አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ አንድ በዚህች ቀን አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር ልደታቸው ነው፣ ታላቁ አባት አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ዕረፍቱ ነው፣ ጃንደረባው ቅዱስ ሱስንዮስ አረፈ፣ አስተዋይ የሆነ የተመሰገነ ቅዱስ አወ ክርስቶስ አረፈ፣ ምፅዋት መስጠትንም የሚወድ ቅዱስ ላእከ ማርያም አረፈ።
አቡነ ኤዎስጣቴዎስ
ሐምሌ ሃያ አንድ በዚህች ቀን አጽፋቸውን እንደጀልባ ተጠቅመው የኢያሪኮን ባሕር ከደቀ መዛሙርቶቻቸው ጋር የተሻገሩት ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር ልደታቸው ነው፡፡
አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ሲሆኑ፤ አባታቸው ክርስቶስ ሞዐ ሲሆን እናታቸው ስነ ሕይወት ይባላሉ፡፡ ደጋግ የሆኑ ወላጆቻቸው በሃይማኖትና በምግባር ኮትኩተው አሳደጓቸው፡፡ በአደጉም ጊዜ ከአባ ዘካርያስ እጅ መነኮሱ፡፡ ታላላቅ ቅዱሳን እስኪያደንቋቸው ድረስ በጽኑ ተጋደሎ ሲኖሩ ጌታችን ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ተገልጦላቸው በንፍሐት መንፈስ ቅዱስን አሳደረባቸው፡፡ "ከእናትህ ማኅፀን የመረጥኩህ ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ ሆይ ለብዙዎች ወንጌልን ትሰብክ ዘንድ ከኢትዮጵያ እስከ አርማንያ ድረስ መምህር አደረግሁህ፡፡ አንተን የሰማ እኔን ሰማ፣ አንተንም ያልሰማ እኔን ያልሰማ ነው" ካለቸው በኋላ ወደ ሰማይ በክብር ዐረገ፡፡
አባታችን ቅስናን ከተሸሾሙ በኋላ ወንጌልን መስበክ ጀመሩ፡፡ እነ አቡነ አብሳዲን ጨምሮ ብዙዎችንም አመንኩሰው ደቀ መዛሙርቶቻቸው አደረጓቸው፡፡ እጅግ አስገራሚ ተአምራትን በማድረግ ለብዙ ሕሙማን መድኃኒት ሆኗቸው፡፡
ልጆቻቸውን ሰብስበው ከመናፍቃን ጋር በፍጹም እንዳይቀላቀሉ በመምከር አቡነ አብሳዲን ሾመውላቸው ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ቅዱሳት ቦታዎችን ተሳለሙ፡፡ በመንገዳቸውም የክርስቶስን ወንጌል እየሰበኩ ብዙዎችን ወደ ቀናች ሃይማኖት መለሷቸው፡፡ ወደ አርማንያም ሄደው ወደ ኢያሪኮ ባሕር በደረሱ ጊዜ መርከበኞችን እንዲያሳፍሯቸው ቢለምኗቸው እምቢ አሏቸው፡፡ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ግን አጽፋቸውን በባሕሩ ላይ ዘርግተው በስመ ሥላሴ አማትበው አጽፋቸውን እንደመርከብ አድርገው ልጆቻቸውን ይዘው ባሕሩን ተሻገሩ፡፡ ልጆቻቸውን ‹‹ልጆቼ በልባችሁ ቂምንና ሽንገላን እንዳታኖሩ ተጠበቁ፣ ለእኔ ግን ከእናንተ አንዱ እንደሚጠፋ ይመስላኛል›› አሏቸው፡፡ ይህንንም እንዳሉ ከመካከላቸው አንዱ የቂም በቀል መከማቻ ነበርና ወዲያው ሰጠመ፡፡
አባታችን አርማንያ ደርሰው ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር ቡራኬን ከተሰጣጡ በኋላ ማስተማር ጀመሩ፡፡ የአርማንያ ሰዎች ሁሉም በሃይማኖት አንድ እስኪሆኑ ድረስ ታላላቅ ተአምራትን እያደረጉ አስተምረው አጠመቋቸው፡፡ አባታችን ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጦላቸው ታላቅ ቃልኪዳን ከሰጣቸው በኋላ መስከረም 18 ቀን ዐርፈው ሊቀ ጳጳሳቱና ካህናቱ በታላቅ ክብር ገንዘው በሰማዕቱ በቅዱስ መርምህናም ቤተ ክርስቲያን ቀብረዋቸዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አቡነ በጸሎተ ሚካኤል
በዚህችም ቀን ታላቁ አባት አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ዕረፍቱ ነው፡፡ ይኸውም ከካህናት ወገን የሆነው አባቱ ማርቆስ ሲሆን እናቱ እግዚእ ክብራ ትባላለች፡፡ እግዚእ ክብራም ወደ ወላጆቿ በሄደች ጊዜ ‹‹ከመኳንንቶቹ ለአንዱ እናጋባታለን›› ብለው ወደ ባሏ ተመልሳ እንዳትሄድ ከለከሏት፡፡ ማርቆስም ስለዚህ ነገር አዝኖ ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ሚስቱን እንደከለከሉት ለአንድ መነኩሴ ነገረው፡፡ መነኩሴውም ሄዶ ቢጠይቃቸው ወላጆቿ ድጋሚ ለመነኩሴውም ከለከሉት፡፡ ማርቆስም እየተመላለሰ መነኩሴውን ቢያስቸግረው ይዞት ሄደ ነገር ግን ወላጆቿ ጥላቻቸውን አበዙባቸው፡፡ መነኩሴውም ‹‹ማርቆስንና ሚስቱን ለአንድ ቀን ብቻ ሁለቱን አንድ ላይ ላናግራቸው›› በማለት ይዟቸው አደረ፡፡ እርሱም በማደሪያው እንዲያድሩ ከነገራቸው በኋላ ‹‹በዚህች ሌሊት ሩካቤ ሥጋ ሳትፈጽሙ እንዳታድሩ›› አላቸው፡፡ ሁለቱም በመነኩሴው ቤት አድረው ሳለ ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለማርቆስ ተገለጠለትና ‹‹ሚስትህ ወንድ ልጅ ትወልዳለች፣ በወለደችም ጊዜ ስሙን በጸሎተ ሚካኤል ትለዋለህ፣ ለቤተ ክርስቲያንም ዐምድ ይሆናል›› አለው፡፡ ማርቆስም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ ከሚስቱ ጋር ተገናኘና አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ተፀነሱ፡፡
እግዚእ ክብራ ከፀነሰች በኋላ ፊቷ እንደፀሐይ የሚያበራ ሆነ፡፡ የታመሙ ሰዎችም ሆዷን በነኩት ጊዜ ይፈወሱ ነበር፡፡ በወለደችም ጊዜ በቤቷ ውስጥ ቀስተ ደመና ተተክሎ ታየ ሲሆን አስቀድሞ መልአኩ ስሙን እንዳወጣለት ‹‹በጸሎተ ሚካኤል›› አሉት፡፡ አባቱም ካህን ነውና ምግባር ሃይማኖትን ጠንቅቆ እያስተማረ አሳደገው፡፡ በጸሎተ ሚካኤል ገና ሕፃን ሳለ መዝሙረ ዳዊትን፣ የነቢያት ጸሎትን በማዘውተር በጾም በጸሎት ሲጋደል ወላጆቹ ‹‹ይህ ሕፃን ልጃችን በረሃብ ይሞትብናል›› በማለት በግድ እየገረፉ እንዲመገብ ያስገድዱት ነበር፡፡ በግድ አፉን ይዘው ምግብ ከጨመሩበር በኋላ ‹‹ይኸው ጾምህን ፈታህ›› ሲሉት እርሱ ግን በሕፃን አንደበቱ ‹‹እኔ በፈቃዴ በአፌ ውስጥ ብጨምረው ጾሜን በሻርኩት ነበር፣ እናንተ በአፌ ውስጥ በግድ ከጨመራችሁት ግን ጾሜ አይሻርም›› እያላቸው እስከ ማታ ይጾም ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ አባቱ ወደ ጳጳስ ዘንድ ወስዶ ዲቁና እንዲሾም አደረገው፡፡ ባደገም ጊዜ አባቱ ማርቆስ ሚስት ያጋባው ዘንድ ባሰበ ጊዜ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ሸሽቶ ወደ ገዳም ገባ፡፡ አበ ምኔቱም ከእርሱ ጋር አስቀምጦ የምንኩስናን ቀንበር ያሸክመው ዘንድ ብዙ ፈተነው፡፡
ወላጆቹም መጥተው አስገድደው ከገዳሙ ሊያወጡት ሲሉ እምቢ ቢላቸው እናቱ ዘመዷ ወደሆነው ንጉሡ ውድም ረአድ በመሄድ ስለ ልጇ ነገረችው፡፡ ንጉሡም ከወታደሮቹ ውስጥ በአለንጋ ይዞ የሚገርፍ ወታደር ላከላት፡፡ የተላከው ወታደርም በጸሎተ ሚካኤልን እየገረፈ በማስገደድ ከገዳም አውጥቶ ለወላጆቹ ሰጠው፡፡
በጸሎተ ሚካኤልም በወላጆቹ ቤት ሳለ ወላጆቹን ‹‹እመነኩስ ዘንድ እስካልተዋችሁኝ ድረስ የቤታችሁን ምግብ አልበላም›› ብሎ ማለ፡፡ አባቱም ‹‹ምግብ ካልበላህ›› በማለት ጽኑ ድብደባ እየደበደበው ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ቆየ፡፡ በጸሎተ ሚካኤልም ሦስቱንም ቀን እቤት ሳይገባ የቀን ፀሐይ ሐሩሩ የሌሊት ውርጭ ቅዝቃዜ እየተፈራረቀበት እቤትም ሳይገባ በደጅ ሆኖ በጾም በጸሎት ቆየ፡፡ በዚህም በአባቱ እጅ ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡ ጌታንም ‹‹ለምድር ሰላምን ያመጣሁ አይምሰላችሁ ሰይፍን ነው እንጂ፡፡ የመጣሁትስ ሰውን ከአባቱ ልጅንም ከእናቷ ልለይ ነው›› ያለው ቃል በአባታችን ላይ ተፈጸመ፡፡ ማቴ 10፡34፡፡ አባቱ ማርቆስም ሥጋው እስኪያልቅ ድረስ በግርፋት ብዛት የልጁን ሀሳብ ለማስለወጥ ቢሞክርም እንዳልተሳካለት ሲያውቅ መልሶ ወደ ገዳሙ እንዲወስዱት አገልጋዮቹን ላካቸው፡፡ አበ ምኔቱም መምህር ሆኖ ያገለግል ዘንድ እንዲማር ሲነግረው ‹‹እኔ መነኩሴ መሆን እንጂ መምህር መሆን አልፈልግም›› በማለቱ ሳይስማሙ ቀሩና ወደ ሌላ ገዳም ወሰዱት፡፡ በዚያም እንዲሁ ሆነ፡፡ መልሰውም ወደ አባቱ ቤት ባመጡት ጊዜ ወላጆቹም ልጃቸው የምንኩስናን ሀሳቡን ይተወው ዘንድ ከአንድ ሴት ጋር ተማክረው በዝሙት እንድትጥለው ተነጋገሩ፡፡ ሴቷም ወደ በጸሎተ ሚካኤል ቀርባ በዝሙት ልትጥለው ብዙ ሞከረች፡፡ እርሱም ዐውቆ ‹‹ከእኔ ጋር አብረሽ መተኛት ደስ ካሰኘሽ እሺ ከእስራቴ ፍቺኝና እንተኛለን›› አላት፡፡ ይህንንም ያላት ከታሰረበት እንድትፈታውና እንዲያመልጥ ነው፣ እርሷ የእውነት መስሏት ደስ አላትና ሄዳ ለወላጆቹ አብሯት እንዲተኛ መስማማቱን ነገረቻቸው፡፡ ነገር ግን በዚያች ሌሊት በጸሎተ ሚካኤል ማንም ሳያየው ተነሥቶ ከእናት አባቱ ቤት ወጥቶ ሄደ፡፡
ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ደብረ ጎል አደረሰው፣ ይኸውም ቀሲስ አኖርዮስ በብቸኝነት ሸሽቶ የሚጋደልባት ደብረ ጽሙና ናት፡፡ በጸሎተ ሚካኤልም በዚያ ከመነኮሰ በኋላ ጽኑውን የተጋድሎ ሕይወት መኖር ጀመረ፡፡ በጾም በጸሎት ሆኖ ቀን የጉልበት ሥራ ይሠራል ሌሊት ቆሞ ሲጸልይ ያድራል፡፡ 90 ሸክም የወይራ ፍልጥ እየፈለጠ ለቤተ ክርስቲያኑና ለአበ ምኔቱ ያመጣ ነበር፡፡ እንጨቱንም ሲቆርጥና ሲፈልጥ የብረት መቆፈሪያ ብቻ ይጠቀም ነበር እንጂ ስለታም የሆኑ ምሳርና መጥረቢያ አይጠቀምም ነበር፡፡ ምክንያቱም የወጣትነት ኃይሉና ሥጋው በእጅጉ ይደክም ዘንድ ነው፡፡ እንዲህም ሲሠራ ጾም፣ ጸሎት፣ ሥግደቱን አያስታጉልም ነበር፡፡ እስከ 4 ቀንም የሚጾምበት ጊዜ አለ፡፡ በጸሎተ ሚካኤል በእንደዚህ ያለ ጽኑ ተጋድግሎ 13 ዓመት በድቁና ሲያገለግል ኖረ፡፡ ከዚህም በኋላ ሥጋውን ማድከም ቢሳነው ከእኩለ ቀን ጀምሮ ፀሐይ ስታቃጥል አለቱ ሲግል ጠብቆ ሄዶ አለቱ ላይ ይተኛል፣ ከግለቱም የተነሣ የሥጋው ቆዳ እስኪበስል ድረስ በአለቱ ላይ ይተኛል፡፡
በጸሎተ ሚካኤልም ከዚህ በኋላ ቅስና ተሾመ፡፡ ወደ ዋሻም ገብቶ በዓቱን አጸና፡፡ ከምግባር ትሩፋቱ የተነሣ ሌሎች ቅዱሳን ሁሉ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልን እንደ መልአክ ያዩት ነበር፡፡ እርሱም ከሰው ጋር ላለመገናት ብሎ በቁመቱ ልክ ጉድጓድ ቆፍሮ መጻሕፍቱን ብቻ ይዞ ከዚያ ገባ፡፡ ቅዱሳንም መጥተው ‹‹አንተንም ሌሎችንም የምትጠቅመው ከዚህ ጉድጓድ ውስጥተህ ብታስተምር ነው…›› እያሉ በብዙ ልመና ከጉድጓዱ አወጡት፡፡ ከዚህም በኋላ የተሰወረውን ሁሉ በግልጥ የሚያይ ሆነ፡፡ ብዙ አስደናቂ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን ያስተምራል፡፡ ወደ በዓቱም እየገባ በቀን 8ሺህ ስግደትን ይሰግዳል፡፡ ከስግደቱም ብዛት የተነሣ ምድሪቱ ጎድጉዳ እስከ ጉልበቱ ትውጠው ነበር፤ ከሰገደበትም ቦታ ወዙ መሬትን ጭቃ እስኪያደርጋት ድረስ እንደ ውኃ ይፈስ ነበር፡፡
ከመነኮሰበት ጊዜ ጀምሮ ተቀምጦ በእጁ ላይ አረፍ ይላል እንጂ በጎኑ ተኝቶ አያውቅም፡፡ ጌታችንም ተገልጦለት ማደሪያው ከጴጥሮስና ከጳውሎስ ጋር መሆኑን ነግሮታል፡፡ አባታችን ወደተለያዩ ገዳማት በመሄድ የቅዱሳንን በረከት ተቀበለ፡፡ወደ ደብረ ዳሞ በመሄድ ከአቡነ አረጋዊ ጋር ተነጋገረ፣ ወደ አባ መጣዕ ቤት በመሄድ ከአባ ሊባኖስ ጋር ተነጋገረ፣ ወደ አባ ገብረ ናዝራዊ ገዳምበሄድም ከጻዲቁ ጋር ተነጋገረ፡፡ ከሰንበት በቀር እህል ባለመቅመስ 40 ቀንና 40 ሌሊት በመጾም ሱባኤ በያዘ ጊዜ እግዚአብሔር የተለያዩ ምሥጢራትን ይገልጥለታል፡፡ በሄኖክ መጽሐፍ ላይ ተጽፎ ያለው የሰማይ ምሥጢር ሁሉ ተገለጠለት፡፡ የፀሐይ፣ የጨረቃ፣ የብርሃናት አፈጣጠራቸው፣ የንፋስ መስኮቶቸን ሁሉ በግልጥ ባየ ጊዜ ነቢዩ ሄኖክን ‹‹ሄኖክ ሆይ የራእይህ ምሥጢር እንደዚህ ብሩህ ነውን? የምሥጢርህ መሰወር እንዲህ ግልጥ ነውን?›› ይለዋል፡፡ ዳግመኛም የነቢያት የትንቢታቸው ራእይ ይገለጥለት ዘንድ 40 ቀንና 40 ሌሊት በመጾም ሱባኤ በያዘ ጊዜ የመጻሕፍቶቻቸው ምሥጢር ይገለጥለታል፡፡
ከዚህም በኋላ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል በመማለጃ (በጉቦ) ክህነት በሚሰጥ ጳጳስ ምክንያት በሐዋርያት ግዝት ዓለም ሁሉ በግዝት እንደሚኖር ተመለከተ፡፡ ወደ ጳጳሱ አባ ዮሐንስ ዘንድ ሄደና አገኘው፡፡ ጳጳሱም ‹‹ልጄ በጸሎተ ሚካኤል ደህና ነህን?›› አለው፡፡ አባታችንም ‹‹ደህና ነኝ›› ባለው ጊዜ ጳጳሱ ‹‹ስለምን መጣህ?›› አለው፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልም ሰው ሁሉ ከአጠገባቸው እንዲርቅ ካደረገ በኋላ ጳጳሱን እንዲህ አለው፡- ‹‹ቅዱሳን ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው መጽሐፍ ‹በመማለጃ ክህነትን የተቀበለና የሰጠ የተለየ የተወገዘ ነው› ያሉትን አልሰማህምን?›› አለው፡፡ ዳግመኛም ‹‹እጄን በጫንኩበት መንፈስ ቅዱስ ይወርድ ዘንድ ተናገሩ ብሎ በሐዋርያት እግር ሥር ወርቁን አምጥቶ ባፈሰሰው ጊዜ ሲሞን መሠርይን ጴጥሮስ እንዳወገዘው አልሰማህምን? ጴጥሮስም ‹ወርቅህና ብርህ ለጥፋት ይሁንህ፣ የእግዚአብሔር ጸጋ በወርቅ የምትገዛ ይመስልሃልን?› አለው፡፡ በመራራ መርዝ ተመርዘህ አይሃለሁና፡፡›› ሐዋ 8፡19፡፡ ‹‹አባቴ ሆይ የውኃ ምንጭ የፈሰሰ የደፈረሰ እንደሆነ የምፈሰውም ውኃ ሁሉ ይደፈርሳል፡፡ ምንጩ ንጹሕ ከሆነ ግን የውኃው ፈሳሽም ሁሉ የጠራ ይሆናል፡፡ አንተ በሐዋርያት ውግዘት ብትገባ ሁሉም የተወገዘ ይሆናል›› አለው፡፡ ጳጳሱም ተቆጥቶ ‹‹አንተ ከእኔ ተማር እንጂ ለእኔ መምህር ልትሆነኝ ትፈልጋለህ?›› በማለት ተናገረው፡፡ በወንጌል ላይ ‹‹እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምዘጉ ወዮላችሁ፣ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም ትከለክሏቸዋላችሁ›› ያለው የእግዚአብሔር ቃል በእርሱ ላይ ደረሰ፡፡ ማቴ 23፡14፡፡
ከዚህም በኋላ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ወደ ካህናተ ደብተራ በመሄድ ከንጉሡ ጋር ያገናኙት ዘንድ ጠየቃቸው፡፡ የቤተ መንግሥት ካህናትም ለንጉሡ ነግረውለት አስጉት፡፡ አባታችንም ንጉሡን ‹‹መንግሥትህ በግዝት ጨለመች፣ ሐዋርያት ጥምቀትም ቢሆን ወይም ክህነት በመማለጃ (በጉቦ) የሚሰጥንና የሚቀበልን አስቀድመው ሐዋርያት አውግዘዋል›› አለው፡፡ ዳግመኛም ‹‹እነሆ ይህ ጳጳስ የሐዋርያትን ትእዛዝ ተላልፎ በጉቦ ክህነት ይሰጣል፣ ጳጳሱም በሐዋርያት ግዝት ከገባ በእጁ የተጠመቁና የተሾሙት ሁሉ የተወገዙ ይሆናሉ፣ እንደዚሁ ዓለሙ ሁሉ በውግዘት ውስጥ ይኖራል›› አሉው፡፡ ንጉሡም ሦስቱ አንድ ላይ ሆነው እንዲመጋገሩ ቀጠሮ ሰጠውና በሌላ ቀን ሦስቱም ተገናኙ፡፡ ጳጳሱም ለንጉሡ ‹‹ይህ በጸሎተ ሚካኤል እኔን ከሹመቴ አንተን ከመንግሥትህ ሊሽረን ይፈልጋል ስለዚህ ልጄ የምነግርህን ስማኝ አስረህ ወደ ትግራይ ይወስዱት ዘንድ እዘዝ›› አለው፡፡ ንጉሡም የጳጳሱት ክፉ የሀሰት ምክር በመስማት ‹‹ይሁን አንተ እንዳልከው ይሁን›› በማለት አቡነ በጸሎተ ሚካኤልን በጽኑ ማሠሪያ አስረው በግዞት ወደ ሳርድ ይወስዱት ዘንድ አዘዘ፡፡ ጭፍሮቹም እንደታዘዙት አደረጉና አባታችን በዚያ በግዞት ሁለት ዓመት ታስሮ ቆየ፡፡ ከዚያም ወደ ጽራይ ምድር ወሰዱትና ቆራር በተባለ ቦታ ለተሾመው ሰው ‹‹እንደ ንጉሡ ትእዛዝ ይህንን መነኩሴ እሰረው›› ብለው ሰጡት፡፡ የሀገሩ ሰዎችም አቡነ በጸሎተ ሚካኤልን እጅግ ወደዱትና ወደ ጽራር ሀገር ገዥ ሄደው እንዲፈታው ለምነው ከእስራቱ አስፈቱት፡፡ በሀገራቸውም ወንጌልን አስተምሮ ብዙ ተአምራት እያደረገላቸው ከቆየ በኋላ ወደ ልጁ ሳሙኤል ለመሄድ ተነሣ፡፡ ሲሄድም አቡነ ገብረ ናዝራዊ ጋር ደረሰና አብረው ሳሙኤል ጋር ደረሱ፡፡
አቡነ በጸሎተ ሚካኤል በቅዳሴ ጊዜ ጌታችን በሕፃን ልጅ አምሳለ በመንበሩ ተቀምጦ ስለሚያየው ሁልጊዜ ሲቀድስ ያለቅሳል፡፡ አንድ ቀን አባታችንን ሲቀድስና ሕፃኑን በመንበሩ ላይ ሲሠዋው ወንድሞቹና ልጆቹ አይተውት በድንጋጤና በፍርሃት ሆነው አልቅሰዋል፡፡ የሕፃኑንም ሥጋ በፈተተው ጊዜ የአባታችን እጁ በለመለመ ሥጋ ይመላል፡፡ ቅዳሴውም ከተፈጸመ በኋላ ሁሉም መጥተው ሥጋወደሙን በፍርሃት ይቀበላሉ፡፡ ከእነርሱም ውስጥ አስቀድመው ስለ ሥጋወደሙ መለወጥ ጥርጣሬ የነበራቸው ሰዎች ስለነበሩ የእነርሱን ጥርጣሬ ዐውቆ አባታችን ቅዳሴውን ከፈጸመ በኋላ ‹‹ኅብስቱ የክርስቶስ ሥጋ ወይኑም ደሙ መሆን ይችላልን እያላችሁ በልባችሁ ስታስቡ አይቻለሁና ይኸው ዛሬ በግልጽ እንዳያችሁት አማናዊ ሆኖ ይለወጣልና ተጠራጣሪ አትሁኑ›› ባላቸው ጊዜ እግሩ ሥር ወድቀው ‹‹አንተ ብፁዕ ነህ የተሸከመችህም ማኅፀን ብፅዕት ናት… ›› ብለው ይቅር እንዲላቸው ለመኑት፡፡ አባታችንም ወንጌልን አስተማራቸው፡፡ መነኮሳት ልጆቹ ሩቅ ቦታ እየሄዱ ውኃ በመቅዳት ቢቸገሩ ውኃን አፍልቆላቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ ሰዎቹ አንድ ነገር ልንነግርህ እንወዳለን አሉት፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልም ንገሩኝ ባላቸው ጊዜ የአባቱን ሚስት ስላገባው ንጉሥ ነገሩትና ሄዶ እንዲያስተምረው እንዲገሠጸው ለመኑት፡፡ አባታችንም ‹‹በጽኑ ማሰሪያ ታስሬ በእስር ስለነበርሁ አልሰማሁም›› ካላቸው በኋላ ሄዶ ቢሰማው እንደሚመክረው ባይሰማውና ባይመለስ ግን እንደሚያወግዘው ነገራቸው፡፡ አባታችንም ልጆቹን አስከትሎ ወደ ንጉሡ ዘንድ ሄደ፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ‹‹ንጉሡ የአባቱን ሚስት በማግባቱ ሄደን ስንገሥጸው መከራ ቢያጸናብን ከሰማዕትነት ይቆጠርልናል›› ብሎ ሲነግራቸው ከሰማይ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ በሁሉም በላያቸው ላይ ሲወርድ አባታችን በግልጽ ተመለከተ፡፡ በረኃብ በጥም ሆነው ከተጓዙ በኋላ ትግራይ ሰወን ከምትባል ሀገር ደረሱ ንጉሡ ከዚያ ነበረና፡፡ ንጉሡም ቅዱሳኑ መክረው ሊመልሱት ካልሆነም ሊያወግዙት መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ ጭፍሮቹን ልኮ ቅዱሳኑን ወደ እርሱ እንዲያመጧቸው አዘዘ፡፡
ለማስፈራራትም ብዙ ጦረኛ ጭፍሮችንና የታሰሩ አስፈሪ አንበሶችን በፊቱ አቆመ፡፡ ቅዱሳኑንም ‹‹ስለምን ወደዚህ ከተማ መጥታችኋል?›› አላቸው፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልም ‹‹እውነትን ስለማጽናት ከአንተ ጋር ለመነጋገር መጥተናል›› አሉት፡፡ ንጉሡም እሺ ንገሩን በላቸው ጊዜ አባታችን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለጠበቁ ደጋግ ነገሥታት ከመጽሐፍ ቅዱስ በመጥቀስ ንጉሡን አስተማሩት፡፡
ትእዛዙንም ያልጠበቁትን አመፀኞችን እንደቀጣቸው ነገሩት፡፡ በመጨረሻም ‹‹የአባትህን ሚስት ሀፍረተ ሥጋ አትግለጥ፣ የአባትህ ሀፍረተ ሥጋ ነውና›› የሚለውን ኦሪት ዘሌ 18፡6 በመጥቀስ አስተማሩት፡፡ ዳግመኛም ‹‹ከአባቱ ሚስት ጋር የተኛ የአባቱን ሀፍረት ገልጧልና መሞትን ይሙት ሁለቱም በደለኞች ናቸውና›› የሚለውን የሙሴን ሕግና ሌላም ከሐዲስ ኪዳን እየጠቀሱ አስተማሩት፡፡ አባታችን ካስተማሩት በኋላም ‹‹የክርስቲያን ሚስቱ አንድ ብቻ ናት አንተ ግን ብዙ ሚስት አግብተህ የአባትህንም ሚስት አግብተሃልና ሕግ ተላልፈሃል›› አሉት፡፡ ንጉሡም ተምሮ ከመመለስ ይልቅ በታላቅ ቁጣ ሆኖ ቅዱሳኑን ይደበድቧቸው አዘዘ፡፡ ሲደብድቧቸውም ታላቅ ጩኸት ተነሣ፡፡ ለየብቻ አስረው ካሳደሯቸው በኋላ ንጉሡ ለየብቻ ወደ እርሱ እያስመጣ አናገራቸው፡፡ እያንዳንዳቸውንም በ7 ገራፊዎች በታላቅ ጅራፍ አስገረፋቸው፡፡ ደማቸውም እንደ ውኃ ምድር ላይ ፈሰሰ፡፡ ከደማቸውም እሳት ወጣና እስከ ሦስት ቀን ድረስ ወደላይ እየነደደ ቆየ፡፡ በዚህም ንጉሡ እጅግ ደንግጦ ብዙ ውኃ ከወንዝ እየቀዱ እሳቱን እንዲያጠፉ አዘዘ፡፡ የበዛ ውኃም ባፈሰሱበት ጊዜ የእሳቱ መጠን ይበልጥ ይጨምር ነበር፡፡ ዳግመኛም ብዙ ጨምረው ውኃ እየቀዱ ቢያፈሱበትም ማጥፋት እንዳልተቻላቸው ባየ ጊዜ ንጉሡ የወንዙን ውኃ በቦይ መልሰው እንዲያመጡ አዘዘ፡፡ ንግሥቲቱ ዛንመንገሣም ንጉሥ ዐምደ ጽዮንን ‹‹የእግዚአብሔርን ቁጣ አታስተውልምን›› ብላ ተናገረችው፡፡ ወዲያውም ነጭ የዝንብ መንጋ መጥቶ የንጉሡን ፈረሶችና በቅሎዎች ነከሳቸውና ሞቱ፡፡ ንጉሡም ፈርቶ በሌሊት ሸሽቶ ወጣ፡፡ ቅዱሳኑንም አንድ መውጫና መግቢያ ብቻ ባላት ደራ ወደምትባል ታላቅ ተራራ ቦታ አውጥተዋቸው እንዲያስሯቸው አደረገ፡፡
በዚያም የሚኖሩት አሕዛብ ስለሆኑ ክርስቶስንም አያውቁም፣ ነፍሰ ገዳዮችም ነበሩ፡፡ ንጉሡም አቡነ በጸሎተ ሚካኤልንና ልጆቹን ይገድሏቸው ዘንድ ወደ እነርሱ መልእክት ይልክ ነበር፡፡ ነገር ግን አባታችን ወንጌልን ሰበከላቸውና አሳምኖ የክርስቶስ ተከታዮች አደረጋቸው፡፡ እነርሱም ወደ ንጉሡ ሄደው ክርስቲያን እንደሆኑ ነገሩት፡፡
የአባታችን የተአምሩ ዜና በሀገሩ ሁሉ በተነገረ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሳንን አሳደው ስሙ ዝዋይ ወደሚባል ታላቅ ባሕር ውስጥ ያገቧቸው ዘንድ አዘዘ፡፡ አባታችንና ልጆቹንም አረማዊያን ወዳሉበት ደሴት አስገቧቸው፡፡ ከብዙ ጊዜም በኋላ ከግዞት መልሰው በማውጣት በሴዋ አውራጃ እንዲያስተምሩ ፈቀደላቸው፡፡ ንጉሡም ናርእት የሚባሉ ሰዎችን በጦር ይወጋቸው ዘንድ ተነሣ፡፡ እነዚህም ሰዎች አስቀድመው በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ስብከት በጌታችን ያመኑ ክርስቲያኖች ሆነዋል፡፡ ንጉሡም ድጋሚ አባታችንን አሠራቸውና ማስፈራራት ጀመረ፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ግን የንጉሡን ማስፈራራት በመናቅ ተናገሩት፡፡ እንዲህም አሉት፡- ‹‹በጦር ብታስወጋኝ ሕዝቅኤልን አስበዋለሁ፤ አንበሶች እንዲበሉኝ ብታዝ ዳንኤልን አስበዋለሁ፤ ወደ እሳት ውስጥ ብትጥለኝ አናንያን አዛርያንና ሚሳኤልን አስባቸዋለሁ፤ በእንጨት መቁረጫ መጋዝ እንዲቆርጡኝ ብታዝ ኢሳይያስን አስበዋለሁ፤ በድንጋይ እንዲወግሩኝ ብታዝ ኤርሚያስን አስበዋለሁ፤ በሰይፍ አንገቴንም እንቆርጡኝ ብታዝ በወንደሙ ፊሊጶስ ሚስት ምክንያት የገደለው የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ መጥምቅን አስበዋለሁ፤ ልዩ ልዩ መከራዎችን ብታጸናብኝም መከራ የተቀበሉትን ሐዋርያትንና ሰማዕታትን አስባቸዋለሁ›› ብለው ለንጉሡ መለሱለት፡፡ ንጉሡም ከዚህ በኋላ አባታችንን ‹‹ይቅር ይበሉኝ›› አላቸው፡፡ በአባታችን ምክር ብዙ የንጉሡ መኳንንቶችም ክፉ ሥራቸውን በመተው በንስሓ ተመለሱ፡፡ ንጉሡም አንዲት ሚስቱን ለጭፍራው አሳልፎ ሰጥቶት ነበርና እርሷም አባታችንን ስታገኛቸው ንስሓ ገባች፡፡ ንጉሡም ይህቺ የተዋት ሚስቱ ንስሓ እንደገባች ሲሰማ ‹‹ዛሬ ሌሊት ከእርሷ ጋር ተኝቼ ንስሓዋን አስተዋታልሁና ይዛችሁ አምጡልኝ›› ብሎ ጭፍሮቹን ላከ፡፡ አባታችንም ሴቲቱን በንስሓዋ ወደዋት ነበርና አሁን ንጉሡ በእርሷ ላይ ሊያደር ያሰበውን ልጆቹ ነገሩት፡፡ አባታችንም ይህን ሲሰማ የቀረበውን ማዕድ ሳይቀምሱ አስነስቶ ሁሉም እንዲጸልዩ አዘዘና እርሱም ቆሞ መጸለይ ጀመረ፡፡ በዚያችም ሌሊት ወዲያው ንጉሡ ድንገት በጠና ታመመ፡፡ ያንጊዜም ንጉሡ ‹‹ይህ ድንገኛ ሕመም የመጣብኝ አቡነ በበጸሎተ ሚካኤል ጸሎት ነው›› ብሎ ያችን ሴት ካመጡበት ቦታ እንዲመልሷት አዘዘ፡፡ ወደ አባታችንም ‹‹አባቴ ሆይ! ይቅር በለኝ፣ ይህ ሕመም ያገኘኝ በአንተ የተማጸነችውንና ንስሐ የገባችውን ሴት በኃጢአት ላረክሳት ስላሰብኩ ነው፤ አሁንም ልጅቷን ወደነበረችብ መልሻታሁና አባቴ ሆይ ከዚህ በሽታዬ ከዳንኩ በሕግህ እኖራለሁ›› ብሎ መልእክተኛ ላከ፡፡ አባታችንም የቤተ መንግሥቱን ካህናተ ደብራዎች ወቀሳቸው፡፡ ‹‹ከእናንተ በቀር ይህን ንጉሥ የሚያስተው የለም ያለ ሥራው እያሞገሳችሁ በኃጢአት ላይ ኃጢአት እንዲሠራ የምታድርጉ እናንተ ናችሁ›› ብለው በተናገሯቸው ጊዜ ደብተራዎቹም ‹‹እኛም በሕግህ እንኖራለን ይቅር በለን፣ ጉሡንም ይቅር ብለህ ከመጣበት ደዌው ፈውሰው›› ብለው ለመኗቸው፡፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልም ‹‹ንጉሡ ከኃጢአቱ ተመልሶ ንስሓ እንደማይገባ እኔ ዐውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ሞቱ በእኔ ቃል ምክንያት እንዳይሆን እግዚአብሔር ከበሽታው ይፈውሰው›› አሏቸው፡፡ ካህናቱም ‹‹ከደዌው በሚድን ነገር እንወስድለት ዘንድ የእግርህን ትቢያ ስጠን›› አሏቸው፡፡ አባታችንም ‹‹የእግሬን ትቢያ አልሰጣችሁም ነገር ግን ሂዱ ከደዌው ሁሉ ተፈውሶ ታገኙታላችሁ›› አሏቸው፡፡ ካህናቱም ወደ ቤተ መንግሥት በሄዱ ጊዜ ንጉሡን ከደዌው ፍጹም ተፈውሶ አገኙት፡፡
አንዲት ድንግል መነኩሲት ከክብር ያሳነሳት ርጉም የሆነ አንድን መነኩሴ አገኙትና አባታችን መክረው ገሥረው ንስሓ ግባ አሉት፡፡ ነገር ግን እርሱ በወቅቱ እሺ ብሎ ንስሓ ሳይገባ ቀረ እንዲያውም በአባታችን ላይ ክፉ ያስበ ጀመር፡፡
እንዲሁም ክህነት ሳይኖረው በውሸት ካህን ነኝ እያለ ሲቀድስ የነበረን አንዲን ዲያቆን አባታችን አግኝተው ‹‹የክርስቶስን ሥጋ ቅዱሳን መላእክትስ እንኳን መንካት የማይቻላቸውን አንተ በውሸት ለመንካት እንዴት ደፈርክ….›› ብለው በመምከር ንስሓ እንዲገባ አዘዙት፡፡ ነገር እነዚህ ሁለት ክፉ ሰዎች ንስሓ ከመግባት ይልቅ በአባታችን ላይ ክፋትን ያስቡ ጀመር፡፡ ወደ ንጉሡም ዘንድ ሄደው ‹‹በጸሎተ ሚካኤል የሚባለው መነኩሴ ‹ፈርዖንና ሠራዊቱን በባሕር ያሰጠመው እንደዚሁ ሁሉ ይህንንም ንጉሥ ያስጥመው› እያለ ይረግምሃል›› ብለው አወሩለት፡፡ ንጉሡም ተቆጥቶ አባታችንን ከነልጆቻቸው አስረው ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ፡፡ አስረው አምጥተውም በንጉሡ ፊት ኦቆሟቸው፡፡ ንጉሠም አባታችንን ‹‹ለምን ትረግመኛለህ›› ሲላቸው እሳቸውም ‹‹ጠላትህን ውደድ ያለንን የአምላክ ሕግ እንከተላለን እንጂ አንተንስ የረገመህ የለም፤ ጳውሎስም በምንኩስና ሥርዓት ሰይጣንንም እንኳ አትርገሙ ብሏል፡፡ ሰይጣንን እንኳ መርገም የሚከለክል ከሆነ ንጉሥን እንዴት ይረግሙታል›› አሉት፡፡ ንጉሡም የከሰሱትን ሁለቱን ሰዎች አምጥቶ ለአባታችን አሳቸው፡፡ እሳቸውም የእያንዳንዳቸውን ክፉ ሥራ ለንጉሡ ነገሩት፡፡ ንጉሡም ይርታ ጠይቆ አባታችንን በሰላም አሰናበታቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ጠላት ዲያብሎስ በቅዱሳን ላይ ክፉ ሥራ ይሠራ ዘንድ በንጉሡ ልብ ክፉ ሀሳብን አስነሣ፡፡ ንጉሡም ‹‹እኔ በምገዛው አገር ሁሉ ያሉ ቅዱሳንን አምጧቸው›› ብሎ በሕዘቡ ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ ቅዱሳንንም ሁሉ ሰብስበው አመጧቸው፡፡ አቡነ ዘአማኑኤል ከልጆቹና ከአባታችን ከአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ጋር ደረሰ፡፡ ንጉሡም በቁርባንና በጸሎት ከእኔ ጋር ተባበሩ (አንድ ሁኑ) የምትፈልጉትን ሁሉ አሟላላችኋለሁ፣ ከእኔ ጋር መተባበርን እምቡ ካላችሁ ግን ወደ እርሱ እሰዳችሁ ዘንድ ሊቀ ጳጳሱ አዘዋልና ወደ ግብጽ በረኃብና በጥም ትሄዳላችሁ በመንገድም ሰውን የሚገድሉ ሽፍቶች አሉ›› አላቸው፡፡ የአቡነ ዘአማኑኤል ደቀ መዛሙርት ግን ‹‹እኛ ከአንተ ጋር እንተባበራለን፣ ያዘዝከንን ሁሉ እንፈጽማለን›› ብለውት የሚሹትን ሁሉ ሰጥቷቸው በሰላም አሰናበታቸው፡፡
መምህራቸው አቡነ ዘአማኑኤል ግን ይህን አልፈልግም ብሎ ብቻውን ተሰደደ፡፡ ንጉሡም ወደ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል መኳንንቱን በመላክ ከእርሱ ጋር እንዲተባበሩ ወርቅና ብሩን ላሞችንና ጥሪቶችን ሁሉ እንደሚሰጣቸው ካልሆነ ግን ወደ ኢሩሳሌም መንገድ እንደሚልካቸውና በመንገድም በሽፍቶች እንደሚገደሉ ነገራቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ወርቅህና ብርህ ጥሪትህም ሁሉ ከአንተ ጋራ ለጥፋት ይሁንህ›› ብለው መለሱለት፡፡ ከልጆቹም ጋር አባታችንን በግዳጅ ወደ ንጉሡ ዘንድ ሲወስዷቸው የንጉሡን ምግብ እንዳይቀምሱ ተማምለው አንደኛው መነኩሴ የገንዘባቸው የገዙትን ጎመን ተሸክሞ አብሯቸው ሄደ፡፡ ንጉሡም ባየው ጊዜ በጽኑ ጅራፍ እያስገረፈው እያለ ሕይወቱ በዚያው አለፈች፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሡ በግዞት ወደ አረማውያን መኖሪያ እየነዱ እንዲወስዷቸው አዘዘ፡፡
ወደ ግሎ ማክዳ ምድር እንዳደረሱት በዚያ ያሉ ቅዱሳን በደስታ ተቀበሉት፡፡ ስማቸውም ማርቆ፣ ክርስቶስ አምነ፣ አባ ሲኖዳና ማማስ ናቸው፡፡ ማማስም ለአባታችን ለጸሎት የሚሆነውን የድንጋይ ዋሻ አሳየው፡፡ አባታችንም ‹‹ይህች ዋሻ ለዘላለም ማረፊያዬ ናት›› ብሎ ውስጧን በድንጋይ ይወቅር ጀመር፡፡ በውስጧም አገልገሎቱን ፈጸመ፡፡ ወደ ቅዱሳኑ ወደ እነ አባ ማርቆስ፣ ክርስቶስ አምነ እና ሲኖዳ መጥተው የመቃብር ጉድጓድ እንዲቆፍሩ መልአክት ላከባቸው፡፡ በቀዳሚት ሰንበት ዕለትም ደቀ መዝሙሩ ዕንባቆም በአገኘውና ‹‹ነገ አባትህን ወደ መቃብር ትጥለዋለህ›› አለው፡፡
በማግሥቱም እሁድ ቀን ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ ሲመክራቸው ዋለ፡፡ በመጨረሻም አንዱን ደቀ መዝሙሩን ብቻ አስከትሎ ወደ ዋሻዋ ግቶ በ4ቱም ማዕዘን ባረካት፡፡ ከዚህም በኋላ እጁንና እግሩን ዘርግቶ ነፍሱን በፈጣሪው እጅ አስረከበ፡፡ ነቢዩ ‹‹የጻዲቅ ሰው ሞቱ በእግዚአብሔር ፊት ክቡር ነው›› እንዳለ ያለ ምንም ጻዕር ዐረፈ፡፡ መዝ 115፡6፡፡
ደቀ መዛሙርቱም በመጡ ጊዜ ዐርፎ አገኙት፡፡ እነርሱም መሬት ላይ ወድቀው ‹‹አባት እንደሌላቸው እን ሙት ልጆች ለማን ትተወናለህ፣ በስውር የሠራነው ኃጢአትስ ማን ይነግረናል….›› እያሉ ጽኑ ልቅሶን አለቀሱ፡፡ አስቀደሞም እርሱ ደቀ መዛሙርቱ በስውር የሚሠሩትን ሥራ ሁሉ እርሱ በግልጽ እያየ ‹‹አንተ ይህን ሠርተሃልና ንስሓ ግባ›› እያለ ይመክራቸው ነበርና፡፡ ልቅሶአቸውንም ከፈጸሙ በኋላ ራሱ በጠረባት የድንጋይ ዋሻ ውስጥ ቀበሩት፡፡ የሀገሪቱም ሰዎች ክፉዎች ናቸውና ከጊዜም በኋላ ደቀ መዛመርቱ የአባታችች ዐፅሙን አፍልሰው ወደ ሌላ ቦታ አስቀመጡት፡፡ እስከ ኢትዮጵያ ጳጳስ አባ ያዕቆብ መምጣት ድረስ ደብቀው አኖሩት፡፡ አባ ያዕቆብም የአባታችንን ዐፅም ያመጡለት ዘንድ አዘዘቸው፡፡ ከጊዜም በኋላ ዐፅሙን ወደ ጋስጫ አፍልሰውታል፡፡ ይኸውም ጋስጫ ከሊቁ አባታችን ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ሥር የሚገኝ ነው፡፡ ዋሻ ቤተ መቅደሱም በግሩም አሠራር የተሠራ ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ሱስንዮስ
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ጸጋ ጥበብ ማስተዋልና ዕውቀት የተሰጠው ጃንደረባው ቅዱስ ሱስንዮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከንጉሥ ቴዎዶስዮስ መኳንንቶች ውስጥ ነበር እርሱም ለሰው ሁሉ ርኅራኄ የሚያደርግ በሽተኞችንም የሚጐበኛቸውና የሚያረጋጋቸው ነበር። በችግርና በመከራ ስለሚኖሩትም ይረዳቸው ዘንድ ወደ ጌታ ይጸልይ ነበር።
ስለ ከሀዲው ንስጥሮስ በኤፌሶን የኤጲስቆጶሳት ጉባኤ በተደረገ ጊዜ የጉባኤው ርእሰ መንበር የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስም በመጣ ጊዜ ይህ ቅዱስ ሱስንዮስ ኤጲስቆጶሳቱንና ቅዱስ ቄርሎስን ያገለግላቸው ነበር። በዚያን ጊዜም በአስጨናቂ ደዌ ተይዞ ታመመ በደዌውም ውስጥ ሳለ ቃል ከሰማይ ወደ ታላቅ ሠርግ እንደሚጠራው ራእይን አየ።
ለቅዱስ ቄርሎስም ነገረው አባት ቄርሎስም ያድንህ ዘንድ ስለ አንተ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እለምነው ዘንድ ትፈቅዳለህን አለው እርሱም ገንዘቤን ለድኆች እስከምሰጥ አዎ አባቴ እሻለሁ ብሎ መለሰ። ቅዱስ ቄርሎስም ጸለየለትና ከደዌው ዳነ።ተነሥቶም ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጠ። ከዚህም በኋላ ተመልሶ ተኛና በሰላም አረፈ። ቅዱስ ቄርሎስም በላዩ ጸሎት አድርሶ ገንዞ ቀበረው በአረፈባት በዚች ዕለትም መታሰቢያውን እንዲአደርጉለት አዘዘ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ አወ ክርስቶስ
በዚህችም ቀን አስተዋይ የሆነ የተመሰገነ አወ ክርስቶስ አረፈ። ሚስት በአገባ ጊዜም በጾምና በጸሎት እያገለገሉ በድንግልና በአንድነት ኖሩ በሌሊትም ማቅ ለብሰው እየብቻቸው ይተኙ ነበር በቀንም እርሱ በጎችን እየጠበቀ በዱር ይውል ነበር እርሷም ለእንግዳ ምግብ እያዘጋጀች ትውል ነበር።
ከስምሪቱም በገባ ጊዜ የእንግዶችን እግር ያጥብ ነበር። እርሷም ማዕድን በማዘጋጀት ታገለግል ነበር። ፍጹማን መነኰሳትም ሥራቸው እንዴት እንደሆነ ይገልጥላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በጠየቁ ጊዜ ገድላችሁ በአወ ክርስቶስና በሚስቱ ተጋድሎ መጠን አልደረሰም የሚል ቃል ከሰማይ ወደ እነርሱ መጣ።
እነዚያ መነኰሳትም ሒደው ሥራቸውን መረመሩ በጭንቅ በግዳጅም ሥራቸውን ገለጡላቸው እያደነቁም ተመለሱ በእንዲህ ያለ ሥራም ኑረው በሰላም አረፉ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ላእከ ማርያም
በዚህችም ቀን ደግ የሆነና በጎ ምግባር ያለው ምፅዋት መስጠትንም የሚወድ ላእከ ማርያም አረፈ። የዚህ ቅዱስም የእናቱ ስም ሮማነ ወርቅ ነው እርሷም መካነ ሥላሴን የሠራች የኢትዮጵያ ንጉሥ የናዖድ ልጁ ናት አባቱም የንጉሠ ገይኝ ልጅ ነው።ይህም ቅዱስ ከተወለደ በኋላ በክርስቲያን ወገኖችና በንጉሥ ልብነ ድንግል ላይ መከራና ስደት ሆነ። የዚህን ንጉሥ ዜና ግን በነገሥታት ታሪክ ተጽፎ ስለሚገኝ ትተንዋል።
ንጉሥ ልብነ ድንግልም ከአረፈ በኋላ ገላውዴዎስ ነገሠ። እስላሞችም በእርሱ ላይ ተነሡ ከቀኖችም በአንዱ ሲዋጋ ድል ለእርሱ ሆነ በኋላ ግን ድሉ ለእስላሞች ሆነ የዚች ዓለም ሥርዓቷ እንዲህ ተለዋዋጭ ነውና ያን ጊዜም ይህን ጻድቅ ላእከ ማርያምን ይዘው አሚም ወደሚባለው አለቃቸው አደረሱት እርሱም በክብር አኖረው።
በሃይማኖታቸውም እንዳልተባበራቸው አየው የተማረኩትንና የተገደሉትን በሚያያቸው ጊዜ ያለቅስ ነበርና። ስለዚህ እንዲሰልቡት አዘዘ። ይህንንም የጃንደራባነት ዕድል ሁሉ የሚያገኘው አይደለም ለተሰጠችው እንጂ። ክብር ይግባውና ጌታችን እንዳለ ከእናታቸው ሆድ ጀምሮ ሕፅዋን የሆኑ አሉ፣ በጦርነት ጊዜ ሰዎች ሕፅዋን ያደረጓቸውም አሉ፣ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን ሕፅዋን ያደረጉ አሉ ይህን ሊፈጽም የሚሻ ይፈጽም።
ከዚህ በኋላም ወደ ቱርክ ወሰዱት በመንገድም ብዙ መከራ አገኘው በግመል ላይ ዘቅዝቀው የሚሰቅሉበት ጊዜ ነበረ፣ በውኃ ጥማትና በፀሐይ ቃጠሎ የሚያሠቃዩበት ጊዜ ነበረ በጌታችንም ፈቃድ ከየመን አገር ደረሰ። የእስላሞች ንጉሥም ወደርሱ እንዲአቀርቡት አዘዘ ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ በየገጹ ሊናገሩት በማይቻል በታላቅ ተአምር ወደ ኢትዮጵያ ሀገር ተመለሰ።
ከዚህም በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሠራ በድኆችና በችግረኞች ላይ ቸርነትን አደረገ። ብዙ ትሩፋትንም አደረገ የጻድቃንና የሰማዕታትንም መታሰቢያቸውን ያደርጋል። ይልቁንም አምላክን የወለደች የቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም የበዓሏን መታሰቢያ በየወሩ ያደርግ ነበር። ዕረፍቱም በደረሰ ጊዜ ይኸውም የጥበብ ሁሉ ፍጻሜ ሞት ነው ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን ነፃ አውጥቶ አባቶቹ ወደ ሔዱበት ዓለም ሔደ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ
No comments:
Post a Comment