ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 6 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, July 25, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 6

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሐምሌ ስድስት በዚች ቀን እንደ ርሱ ያሉ ኤልያስና ኄኖክ ወደ አሉባት ብሔረ ሕያዋን የነቢዩ ዕዝራ ዕርገት ሆነ፣ ቅድስት ንስተሮኒን አረፈች፣ ጳውሎስ የተባለ ቅዱስ መርቄሎስ በሰማዕትነት ሞተ፣ የቅዱስ አብሮኮሮንዮስ እናት ገድለኛዋ ቴዎዳስያ በሰማዕትነት ሞተች፣ የገርአልታው አቡነ አብርሃም መታቢያቸው ነው፣ ሐዋርያው ቅድስ በርተሎሜዎስ መታሰቢያ ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ነቢዩ ዕዝራ
ሐምሌ ስድስት በዚች ቀን እንደ እርሱ ያሉ ኤልያስና ኄኖክ ወደ አሉባት ብሔረ ሕያዋን የዕዝራ ዕርገት ሆነ። ይህም ነቢይ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጽፍ ነበረ እርሱም ከሌዊ ወገን ነበረ። ከእግዚአብሔርም ጋራ ግሩም የሆነ ነገርን መናገር ጀመረ እንዲህም አለ ምድርን በፈጠርካት ጊዜ አዳምን ታስገኝ ዘንድ አዘዝካት አስገኘችውም።
ሁለተኛው የጥፋት ውኃ በጊዜው እንደ መጣና ሁሉን እንዳጠፋ ተናገረ ኖኅ አብርሃምና ዳዊት እንዴት እንደ ተመረጡ ደግሞ ተናገረ። ዳግመኛም ነፍስ ከሥጋዋ እንደምትወጣና ሰባት ቀኖች እንደምትዞር ከዚያም በኋላ እንደ ሥራዋ ወደተዘጋጀላት ቦታዋ እንደምትገባ ተናገረ።
ከዚያም ስለ ፍርድ ቀን ተናገረ። ከእግዚአብሔር ከጌትነቱ ብርሃን በቀር ፀሐይና ጨረቃ መብራትና ብርሃንም እንደሌሉ ተናገረ። ዳግመኛም በልቧ እጅግ በምትጨነቅ በምታዝንና በምትተክዝ ሴት አምሳል ጽዮንን አያት ልብሶቿም የተቀደዱ ነበሩ ልጇም ወደ ጫጕላው ቤት በገባበት ቀን እንደሞተ ነገረችው። ከዚህም በኋላ እርሷን ከማየቱ የተነሣ ፈርቶ በድንጋፄ እስከ ወደቀ ድረስ ፊቷ በድንገት እንደ መብረቅ በራ።
ደግሞም ዐሥራ ሁለት ክንፎችና ሦስት ራሶች ያሉት ንስር ከባሕር ሲወጣ ከክንፎቹም ውስጥ ራሶች ሲወጡ አየ እኒህም በየዘመናቸው ገዝተው የጠፉ ነገሥታት ናቸው። ደግሞም ስለ መድኃኒታችን ክርስቶስ መወለድ ተናገረ እንዲህም አለ። አንበሳ እያገሣ ከበረሀ ወጣ በሰው አንደበትም ሲናገር ንስሩንም ሲገሥጸው ሰማሁት አለ።
ዳግመኛም ስለ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ። በሌሊት ታላቅ ነፋስ ከባሕር ሲወጣ አየሁ ከማዕበሉ የተነሣ ባሕሩ ይታወክ ነበር ነፋሱም እንደ ሰው አምሳል ሁኖ ከባሕር ሲወጣ አየሁ። ደግሞም ከብዙ ኃይልና ክብር ጋር በሰማይ ደመና ማረጉን በአብ ቀኝ መቀመጡንም አይቶ ተናገረ።
ዳግመኛም በፈሳሹ ማዶ ያኖራቸው ዘጠኙ ነገድ እንደሚሰበሰቡ ተናገረ። ከዚህም በኋላ የነቢያት መጻሕፍትና የአባቶችን ትውልድ የያዙ መጻሕፍት ተደምስሰው መጥፋታቸውን በአሰበ ጊዜ ወደ በረሀ ገብቶ በጾምና በጸሎት ምሕላ ያዘ። ከእርሱም ጋር አምስት ጠቢባን ጸሐፊዎችን ወሰደ።
ከዕንጨቱም አንጻር ቃል ጠርቶት ዕዝራ አፍህን ክፈት ብሎ ኅብሩ እሳት የሚመስል ውኃን የተመላ ጽዋን ሰጠው። ያንንም ጽዋ ጠጣ ያን ጊዜም ልቡናው ጥበብን አገሣ። ተገልጾለትም መጻሕፍትን ሁሉ ሰበሰበ ለእነዚያም ሰዎች ልዑል አምላክ ዕውቀትን ሰጣቸው። መጻሕፍትንም ሁሉ በየተራቸው ጻፉ። በዚያም አርባ ቀን ኖሩ እነዚያ ግን ቀን ቀን ይጽፋሉ ማታ ማታም ይመገባሉ እርሱ ግን ቀን ይጽፋል ማታም ዝም አይልም በእነዚያ አርባ ቀኖችም ሁሉ መጻሕፍት ተጻፉ።
ከዚህም በኋላ ልዑል እንዲህ ሲል ተናገረው የዕውቀት ምሥጢር የጥበብም ምሥጢር እንደ ፈሳሽ ውኃም ያለ ዕውቀት ላላቸው ታስተምራቸው ዘንድ ይህን ተመልከት እንዳለውም አደረገ። በአራተኛውም ዘመን ከሚቈጠሩ ከብዙ ሱባዔ በአምስተኛው ሱባዔ ይህ ዓለም ከተፈጠረ ከአምስት ሺ ዘመን በኋላ ጨረቃ ሠርቅ አድርጋ ጨለማዋን ባጣች በአሥረኛው ቀን በሦስተኛው ወር በዘጠና አንድ እንደእርሱ ያሉ ደጋግ ሰዎች ወዳሉበት ዕዝራን ወሰዱት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅድስት ንስተሮኒን
በዚህችም ዕለት ቅድስት ንስተሮኒን አረፈች። እርሷም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ውስጥ ነበረች። እርሷም አስቀድማ ኃጢአተኛ ነበረች ከዚያም በኋላ ንስሓ ገብታ ወደ እግዚአብሔር በተቃጠለ ልብ ተመለሰች የሥጋን ፍላጐቶች ሁሉ ናቀች እመምኔት እስከ ሆነች ድረስ በበጎ ሥራ ሁሉ ትሩፋትንና ተጋድሎን አበዛች።
እኅቶችም ከገድል ብዛትና ምግብን ከመተው የተነሣ ሥጋዋ እንዳለቀ አይተው ሥጋሽን እንድትረጂ ጥቂት እህል በወጥ ብዪ አሏት። አብዝተውም ግድ ባሏት ጊዜ ልጆቼ ሆይ ወደ ቀድሞ ልማዴ እንዳልመለስ ጥቂት ወጥ ስለመብላት አትድከሙ ስለዚህ ወጥ አልበላም አለቻቸው። ከዚህ በኋላ በሰላም አረፈች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ መርቄሎስ
በዚህችም ዕለት ጳውሎስ የተባለ ቅዱስ መርቄሎስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ ነው። እርሱም ሐዋርያትን አገልግሎአቸዋል። ወንጌልንም ለመስበክ ከእነርሱ ጋር ሔደ። የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስን መልእክቶች አደረሰ በመከራውም ጊዜ አገለገለው። ከእርሱም ጋር መከራ ተቀበለ ከእርሱም አልተለየም።
ወደ ሮሜ አገርም ከርሱ ጋር ገብቶ ቅዱስ ወንጌልን አስተማረ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማመን ከአረማውያን ብዙዎቹን መለሳቸው። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በሰማዕትነት በሞተ ጊዜ ይህ ረድእ መርቄሎስ መጥቶ ከመስቀል ላይ አወረደው በከበሩ ልብሶችም ከሽቱ ጋር ገነዘው። በሣጥንም አድርጎ ከምእመናን በአንዱ ቤት አኖረው።
የሐዋርያው ጴጥሮስ ደቀ መዝሙርም እንደሆነ በኔሮን ዘንድ ወነጀሉት ንጉሡም ወደ እርሱ አቅርቦ ጠየቀው እርሱም ለሐዋርያው ጴጥሮስ ደቀ መዝሙሩ እንደሆነ አመነ ደግሞም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕውነተኛ አምላክ እንደሆነ ታመነ።
ስለዚህም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ገረፈውም ዘቅዝቀው ሰቅለውም ከበታቹ ጢስን አጤሱበት። ከዚህም በኋላ ንጉሡ እንዴት ሁነህ መሞት ትሻለህ በምን አይነት ሞት ልግደልህ ንገረኝ አለው። ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰ እኔ ሕይወት በሆነ በክርስቶስ ስም መሞት እሻለሁ አንተ ግን በፈለግኸው ዓይነት ግደለኝ ፈጥነህም ወደ ፈለግኸው አድርሰኝ።
ያን ጊዜም ንጉሡ ኔሮን እንዲገርፉትና እንደ መምህሩ ጴጥሮስ ዘቅዝቀው እንዲሰቅሉት አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት። የሰማዕታትንና የሐዋርያትን አክሊል ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ገድለኛዋ ቴዎዳስያ
በዚህችም ቀን የቅዱስ አብሮኮሮንዮስ እናት ገድለኛዋ ቴዎዳስያ በሰማዕትነት ሞተች፡፡ ከእርሷ ጋርም ሁለት መኳንንቶችና አሥራ ሁለት ሴቶች በሰማዕትነት ሞቱ።
ይህም እንዲህ ነው ይቺ ቅድስት ልጇ አብሮኮሮንዮስን ክርስቲያን ነው ብለው እንደወነጀሉትና ለሞት እስቲደርስ ጽኑዕ ሥቃይን እንዳሠቃዩት ሰማች። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚያች ሌሊት ተገለጠለት ከሥቃዩም አዳነው ያለ ምንም ጉዳት ጤናማ ሆነ።
እኒህ ሁለቱ መኳንንትና ዐሥራ ሁለት ሴቶች ከእናቱ ጋር በአዩት ጊዜ እጅግ አደነቁ እንዲህ ብለውም ጮኹ እኛ በአብሮኮሮንዮስ አምላክ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን መኰንኑም ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ በመንግሥተ ሰማያትም የክብር አክሊልን ተቀበሉ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የገርአልታው አቡነ አብርሃም
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የገርአልታው አቡነ አብርሃም መታቢያቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ሲሆኑ የትውል ሀገራቸው ትግራይ ነው፡፡ በሥርዓተ ገዳማትና በሥርዓተ ቀኖና ዐዋቂነታቸው ወደር የማይገኝላቸው አባት ናቸው፡፡ ከመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በስማቸው የተሠራው ገዳም በትግራይ ገርዓልታ የሚገኝ ሲሆን አጽቢ መንበርታ ደብረ ጽዮን አቡነ አብርሃም ገዳም ይባላል፡፡ ስለ አቡነ አብርሃም ከዚኽ ያለፈ ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በገዳማቸው ያሉ አባቶችም የጻድቁን የዕረፍታቸውን ቀን ከመጠቆም ያለፈ ነገር ለመናገር ገድሉ የላቸዉም፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅድስ በርተሎሜዎስ
በዚህች ዕለት ሐዋርያው ቅዱስ በርተሎሜዎስ መታሰቢያ ነው፡፡ ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ ዕጣ የደረሰው አልዋሕ በሚባል አገር ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሊያደርሰው አብረው ወደ አልዋሕ ሄዱ፡፡ ወደ ከተማው ለመግባት ምክንያት ፈለጉና ቅዱስ ጴጥሮስ ቅዱስ በርተሎሜዎስን ‹‹አትክልተኛ ባለሙያ ነው›› ብሎ የወይኑን ቦታ እንዲጠብቅለት ለአንድ ባለጸጋ መኰንን ባሪያ አድርጎ ሸጠው፡፡ ባለጸጋውም በርተሎሜዎስን በ30 እስቴታር ገዝቶት ሄደ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ገንዘቡን ደብቆ ለቅዱስ በርተሎሜዎስ በድብቅ ሰጥቶት እንዲመጸውተው ነግሮት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፡፡ አልዋሕ ከገባ በኋላ ቅዱስ በርተሎሜዎስ የወይን ቦታው አለቃ ሆኖ 40 ቀን ተቀመጠ፡፡ ወንጌሉን ባለመስበኩ በሀዘን እያለቀሰ ጌታችንን በጸሎት ጠየቀው፡፡ በገንዘቡ ገዝቶት ባሪያው ያደረገው ባለጸጋውም የወይኑን ቦታ ያይ ዘንድ እንደመጣ መርዘኛ እባብ ነድፎት ሞተ፡ ሕዝቡም ተሰብስቦ ሲያለቅስ በርተሎሜዎስ ግን ወደ ጌታችን ከጸለየ በኋላ ሄዶ ባለጸጋውን ሰው ከሞት አስነሣው፡፡ በዚህም ሕዝቡ ሁሉ አምነው ተጠምቀዋል፡፡
በርተሎሜዎስም ወደ ሌሎች አገሮች ሄዶ አስተማረ፡፡ ጌታችን ወደ በርበሮች ዘንድ ሄዶ ወንጌልን እንዲሰብክ አዘዘው፡፡ ረዳት እንዲሆነውም እንድርያስን ከደቀ መዝሙሩ ጋር ላከለት፡፡ የሀገሪቱ ሰዎች ግን እጅግ ክፉዎች ነበሩ፡፡ በሐዋርያቱም ፊት በአስማት አስደናቂ ተአምራት እያሳዩ ትምህርታቸውን የማይቀበሏቸው ሁኑ፡፡ ይህን ጊዜ ጌታችን ሰውን ከሚበሉ አገር አንዱን ገጸ ከልብ ይታዘዝላቸው ዘንድ በሚያዙትም ነገር ሁሉ ከትእዛዛቸው እንዳይወጣ አዘዘው፡፡ ሐዋርያትም ወደ በርበሮች አገር ዳግመኛ በገቡ ሰዓት ይበሏቸው ዘንድ ኃይለኛ አራዊትን አውጥተው ለቀቁባቸው፡፡ ያ ገጸ ከልብም በአራዊቱ ላይ ተነሥቶ እየነጠቀ በላቸው፡፡ ይህንንም የተመለከቱት በርበሮች እጅግ ፈርተው በድንጋጤ ብቻ የሞቱ አሉ፡፡ በሐዋርያቱም እግር ሥር ወደቁ፡፡ ሐዋርያቱም አስተምረው ካሳመኗቸው በኋላ አጥምቀዋቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ በርተሎሜዎስ እግዚአብሔርን ወደማያውቁ አገሮች ሄዶ ብዙ ተአምራትን እያደረገ አስተምሮ አጠመቃቸው፡፡ የከሃዲው ንጉሡ የአግሪጳን ሚስትም ትምህርቱን ሰምታ በጌታችን አመነች፡፡ ንጉሡ አግሪጳም በዚህ እጅግ ተቆጥቶ ቅዱስ በርተሎሜዎስን ብዙ ካሠቃየው በኋላ አሸዋ በተሞላ ትልቅ ከረጢት ውስጥ ከቶ ከነሕይወቱ ባሕር ውስጥ እንዲጥሉት አደረገ፡፡ ምእመናንም ሥጋውን አውጥተው በክብር ቀብረውታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ በርተሎሜዎስ ይኽች ዕለት መታሰቢያ በዓሉ እንድትኾን አባቶቻችን አዘዋል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages