አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሰኔ ሦስት በዚች ቀን አባታችን ዜና ማርቆስ መታሰቢያቸው ነው፣ በትኅርምትና በተጋድሎ የጸናች ቅድስት ማርታ አረፈች፣ ቅዱስ ኤሳርዮስ የሚባል ኤጲስቆጶስ ሰማዕት ሆኖ አረፈ፣ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተጠምቀ መድኅን እረፍታቸው ነው፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስ
ሰኔ ሦስት በዚች ቀን አባታችን ዜና ማርቆስ መታሰቢያቸው ነው፡፡ ሀገራቸው ጽላልሽ አውራጃ ምድረ ዞረሬ ስትሆን ትውልዳቸው ከነገደ ሌዊና ከእስራኤል ነገሥት ወገን ነው፡፡ ወላጆቻቸው ልጅ በማጣት ሲያዝኑ አንድ ዕለት ሐዋርያውና ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ወደ እናታቸው ማርያም ዘመዳ ሌሊት መጥቶ ገድሉና ትሩፋቱ በዓለም ሁሉ የመላ ጻዲቅ ልጅ እንደምትወልድ ነገራት፡፡ ለአባቱ ለቀሲስ ዮሐንስም እንዲሁ ተገልጦለት ‹‹ሚስትህ ማርያም ዘመዳ የካቲት 24 ፀንሳ ኅዳር 24 ቀን ይኸውም በካህናተ ሰማይ በዓል ቀን ትወልዳለች፣ ስሙም ዜና ማርቆስ ይባላል›› በማለት ብስራቱን ነግሮታል፡፡
በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ብሥራት መሠረት አባታችን በተወለዱም ዕለት ቅዱስ ዑራኤልና ቅዱስ ሩፋኤል የብርሃን ልብስ አልብሰው በክንፋቸው ሲጋርዱአቸው ለሰዎችም ሁሉ ታይቷል፡፡ በወቅቱም የአባ ሳሙኤል ዘወገግ አባት እንድርያስና የአቡነ ተክለሃይማኖት አባት ቅዱስ ጸጋ ዘአብ እስኪደነቁ ድረስ ይህን በዓይናቸው ተመልክተዋል፡፡ ሁለቱ መላእክትም ከእናታቸው ዕቅፍ ወስደው ወደ ሐዋርያው ማርቆስ መቃብር ወስደው ለማርቆስና ለቅዱሳን ጳጳሳት አስባርከዋቸው መልሰው ለእናቱ ሰጧቸው፣ እናቱ ግን ይህን አታውቅም ነበር፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስም በተወለዱ በሦስተኛው ቀን በእግራቸው ቆመው ‹‹አንድ አምላክ ለሆኑ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ እሰግዳለሁ›› ብለው ሦስት ጊዜ አምላካቸውን አመስግነው ሰግደዋል፡፡ በ40 ቀኑ ሲጠመቅ የሚያጠምቀው ካህን የአባቱ ወንድም እንድርያስ ውኃው ሲፈላ አይቶ ሸሽቷል፡፡ መልአኩም እንዳይፈራ ነግሮት ለእርሱም ተአምር እንደሚደረግለት አስረዳው፡፡ እንድርያስም ዕድሜው 72 ነበርና ራሰ በራ ስለነበር በውኃውም ራሱን ቢታጠብበት ጸጉር አብቅሏል፡፡ ሕዝቡም ሁሉ ይህን አይቶ አደነቀ፡፡ ያችም ውኃ ሌሎች በጣም ብዙ ተአምራትን አደረገች፡፡
አንድ ዓመት በሆነውም ጊዜ ቤተክርስቲያን ውስጥ እየዳኸ ሲሄድ መልአክ በክንፎቹ አቅፎ ወስዶ ጌታችንና እመቤታችን ጋር አቅርቦት አስባርኮታል፡፡ እንዲሁም የ15ቱን ነቢያት፣ የ12ቱን ሐዋርያት የ72ቱን አርድእት፣ ሃይማኖታቸው የቀና የ318ቱን ሊቃውንት፣ የጻድቃንን፣ የሰማዕታትን የእነዚህን ሁሉ በረከት እንዲቀበል ካደረገው በኋላ ወደዚያች ቤተክርስቲያን መለሰው፡፡ ከጳጳሱ ከአቡነ ጌርሎስ ድቁናን ተቀብሎ ከአባቱ ጋር ወደ ሀገሩ ሲመለስ ዘራፊዎች ደብድበው በትራቸውንም ሳያስቀሩ ዘረፏቸው፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስም ወደ ፈጣሪው በጸለየ ጊዜ በትራቸው እባብ ሆና ነድፋ ገደለቻቸው፡፡ በኋላም ወደ አምላካቸው ጸልየው ከሞት እንዲነሱ በማድረግ በአካባቢውም ያሉ ሰዎች ሁሉ በእርሱ አምላክ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል፡፡
ከዚህም በኋላ ብሉያትንና ሐዲሳትን ጠንቅቆ ከተማረና ካደገ በኋላ ሚስት አጭተው አጋቡት፡፡ እርሱ ግን በዚያው በሠርጉ ዕለት ማታ ጌታ ‹‹እናትና አባቱን ሚስቱን ቤቱን ንብረቱን ያልተወ ሊያገለግለኝ አይችልም›› ያለውን ቃል አስቦ ሚስቱን እንዲህ አላት፡- ‹‹እኅት ሆይ! የዚህ ዓለም ኑሮ ምን ይጠቅመናል፣ ዓለሙም ፍላጎቱም ያልፋል፡፡ ስለዚህ የነፍሴን ድኅነት ለመሻት እሄድ ዘንድ አሰናብችኝ›› ሲላት እርሷም ‹‹አንተ የተውከው ዓለም ለእኔስ ምን ይጠቅመኛል?›› በማለት ሁለቱም ሰው ሳያያቸው ከጫጉላ ቤታቸው በሌሊት ወጥተው ሄዱ፡፡ ቅዱስ ዑራኤልና ቅዱስ ሩፋኤልም እየመራቸው ዜና ማርቆስን ምሁር ገዳመ ኢየሱስ እርሷን ደግሞ ወደ ቤተ ደናግል ማማስ ደብር አደረሷቸው፡፡ እርሷም ሙትን እስከማስነሣት ድረስ ታላላቅ ተአምራትን እያደረገች ቆይታ ተጋድሎዋን ፈጽማ በጥር 21 ቀን በክብር ዐርፋለች፡፡ ዐርፋ የተቀበችውም በደመና ተነጥቃ ኢየሩሳሌም ከሄደች በኋላ እመቤታችን በተቀበረችበት በጌቴሴማኒ ሲሆን ሁለት አንበሶች ጉድጓድ ቆፍረው ቀብረዋታል፡፡
አባታችንም በምሁር ሀገር ይመለክ የነበረውን ማኮስ የተባለውን ጣዖት በመሬት ውስጥ ቀበረውታል፡፡ ገዥውም ተቆጥቶ በአባታችን ላይ ክፉ ሲያደርግ ‹‹ካላመንክ አንተም እንደ አምላክህ እንደ ማኮስ መሬት ተከፍታ ትውጥሃለች›› ብሎ በተናገረበት ቅጽበት ገዥውን ከነሠራዊቱ መሬት ተከፍታ ዋጠቻቸው፡፡ ከዚያም ፈጥነውና በደመና ተነጥቀው ወደ ግብፅ በመሄድ ከአባ ብንያሚን ቅስና ተቀብለው መጡና መሬት ተከፍታ የዋጠችውን የገዥውን ቤተሰቦች ጨምሮ ብዙ ሺህ የምሁር ሕዝቦችን አስተምረው አጠመቋቸው፡፡ ያንን ገዥም ስለ ተጠመቁ ልጆቹና ሚስቱ ብለው ከ5 ዓመት በኋላ በጸሎታቸው ኃይል ከሞት አስነስተውታል፡፡ በዚሁ ሀገር ከአባ ዜና ማርቆስ ጋር ሳሉ የኢትዮጵያው ጳጳስ አባ ጌርሎስ በድንገት ዐርፈው ሳለ ጻዲቁ ዜና ማርቆስ ጸሎት አድርገው ከሞት አስነሥተዋቸዋል፡፡ ሌላም እንዲሁ በጉራጌ ሀገር ገርዳን የሚባለውን ጣዖት ሰባብረው በውስጡ የነበረውን ሰይጣንን እንደ ትቢያ በኖ እስኪጠፋ ድረስ አስጨንቀውታል፡፡ ሕፃናቱን ጨምሮ ከ124 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ሕዝቦችም አስተምረው አጥምቀዋቸዋል፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልም ሁልጊዜ እንደ ጓደኛ እያናገራቸው ይረዳቸው ነበር፡፡
አባታችን ዜና ማርቆስ የሚያደርጓቸው እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራት በሕዝብ ዘንድ ውዳሴን እያመጣ እንዳያስቸግራቸው ብለው ይህን ተአምር የማድረግ ሥራ እግዚአብሔር እንዲያርቅላቸው ይለምኑት ነበር፡፡ ወግዳ በምትባል ሀገር ሄደው በዋሻ ውስጥ ሳሉ አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ እርሳቸው መጥተው አብረው በዋሻው ብዙ ተአምራትን እያደረጉ ቆይተዋል፡፡ ለአባ ዜና ማርቆስና ለሌሎች ለብዙ አባቶች የምንኩስና አባት የሆኑት አቡነ ተክለሃይማኖት ትሕትናቸውን ያሳዩ ዘንድ አቡነ ዜና ማርቆስን ያገለግሏቸው ነበር፡፡ ወደ ሞረት ሀገር እንዲሄዱ መልአክ ነግሯቸው ሁለቱም ሄደው በዚያም አብረው ተቀምጠዋል፡፡ ጣዖት አምላኪውን የሞረቱ ገዥ ሊገድላቸው ፊልጎ ከነሠራዊቱ ወዳሉበት ዋሻ ሄደ፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስም ተራራዋን በሥላሴ ስም ባርከው ቢያዟት የገዥውን ጭፍሮች አፏን ከፍታ ዋጠቻቸው፡፡ ገዥውን ድል አሰግድንም በተአምራቸው አሳምነውት አስተምረው አጠመቁት፡፡
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ለአቡነ ተክለሃይማኖት ተገልጦላቸው ወደ ግራርያ ሀገር እንዲሄዱ ስለነገራቸው አቡነ ተክለሃይማኖት የመላእክትን አስኬማ ለአቡነ ዜና ማርቆስ አልብሰዋቸው ዜና ማርቆስንም በደብረ ብስራት እንዲጸኑ ነግረዋቸው ወደ ግራርያ ሄዱ፡፡ ሲሄዱም የደብረ ብስራት ዛፎቹ እንጨቶቹና ደንጊያዮቹ ሁሉ አቡነ ተክለሃይማኖትን እንደ ንጉሥ ሠራዊት ከፊት ከኋላ ሆነው ሸኝተዋቸዋል፡፡ አባታችንም ‹‹የወንድሜን የዜና ማርቆስን ቦታ ትታችሁ ከዚህች ምድር ትሄዱ ዘንድ አልፈቅድምና ሁላችሁ በየቦታችሁ ቁሙ›› ብለዋቸዋል፡፡ ‹‹ሰውም እንኳ ቢሆን ለምንኩስና ወደ እኔ ዘንድ ወደ ግራርያ ከመምጣቱ በፊት ይህን ምድር ሳይሳለም ወደ እኔ አይምጣ›› በማለት ቃልኪዳናቸውን ከደብረ ብስራት ጋር አድርገዋል፡፡
አባታችን ዜና ማርቆስ በኤልያስ ሠረገላ ሆነው እግዚአብሔርን ወደማያውቁት ወደ አዳል ሕዝቦች ሄደው ከጣዖት አምላኪው ንጉሥ ከአብደልማል ፊት ወንጌልን ሲያስተምሩ ንጉሡ በጦር ወግቶ ገድሏቸዋል፣ ነገር ግን መልአኩ ሩፋኤል መጥቶ ከሞት አሥተስቷቸዋል፡፡ የንጉሡን ጣዖትና አገልጋዮቹን መብረቅ ከሰማይ ወርዶ ሲያጠፋቸው ንጉሡ ሠራዊታቸው ደግሞ በመሬት ላይ ወድቀው ቀርተዋል፡፡ ከዓርብ እስከ ሰኞም ድረስ ጨለማ ሆኖ ከቆየ በኋላ ከአባታችን ከተወጋ ጎናቸው የፀሐይ ብርሃን ወጥቶ ለንጉሡ አብደልማል አብርቶለታል፡፡ እርሱም አምኖ ከነቤተሰቡ የተጠመቀ ሲሆን ሚስቱም በአረማውያን ዘንድ ለክርስቶስ ምስክር ሆና አንገቷን ተሰይፋ ሰማዕትነትን ተቀብላለች፡፡ በሀገሪቱም የተጠመቁት ሰዎች ቁጥር ከስምንት መቶ ሺህ በላይ ናቸው፡፡
ከዚህም በኋላ አቡነ ዜና ማርቆስ እንደ ሐዋርያትም ደመና በመጥቀስ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ሄደው ሁሉንም የተቀደሱ ቦታዎችን ተሳልሟዋል፡፡ ከጌታችን መቃብር ላይ አፈር ዘግነው ከዮርዳኖስም ወንዝ ውኃ ቀድተው ለንስር አሞራዎች አሸክመው ወደ ገዳማቸው በማምጣት በደብረ ብስራት ምድር ካለው አፈርና ውኃ ጋር ጨምረውታል፡፡ ጌታችም ‹‹ይህችን ምድርህን እንደ ኢየሩሳሌም አድርጌልሃለሁ›› የሚል ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ አባታችን ከደብረ ሊባኖስ አውራጃ ራሱን ያስመልክ የነበረን ሰይጣን ገዝተው ይዘው እስከ ደብረ ብስራት ድረስ የቤተክርስቲያን መሥሪያ እንጨት አሸክመውታል፡፡ በዚያም እንጨት በመሸከም ሲያገለግላቸው ኖሯል፡፡
አባታችን ዜና ማርቆስ ወደ ዋልድባ በመሄድ ከአባ ሳሙኤል ጋር ተገናኝተው እንዲሁም ከሌሎች በርካታ አባቶች በየቦታው እየሄዱ በረከት ተቀብለዋል፡፡ ወደ ትግራይም በመሄድ የተሰዓቱ ቅዱሳንን ገዳማት ተሳልመው ወደ ሰሜንም ሄደው ዜማውን ሲያዜም ያሳያቸው ዘንድ ወደ ቅዱስ ያሬድ መቃብር ሄደው ሰባት ቀን ሲማጸኑ ከቆዩ በኋላ ወደ አክሱም ጽዮን ሄደው በዚያ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱስ ኤፍሬምና ከቅዱስ አባ ሕርያቆስ ጋር ሆኖ እነርሱ ድርሰታቸውን ሲያነቡ ያሬድ ደግሞ ድርሰታቸውን እያዜመው ተገልጠውላቸዋል፡፡ አባታችን ወደ ላሊበላም ሄደው ከቅዱስ ላሊበላ በረከትን ተቀብለዋል፡፡ ወደ ጣና ደሴትም ሄደው በዚያ ካሉ ቅዱሳን ተባርከዋል፡፡ ሐይቅ እስጢፋኖስም አባ ኢየሱስ ሞዐ ጋር በመሄድ እንዲሁ ተባርከዋል፡፡ በታናሽ ደመናም ወደ ብሔረ ሕያዋን ተነጥቀው ሞትን ካልቀመሱት ከሄኖክ፣ ከኤልያስና ከዕዝራ በረከትን ተቀብለዋል፡፡ ወደ እስላም ሀገርም በመሄድ ለአንድ ዓመት ቆይተው በዚያ ያሉ ሕዝቦችን በተአምራቸውና በትምህርታቸው አሳምነው አጥምቀዋቸዋል፡፡ ጌታችን በምድር ላይ ብዙ ቃልኪዳን ከሰጣቸው በኋላ ወደ ሰማይ አውጥቶ ገነትንና ሲኦልን ሁሉን አሳይቷቸዋል፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስ 8 እንጀራን አበርክተው 8ሺህ ሰዎችን በመመገብ ጌታችንን መስለውታል፡፡ ቀድሰው ሕዝቡን ሁሉ ሲያቆርቡ ቢመሽባቸው ፀሐይን እንደ ኢያሱ ገዝተው አቁመዋታል፡፡ በታኅሣሥ ወር መባቻ አባታችን በገዳመ ደንስ በረሃ ያገኛት ተአምረኛዋ ሥዕለ ማርያም ወዳለችበት ቤተክርስቲያን ሄደና ለመቀደስ ሠራዒ ካህን ሆኖ ተሠየመና እንደሚገባ የቅዳሴውን ሥርዓት ጀመረ፡፡ ማዕጠንት ይዞ እየዞረ የቤተ ክርስቲያኑን በሮች በሚያጥንበት ጊዜ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል እርስ በእርሳቸው ሲጨናነቁ የልጆቹ መነኮሳትን ብዛት ተመለከተ፡፡ ያን ጊዜም በልቡ አሰበ፣ እንዲህም አለ፡- ‹ይህን ያህል ያለውን ሰው ቅዱስ ቊርባን ማቀበል እንዴት ይቻላል? ይህ ሁሉ ሰው በተራ እስከሚቀበል ድረስ ፀሐይ ይገባል፣ መሽቶ ሌሊትም ይሆናል› አለ፡፡ ከዚህም በኋላ ዐይነ ልቡናውን ወደ ሰማይ አቅንቶ ‹አቤቱ ጠላቶቹን እስከደመሰሰና ለእስራኤል ልጆች ርስታቸውን እስካካፈለ ድረስ ለኢያሱ ፀሐይን በገባዖን ያቆምክ አንተ ነህ፤ ዛሬም ቅዱስ ሥጋህን ክቡር ደምህን ለእነዚህ ባሮችህ ቅዱሳን መነኮሳትና ለሕዝቦችህ እስከማቀብላቸው ድረስ እንዲሁ በቸርነትህ ብዛት ፀሐይን አቁማት› ብሎ በጸለየ ጊዜ ፀሐይዋ ወዲያውኑ ቆመች፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዳሴውን ጨርሶ ሕዝቡን ሁሉ አቆረባቸው፡፡››
ቅዱስ አባታችን በምሁር ኢየሱስ ገዳም ከሬብ በሚባል ዋሻ ውስጥ 40 ዓመት ዘግተው ተጋድለዋል፡፡ በዚህም ሳሉ መልአክ የዕረፍታቸውን ዕለት ታኅሣሥ ሦስት ቀን እንደሚሆን ስለነገራቸው ታኅሣሥ አንድ ቀን ወደ ገዳማቸው በመሄድ ቀድሰው ሕዝቡን ሁሉ ሲያቆርቡ ቢመሽባቸው ፀሐይን ለሁለተኛ ጊዜ እንደ ኢያሱ ገዝተው አቁመዋታል፡፡ አባታችን ዜና ማርቆስ የዕረፍታቸውን ዕለት ከመልአኩ ከተረዱ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አሏቸው፡- ‹‹ከዚህ ዓለም የምለይበት ጊዜ ደርሷልና ወደ ፈጣሩዬ እሄዳለሁ፣ እኔ ሽማግሌ አባታችሁ የምመክራችሁን ስሙ፣ ከበጎ ሥራ ሁሉ አስቀድማችሁ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ፣ ፍቅር ሰማያዊ መንግሥትን ለማግኘት በባለሟልነት ወደ እግዚአብሔር ፊት ያደርሳልና›› ብለው መከሯቸው፡፡ ዳግመኛም ጾመኛ ነኝ አትበሉ አሏቸው፡፡ ‹‹ስለ ነፍሳችሁ ድኅነት፣ ከመከራና ከጥፋትም ሁሉ ለማምለጥ በምትጾሙ ጊዜ እንዲህ እየጾማችሁ ሳላችሁ ስለምትሹት ግብር ወደ ዓለም ሰዎች ብትደርሱና በጾም ቀን ሲበሉና ሲጠጡ ብታዩአቸው መብልና መጠጥን በሚወዱ ሰዎች ፊት በውጭ በአደባባይ ‹ዛሬ የጾም ቀን ስለሆነ እኛ እንጾማለን› አትበሉ፡፡ ስለ እናንተ መጾምና ስለ እነርሱም አለመጾም አንዳች አትናገሩ፣ ባለመጾማቸውም አትንቀፏቸው፡፡ ስለ ሌላ ሥራ ወደማይጾሙ ሰዎች ብትደርሱ ግን በጾም ዕለት ወንድሞቻችን ‹ኑ አብረን እንብላ› ቢሏችሁ እኛ እንጾማለን አትበሉ፣ እንዲህ በሉ እንጂ፡- ‹ወደ እናንተ ከመምጣታችን በፊት ከቤት በልተናል፣ ጠግበናል› ስትሏቸው እናንተ እንደምትጾሙ ያውቃሉ፡፡›››
ከዚህም በኋላ አቡነ ዜና ማርቆስ ታኅሣሥ ሁለት ቀን የደቀ መዛሙርቶቻቸውን እግር ሲያጥቡ ውለው አስቀድሞ መልአኩ እንደነገራቸው ታኅሣሥ ሦስት ቀን በ140 ዓመታቸው ነቢይም፣ ሐዋርያም፣ ካህንም፣ ባለራእይም፣ የሀገራችንም ብርሃን የሆኑት ጻዲቁ አባታችን በክብር ዐርፈዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅድስት ማርታ ተሐራሚት
በዚህች ቀን በትኅርምትና በተጋድሎ የጸናች ቅድስት ማርታ አረፈች። ይቺም ቅድስት ከምስር ተወላጆች ውስጥ ነበረች ወላጆቿም እጅግ ባለጸጎች ነበሩ ከታናሽነቷም ጀምራ የረከሰ ዝሙትን የምትወድ ነበረች የከተማ ጐልማሶችና ታላላቆችም በሥውር ወደርሷ እየመጡ ያመነዝሩ ነበር። ከዚህ በኋላም ሥራዋ ተገለጠ የርኲሰት ሥራንም በግልጥ አብዝታ የምትሠራ ሆነች።
ክብር ምስጋና ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የከበረ ልደቱ በዓል በሆነ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔደች ልትገባም በፈለገች ጊዜ የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ከለከላት እንዲህም አላት አንቺ በምግባር የረከስሽ ስለሆነ ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መግባት አይገባሽም ይተዋትም ዘንድ አባበለችው እርሱ ግን ከለከላት በመካከላቸውም ታላቅ ጸብ ሆነ።
ኤጲስቆጶሱም ጩኸት ሰምቶ ተነሥቶ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ደጃፍ ደረሰ ማርታንም በአያት ጊዜ የእግዚአብሔር ቤቱ የከበረና የነጻ እንደ ሆነ አታውቂምን አንቺም የረከስሽ ስለሆንሽ ወደ እግዚአብሔር ቤት ትገቢ ዘንድ አይገባሽም አላት።
በዚያን ጊዜም አለቀሰች ንስሓ እገባለሁ እንጂ ወደዚህ ሥራ እንግዲህ አልመለስም ብትቀበለኝም እመነኲሳለሁ አለችው። ኤጲስቆጶሱም ገንዘብሽንና ጥሪትሽን ሁሉ ወደዚህ አምጥተሽ በፊትሽ ካላቃጠልነው አላምንሽም አላት።
ያን ጊዜም ሒዳ ጥሪቷንና ዋጋው ብዙ የሆነ ጌጥዋን አምጥታ በኤጲስቆጶሱ ፊት ጣለችው እርሱም በፊቷ አቃጠለው።
ከዚህም በኋላ የራስዋን ጠጉር ተላጨች ኤጲስቆጶሱም ማቅ አልብሶ ወደ ደናግል ገዳም ላካት በዚያም ታላቅ ተጋድሎን በፍጹም ልቧ ጀመረች ነፍሷንም እንዲህ እያለች ትገሥጻት ነበር በጭቃና በደንጊያ ወደ ታነፀው ቤት ለመግባት ካልተውሽ በብርሃን ወደ ተሠሩ ቤቶችማ ለመግባት እንዴት ትሆኛለሽ ሁለተኛም በጸሎቷ አቤቱ ቤተ ክርስቲያንህን ከሚጠብቀው የደረሰብኝን ኀፍረት ልሸከመው ያልቻልኩ እኔን በቅዱሳን መላእክቶችህ ፊት አታሳፍረኝ አለች።
ይችም ቅድስት ሰይጣንን ድል እስከ አደረገችው ድረስ ሃያ አምስት ዓመት ስትጋደል ኖረች በዚህ ሁሉ ከገዳም ግቢ ወደ በር አልወጣችም ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አሳርዮስ ሰማዕት
በዚህችም ቀን ደግሞ ኤላርዮስ የሚባል ኤጲስቆጶስ ሰማዕት ሆኖ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከሀዲውን ንጉሥ ዮላኪዮስን ጣዖታትን ስለማምለኩ ይገሥጸውና ይመክረው ነበር ንጉሥ ዮላኪዮስም አይሁድ የሰቀሉትን ባለማምለኬ አንተ ከሀዲ ትለኛለህ እነሆ አሁን እኔ አንተን ከሥቃይ ጽናት የተነሣ ያን የተሰቀለውን አምልኮቱን አስተውኻለሁ አለው።
ከዚህ በኋላም ከመኳንንቶቹ ለአንዱ መኰንን ሰጥቶ ባለመራራት ያለማቋረጥ ሁልጊዜ እንዲአሠቃየው አዘዘው መኰንኑም ወስዶ በየራሱ በሆነ ሥቃይ አንዲት ቀን እንኳ ከቶ ሳያቋርጥ ሁልጊዜ እያሠቃየው አንድ ዓመት ሙሉ ኖረ።
በዓመቱም ፍጻሜ በእሳት ውስጥ ጣሉት እርሱም ከእሳት መካከል ቆሞ እግዚአብሔርን ፈጽሞ እያመሰገነ ጸለየ ስለዚህችም ምልክት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ብዙዎች አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።
ከዚህም በኋላ ከአታክልት መካከል እንደ ሚወጣ ሆኖ ከእሳት አወጡት። መኰንኑም ከማሠቃየት በደከመ ጊዜ በእርሱ ላይም የሚያደርገውን በእጣ ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡት አዝዞ ቂረጡት በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ ተጠምቀ መድኅን
በዚህች እለት ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተጠምቀ መድኅን መታቢያቸው ነው፡፡ ጻድቁ የተወለዱት በአፄ ሱስንዮስ ዘመን በ1610 ዓ/ም ሲሆን ወላጆቻቸው ወልደ ክርስቶስና ወለተ ማርያም ይባላሉ:: ታሕሳስ 2 ቀን እንደ መወለዳቸው ክርስትና የተነሱት ጥር 11 ቀን ነበርና ካህኑ "ተጠምቀ መድኅን" አላቸው:: በምድረ ጐጃም ከበቀሉ ታላላቅ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አባ ተጠምቀ መድኅን ገና ከሕጻንነታቸው ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር የጠራቸው ነበሩ::
ሕጻን እያሉ ቃለ እግዚአብሔር መማር ቢፈልጉም አባታቸው በግድ እረኛ አደረጋቸው:: እርሳቸው ግን በሕጻን ልባቸውም ቢሆን ቤተሰብን ማሳዘን አልፈለጉም:: ይልቁኑ ወደ በርሃ ይወርዱና አንበሳውን፣ ነብሩን፣ ተኩላውን ሰብስበው "በሉ እኔ ልማር ልሔድ ስለ ሆነ እስከ ማታ ድረስ ጠብቁልኝ" ብለው ለአራዊቱ አደራ ይሰጣሉ:: አራዊቱ ከበጉ፣ ከፍየሉ፣ ከላሙ ጋር ሲቦርቁ ይውላሉ:: ተጠምቀ መድኅን ደግሞ ዳዊቱን ወንጌሉን ሲማሩና ሲጸልዩ ውለው ማታ ይገባሉ::
ተጠምቀ መድኅን በሕጻንነታቸው ቁርስና ምሳቸውን ለነዳያን በመስጠት በቀን አንድ ማዕድ ብቻ ይቀምሱ ነበር:: 23 ዓመት ሲሞላቸው ወደ መርጡለ ማርያም ሔደው መንኩሰዋል::
ከዚህ ጊዜ በሁዋላ ለ37 ዓመታት በፍጹም ተጋድሎ ኖረዋል፣ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው አገልግለዋል፣ ከጐጃም እስከ ሱዳን ድረስ ወንጌልን ሰብከው በርካቶችን አሳምነው አጥምቀዋል (ካህን ናቸውና) እንዲሁም "7" ገዳማትንና "12" አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል::
ጻድቁ በተሰጣቸው መክሊት አትርፈው በ60 ዓመታቸው በ1670 ዓ/ም (በአፄ ዮሐንስ ዘመን) ጻድቁ ዐርፈዋል:: እግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን የገባላቸው ሲሆን አጽማቸው ዛሬም በጋሾላ ቅዱስ ጊዮርጊስ የእናቶች ገዳም ውስጥ ይገኛል::
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ
No comments:
Post a Comment