አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ዳግመኛም በዚህ ቀን ታላቁ አባት አባ አጋቶን መታሰቢያው ነው፡፡ ይህን ቅዱስ ታላቅ ጻድቅ ገዳማዊና የእግዚአብሔር ሰው ሲሆን አንደበቱን ከክፋት ይከለክል ዘንድ ለ30 ዓመታት ድንጋይ ጐርሶ ኖሯል። ይህንን ቅዱስ ሊቃውንት ሲገልጹት "ክምረ ክምር ጽድቁ እስከ አስተርአየ" ይሉታል። ትእግስቱ ደግነቱ አርምሞው ትሩፋቱ ከመነገር በላይ ነው። በነበረበት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም እንደ ኮከብ ያበራ ታላቅ አባት ነው።
ታላቁ ገዳማዊ አባት አጋቶን የታላቁ መቃርዮስ የመንፈስ ልጅ ነው። ገዳመ አስቄጥስ እልፍ አእላፍ ቅዱሳንን ስታፈራ ይህ አባት ቅድሚያውን ይይዛል። ምንም በብዛት የሚታወቀው በአርምሞው (በዝምታው) ቢሆንም ባለ ብዙ ትሩፋት አባት ነው። የሚገርመው የቀደሙ አባቶቻችን የፈለገውን ያህል መናኝ ቢሆኑም የሰው ጥገኛ መሆንን አይፈልጉም። "ሊሠራ የማይወድ አይብላ" የሚለውን መለኮታዊ ትዕዛዝ መሠረት አድርገው ከተጋድሎ በተረፈቻቸው ሰዓት ሥራ ይሠራሉ። አንዳንዶቹ እንደሚመስላቸው ምናኔ ሥራ መፍታት አይደለምና ሰሌን ዕንቅብ ሠፌድ የመሳሰለውን ይሠፋሉ። ታላቁ አባ አጋቶንም በአንደበቱ ድንጋይ ጐርሶ በእግሮቹ ቀጥ ብሎ ቆሞ እንቅቦችን ይሠፋ ነበር። ቅዱሱ የሰፋውን ወደ ገበያ ይወጣል በጠየቁትም ዋጋ ሽጦት አንዲት ቂጣ ይገዛል። የተረፈውን ገንዘብ ግን እዚያው ለነዳያን አካፍሎት ይመጣል እንጂ ወደ ገዳሙ አይመልሰውም።
አንድ ቀን እንደልማዱ የሠፋቸውን እንቅቦች ተሸክሞ ወደ ገበያ ሲሔድ መንገድ ላይ አንድ የኔ ቢጤ ወድቆ ያገኛል። እንደ ደረሰም ስመ እግዚአብሔር ጠርቶ ይለምነዋል። አባ አጋቶን ከእንቅቦቹ ውጪ ምንም ነገር አልነበረውምና "እንቅቡን እንካ" አለው። ነዳዩ ግን ወይ የሚበላ ካልሆነም ገንዘብ እንደሚፈልግ ይነግረዋል። ወዲያው ደግሞ "የምትሠጠኝ ነገር ከሌለህ ለምን ወደ ገበያ ተሸክመህ አትወስደኝም?" አለው። የነዳዩ አካል እጅግ የቆሳሰለ በመሆኑ እንኩዋን ሊሸከሙት ሊያዩትም የሚከብድ ነበር። ጻድቁ ግን ደስ እያለው ያለማመንታት አንስቶ ተሸከመው። ከረጅም መንገድ በኋላ ከገበያ በመድረሳቸው አውርዶ ከጐኑ አስቀመጠው። ያ ነዳይ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ ቢለምንም የሚዘከረው አጣ። አባ አጋቶን አንዷን እንቅብ ሲሸጥ "ስጠኝ?" ይለዋል። ጻድቁም ይሠጠዋል። እንዲህ "ስጠኝ" እያለ የእንቅቦችን ዋጋ ያ ነዳይ ወሰደበት። አባ አጋቶን ግን ምንም ቂጣ ባይገዛም በሆነው ነገር አልተከፋምና ሊሔድ ሲነሳ ነዳዩ "ወደ ቦታየ ተሸክመህ መልሰኝ" አለው። አባቶቻችን ትእግስታቸው ጥግ የለውምና ጐንበስ ብሎ በፍቅር አንስቶት አዘሎት ሔደ። ካነሳበት ቦታ ላይ ሲደርሱ ይወርድለት ዘንድ ጻድቁ ቆመ። ነዳዩ ግን አልወርድም አለ። ትንሽ ቆይቶ ግን ለቀቀው ሊያየው ዞር ቢል መሬት ላይ የለም። ቀና ሲል ግን ያየውን ነገር ማመን አልቻለምና ደንግጦ በግንባሩ ተደፋ። ነዳይ መስሎ እንዲያ ሲፈትነው የነበረው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነበርና ክንፎቹን ዘርግቶ በብርሃን ተከቦ በግርማ ታየው ከወደቀበትም አነሳው። "ወዳጄ አጋቶን ፍሬህ ትእግስትህ ደግነትህ ግሩም ነውና ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎት ተሰወረው፤ ጻድቁም በደስታ ወደ በዓቱ ሔደ። አባ አጋቶን ተረፈ ዘመኑን በአርምሞ ኑሮ ዐርፏል።
#ቅዱስ_መጥራ_አረጋዊ (ሰማዕት)
ጥቅምት ስምንት በዚች ቀን ሽማግሌው አባ መጥራ በሰማዕትነት አረፈ። ከእርሱም ጋር ብዙዎች ሰዎች በሰማዕትነት አረፉ። ይህም ቅዱስ ከእስክንድርያ አገር አማኒ ክርስቲያን ነው። ከሀዲ ንጉሥ ዳኬዎስ በነገሠ ጊዜ የጣዖትን አምልኮ አቁሞ የክርስቲያንን ወገኖች አሠቃያቸው።
ትእዛዙም ወደ እስክንድርያ አገር ደርሶ ሰዎቿን ሁሉንም አሠቃያቸው የብዙዎች ምእመናንንም ደማቸውን አፈሰሰ። ያን ጊዜ ክርስቲያን እንደ ሆነ ቅዱስ መጥራን በመኰንኑ ዘንድ ወነጀሉት፤ መኰንኑም ወደርሱ አስቀረበው እርሱም ብቻውን እውነተኛ አምላክ እንደ ሆነ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ።
መኰንኑም ለአማልክት ስገድ እኔም ብዙ ገንዘብን እሰጥሃለሁ ታላቅ ክብርንም አከብርሃለሁ አለው። እርሱም ቃል ኪዳኑን አልተቀበለም ኪዳንህና ገንዘብህ ካንተ ጋራ ወደ ጥፋት ይሒድ አለው እንጂ። መኰንኑም በእርሱ ላይ ተቆጥቶ እኔ በጽኑዕ ሥቃይ እቀጣሃለሁ አለው።
ቅዱስ መጥራም ፈርቶ ከበጎ ምክሩ አልተመለሰም እንዲህም አለው እንጂ እኔ ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ለሕያው እግዚአብሔር እሰግዳለሁ። ለረከሱ ጣዖታት ከደንጊያና ከዕንጨት ለተሠሩ ለማያዩ ለማይሰሙ ለማይናገሩ ለማያሸቱ ለማይንቀሳቀሱ እንሰግድ ዘንድ እንዴት ይገባል አለው።
መኰንኑም በሰማ ጊዜ አፈረ። ጽኑ ግርፋትንም እንዲገርፉት አዘዘ። ከዚህም በኋላ በክንዱ ሰቀሉት በደረቀች ሽመልም ጎኖቹን ሠነጠቁ ቀደዱትም ክብር ይግባውና ጌታ ኢየሱስም አዳነው። ያለ ጥፋትም በጤንነት አስነሣው መኰንኑም ማሠቃየቱን በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። ከከተማውም አውጥተው የከበረች ራሱን ቆረጡ። ሌሎች ብዙዎች ሰማዕታትንም ከእርሱ ጋር ራሶቻቸውን ቆረጡ። የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።
ዳግመኛም በዚችም ቀን በላይኛው ግብጽ ከሚኖሩ ሰዎች ወገን የሆነ ቅዱስ አባት አባ ሖር መታሰቢያው።
ደግነት ያለው መነኰስ በመሆን ጽኑዕ ገድልን ተጋደለ በአምልኮቱና በተጋድሎው ከቅዱሳን ሁሉ ተለይቶ በብዙዎች ላይ ከፍ ከፍ አለ ለብቻ መኖርን ስለወደደ ወደ በረሀ ወጥቶ በገድል ተጠምዶ ብዙ ዘመናት ኖረ። የበጎ ሥራ ጠላት የሆነ ሰይጣንም ቀንቶበት በግልጥ ታየውና በበረሀ ውስጥ ግን አንተ ድል ትነሣናለህ በዚህ ሰው የለምና ጽኑ ኃይለኛ ከሆንክ ወደ እስክንድርያ ከተማ ና ብሎ ተናገረው።
አባ ሖርም ይህን በሰማ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኃይል ተማምኖ ወደ እስክንድርያ ከተማ ሒዶ ለእሥረኞችና ለችግረኞች ደካሞች ውኃ የሚቀዳ ሆነ በአንዲት ዕለት ሦስት ፈረሶች በከተማው ውስጥ እየዘለሉ ሲያልፉ አንዱ ፈረስ አንዱን ሕፃን ረገጠውና ወዲያውኑ ሞተ ሰይጣንም በሰዎች ልብ አደረና ይህን ሕፃን ያለዚህ አረጋዊ መነኵሴ የገደለው የለም ብለው አሰቡ አባ ሖርም መጣና ሕፃኑን አንሥቶ ታቀፈው በልቡም በመጸለይ ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር ማለደ በመስቀል ምልክትም በላዩ አማተበ የሕፃኑም ነፍስ ተመለሰች ድኖም ተነሣ ለአባቱም ሰጠው ወደ ከተማ ውጭ ሸሽቶ በመሔድ ወደ በዓቱ ገባ ፈልገውም አላገኙትም ጽድቅንና ትሩፋትንም በመሥራት ብዙ ዘመናት በገድል ተጠምዶ ኖረ።
የሚሞትበት ጊዜ ሲቀርብ ብዙዎች ቅዱሳንን ሲጠሩት አያቸው እጅግም ደስ አለው ልጆቹንም ሰብስቦ በምንኲስና ሥርዓት ጸንተው ትሩፋትን እንዲሠሩ አዘዛቸው ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እርሱ እንደሚሔድ ነገራቸው እነርሱም እጅግ አዘኑ ጥቂት ቀንም ታሞ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment