ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 11 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, December 9, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 11

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ዐሥራ አንድ በዚች ዕለት አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናቷ የሆነች የተመሰገነች የቅድስት ሐና የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው።


ይችም ቅድስት ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት ልጁ ናት። ለማጣትም ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱም ስሟ ማርያም ናት ሁለተኛዋም ስሟ ሶፍያ ሦስተኛዪቱም ስሟ ሐና ናት ታላቂቱ ማርያምም ለባል ተድራ አዋላጅ የሆነች ሰሎሜን ወለደቻት እርሷም መድኃኒታችንን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ በስደቷም ወራት ከአረጋዊ ዮሴፍ ጋር እመቤታችንን ድንግል ማርያምን ያገለገለቻት ናት።
ሶፍያም ለባል ተድራ ለመጥመቁ ዮሐንስ እናቱ የሆነች ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደቻት። ይችንም ቅድስት ሐናን ከይሁዳ ነገድ ለሆነ ጻድቅ ስሙ ኢያቄም ለሚባል አጋቧትና እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደቻት እሊህም ሰሎሜና ኤልሳቤጥ ለቅድስት ሐና የእኅትማማች ልጆች ናቸው።
የዚችንም የቅድስት ሐናን በሥውር የምትሠራውን ገድሏንና ትሩፋቷን እንዳናስታውሰው አናውቀውም ግን ከሴቶች ሁሉ እንደምትበልጥና እንደምትከብር እናውቃለን እንረዳለን እርሷ አምላክን በሥጋ ለወለደችው ወላጅዋ ትሆን ዘንድ የተገባት ሁናለችና ከሴቶች ሁሉ የሚበልጥና የሚበዛ ትሩፋትና ተጋድሎ ባይኖራት ይህ ታላቅ ጸጋ ባልተገባት ነበር።
ይህችም ጻድቅት ሐና መካን በመሆንዋ ልጅን ይሰጣት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር በጸሎት ትማልድ ነበር እግዚአብሔርም በእርሷ ለዓለም ሁሉ ድኅነት የተደረገባትን ይቺን የተባረከችና የከበረች ልጅን ሰጣት እርሷም አምላክን የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት።
ስለዚህም ይህን ታላቅ ጸጋ ስለሰጣት የበዓሏን መታሰቢያ በደስታ ልናከብር ይገባናል።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በጸሎቷ የሚገኝ በረከቷም ከእኛ ጋር ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages