ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 10 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, October 21, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 10

 
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ዐሥር በዚህች ቀን የቅዱስ ባኮስ ባልንጀራ የሆነ #ቅዱስ_ሰርጊስ በሰማዕትነት አረፈ፣ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አውማንዮስ አረፈ፣ መስተጋድል የሆነ #ቀሲስ_ዮሐንስ አረፈ።

ዳግመኛም በዚችም ቀን ከከሀዲ ንጉሥ መክስምያኖስ ሠራዊት ውስጥ የቅዱስ ባኮስ ባልንጀራ የሆነ ቅዱስ ሰርጊስ በሰማዕትነት አረፈ። ንጉሥ መክስምያኖስም ወደ ሶርያ አገር ወደ አንጥያኮስ በላካቸው ጊዜ ቅዱስ ባኮስን ከውኃ በማስጠም በዚህ ወር በአራተኛ ቀን ገደሉት። ቅዱስ ሰርጊስን ግን አሥሮ በወህኒ ቤት አኖረው።
ከዚህም በኋላ በእግሮቹ ውስጥ ረጃጅም የብረት ችንካሮችን ቸንከረው ከፈረሰኞች ጋር ሩጻፋ ወደሚባል አገር እንዲወስዱት መኰንኑ አዘዘ።
ሲወስዱትም ያስሮጡት ነበር ደሙም በምድር ላይ እንደ ውኃ ይፈስ ነበር በጐዳናም አንዲት ድንግል ብላቴና አገኘ ከእርሷም ዘንድ ውኃን ጠጣ ሥጋዬን ትወስጂ ዘንድ እስከ ሩጻፋ ተከተይኝ አላት እርሷም ራራችለት ለጒልምስናውም አዘነችለትና ተከተለችው።
አንጥያኮስም እንዲህ ብሎ ጽፎአልና ሰርጊስ ትእዛዜን ተቀብሎ ለአማልክት ካልሠዋ ራሱን በሰይፍ ይቁረጡ። እርሱም ለቅዱስ ሰርጊስ ወዳጅ ነበርና ስለርሱም ይችን ሹመት አግኝቷት ነበርና በዚያንም ጊዜ ወታደሩ የቅዱስ ሰርጊስን ራስ ቆረጠው ያቺም ብላቴና ቀርባ ከእርሷ ጋር በነበረ የፀጕር ባዘቶ ከአንገቱ የፈሰሰውን ደሙን ተቀበለች። የስደቱም ወራት እስከ አለፈ ድረስ ሥጋውን ጠበቀች።
ከዚህም በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ተሠራችለት ዐሥራ አምስት ኤጲስቆጶሳትም አከበሩዋት የቅዱስ ሰርጊስንም ሥጋ በውስጥዋ አኖሩ ከእርሱም ብዙ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ እጅግ ሽታው ጣፋጭ የሆነ በሽተኞችን የሚፈውስ የሽቱ ቅባት ከሥጋው ይፈስ ነበርና።

ጥቅምት ዐሥር በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰባተኛ የሆነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት አውማንዮስ አረፈ።
ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ ንጹሕ ትሑት የሆነ ለዕውነተኛ ሥራ ሁሉ የሚያገለግል ነበር ቅዱስ አብርምዮስም ትሩፋቱን አይቶ ዲቁና ሾመው በዲቁና አገልግሎትም ዐሥር ዓመት ኖረ።
ዮስጦስም ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ትሩፋቱንና የሃይማኖቱን ቅንነት ተመለከተ ምእመናንንም ማስተማር እንደሚችል አውቆ ቅስና ሾመው። ከዚህም በኋላ ቅዱስ ዮስጦስ በአረፈ ጊዜ ይህን አባት አውማንዮስን መርጠው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት የአብያተ ክርስቲያናትንም ሥራ ሁሉ ተረከበ።
መናፍቃንንም ተከራክሮ የሚረታቸው ሆነ ብዙዎችንም ከስሕተታቸው መለሳቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመለኮቱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል እንደሆነ ግልጽ አድርጎ አስተማራቸው። በሹመቱም ዐሥራ ሦስት ዓመት ከኖረ በኋላ በአንስጣዮስ ሰባተኛ ዘመነ መንግሥት በዚች ቀን አረፈ። በዘመኑም የሶፍያ ሦስቱ ልጆቿ በሰማዕትነት አረፉ።

ዳግመኛም በዚችም ቀን መስተጋድል የሆነ ቀሲስ ዮሐንስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከተጋድሎው ብዛት የተነሣ ራሱን በሚላጭ ጊዜ በውኃ አያርሰውም ነበር።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይግባው እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages