ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 21 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, October 30, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 21


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት 21 በዚህችም ቀን #እመቤታችን_ተአምራትን_አድርጋ_ሐዋርያው_ማትያስን ከእሥራት ቤት ያወጣችበት፣ #የነቢይ_ኢዩኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ፣ የማርታና የማርያም ወንድም #የቅዱስ_አልዓዛር ሥጋው ከቆጵሮስ አገር የፈለሰበት፣ የቅዱስ አባት #አባ_ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም እረፍት ነው፣ ታላቁ ጻድቅ #አቡነ_አላኒቆስ ዕረፍታቸው ነው፡፡


በዚህችም ቀን እመቤታችን ማርያም ተአምራትን አድርጋ ደቀ መዝሙር ማትያስን ከእሥራት ቤት አዳነችው።
የከበሩ ቅዱሳን ወንጌልን በዓለም ዞረው ይሰብኩ ዘንድ ዕጣ ሲጣጣሉ ለቅዱስ ማትያስ ዕጣ የደረሰው ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ነበር፡፡ ይህችም ሀገር እስኩቴስ የተባለች ሩሲያ እንደሆነች የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ማትያስም እነዚህ ሰውን የሚበሉ ሰዎች አገራቸው እንደደረሰ ዐይኑን አውልቀው አሠሩት፡፡ ምግባቸውም የመጻተኛ ሰው ሥጋ ነው፡፡ በልማዳቸው መሠረት መጻተኛን ሰው ገና እንደያዙት ዐይኖቹን ዐውልቀው በእሥር ቤት ያኖሩታል፡፡ እስከ 30 ቀንም ድረስ ሳር እያበሉ ያስቀምጡትና በ30ኛው ቀን አውጥተው አርደው ይበሉታል፡፡
ሐዋርያው ማትያስንም በልማዳቸው መሠረት ዐይኖቹን አውልቀው አሠሩት፡፡ ሐዋርያውም በእሥር ቤት ሆኖ በዚያ ላይ ዐይኖቹን ታውሮ ሳለ በጭንቅ ወደ ጌታችንና ወደ እመቤታችን ይለምን ነበር፡፡ ነገር ግን እመብርሃንና ልጇ መድኃኔዓለም 30ኛው ቀን ሳይፈጸም ሐዋርያው እንድርያስን ወደ እርሱ ላኩለት፡፡ ማትያስም ዐይኑን ፈወሱለትና ማየት ቻለ፡፡
እንድርያስም በተዘጋው በር በተአምራት ገብቶ አሥርቤቱ ውስጥ ያሉ እሥረኞችን በስውር አውጥቶ ከከተማው ውጭ ካስቀመጣቸው በኋላ ሁለቱ ሐዋርያት ተመልሰው ሰውን ለሚበሉት ሰዎች ተገለጡላቸው፡፡ እነርሱም ይዘው በአንገታቸው ገመድ አግብተው ለ3 ቀን በሀገራቸው ጎዳናዎች ላይ ሁሉ ጎተቱዋቸው፡፡ ሁለቱም ሐዋርያት በጸሎታቸው ከእሥር ቤቱ ምሰሶ ሥር ውኃ አፈለቁና ውኃው ሀገራቸውን ሁሉ እስኪያጥለቀልቅና ሰዎቹንም እስከ አንገታቸው ድረስ እስከሚደርስ ሞላ፡፡ ሁሉም በተጨነቁ ጊዜ ሁለቱ ሐዋርያት በፊታቸው ተገለጡና ‹‹በጌታችን እመኑ ትድናላችሁ›› በማለት ወንጌልን ሰብከውላቸው አሳመኗቸው፡፡ ምሥጢራትንም ሁሉ ገለጡላቸው፡፡ ደግሞም የአራዊት ጠባይን ከሰዎቹ ያርቅላቸው ዘንድ ወደ ጌታችንና ወደ ተወደደች እናቱ ከጸለዩ በኋላ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው፡፡ ያ የአውሬነት ጠባያቸውም ጠፍቶላቸው የዋህ፣ ቅንና ሩኅሩኆቸ ሆኑ፡፡ ሐዋርያትም ሃይማኖትን እያስተማሯቸው 30 ቀን አብረዋቸው ከተቀመጡ በኋላ አገልጋይ ኤጲስ ቆጶሳትን፣ ካህናትንና ዲያቆናትን ሾመውላቸው ወደ ሌላ ሀገር ሄዱ፡፡
ለሐዋርያት ሞገሳቸው ጣዕመ ስብከታቸው የኾነች ክብርት እመቤታችን ለእኛም ትለመነን!

ዳግመኛም በዚህችም ቀን የነቢይ ኢዩኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። ይህም የእስራኤልን ልጆች የሚያስተምርና የሚገሥጻቸው ነበር ስለ ክርስቶስም በኢየሩሳሌም መኖርና ማስተማር ትንቢት ተናገረ። ደግሞም ስለ መከራው በሐዋርያትና በሰባ ሁለቱ አርድእት በሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ላይ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ እንዲህ ሲል ተናገረ።
ከዚህ በኋላ በሥጋዊ በደማዊ ሰው ሁሉ ከመንፈሴ አሳድርበታለሁ ሴቶች ልጆቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ ትንቢትን ይናገራሉ አለቆቻችሁ ሕልምን ያልማሉ ጎልማሶቻችሁም ራእይን ያያሉ። ሁለተኛም እንዲህ አለ ያን ጊዜ ከተራራው ማር ከኮረብታውም ወተት ይፈሳል በቤተ እግዚአብሔር አጠገብ ካሉ ከይሁዳ አገሮች ሁሉ ምንጩ ከላይ ወደታች ይፈሳል።
ሙታን በሚነሡ ጊዜ ስለሚሆነው የፍርድ ሰዓት እንዲህ አለ ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ የከዋክብትም ብርሃናቸው ይጠፋል። የትንቢቱንም ወራት አድርሶ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

ቅዱስ_አልዓዛር የማርታና የማርያም ወንድም
በዚችም ቀን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው የቅዱስ አልዓዛር ሥጋው ከቆጵሮስ አገር የፈለሰበት ሆነ።
ከክርስቲያን ነገሥታትም አንዱ ሥጋው በቆጵሮስ እንዳለ በሰማ ጊዜ ከቆጵሮስ ደሴት ወደ ቊስጥንጥንያ አፈለሰው። ሊአፈልሱትም በወደዱ ጊዜ በከበረ የደንጊያ ሣጥን ውስጥ ሁኖ በምድር ውስጥ ተቀብሮ አገኙት በላዩም እንዲህ የሚል ጽሑፍ ነበረ ይህ በመቃብር ውስጥ አራት ቀን ከኖረ በኋላ ከሙታን ለይቶ ላስነሣው ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጁ የሆነ የቅዱስ አልዓዛር ሥጋ ነው።
ይህንንም በአዩ ጊዜ ደስ ተሰኙበት ተሸክመውም ወደ ቊስጥንጥንያ አገር ወሰዱት ካህናቱም ሁሉ ወጥተው በታላቅ ክብር በመዘመርና በማመስገን ተቀበሉት በአማረ ቦታም አኖሩት በዚችም ቀን በዓልን አደረጉለት።

በዚህችም ቀን ለከበረች አገር ኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት የሆነ ቅዱስ አባት አባ ዮሐንስ እግዚአብሔርን በሚወድ የንጉሥ ሰይፈ አርዕድ ደግሞ ቈስጠንጢኖስ ለሚባል ልጁ በሆነ በንጉሣችን በዳዊት ዘመን አረፈ።
ይህም ቅዱስ ከምስር አገር ታላላቆች እግዚአብሔርን የሚፈሩ የክርስቲያኖች አባቶች ልጅ ነው። የዲቁና መዓረግንም ለመሾም እስከ ተገባው ድረስ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማሩ በበጎ አስተዳደግ አሳደጉት። ከዚህም በኋላ በዲቁናው ሹመት አገልግሎቱን በአሳመረ ጊዜ የቅስና መዓረግ የሚገባው ሁኖ ቅስና ተሾመ።
በጾም በጸሎት እግዚአብሔርንም በመፍራት የተጠመደ ሁኖ ድኆችንና ችግረኞችን የሚወዳቸው የሚረዳቸው ሆነ ያን ጊዜ የሐዋርያት የሆነች የጵጵስና ሹመት የምትገባው ሁና በከበረች አገር በኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ፈቃድ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ ሕዝቡንም በፈሪሀ እግዚአብሔርና በትሕትና የሚያስተምራቸው ሆነ።
እነርሱም ስለ ቅድስናው እጅግ የሚወዱት ሆኑ መልኩና የአንደበቱ አገላለጥ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ያማረ ነበር። በሹመቱም ጥቂት ዘመናት ከኖረ በኋላ ከመንበረ ሢመቱ እስከ አራቀው ድረስ በላዩ ሰይጣን ምክንያትን አመጣ።
ይህም እንዲህ ነው በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአባ ማርቆስ ዘመን በግዛቱ ውስጥ ያሉ እስላሞች ስለ ዐመፁበት የኢትዮጵያ ንጉሥ ፈጅቷቸው ነበርና ስለዚህ በግዛቱ ውስጥ በሚኖሩ እስላሞች ላይ ክፉ እንዳያደርግ ለኢትዮጵያ ንጉሥ መልእክት እንዲልክ ሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስን የምስር ንጉሥ አዘዘው።
አባ ማርቆስም ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥ ስለሚላኩ ሰዎች ከመኳንንቱ ከኤጲስ ቆጶሳቱና ከሀገር ታላላቆች ሽማግሌዎች ጋር ተማክሮ እሊህን ብሩሀን ከዋክብት የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስን የምስር ኤጲስቆጶስ አባ ሳዊሮስን በእውቀታቸው በአስተዋይነታቸውና በቅድስናቸው መረጡአቸው ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥም ይሔዱ ዘንድ ግድ አሏቸው።
እነርሱም ታዛዦች ሁነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ የኢትዮጵያ ንጉሥም መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው እሊህንም ቅዱሳን አባቶች ይቀበሏቸው ዘንድ አሽከሮቹን በቅሎዎችን አስይዞ ላከ በመጡም ጊዜ በታላቅ ደስታ ሰላምታ አቀረበላቸው ከእርሳቸውም ቡራኬን ተቀበለ ታላቅ ክብርንም አከበራቸው ። እነርሱም የሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስን ደብዳቤ ሰጡት እርሱም ተቀብሎ አንብቦ ለሊቀ ጳጳሳቱ ቃል ታዛዥ መሆኑን ገለጠላቸው።
ከዚህም በኋላ ወደ ሀገረ ስብከታቸውና ወደ ሕዝባቸው መመለስን በአሰቡ ጊዜ ስለ ቅድስናቸውና ስለ ትምህርታቸው ጣዕም ስለ ወደዳቸው የተከበረው ንጉሥ መመለስን ከለከላቸው በእርሱ ዘንድ እነርሱ እንደ እግዚአብሔር መላእክት ሁነዋልና ፊታቸውም እንደ ፀሐይ ያበራል።
ከጥቂት ወራትም በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው እግዚአብሔር በወደደ ጊዜ በላዩ ደዌ ላከበት በዚያውም ደዌ በሰላም አረፈ።

ዳግመኛም በዚህች ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ አላኒቆስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ አቡነ አላኒቆስ የትውልድ ቦታቸው ሸዋ አንኮበር ሲሆን አባታቸው ንጉሡ ዐፄ ይኩኖ አምላክ ነው፡፡ ንጉሡ አባታቸው ‹‹አግባና መንግሥቴን ይዘህ ተቀመጥ›› ቢላቸው እርሳቸው ግን ንግሥናን በመናቅ እምቢ ብለው ሄደው ከእመቤታችን ሥዕል ሥር ወድቀው ቢለምኗት እምቤታችን ተገልጣላቸው ‹‹ክፍልህ ምናኔ ነው፣ የአባትህ መንግሥት ያልፋል የልጄ መንግሥት ግን ዘላለማዊ ነው›› አለቻቸው፡፡ ጻድቁም ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ሄደው በዚያው መንኩሰው ገዳሙን እያገለገሉ ተቀመጡ፡፡ ከጸሎታቸው በኋላ ራሳቸውን ወደ ባሕሩ ይጥሉ ነበርና አንድ ቀን እንዲሁ ራሳቸውን ወደ ባሕሩ ሲጥሉ መላእክት አውጥተዋቸዋል፡፡ አቡነ አላኒቆስ ወደ አክሱም እንዲሄዱ ታዘው ከሄዱ በኋላ በዚያም የጽላተ ሙሴ የታቦተ ጽዮን አጣኝ ሆነው 40 ዓመት ተቀምጠዋል፡፡ እመቤታችንም ተገልጣላቸው በዓታቸውን እንዲያጸኑ ከነገረቻቸው በኋላ ከአክሱም ወጣ ብሎ የሚገኘውን ማይበራዝዮ ገዳምን መሠረቱ፡፡ በዚያም እጅግ አስገራሚ ተአምራትን እያደረጉ ወንጌልን እያስተማሩ አገልግለዋል፡፡
አንድ ቀን መኰንኑ ወደ ሩቅ ቦታ ሲሄድ ቤተሰባቸውን ለንስሓ አባታቸው አደራ ሰጥተው ሄዱ፡፡ የንስሓ አባታቸውም የአቡነ አላኒቆስ ጓደኛ ነበሩ፡፡ መኰንኑም ከሄዱበት ሲመለሱ ሚስታቸው ከአሽከሯ አርግዛ ጠበቀቻቸው፡፡ ‹‹ከማን አረገዝሽ?›› ብለው ጽኑ ግርፋት ቢገርፏት ዋሽታ ‹‹ያረገዝኩት ከንስሓ አባቴ ነው›› አለች፡፡ መኰንኑም መነኩሴውን እገላለሁ ብሎ ሲነሣ መነኩሴውም ወደ አቡነ አላኒቆስ ሄደው አለቀሱ፡፡ አቡነ አላኒቆስም የመኰንኑን ሚስት ቢጠይቋት ባሏን ፈርታ ‹‹አዎ ከመነኩሴው አባት ነው ያረገዝኩት›› አለች፡፡ እሳቸውም ‹‹የተረገዘው ከዚህ መነኩሴ ከሆነ በሰላም ይወለድ፣ ካልሆነ ግን አይወለድ›› ብለው በቃላቸው አስረውና ገዝተው ሸኟቸው፡፡
በግዝታቸው መሠረት ሴቲቱ ድፍን 22 ዓመት ሙሉ ሳትወልድ በጭንቅና በጣር ኖረች፡፡ በአልጋ ላይ ሆና ተጨንቃ ስትኖር በመጨረሻ ለቤተሰቦቿ ተናግራ ወደ አቡነ አላኒቆስ ዘንድ በቃሬዛ ወሰዷትና ይቅርታ ጠይቃ እውነቱን ተናገረች፡፡ እሳቸውም ‹‹እግዚአብሔር ይፍታሽ›› ቢሏት 22 ዓመት ሙሉ ተረግዞ የነበረው ልጅ ትልቅ ሰው ሆኖ ጥርስ አውጥቶ፣ ፂም አብቅሎ በሰላም ተወለደ፡፡ እርሱም ከተወለደ በኋላ አባቱ ማን እንደሆነ ተናገረ፡፡ ጻድቁ አባታችንም ልጁን አሳድገውት አስተምረው አመንኩሰውታል፡፡ ስሙንም ተወልደ መድኅን አሉት፡፡ በስሙ የተሠሰራ ቤተ ክርስቲያን በትግራይ ጽንብላ ወረዳ ይገኛል፡፡
ጻድቁ አቡነ አላኒቆስ ሌላም የሚታወቁበት አንድ ግብር አላቸው፡፡ የማይበራዝዮ ገዳማቸው አገልጋይ የሆነው መነኩሴ በሬ ጠምዶ ሲያርሱ አንበሳ ከጫካው ወጥቶ አንዱን በሬ በላው፡፡ መነኩሴውም መጥተው ለአቡነ አላኒቆስ ነገሯቸው፡፡ እሳቸውም ‹‹ጸሎቴን እስክጨርስ ድረስ ወደ ጫካው ሂድና አንበሳውን ‹አላኒቆስ ባለህበት ጠብቀኝ እንዳትንቀሳቀስ ብሎሃል› ብለህ ተናገር›› ብለው ለመነኩሴው ነገሯቸው፡፡
መነኩሴውም እንደታዘዙት ወደ ጫካው ሄደው ጮኸው በሉ የተባሉትን ተናገሩ፡፡ አቡነ አላኒቆስም ጸሎታቸውን ሲጨርሱ ወደ ጫካው ሄደው አንበሳውን የበላውን በሬ አስተፍተውት በሬውን ነፍስ ዘርተውበት ከሞት አስነሥተው ዕለቱን እንዲታረስ አድርገውታል፡፡ አንበሳውንም ገዝተው ወደ ገዳማቸው ወስደው ሰባት ዓመት ውኃ እያስቀዱት እንዲያገለግላቸው አድርገውታል፡፡
አቡነ አላኒቆስ አንበሳውን አስረው ያሳድሩበት የነበረው ዛፍና ውኃ ያጠጡበት የነበረው ትልቅ የድንጋይ ገበታ ዛሬም ድረስ በገዳሙ ይገኛል፡፡ ከ22 ዓመት እርግዝና በኋላ ሴቲቱ ጥርስና ፂም ያለው ልጅ እንድትወልድ ያደረጉበት ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይም ከነቅርጹ በገዳሙ በግልጽ ይታያል፡፡ ጻድቁ ጥቅምት 21 ቀን ዐርፈው በዚያው በማይባራዝዮ ገዳማቸው ተቀብረዋል፡፡ ጸበላቸው እጅግ ልዩ ነው፣ ያላመነውን ሰው አስፈንጥሮና ገፍትሮ ይጥለዋል እንጂ አያስቀርበውም፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶች ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages