በዕለተ ምጽአት ጌታችን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት ከአእላፋት መላእክቱ ጋር ሲመጣ የሚሆነውን ሲናገር :-
"የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል" ብሎአል:: ማቴ. 24:30
የሰው ልጅ የተባለው መድኃኔዓለም ክርስቶስ በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ከመምጣቱ በፊት ፣ የምድር ወገኖች ዋይታ ከመሰማቱ በፊት አንድ ነገር ይከሰታል?
ይህ የሰው ልጅ ምልክት ምንድር ነው?
"ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው" ተብሎ የተነገረለት ቅዱስ መስቀሉ ነው::
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን የወንጌል ክፍል ሲተረጉም ከጌታችን መምጣት ቀድሞ በሰማይ ስለሚታየው የሰው ልጅ ምልክት (መስቀል) እንዲህ ይላል:-
"መስቀል ከፀሐይ ይልቅ ብሩሕ ይሆናል:: ፀሐይም ትጨልማለች ብርሃንዋንም ትሰውራለች:: ከዚያም በተለምዶ በማትታይበት ሰዓት ትታያለች:: ይህም የአይሁድ ጠማማነት ይቆም ዘንድ ነው" (Homily on Matthew 24)
ጌታችን በምድር ላይ ከተመላለሰ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው መስቀል ዳግም ሊፈርድ ሲመጣ ግን መስቀሉ ሐዋርያ ሆኖ ቀድሞ በሰማይ ላይ ያበራል::
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 17 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)
No comments:
Post a Comment