ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 27 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, June 6, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 27

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ግንቦት ሃያ ሰባት በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳኛ የሆነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ አረፈ፣ የማርያና የማርታ ወንድም ጻድቅ አልዓዛር አረፈ።


ሊቀ ጳጳስ አባ ዮሐንስ
ግንቦት ሃያ ሰባት በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳኛ የሆነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ደግ የተማረም ነበር። ከልጅነቱም ጀምሮ በገድል ተጠምዶ የሚኖር ነበር። ከዚህም በኋላ በዋሻ ውስጥ ራሱን እሥረኛ አደረገ። የትሩፋቱና የዕውቀቱም ዜና በተሰማ ጊዜ በእስክንድርያ አገር ላይ ይዘው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት። ብዙ ድርሳናትንም ደረሰ እግዚአብሔርም በዘመኑ የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን አጸና።
ይህ አባት በተሾመበት ወራት ደግ ምእመን አንስጣስዮስ የሚባል ንጉሥ ነበር። በአንጾኪያም የከበረ አባት አባ ሳዊሮስ ነበረ እርሱም ወደ አባ ዮሐንስ ስለ ቀናች ሃይማኖት እንዲህ ብሎ በመልእክቱ ውስጥ ጻፈ። ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተዋሕዶው በኋላ እንደ አባቶቻችን እንደ አባ ድሜጥሮስና እንደ አባ ዲዮስቆሮስ እምነት ያለ መቀላቀል ያለ መለወጥ ያለ መለያየትና ያለ መጨመር አንዲት ባሕርይ አለችው።
አባ ዮሐንስም መልእክቱን ተቀበለው ኤጲስቆጶሳቱም ሁሉ ተለያይተው የነበሩ ሕዋሳትም ተመልሰው አንድ ስለ ሆኑ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰገኑት።
ከዚህም በኋላ ለመልእክቱ መልስ አባ ዮሐንስ ለአባ ሳዊሮስ እንዲህ ብሎ ጻፈለት። ይኸውም ስለ መለኮትና ትስብእት የአንድ ባሕርይ ህልውና ስለ ወልደ እግዚአብሔር ያለ መለያየት ያለ መቀላቀልና ያለ መለወጥ ሁለት ያይደለ የሰውን ባሕርይ ከመለኮቱ ባሕርይ ጋራ አንድ አድርጎ በመዋሐድ ሰው ስለ መሆኑ።
ጌታችንንም የሚከፋፍሉትን ወይም ተጨመረበት የሚሉትን ወይም ስለእኛ መከራ ተቀብሎ ተሰቅሎ የሞተው ዕሩቅ ብእሲ ነው የሚሉትን በመለኮቱ ባሕርይ መከራ ተቀበለ የሚሉትን አወገዘ። የቀናች ሃይማኖትስ ይቺ ናት እግዚአብሔር ከእኛ በነሣው ሥጋ ስለ እኛ መከራ እንደ ተቀበለ እናውቃለን እኮን። ይቺም የሚጓዝባት የማይሳሳትባትና የማይደናቀፍባት የሕይወት መንገድ ናት አለ።
አባ ሳዊሮስም ይቺን የአባ ዮሐንስን መልእክት በአነበባት ጊዜ በመልካም አቀባበል ተቀበላት። በአንጾኪያ አገርም ሰበከባት ስለ ቀናች ሃይማኖትም በመካከላቸው ሰላም ፍቅርና ስምምነት ሆነ። ይህም አባት ሕዝቡን እያስተማረ ዐሥራ አንድ ዓመት ኑሮ ከዚህ በኋላ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ጻድቅ አልዓዛር
በዚችም ዕለት የማርያና የማርታ ወንድም ጻድቅ አልዓዛር አረፈ። ይህንንም ጻድቅ ሰው በአራተኛ ቀን ከመቃብር ከአስነሣው በኋላ በዚሁ ሳምንት ውስጥ መድኃኒታችን መከራ ተቀብሎ ተሰቅሎ ሞተ። ከትንሣኤውም በኋላ አልዓዛር ከሐዋርያት ጋራ አንድ ሆነ።
አጽናኝ መንፈስ ቅዱስም በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋራ ጸጋውን ተቀበለ። ሐዋርያትም በቆጵሮስ አገር ላይ በአንብሮተ እድ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት። መንጋውንም በመልካም አጠባበቅ ጠበቀ። በሹመቱም አርባ ዓመት ኑሮ በሰላም በፍቅር አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages