነገር ግን ሽታው እንደ ሙታኖች ሽታ አልተለወጠም እንደ አንቀላፋ ሰው ሆነ እንጂ። ከዚህም በኋላ አንድ ደግ ዲያቆን ወደ ቅዱሱ ሥጋ ቀርቦ አባቴ ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ አንተ ባለሟልነት እንዳለህ እኔ አውቃለሁ። ብትፈቅድስ ክፉዎች ተቃዋሚዎችን ልታሸንፋቸው ትችላለህ አለ። የቅዱስ ኤጲፉንዮስንም እጅ ይዞ ምድሩን መታባት በዚያንም ጊዜ ሁለቱ ዲያቆናት በግምባራቸው ተደፉ። ለመሞትም ደረሱ ወደ ቤታቸውም ወስደዋቸው ሞቱ።
ቅዱስ ኤጲፋንዮስንም ካህናቱ በሚጣፍጡ ሽቱዎች ገነዙት። በከበሩ ልብሶችም ጠቅልለው ከከበረ ደንጊያ በተሠራ ሣጥን ውስጥ ጨምረው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀበሩት። ቀድሞ በሕይወቱ ሳለ እንደሚሠራው ከሥጋው ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages