የእመቤታችን ስደት (ክፍል አንድ) - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 8, 2022

የእመቤታችን ስደት (ክፍል አንድ)

 


ክፍል አንድ
አዘክሪ ድንግል ንግደቶ ዘምስሌኪ አንዘ ትጎይዩ ምስሌሁ እም ሃገር በመዋእለ ሄሮድስ ርጉም።
አዘክሪ ድንግል አንብአ መሪረ ዘውኅዘ እማእይንትኪ ወወረደ ዲበ ገጸ ፍቁር ወልድኪ።
አዘክሪ ድንግል ረሃበ ወጽምአ ምንዳቤ ወሃዘነ ወኩሎ አጸባ ዘበጽሃኪ ምስሌሁ።
ድንግል ሆይ፤ ርጉም በሆነ በሄሮድስ ዘመን ከርሱ ጋራ ከሃገር ወደ ሃገር ስትሸሺ ከአንቺ ጋራ መሰደዱን አሳስቢ።
ድንግል ሆይ፤ ከአይኖችሽ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር አንባ አሳስቢ።
ድንግል ሆይ፤ ረሃቡንና ጥሙን ችግሩንና ሃዘኑን ከእርሱ ጋራ የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ። ቅዳሴ ማርያም 
ጽጌ የሚለው ቃል የግዕዝ ሲሆን አበባ የሚል የአማርኛ ትርጉም አለው።  ከመስከረም 26  ጀምሮ እስከ ሕዳር 6  ቀን ድረስ ያለው ወቅት “ወርሃ ጽጌ” የሚባል ሲሆን ስያሜው በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለውን ተፈጥሯዊ ሁኔታ ያገናዘበ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የክረምቱ ጨለማ ተገፎ ብርሃን የሚፈነጥቅበት፤ አበቦች ለዓይን ማራኪ የሆነውን ንጉስ ሰሎሞን እንኳን በክብሩና በጥበቡ ሊለብሰው ያልተቻለውን በእደ ሰብእ ያልተዘጋጀውን ውብ የሆነ ልብሳቸውን ተጎናጽፈው የሚመለከታቸውን ሁሉ ትኩረት የሚስቡበት፤ ለአፍንጫ ተስማሚ የሆነውን ጥዑም መዓዛቸውንም እንካችሁ ብለው ያለስስት የሚቸሩበት፤ አእዋፍ ዝማሬያቸውን ከወትሮው በላቀ ሁናቴ  የሚያንቆረቁሩበት፤ ንቦች ከአበባ አበባ እየዘለሉ ጣፋጭ ማርን የሚያዘጋጁበት፤ ሁሉ አምሮ፤ ሁሉ ደምቆ፤ አዲስ ሆኖ የሚገኝበት ወቅት በመሆኑ፤ ይህን ጊዜ ወርሃ ጽጌ፣ ዘመነ ጽጌ፣ በመባል ይታወቃል፡፡
በወንጌል እንዲህ የሚል መልእክት እናገኛለን
“አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም።” ሉቃ 12፥27
::   አዳምና ሔዋን አትብሉ የተባሉትን ዕፅ በልተው የእግዚአብሔርን ሕግ በማፍረስ በደሉ፡፡ ከፈጣሪያቸው ጋር ራሳቸውን ለማስተካከል /አምላክ ለመሆን/ በማሰብና በመመኘታቸው ይቅርታ የማይገባውን ዓመጽ ፈፀሙ፡፡ 
በዚህም ምክንያት «ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ» /ዘፍ. 2:18 / ተብሎ አስቀድሞ በተነገራቸው ሕግ መሠረትም:-                   
* ለሔዋን «በፀነሰሽ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛዋለሁ፣ በጭንቅ ትወልጃለሽ፣
* ለአዳም ደግም ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፣ በሕይወት ዘመንህ ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህና አሜከላ ታበቅልብሃለች. . . »/ዘፍ.3.15-19/ ተብለው ተረገሙ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣሉ፤ ከገነት ተባረሩ፤ የሞት ሞት ተፈረደባቸው፤ ሞት ሰለጠነባቸው፡፡አዳምና ሔዋን በበደሉት በደል ምክንያት ከገነት ከተሰደዱ በኋላ ከእግዚአብሔር የተለዩና የተዋረዱ  ሆኑ። የሚወልዷቸው ልጆችም እንዲሁ ከእግዚአብሔር የተለዩና የተዋረዱ የተረገሙ ስለነበር በተለያየ መልኩ መከራዎች ሁሉ የሚደርሱባቸው ሆኑ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ቸርና ሩህሩህ አምላክ  ስለሆነ የፈጠረውን ፍጥረት የማይንቅ፤ ስቃይን የሚመለከት ቸር አምላክ ነውና የአዳም ስቃይ ስላሳዘነው ከራሱ ጋር የሚታረቅበትን መንገድ አዘጋጀለት፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነውና ወደ ቀደመ ክብሩ እንደሚመልሰው ቃል ኪዳን ገባለት።  የዘመኑ ፍጻሜ /የቀጠሮው ቀን/ በደረሰ ጊዜ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል የእግዚአብሔር ቃል /ወልድ/ መጣ፤ ከነፍሷ ነፍስ ከሥጋዋ ሥጋ ነሥቶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ፡፡ በዚያን ጊዜ ዮሴፍ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ። ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው። እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ።

ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል። የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ምድራዊ ንግስናውን የሚነጥቀው መስሎት ደነገጠ፥ ተጨነቀ፤ ተጠበበ።  ንጉስ ሄሮድስም አንድ ዘዴ አፈለቀ እሱም ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ከተረዳ በኋላ፥ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ላከ። እንዲህም ብሎ የሽንገላ ቃል ተናገራቸው።  ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ ብሎ አላቸው። እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ሰብአ ሰገልም ከሄሮድስ ከተለዩ በኋላ በኮከቡ እየተመሩ ጉዞአቸውንቀጠሉ።  ጌታችንን ከእናቱ ጋር አገኙት  ተንበርክከው ሰገዱለት፤ ወርቅ  ዕጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻአቀረቡለት፡፡የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ፤ ነገር ግን መንገድ ቀይረው ወደሀገራቸው እንዲሄዱ በነገራቸው መሠረት በሌላ መንገድ ወደ መጡበት  ተመለሱ፡፡
«እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ «ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለውይፈልገዋልና ተነስ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሸ፤ እስክነግርህም በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡» /ማቴ. 2 13 14/

ታዲያ ይህ ሽሽት፤ ይህ የስደት ወቅት ዘመነ ጽጌ በመባል ይታወቃል።  ዮሴፍም በህልሙ ከመልአኩ እንደተነገረው አህያውንና ስንቁን፤ እመቤታችንን እስከ ልጇ፤ ሰሎሜንም ጭምር ይዞ ጉዞውን ከእስራኤል ወደ ግብጽ ሐገር ሸሸ። መንገዳቸውን በእግዚአብሔር መልአክ እየተመሩ፤ የሲናን በረሃ አቋርጠው ወደ ግብጽ ሐገር ሄዱ።  በዚያን ሰዓት ውርጩ፤ ብርዱ፤ ርሃቡ፤ እንግልቱ በዝቶባቸው ነበር፤ ጉዞውም አስጨናቂ ነበር፤ ምግባቸውን ግን ከሰማይ መና እየወረደላቸው ይመገቡ ነበር። በዚህ ወቅት ደግሞ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር የደረሰባት እንግልት፤ ስቃይ፤ ርሃብ፤ ጥሙን ሁሉ የሚታሰብበት እለት ነው። 
ይቆየን……..

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages