ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለመምህር የኔታ ሀብተ ኢየሱስ ጋርደው - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 22, 2022

ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለመምህር የኔታ ሀብተ ኢየሱስ ጋርደው

 

ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመመሪያ ኃላፊዎች፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ ኃላፊዎች፣ አበው መነኮሳት ምዕመናንና ምዕመናት በተገኙበት ሥርዓተ ቀብራቸው በመርጡለ ማርያም ገዳም በዛሬው ዕለት ተፈጽሟል፡፡


(ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ)
ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለመምህር የኔታ ሀብተ ኢየሱስ ጋርደው
መምህር የኔታ ሀብተ ኢየሱስ ጋርደው ከአባታቸው ከአቶ ጋርደው ቦልኬ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፀሐይ ወርቁ በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሀገር ፍች አውራጃ በየጀሬ ወረዳ አድአ ቅዱስ ገብርኤል በ1926 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
መምህር የኔታ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ከቤ ሚካኤል ከተባለው ደብር ከመምህር ኤፍሬምና ከመምህር ወንድይፍረድ ከፊደል እስከ ጸዋተወ ዜማ ተምረዋል፡፡ መዝገበ ቅዳሴ ከየኔታ ስዩም ፍት ከተባለው ቦታ ተምረዋል፡፡ በ1951 ዓ.ም ቅኔ ለመማርና ብሎም በሙያው መምህር ሆነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በማሰብ ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገር በመምጣት በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር ሞጣ አውራጃ በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ጥንታዊትና ታሪካዊት መርጡለ ማርያም ገዳም የቅኔ ቤተ ጉባኤያቸውን አስፍተው በማስተማር ከሚታወቁት ታላቁ ስመጥር ሊቅ መምህር የኔታ ኢሳይያስ እጅጉ ቤተ ጉባኤ ገብተው በመማር ባላቸው ከፍተኛ ትምህርት የመቀበል አቅም በ1953 ዓ.ም ቅኔ ከነአገባቡ በሚገባ ተምረዋል፡፡
ከዚያም ቢቸና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር በመሄድ ከ1954 እስከ 1955 ዓ.ም ለ2 ዓመታት ከመምህር ፈረደ የቅኔ ትምህርታቸውን አጠናክረው ተምረዋል። የትምህርት ፍላጎታቸው እየጨመረ በመሄዱ በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር ቦረና አውራጃ ሣይንት ወረዳ በሮ ሚካኤል ከተባለው ደብር ከአለቃ ከበደ በ1956 ዓ.ም የቅኔ የውዳሴ ማርያም እና የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ትምህርታቸውን አጠናክረው ተምረዋል፡፡
በ1957 ዓ.ም ወደ ጥንታዊትና ታሪካዊት መርጡለ ማርያም ገዳም ተመልሰው በመምጣት ከመምህር የኔታ ኢሳይያስ እጅጉ ቅኔ ከነአገባቡ ግስ ከነእርባ ቅምሩ ተምረው በማጠናቀቅና ለቅኔ መምህርነት የሚያበቃቸውን ሙያ ተምረው እንዲሁም መጽሐፈ ነገሥት ትርጓሜ ትምህርታቸውንም በማጠናቀቃቸው ከአባቶች ሲየያዝ በመጣው ሥርዓት መሰረት ሀብተ ኤልያስ በኤልሳዕ፣ በረከተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዋርያት እንዳደረ ሀብተ መምህራን በረከተ መምህራን ይደርብህ ብለው መምህራቸው በመመረቅ በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ጥንታዊትና ታሪካዊት ገዳምና ደብር ደብረ መንክራት ድቦ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ለአንድ ዓመት በቅኔ መምህርነት አገልግለዋል፡፡
በ1959 ዓ.ም ያላቸውን ሀብተ ጉባኤ በመንፈስ የተቃኙት መምህራቸው የኔታ ኢሳይያስ እጅጉ ወደ ጥንታዊትና ታሪካዊት መርጡለ ማርያም ገዳም ተመልሰው ከመምህራናቸው ጎን ሆነው ቢያስተምሩ በርካታ ደቀ መዛሙርትን እንደሚያፈሩ ስለተረዱ አባታዊ ቃላቸውን ልጄ እኔ እያለሁ ከእኔ ጎን ሁነህ እኔም በሞተ ሥጋ ብለይ ጥንታዊትና ታሪካዊት መርጡለ ማርያም ገዳምን እንድታገለግል ደቀ መዛሙርትን እስከ ህይወት ፍፃሜህ ድረስ እንድታፈራ በማለት ቃላቸውን ስለአሳደሩባቸው የአባታቸውን ቃል በማክበር ወደ ጥንታዊትና ታሪካዊት መርጡለ ማርያም ገዳም መጥተው ከ1960 ዓ.ም እስከ 2015 ዓ.ም ለ55 ዓመታት ጉባኤያቸውን አስፍተው በንቃትና በትጋት በሠላምና በፍቅር በርካታ ደቀ መዛሙርትን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አብቅተዋል፡፡ ከ35 በላይ የቅኔ መምህራንን አስመርቀው ለአገልግሎት ያበቁ ሲሆን የቅኔ ትምህርታቸውን አጠናቀው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ብቁ የሆነ በርካታ አበው መነኮሳትን መምህራንን ካህናትን አስተምረዋል፡፡
ለሊቀ ጵጵስና ማእርግ ያበቋቸው ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም
1. ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ፣የሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ
2. ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ክልል እና የጌዴዎ ዞን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
3. ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የጀርመን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት
4, ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የምዕራብ አሩሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና እና ሌሎችም ናቸው፡፡
መንፈሳዊ ሕይወትን በተመለከተ
መምህር የኔታ ሀብተ ኢየሱስ ጋርደው በጥንታዊትና ታሪካዊት መርጡለ ማርያም ገዳም ለ55 ዓመታት ለሰጡት ታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎትና በርካታ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን አስተምረው ለአገልግሎት በማብቃታቸው የመርጡለ ማርያም ከተማ ማዘጋጃ ቤት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ሰጥቷቸው በመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው የገንዘብ ድጋፍ ያሠሩትን ቤት የእኔ እናቴ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፣ የእኔ ቤቴ በሰማይ እንጅ በምድር አይደለም ምድራዊ ቤት ለእኔ አልተፈቀደልኝም በማለት ለጥንታዊትና ታሪካዊት መርጡለ ማርያም ገዳም ሰጥተው ከሰበካ ጉባኤው በሚሰጣቸው የወር ደመወዝ ክፍያ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ሰርከ ኀብስት እየተመገቡ በፍፁም ድንግልና በንጽህና በቅድስና የኖሩ ታላቅ አባት ነበሩ፡፡
"ዘተወክፈ ጻድቀ በስመ ጻድቅ አስበ ጻድቅ ወእሴተ ጻድቅ ይነስዕ"ማቴ 10፡ 41 ያለውን አምላካዊ ቃል በተግባር በመተርጎም ካላቸው ውስን የወር ገቢ እና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውን በማስተባበር በየወሩ የበዓለ እግዚአብሔር፣ በየዓመቱ ጥቅምት 4 ቀን የፍቁራን አኃው አብርሃ ወአጽብሓ በዓለ ዕረፍት መታሰቢያ፣ በነሐሴ 13 የደብረ ታቦር ዝክር ይዘክሩ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየዓመቱ ከነሐሴ 1-16 ቀን በጾመ ማርያም በጉባኤ ቤታቸው ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ያሰሙ ነበር። የኔታ ሀብተ ኢየሱስ በጾምና በጸሎት ተወስነው በአታቸውን አጽንተው የኖሩ በመሆናቸው ወደፊት የሚመጡትን ጉዳዮች ከእግዚአብሔር ይረዱ ነበር፡፡
ለዚህም ማስረጃው ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም በቅርብ በሞተ ሥጋ የተለዩትን ቄሰ ገበዝ የኔታ ታምሬ እጅጉን ጠርተው መወያየት የሚገባቸውን ጉዳዮች ተወያይተው እና የጋራ ማዕድ ተመግበው እጅ በመነሣሣት ተሰነባብተዋል፡፡ ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም የኔታ ቄስ ገበዝ ታምሬ እጅጉ ታመው ነሐሴ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም በሞተ ሥጋ ሲያርፉ ለዝክረ ነገር ያህል የሚከተለውን መወድስ ቅኔ ተቀኝተዋል፡፡
መወድስ
መፍትው ትኅዝን ዘምስለ ደቂቃ እንተ ዕድሜሃ ብዙኅ መርጡለ ማርያም እመ ሀገር
ወበአርምሞ ነበረት እምልቡናሃ መሪር
ሎቱ እስመ ተገብረ ለዘሞተ ወልዳ ተአምር መንክር
ወውሉደ ጽዮን ካሕናት በየማን ወጽግም ነበሩ በገዓር
ለዓለም
ደንገፁሂ አበዊነ ካሕናተ መርጡል ደብር
እስመ ጠፍአ ወማሰነ መጽሐፈ ማርያም ተአምር
ባህቱ ተረክበ ማዕከለ ጽንፋ ለባሕር
በመንፈስ ቅዱስ እመ ሀሠሦ ማዕቀበ ዓልፋ ሊቀ ሐመር፡፡
መምህር የኔታ ሀብተ ኢየሱስ ጋርደው በቤተሰቦቻቸው ቤት 10 ዓመታት፣ በቤተ ጉባኤ 23፣ ዓመታት በመምህርነት 55 ዓመታት ጠቅላላ 88 ዓመታት በዚህ ዓለም ሲቆዩ የሥጋ ዘመዶች አሉኝ የትውልድ ቦታ ናፈቀኝ ብለው ልሒድ ያላሉ መንፈሳዊ አባት ነበሩ፡፡ምክንያቱም “ዘኢኀደገ አባሁ ወእሞ ኢይክል ይፀመደኒ ያለውን የወንጌል ቃል ለመፈጸም ዝግጁ አባት ስለሆነ ቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ትናንት የኔታ ታምሬ እጅጉን ዛሬ መምህር የኔታ ሀብተ ኢየሱስ ጋርደውን በማጣቷ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ካሕናቱ መነኮሳቱና መምህራኑ እንዲሁም ምዕመናን ሀዘናቸው ጥልቅ ነው፡፡ ሆኖም ግን የመምህራችን መልካም ሥራ ዘመን የማይሽረው ስለሆነ በእያንዳንዳችን ልብ ታትሞ ያለ ሲሆን ታሪካቸውም በገዳሟ እና በኢትዮጵያ ኦርቶደዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ይኖራል፡፡
የኔታ መስከረም 22 ቀን 2015 ዓ.ም የመንፈስ ወንድማቸውን ቄሰ ገበዝ የኔታ ታምሬ እጅጉን በተሰናበቱ በአንድ ወር ከ5 ቀናቸው ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት በመርጡለ ማርያም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና በባሕርዳር ጋምቢ ሆስፒታል የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ቢቆዩም ሊሻላቸው ባለመቻሉ ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም በተወለዱ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈው ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ እዝቅኤል፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ፣ የጠቅላይ ቤተ-ክሕነት የመመሪያ ኃላፊዎች፣ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች የታላላቅ አድባራትና ገዳማት መምህራንና አስተዳዳሪዎች፣ አበው መነኮሳት ምዕመናንና ምዕመናት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሥርዓተ ቀብራቸው በመርጡለ ማርያም ገዳም ተፈጽሟል፡፡
መረጃው የኢኦተቤ ቴቪ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages