ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 6 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, June 13, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 6

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሰኔ ስድስት በዚች ዕለት ከእስክንድርያ ከተማ የሆነ መነኮስ አባ ቴዎድሮስ በሰማዕትነት ሞተ፣ ቅዱሳን አውሳብዮስ ታማን ሐርዋግና ባኮስ የተባሉ የሀገረ እስና አራት መኳንንት የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው።


መነኮስ አባ ቴዎድሮስ
ሰኔ ስድስት በዚች ዕለት ከእስክንድርያ ከተማ የሆነ መነኰስ አባ ቴዎድሮስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም የታመነና ንጹሕ ቅዱስ ተጋዳይ በእስክንድርያ ከሚገኙ ገዳማት በአንዱ በመልካም ገድል ተጠምዶ ኖረ።
ታናሹ አርዮሳዊ ቈስጠንጢኖስ በነገሠ ጊዜ አርዮሳዊ ጊዮርጊስን በእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት አድርጎ ሾመው። ሐዋርያዊ ቅዱስ አትናቴዎስንም ከመንበሩ አሳደደው ይህ አርዮሳዊ ጊዮርጊስም በማርቆስ ወንበር ላይ ሲቀመጥ ያን ጊዜ በአርዮሳውያንና በእስክንድርያ ምእመናን መካከል ታላቅ መተላለቅ ሆነ ሃይማኖታቸው የቀና ብዙዎች ምእመናንም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተገደሉ።
ከዚህ በኋላም ይህ አርዮሳዊ ጊዮርጊስ ስለ አባ ቴዎድሮስ እርሱ እርዮሳውያንን ተከራክሮ እንደሚአሸንፋቸው ከቅዱሳት መጻሕፍትም ማስረጃ በማምጣትና በማስፈረድ ያሳፍራቸው ነበር ያን ጊዜ ይህን መነኰስ አባ ቴዎድሮስን ይዘው በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ እንዲአሠቃዩት አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት ግን ምንም ምን ጉዳት አልደረሰበትም።
ከዚህ በኋላም ኃይለኞች ሩዋጮች በሆኑ ፈረሶች ላይ እግሮቹንና እጆቹን አሥረው በሰፊ ሜዳ ውስጥ እንዲአስሮጡአቸው አዘዘ ይህንንም በአደረጉ ጊዜ ሕዋሳቱ ሁሉ ተበጣጠሱ ራሱም ተቆረጠች እንደዚህም ሁኖ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።
ሦስት አክሊላትንም ተቀዳጀ አንዱ ድንግልናውን ጠብቆ ስለ መመንኰሱ ሁለተኛው ሃይማኖትን ስለ ማስተማሩና ተከራክሮ መናፍቃንን ስለመመለሱ ሦስተኛውም ስለ ቀናች ሃይማኖት ደሙን በማፍሰሱ ነው።
ከዚህም በኋላ ምእመናን የተቆራረጡና የተበተኑ ሕዋሳቱን ሰብስበው በሣጥን ውስጥ አደረጓቸው በዚች ዕለትም መታሰቢያ በዓሉን አደረጉ እንደ ሌሎቹ ቅዱሳን ሁሉ የምስጋና ድርሰትን በሮማይስጥ ቋንቋ ደረሱለት በጸሎት መጽሐፋቸውም ውስጥ ጻፉት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱሳን አውሳብዮስ ታማን ሐርዋግና ባኮስ
ዳግመኛም በዚህች ቀን አውሳብዮስ ታማን ሐርዋግና ባኮስ የተባሉ የሀገረ እስና አራት መኳንንት የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው።
እሊህም ቅዱሳን ለእስና አገር ምሰሶዎቿ ነበሩ ጸሐፊዎቿም ነበሩ ለብዙዎች ድኆችና ምስኪኖች ይመጸውቱ ነበር። ወደዚያች አገርም መኰንኑ አርያኖስ ዳግመኛ በተመለሰ ጊዜ እኛ ክርስቲያን ነን ክብር ይግባውና ሰማይና ምድር በጸኑበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን በማለት በግልጥ በፊቱ እየጮኹ ተቀበሉት። አርያኖስም ሰምቶ በየራሱ በሆነ ሥቃይ አሠቃያቸው ከዚህም በኋላ ራሶቻቸውን በሰይፍ ቆረጠ የምስክርነትን አክሊል ተቀበሉ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን። በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages