ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 29 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 8, 2022

ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 29

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ ዘጠኝ በዚህችም ቀን #ከቅድስት_አርሴማና_ከእመምኔቷ_ከአጋታ ጋር ደናግላን በሰማዕትነት አረፉ፤ ዳግመኛም #የቅዱስ_ዮሐንስ_ነባቤ_መለኮት (ወንጌላዊው) እንደ ንስር መጥቆ "ቀዳሚሁ ቃል.." (ዮሐ. ፩፥፩) ብሎ ወንጌሉን የጻፈበት ዕለት ነው።



በዚችም ቀን ከቅድስት አርሴማና ከእመምኔቷ ከአጋታ ጋር ደናግል በሰማዕትነት አረፉ። ይህም እንዲህ ነው በከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን እርሱ መልኳ ውብ የሆነ ብላቴና ድንግል ሊአገባ ሽቶ በየሀገሩ ሁሉ ሒደው መርጠው ያመጡለት ዘንድ አሽከሮቹን አዘዘ።
ይችንም የሚመስላት የሌለ ቅድስት አርሴማን በሮሜ አገር በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ አገኙዋት። ሥዕሏንም ሥለው ለንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ላኩለት ንጉሡም ሥዕሏን በአየ ጊዜ እጅግ ደስ አለውና ለሠርግ እንዲመጡ ወደ መኳንንቱ ላከ።
እሊያ ደናግልም ይህን ነገር በአወቁ ጊዜ ይረዳቸው ዘንድ ድንግልናቸውንም ይጠብቅ ዘንድ አልቅሰው ወደ እግዚአብሔር ለመኑ። ከዚህም በኋላ ተነሥተው በሥውር ሸሹ የንጉሥ ድርጣድስ ግዛት ወደ ሆነ ወደ አርማንያ ሀገርም ደርሰው በአንድ ቦታ ተቀመጡ ከእርሳቸውም ጋር የተሰደዱ ቁጥራቸው ሰባ አምስት የሆነ ወንዶች፣ ሴቶችም ሠላሳ ዘጠኝ የሆኑ ከእርሳቸው ጋራ አሉ። ምግባቸውን አያገኙም ነበርና በታላቅ ችግር ውስጥ ኖሩ ከእነርሱም መብራት የምትሠራ አንዲት ሴት ነበረች ከእርሷም የእጅ ሥራ ከሚገኘው በየጥቂቱ ይመገባሉ።
ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም የከበረች አርሴማን በፈለጋት ጊዜ አላገኛትም ግን በአርማንያ አገር እንዳለች ስለርሷ ሰማ። ደግሞ ለአርማንያ ንጉሥ ለድርጣድስ ስለርሷ ከዲዮቅልጥያኖስ ሸሽታ እንደ መጣች የአርሴማን ሥራ ነገሩት እርሱም አንዱን የአርማንያ መኰንን ለእኔ ጠብቃት ወደ እኔም ላካት ብሎ አዘዘው።
ደናግሉም ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ ሌላ ቦታ ተሠወሩ ወደ ንጉሥም ወነጀሉአቸው ንጉሡም ቅዱስት አርሴማን በክብር አድርገው ያመጧት ዘንድ አዘዘ እርሷም ወደ እርሱ መምጣትን እምቢ በአለች ጊዜ እየጎተቱ ወስደው ወደርሱ አደረሷት።
የቅድስት አርሴማንም ላህይና ደም ግባቷን በአየ ጊዜ ድንግልናዋን ሊያረክስ ሽቶ እናቷ አጋታን አባብላ እሺ ታሰኝለት ዘንድ አዘዛት አጋታም ወደርሷ ሒዳ ልቧን አስጨከነች እንዲህም አለቻት። ዕወቂ ይህ ርኲስ አረሚ እንዳያረክስሽና ሰማያዊ ሙሽራሽን እንዳትተዪ እርሱም ክብር ይግባውና የእግዚአብሔር ልጅ ሕያው ክርስቶስ ነው።
ንጉሡም ይዞ ወደ እልፍኙ ሊአስገባት ከአደባባይ መካከል ተነሥቶ ድንግል አርሴማን ያዛት። በዚያንም ጊዜ በቅድስት አርሴማ ላይ የእግዚአብሔር ኃይል አደረባትና በምድር ላይ ጣለችው እርሱ ግን በጦርነት እጅግ የጸና አርበኛ ስለ ነበር በታናሽ ሴት ብላቴና ስለተሸነፈ ያን ጊዜ አፈረ። ራሷንም በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጧት ከዚህም በኋላ ደናግሉን ሁሉ ከእናታቸው አጋታ ጋር ይገድሏቸው ዘንድ አዘዘ።
አንዲት የታመመች ድንግል ነበረች በዐልጋዋ ላይም እንደተኛች ወደ ወታደሮች ጮኸች መጥተውም እንደ እኅቶቿ ራሷን ቆረጡ ሁሉም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ እነዚያንም ከሮሜ አገር አብረው የመጡ ወንዶችን ገደሏቸው ቁጥራቸውም ሰባ አምስት ናቸው ሥጋቸውም በተራራ ላይ የተጣለ ሁኖ ቀረ።
ሰማዕታትም ከተገደሉ በኋላ በንጉሡ ላይ ጋኔን ተጫነበት መልኩም ተለውጦ እንደ እርያ ሆነ። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ወደርሱ መጥቶ በላዩ ጸልዮ እስከ አዳነው ድረስ ስለዚህም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ። የቅዱሳን ሰማዕታትንም ሥጋቸውን ከተጣለበት ሰብስበው በአማረ ቦታ አኖሩአቸው ያማረች ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንም ተሠራችላቸው። ከእነርሱም ታላላቅ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ እንደ ንስር መጥቆ "ቀዳሚሁ ቃል.." ( ዮሐ. ፩፥፩) ብሎ ወንጌሉን የጻፈበት ዕለት እንደሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፡- ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን ለመስበክ ዕጣ የደረሰው እስያ ስለነበር ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን አስከትሎ ሄደ፡፡ ይኽችውም ኤፌሶን በጥንቱ በታናሽ እስያ በዛሬው የቱርክ ግዛት ውስጥ ከተማ ናት፡፡ ዛሬ ኢያዞሎክ ተብላ የጥንት ታሪኳ ጠፍቷል፡፡ አስቀድሞ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ሰብኮባታል፡፡ ደቀ መዝሙሩን ቅዱስ ጢሞቴዎስንም በከተማዋ ላይ ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ እርሱም በግፍ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ቅዱስ ዮሐንስን እየረዳው በከተማዋ ብዙ አገልግሏል፡፡ በኋላ ግን በግፍ ገድለውታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ኤፌሶን ለመሄድ በመርከብ ሲሳፈር መርከቡ በማዕበል ተሰበረ፡፡ ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን መዕበሉ ወደ አንዲት ደሴት አደረሰው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በመርከቡ ስባሪ ተንጠልጥሎ በባሕሩ ማዕበል መካከል 40 ቀንና 40 ሌሊት ከኖረ በኋላ ማዕበሉ ተፍቶ አብሮኮሮስ ካለበት ደሴት አደረሰውና ተያይዘው ኤፌሶን ከተማ ገቡ፡፡ የከተማይቱም ሰዎች እጅግ ክፉዎች ስለነበሩ መጀመሪያ ላይ ቅዱስ ወንጌልን መስበክ አልቻሉም ነበር፡፡ እነርሱም እጅግ ክፉዎች መሆናቸውን ስላወቀ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ዕጣው ሲደርሰው በሀዘን አልቅሶ ነበር፡፡ አሁንም ከተማው በገቡ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ምክንያት በመፍጠር ሮምና ለምትባል ሴት የውሽባ ቤቷ እሳት አንዳጅ ሆኖ አብሮኮሮስም ዕቃ አጣቢ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ የቀጠረቻቸው ሴትም እጅግ ታሠቃያቸው ጀመር፡፡ ባሮቿ እንደሆኑ ተስማምተው ስለጻፉላት ትደበድባቸውም ነበር፡፡
እነርሱም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ እየኖሩ እያለ በአንዲት ዕለት የአገረ ገዥው ልጅ ለመታጠብ ወደ ውሽባው ቤት ገባ፡፡ በውሽባ ቤቱም የሰይጣን ኃይል ስለነበረበት የመኰንኑን ልጅ አንቆ ገደለው፡፡ የአገሪቱም ሰዎች ሁሉ ለሞተው የመኰንን ልጅ ሊያለቅሱ ሲሰበሰቡ ቅዱስ ዮሐንስም አብሮ ቆሞ ሲመለከት ሮምና መጥታ "በጌታዬ ልጅ ሞት ልትደሰት መጣህን" እያለች ረገመችው፡፡ እርሱም "አይዞሽ አትዘኚ" አላትና ወደ ሞተው ልጅ ቀርቦ በመስቀል ምልክት ካማተበበት በኋላ በፊቱ እፍ አለበት፡፡ የሞተውም ልጅ ድኖ ተነሣ፡፡ የሀገሪቱም ሰዎች እጅግ ደነገጡ፡፡ ሮምናም ደንግጣ "እግዚአብሔር የሚሉት አምላክ አንተ ነህን" ብላ ጠየቀችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም "በፍጹም እኔ አምላክ አይደለሁም፣ እኔ የእርሱ አገልጋዩና ሐዋርያው ነኝ እንጂ" አላት፡፡ ሮምናም ስለበደለቻቸው በደል ሁሉ መሪር ዕንባን እያለቀሰች ይቅር እንዲሏት ለመነቻቸው፡፡ እነርሱም አረጋጉዋት፡፡ ከሕዝቡም ውስጥ ብዙዎቹ በጌታችን አመኑ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ሌሎች ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን እየሰበከ ከጣዖት አገልጋዮች በቀር ሁሉንም አሳምኖ አጠመቃቸው፡፡ አገልጋዮችን ኤጲስቆጶሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ከሾመላቸው በኋላ ወደ ሌሎች አቅራቢያ አገሮች ሄደ፡፡
በመጨረሻም በከሃዲውና በጨካኙ በድምጥያኖስ ዘመን በጣዖት አምላኪዎች ተከሶ ለፍርድ ቀረበ፡፡ በፈላ ውኃ ካሠቃዩት በኋለ በፍጥሞ ደሴት አጋዙት፡፡ በዚያም ሳለ ራእዩን ተመልክቶ ጻፈው፡፡ ድምጥያኖስም ከተገደለ በኋላ ከግዞቱ ተመልሶ ሦስቱን መልእክታቱንና ቅዱስ ወንጌሉን ጽፏል፡፡ ጌታችንም አስቀድሞ ሞትን እንደማይቀምስ ለዮሐንስ ቃል ገብቶለት ነበርና (ዮሐ 21፡22) ጥር 4 ቀን እንደ ኤልያስና ሄኖክ ሞትን እንዳያይ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወስዶታል።
ጌታችን ለዮሐንስ ያልነገረው እርሱም ያላስተማረው ምሥጢር የለም፡፡ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር "በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ…" ብሎ የጌታችን ነገር ተመራምሮ ለመድረስ ሲል በመሀል መልአኩን በዮርዳኖስ ባሕር ላይ ሲሄድ አገኘው፡፡ መልአኩም የዮርዳኖስን ባሕር በእንቁላል ቅርፊት እየጨለፈ ወደ ውጭ ሲያፈስ ተመለከተው፡፡ ዮሐንስም ተገርሞ "ምን ማድረግህ ነው" አለው፡፡ መልአኩም "የዮርዳኖስን ባሕር ቀድቼ እየደፋሁ ልጨርሰው ነው" ሲለው ዮሐንስም መልሶ "ታዲያ በእንቁላል ስባሪ ነውን?" አለው፡፡ መልአኩም "አዎን" አለው፡፡ ዮሐንስም "በከንቱ ደከምክ" አለው፡፡ ይህን ጊዜ መልአኩም መልሶ "አንተስ እንጂ ደግሞ የአምላክን መገኘት፣ አኗኗሩንም ተመራምረህ በጥበብ ለማግኘት ብለህ 'በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ..' ብለህ ጀምረህ የለምን? አንተ ጌታን ተመራምረህ ካገኘህና ከደረስክበት እኔም የዮርዳኖስን ወንዝ በዚህ እንቁላል ቅርፊት ቀድቼ እጨርሰዋለሁ" አለው፡፡ ዮሐንስም ይህን ጊዜ ደንግጦ ዝቅ ብሎ "ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ…" ብሎ ሀሳቡን ለወጠና ሌላ ታሪክ ቀጠለ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ወክሎ እመቤታችንን በአደራ የተቀበለ እርሱም ለመቤታችን በአደራ የተሰጠ ሲሆን እመቤታችንን ከወሰዳት በኋላ ለ16 ዓመት እየተንከባከበ ጠብቋታል፡፡ እናቱም በሕፃንነቱ ስለሞተች እመቤታችን ናት እየተንከባከበች ያሳደገችው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በመልኩም ከጌታችን ጋር ይመሳል ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሥዕል የመሳል ተሰጥኦም ነበረው፡፡ ጌታችን በተሰቀለበት ዘመን የነበረው ጢባርዮስ ቄሳር ልጁ በሽተኛ ነበር፡፡ የጌታችንን የማዳን ሥራ እየሰማ እነ ጲላጦስም ስለጌታችን የሚጽፉለትን ይሰማ ስለነበር ልጁን ከጌታችን መቃብር ላይ እንዲያኖሩለት ላከው፡፡ ልጁም ፈጥኖ ተፈወሰለት፡፡ ጢባርዮስ ቄሳርም በልጁ መዳን ምክንያት የጌታችንን ውለታ ማስቀመጥ ፈልጎ የጌታችንን ሥዕሉን የሚሥልለትን ሲያጠያይቅ ዮሐንስን አገናኙት፡፡ ዮሐንስም ጌታችንን ልክ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ አድርጎ በመሣል ለጢባርዮስ ቄሳር ሰጠው፡፡ ሲሥለውም በመጀመሪያ ጌታችንን ልክ እንደተሰቀለ አድርጎ ራቁቱን ነበር የሳለው፡፡ ዮሐንስ የሳለው የጌታችን ሥዕልም አፍ አውጥቶ "በመጀመሪያ አይሁድ በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?" ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ "እንዴት አድርጌ ልሳልህ?" ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም "ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ" አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ከሳለው በኋላ ሥዕሉን ትኩር ብሎ ተመልክቶ ቢስመው ከንፈሩ አንድ ቀን ተኩል ያህል ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸውን የጌታችንን ስነ ስቅለት የሚያሳዩ ሥዕሎች መገኛቸው ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስ የሳለው ሥዕል ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፦
በሕይወቱና በኑሮው ሁሉ ጌታችንን ለመምሰል ይጥር ነበርና ጌታችንም እጅግ ይወደው ስለነበር "#ፍቁረ_እግዚእ" ተባለ፣ የታላቁ ያዕቆብ ታናሽ ወንድም ስለሆነና አባቱም ዘብድዮስ ስለሚባል "#ዮሐንስ_ወልደ_ዘብድዮስ" ተባለ፣ ለጌታችን ባለው ቅናትና ከወንድሙ ጋር ሆነው ባሳዩት የኃይል ሥራ እንዲሁም የጌታችንን አምላክነት በመግለጡ "#ወልደ_ነጎድጓድ" ተብሏል፣ ነገረ መለኮትን ከሌሎቹ በበለጠ ሁኔታ አስፍቶና አምልቶ በማስተማሩ "#ነባቤ_መነኮት ወይም #ታኦሎጎስ" ተብሏል፣ ኃላፊውንና መጻዒውን ጊዜ በራእዩ ስለገለጠ "#አቡቀለምሲስ" ተባለ፣ ይህም በግሪክኛ #ባለራእይ ማለት ነው፣ የጌታችንን መከራ መስቀሉን እያስታወሰ 70 ዘመን ሙሉ እያለቀሰ ስለኖረና ፊቱም በሀዘን ስለተቋጠረ "#ቁጹረ_ገጽ" ተብሏል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages