ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 7 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, June 13, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 7

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሰኔ ሰባት በዚህች ቀን ዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ እረፍቱ ነው፣ ቀሊን ከምትባል አገር ቅዱስና ቡሩክ ድል አድራጊም የሆነው አባ አበስኪሮን በሰማዕትነት ሞተ።


ዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ
ሰኔ ሰባት በዚህች ቀን ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ እረፍቱ ነው። ይህም ቅዱስ አባት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በደራሲነታቸው በወንጌል አገልግሎታቸውና በቅድስናቸው ከተመሠከረላቸው ዐበይት ሊቃውንት አንዱ ነው።
ሊቁ የተወለደው መጋቢት 27 ቀን በ433 ዓ/ም ሲሆን ሃገሩ ሶርያ ነው:: ወላጆቹ ክርስቲያኖች ለዚያውም አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር:: ቅዱስ ያዕቆብ ገና በልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር የጠራው ነውና በብዙ ነገሩ የተለየ ነበር::
አንድ ቀን በዕለተ ሰንበት ገና በ3 ዓመቱ እናቱ አቅፋ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደችው:: ምዕመናን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበሉ ሕጻኑ ያዕቆብም ይቆርብ ዘንድ ቀረበ:: ሊቀ ጳጳሱ ደሙን በዕርፈ መስቀል ሊያቀብለው ሲል መልአኩ መጥቶ "በጽዋው ጋተው" አለው።
የጌታን ደም በጽዋ ቢጠጣ ምስጢር ተገለጸለትና "አንሰ እፈርሕ ሠለስተ ግብራተ - እኔስ 3 ነገሮች ያስፈሩኛል" ሲል አሰምቶ ተናገረ። ጳጳሱና ሕዝቡ ወደ ሕጻኑ ያዕቆብ ቀርበው "ምን ምን?" አሉት። እርሱም:- ነፍሴ ከሥጋየ ስትለይ፣ ቅድመ እግዚአብሔር ለፍርድ ስቀርብ እንዲሁም ከፈጣሪየ የፍርድ ቃል ሲወጣ" አላቸው። ያን ጊዜ ሕዝቡና ሊቀ ጳጳሳቱ "እግዚአብሔር በዚሕ ሕጻን አድሮ ዘለፈን" እያሉ ለንስሃ በቅተዋል።
ቅዱስ ያዕቆብ 7 ዓመት ሲሞላው ይማር ብለው ወደ ጉባዔ አስገቡት። በ5 ዓመታት ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቆ በ12 ዓመቱ ሊቅ ሆኗል። በዚህ ወቅት የነበሩ ታላላቅ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ እርሱ ተሰበብስበው "እንግዳ ድርሰት ድረስልን። አዲስ ምሥጢር ንገረን" አሉት። እርሱ ግን ሲቻለው ስለ ትሕትና "አልችልም" አላቸው። "እንግዲያውስ ትንቢተ ሕዝቅኤልን ተርጉምልን" ቢሉት ባጭር ታጥቆ አመሥጥሮላቸው ተደስተዋል። ፈጣሪንም አመስግነዋል::
ቅዱስ ያዕቆብ ከዚህ በኋላ ወደ ገዳም ገብቶ ትሕርምተ አበውን፣ ዕጸበ ገዳምን፣ ሕይወተ ቅዱሳንን በተግባር ተምሯል። በድንግልናው ጸንቶ ጾምና ጸሎትን እያዘወተረ ኑሯል። በፈቃደ እግዚአብሔር የሥሩግ (በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል የምትገኝ የሶርያ ግዛት ናት) ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሟል::
ቅዱስ ያዕቆብ በዘመኑም የ451ን የኬልቄዶን ጉባኤ አውግዟል፣ ብዙ መናፍቃንን ተከራክሮ ምላሽ አሳጥቷል፣ በወንጌል አገልግሎት መልካም እረኝነቱን አሳይቷል፣ዛሬ የምንገለገልበትን መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::
በመጨረሻም ከብዙ የተጋድሎና የቅድስና ዓመታት በኋላ በተወለደ በ72 ዓመቱ በ505 ዓ/ም በዚህች ቀን አርፏል:: አንዳንድ ምንጮች ደግሞ ሰኔ 27 ቀን እንዳረፈ ይናገራሉ:: ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ለቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ተወዳጅ ልጇ ነውና በእጅጉ ታከብረዋለች::
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አባ አበስኪሮን
ዳግመኛም በዚህች ቀን ቀሊን ከምትባል አገር ቅዱስና ቡሩክ ድል አድራጊም የሆነው አባ አበስኪሮን በሰማዕትነት ሞተ።
ይህም ቅዱስ ከእንዴናው ገዥ ከአርያኖስ ጭፍራ ውስጥ ነበር የከሀዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ ስለ አምልኮ ጣዖት የሆነች ትእዛዙ በደረሰች ጊዜ። ወዲያውኑ ይህ ቅዱስ በሕዝብ መካከል ተነሥቶ ንጉሡን ረገመው ጣዖታቱንም ሰደበ ወታደር ስለ ሆነም ያሠቃየው ዘንድ ማንም አልደፈረም ነገር ግን በንጉሥ አዳራሽ ውስጥ አሠሩት።
መኰንኑም ወደ ሀገረ አስዩጥ በሔደ ጊዜ ወደ ንጉሥ ላከው ከእርሱም ጋራ ሌሎች ወልፍዮስ፣ አርማንዮስ፣ አርኪያስ፣ ጴጥሮስ፣ ቀራንዮስ የተባሉ ነበሩ እሊህም ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደማቸውን ሊአፈሱ ከአባ አበስኪሮን ጋራ ተስማሙ።
በንጉሡም ፊት በቆሙ ጊዜ በጌታችን ታመኑ ንጉሡም ትጥቃቸውን ይቆርጡ ዘንድ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይም እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ ንጉሡ እንዳዘዘም አደረጉባቸው። ከእኒህ ከአምስቱ ግን ራሶቻቸውን የቆረጡአቸው አሉ የሰቀሉአቸውም አሉ እንዲህም ገድላቸውን ፈጽመው የሕይወት አክሊልን ተቀበሉ።
የከበረ አበስኪሮስን ግን ታላቅ ግርፋትን እንዲገርፉት አዘዘ ከዚያም በኋላ ከራሱ እስከ አንገቱ ቆዳውን እንዲገፉ በፈረስ ጅራትም አሥረው በከተማው ውስጥ እንዲጐትቱት አዘዘ ይህንም ሁሉ አደረጉበት።
ከዚህም በኋላ በብረት ምጣድ ውስጥ አድርገው በላዩ አፉን ዘግተው ተሸክመው ወስደው በውሽባ ቤት ማንደጃ ውስጥ ጨመሩት በሥቃዩም ውስጥ ሁሉ የእግዚአብሔር መልአክ ወደርሱ ይመጣና ያጽናናው ነበር ያስታግሠውም ነበር ያለ ምንም ጉዳት አድኖ በደኅና ያስነሣው ነበር።
ከማሠቃየቱም በደከመ ጊዜ ከሥራየኞች ሁሉ የሚበልጥ በሥራዩም ወደ አየር ወጥቶ ከአጋንንት ጋራ የሚነጋገር ሥራየኛ አመጣለት። እርሱም የውሽባ ቤቱን ዘግተው ሽንት እንዲረጩበት አዘዘ እንዲሁም አደረጉ። እባብንም ይዞ በላዩ አሾከሾከና ለሁለት ክፍልም ሁኖ ተሠነጠቀ መርዙንና ሆድ ዕቃውን ወስዶ በብረት ወጭት አድርጎ አበሰላቸው በውሽባ ቤቱ ውስጥ ወደ አባ አበስኪሮን አቅርቦ ያንን መርዝ ይበላ ዘንድ ሰጠው ቅዱሱም በላ ግን ምንም ምን ጉዳት አልደረሰበትም።
ያም መሠርይ የመኳንንተ ጽልመት አለቃቸው ሆይ በዚህ ክርስቲያናዊ ላይ ኃይልህን አድርግ ብሎ ጮኸ ምንም ምን ጥፋት ባልደረሰበት ጊዜ መሠርዩ አደነቀ።
ቅዱስ አበስኪሮንም መሠርዩን የሚራዳህ ሰይጣንህስ በክብር ባለቤት በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃያል አንተን ይቀጣሃል አለው። ወዲያውኑ ጥሎ የሚያንከባልለው ክፉ ሰይጣን ተጫነበት ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ታመነ ድረስ አሠቃየው። መኰንኑም የመሠርዩን ራስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና በሰማዕትነት ሞተ።
በቅዱስ አበስኪሮን ላይ ግን ቁጣና ብስጭትን በመጨመር ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው አባለ ዘሩንም እንዲቆርጡ አዘዘ እርሱ ግን በመከራው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር። ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡት የድል አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ከቅዱስ አበስኪሮን ተአምራትም አንዱን አንነግራችኋለን በግብጽ ደቡብ በስሙ የታነፀች ቤተ ክርስቲያን ነበረች ካህናቷም ከፉ ሥራ የሚሠሩ ክፉዎች ነበሩ ቅዱስ አበስኪሮንም ከክፋታቸው ተመልሰው ንስሓ ቢገቡ ብሎ ጠበቃቸው። ባልተመለሱ ጊዜ ግን የንዳድ በሽታ አምጥቶ ሁሉም በአንዲት ጊዜ ሞቱ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ አበስኪሮን ተቀምጦ የላዕላይ ግብጽ የሆነች ብያሁ ወደምትባል አገር ደረሰ የአገር ሰዎችም በደጃቸው ተቀምጠው ሳይተኙ በጨረቃ ብርሃን እርስ በርሳቸው ያወሩ ነበር። የከበረ አበስኪሮንም ከፊታቸው ደርሶ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው በአዩትም ጊዜ የሰላምታውን አጸፋ እየመለሱ ተነሥተው ተቀበሉት ሁለተኛም ያቺን የሚሻትን ምድር እያመለከታቸው ከምድራችሁ ጥቂት እንድትሰጡኝ እሻለሁ አላቸው እነርሱም ጌታችን እንደወደድክ ይሁንልህ አሉት መቶ የወርቅ ዲናርም ሰጥቷቸው ተሠወራችው።
እነርሱም ከዚህ ራእይ የተነሣ አደነቁ። ከተኙ በኋላም ቤተ ክርስቲያኒቱን አፍልሶ ከግብጽ ደቡብ ወደ ላዕላይ ግብጽ ብያሁ ወደምትባል አገር በመቶ የወርቅ ዲናር ወደ ገዛት ምድር ከንዋየ ቅድሳቷ ሁሉና ከዐፀዷ ጋር አምጥቶ በዚያ አቆማት።
የአገር ሰዎችም በጥዋት ነቅተው ወደ ውጭ በወጡ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን በደጃቸው አገኙዋት እጅግ ፈጽሞም አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት። ከዚያች ጊዜ ጀምሮ ድንቅ ተአምር የሚደረግባት ሆነ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages