በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን 10 ዓይነት ጉባኤ ቤቶች አሉ።እነዚህም፦
1ኛ=የቁጥር ትምህርት ቤት፦
በዚህ ጉባኤ ቤት ከፊደል ጀምሮ ውዳሴ ማርያም መልክአ ማርያም መልክአ ኢየሱስን እና አንቀጸ ብርሃንን በቃል የሚያጠኑበት ክፍል ነው። የዮሐንስ ወንጌልንና መዝሙረ ዳዊትን እንዲሁም መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞንና መኃልየ ነቢያትን በንባብ የሚማሩበት ጉባኤ ቤት ነው።
2ኛ= የዜማ (ድጓ) ጉባኤ ቤት:-
ይኽውም ከውዳሴ ማርያም ጀምሮ ምዕራፉን ጾመ ድጓውን እና ድጓውን በዜማ የሚማሩበት ጉባኤ ነው። የአጫብር ዜማ፣ የቤተልሔም ዜማ፣ የቆማ ዜማ እየተባለ ይከፋፈላል።
3ኛ=የዝማሬ መዋስእት ጉባኤ ቤት:-
ይህ ደግሞ ቅዱስ ያሬድ ከደረሳቸው መንፈሳዊ ድርሰቶች ሁለቱ ማለትም ዝማሬ መዋስእት የሚሰጥበት ጉባኤ ቤት ነው።
4ኛ=የቅዳሴ ጉባኤ ቤት:-
ይህ ደግሞ የቅዳሴ እና የሰዓታት እንዲሁም ሌሎች የቅዳሴ ጓዝ የሆኑ ትምህርቶች የሚሰጥበት ጉባኤ ቤት ነው። የደብረ ዓባይ ቅዳሴ እና የሰደድኩላ ቅዳሴ ተብሎ ይከፋፈላል።
5ኛ= የአቋቋም ጉባኤ ቤት:-
ይህ ደግሞ በክብረ በዓላት ጊዜ እንዲሁም እሑድ እሑድ በሚቆመው መዝሙር የሚባል የማኅሌት ትምህርት ነው። በዚህ ጉባኤ ቤትም ጸናጽል አጣጣልን ጨምሮ ወረቡን ዝክረ ቃሉን መዳልውን ወዘተ የሚማሩበት ጉባኤ ቤት ነው። ይህም የላይ ቤት አቋቋም፣ የታች ቤት አቋቋም፣ የሳንኳ አቋቋም፣ የተክሌ አቋቋም፣ የቤተማርያም አቋቋም ተብሎ ይከፋፈላል።
6ኛ=የቅኔ ጉባኤ ቤት:-
ግእዝ ቋንቋን ጠንቅቀን የምንማርበት ከዚህም አልፎ ተራቅቀን አምላካችንን በአዲስ ድርሰት የምናመሰግንበት የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ የፍልስፍና ትምህርት ነው። የዋሸራ ቅኔ፣ የጎንጅ ቅኔ፣ እና የዋድላ ቅኔ በመባል ይከፈላል።
7ኛ=የመጻሕፍተ ብሉያት ትርጓሜ ጉባኤ ቤት:-
ይህ ደግሞ 46ቱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የሚተረጎሙበት ጉባኤ ቤት ነው።
8ኛ=የመጻሕፍተ ሐዲሳት ጉባኤ ቤት:- ይህ ደግሞ 35ቱ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት የሚተረጎሙበት ጉባኤ ቤት ነው።
9ኛ=የመጻሕፍተ ሊቃውንት ጉባኤ ቤት:-
ይህ ደግሞ ሃይማኖተ አበው፣ 14ቱ ቅዳሴያት፣ ድርሳነ ቄርሎስ ተረፈ ቄርሎስ ጰላድዮስ፣ ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ፍትሐ ነገሥት፣ ተግሣጽ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እና አቡሻህር የሚተረጎሙበት ጉባኤ ቤት ነው።
10ኛ የመጻሕፍተ መነኮሳት ጉባኤ ቤት:-
ይህ ደግሞ ሦስቱ መጻሕፍት ማለትም ፊልክስዩስ፣ አረጋዊ መንፈሳዊ እና ማር ይስሐቅ የሚተረጎሙበት ጉባኤ ቤት ነው። በመጻሕፍት ትርጓሜ ጉባኤ ቤትም የላይ ቤት ትርጓሜ እና የታች ቤት ትርጓሜ እየተባለ ይከፈላል። እንግዲህ ከላይ ያሉት ጉባኤ ቤቶች በብዛት በትግራይ በወሎ በጎጃም በጎንደር በሸዋ በስፋት ይገኛሉ።
No comments:
Post a Comment