ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 22 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, October 31, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 22

 

ጥቅምት 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
 
1/ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ ሐዋርያዊ
2/ቅዱስ ሲላሰ (አረጋዊ የቅዱሰ ሉቃስ ረድእ)
3/ቅዱስ ታኦፊላ
4/"477 "ሰማዕታት (የቅዱሰ ሉቃስ ማሕበር)
 
ወርሐዊ በዓላት
 
1/ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2/ቅዱስ ደቅሰዮሰ( የእመቤታችን ወዳጅ)
3/አባ እንጦንሰ አበ መነኮሳት
4/ቅዱስ ጳዉሊ የዋህ
5/ቅዱስ ዮልዮሰ ሰማዕት
 
 

 
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ሁለት በዚህች ቀን ብልህ ጥበበኛ የሆነ ቅዱስ ወንጌላዊ ሉቃስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ የከበረ ወንጌል ከመዘገባቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የተቆጠረ ነው።
እርሱም ወንጌልን ስለማስተማር በሥራው ሀሉ ሐዋርያት ጴጥሮስንና ጳውሎስን የሚአገለግላቸው ሆነ ለታኦፊላም ወንጌልንና የሐዋርያትን ዜና የጻፈ ሉቃስ ነው።
ቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስም ከተገደሉ በኋላ በሮሜ ሀገር የሚያስተምር ሆነ በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ ለምእመናን መልእክትን ይጽፍ ነበር። ስለዚህም ጣዖት አምላኪዎች ከአይሁድ ጋር በመስማማት አንድ ግምባር ፈጠሩ በንጉሥ ኔሮን ፊት ቁመው ስለ ሐዋርያው ሉቃስ እንዲህ ብለው ጮኹ ይህ ሉቃስ ብዙዎች ሰዎችን በሥራዩ ወደ ትምህርቱ አስገባቸው። ንጉሥ ኔሮንም ወደ ፍርድ አደባባይ ሉቃስን እንዲአቀርቡት አዘዘ።
ሐዋርያ ሉቃስም ከዚህ ዓለም መውጫው እንደ ደረሰ በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ወደ ባሕር ዳርቻ ሔደ። በዚያም ዓሣ የሚያጠምድ አንድ ሽማግሌ ሰው አገኘ። መጻሕፍቱንና ደብዳቤዎቹን ሰጠው ወደ እግዚአብሔር መንገድ መርተው ያደርሱሃልና እሊህን መጻሕፍት ጠብቃቸው አለው።
በንጉሥ ኔሮንም ፊት ቀርቦ በቆመ ጊዜ ንጉሡ በሥራይህ ሕዝቡን የምታስት እስከመቼ ነው አለው ቅዱስ ሉቃስም እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያው ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም ብሎ መለሰለት።
ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይቺን እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡ አዘዘ በቆረጡትም ጊዜ ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ እወቅ ነገር ግን የጌታዬንና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ። ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት። ከዚህም በኋላ ለያት በዚያም የነበሩ አደነቁ የሠራዊት አለቃውና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ቁጥራቸውም አራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡአቸው የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።
ከዚህም በኋላ የቅዱስ ሉቃስን ሥጋ በማቅ አይበት ውስጥ አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት በእግዚአብሔርም ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ። ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት በአማረ ቦታም አኖሩት።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ሐዋርያ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages